ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, December 23, 2021

የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ሕዝብ ድርጊት በመቀየሙ ወደ መቀሌ ሰራዊቱን ላለመላክ ወስኗል።ውሳኔው መንግስት በተለያየ ጊዜ ወደ ትግራይ እየገባ እርምጃ እንደሚወስድም ገልጧል።የዛሬው የመንግስት ውሳኔ ሲፈተሽ



=============
Gudayachn /ጉዳያችን 
==============

በእዚህ ጽሁፍ ውስጥ የሚከተሉት ርዕሶች ያገኛሉ። 
  • ውሳኔው ሲፈተሽ ምን ይመስላል?
  • መከላከያ መቀሌ አይገባም ማለትስ ምን ማለት ነው?
  • በቀጣይ የመንግስት ሦስት ትኩረቶች  ምን መሆን አለባቸው?

  • ውሳኔው ሲፈተሽ ምን ይመስላል?

በዛሬው የመንግስት መግለጫ ላይ በዘመቻ ኅብረ ብሔራዊነት በተሰኘው ዘመቻ  የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች  የሽብርተኛው ህወሓትን ወረራ በአፋር እና በአማራ ክልል በድል ካጠናቀቁ በኃላ ሰራዊቱ በአፋር እና ምስራቃዊ የአማራ ክልል ይዞታውን አጠናክሮ እንዲጠብቅ መታዘዙን እና ለእዚህም ሦስት ምክንያቶች መኖራቸውን ገልጧል። ምክንያቶቹም - 

1) ከዚህ ቀደም መከለከያ ሰራዊቱ በትግራይ በነበረበት ጊዜ የተፈፀመበትን ክህደት መነሻ በማድረግና ካለፈው መማር ስለሚያስፈልግ፣

2)  የሽብር ቡድኑ የተገደሉበትን ታጣቂዎች ሬሳ የቻለውን ሁሉ ጭኖ በመሸሹና የመንግሥት ኃይል ወደ ትግራይ ሲገባ መንግሥት በትግራይ ጅምላ ጭፍጨፋ ፈፀመ የሚል በአስከሬን የመነገድ እቅድን እንዳሰበ ስለተደረሰበት እና ከእውነት የራቁ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ የሽብር ቡድኑን ክስ መነሻ በማድረግ የተለያዩ ወሳኔ ለማሳለፍ እንደሚሰሩ ስለታወቀ፡፡

3) መንግሥት የአገሪቱን የግዛት አንድነት የመጠበቅ ሙሉ ኃላፊነቱን ለመወጣት በየትኛውም ጊዜ ወደ ትግራይ ክልል እየገባ እርምጃ መውሰድ እንደሚችል የሚታመን ስለሆነ መሆኑን የዛሬው መግለጫ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ  ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ የመንግስትን ውሳኔ አሳውቀዋል

ከእዚህ በተጨማሪ በእዚሁ መግለጫ ላይ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ''መንግሥት አሁን ላይ ምንም የማድረግ አቅም የሌለውን ትሕነግ መልሶ እንዳይነሳ ለማድረግ የሚያስችሉ የተጠኑ እርምጃዎችን በየትኛውም ስፍራ እየገባ ይፈፅማል'' ካሉ በኃላ ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት የአሸባሪውን ትሕነግ ቡድንን ጠራርጎ በማስወጣትና እጁን እንዲሰጥ በማድረግ ስኬታማ እንደነበር ተገልጿል፡፡

ሆኖም ግን የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ መንግሥት በኦሮሚያ ክልል በሸባሪው ሸኔ የሚደርሱ ችግሮችን እንዲሁም በምዕራብ አማራ አካባቢዎች የሚወስዳቸው የተጠኑ እርምጃዎች ይቀጥላል፤ ቀጣይ አቅጣጫዎችንም ያሳውቃል ማለታቸውን ዋልታ ዘግቧል።

ውሳኔው ሲፈተሽ ምን ይመስላል?

የዛሬው የመንግስት ውሳኔ በአንዳንድ ማኅበራዊ ሚድያዎች እንደሚባለው መንግስት ፈጽሞ በትግራይ ያለውን ሁነታ በወታደራዊ የተለያዩ የመቆጣጠርያ መንገዶች አልቆጣጠርም አስፈላጊ ሲሆንም ጥቃት አልፈጽምም አላላለም። ከላይ የመግለጫው ዓረፍተ ነገር ላይ እንደተገለጠው ይልቁንም ከመግለጫው አንዱ ምክንያት መንግስት አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ ኢርምጃ የመውሰድ አቅም ስላለው መሆኑን ይገልጣል። 

የዛሬው የመንግስት ውሳኔ መንግስት ባለበት ሃላፊነት እንደ መንግስት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ እንደ ህዝብ ለወንድሙ ለትግራይ ህዝብ ያደረገውን እና የሆነውን የትግራይ ህዝብ ከመጤፍ እንዳልቆጠረው እና ይልቁንም ህወሃት ለፈጸመው ክህደት ተብብሮ መገኘቱ እንዳሳዘነው በደንብ ያሳያል። 

መከላከያ መቀሌ አይገባም ማለትስ ምን ማለት ነው?

ይህ ማለት የኢትዮጵያ ህዝብ በ1983 ዓም ህወሃት በትግራይ ስም ተደራጅታ ስትመጣ ትግራይ መጣ ወይንም የእገሌ ዘር ሳይል አዲስ አበባ ድረስ አስገብቶ ነበር የኢትዮጵያ ህዝብ ዘረኛ አይደለም ማለትም ነው።

ይህ ማለት የትግራይ ህዝብ የኢሳያስ ጦር ወጋኝ ሲል የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ተነስቶ ባድሜ ላይ ከቶ እስከ 70 ሺህ ሰው የረገፈውን አጥንት ተረስቶ ሰሜን ዕዝ ሲወጋ፣የትግራይ ህዝብ ዝም ማለቱ አሳዝኖናል ከባለፈው ትምህርት ወስደናል ማለት ነው።

ይህ ማለት ከሰሜን ዕዝ የተወሰነ ሜካናይዝድ ጦር ወደ ሌላ የኢትዮጵያ ክፍል ይንቀሳቀስ ሲባል የትግራይ ህዝብ ነጠላ አንጥፎ ህጻናት አሰልፎ እንዳልለመነ በኋላ ህወሃት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ሲፈጽም መጨፈሩ አሳዝኖናል ማለት ነው።

ይህ ማለት በትግራይ ከ20 ዓመታት በላይ ኖረው እዝያው ተዋልደው የኖሩ፣የህዝቡን ሰብል ከመሰብሰብ እስከ ቤቶች እና ትምህርት ቤቶች ሲገነቡ የነበሩ የሰሜን ዕዝ አባላት ላይ ጥቃት ሲፈጻም ልጆቻችን ናቸው ብሎ ለማስጣል የሞከረ ከትግራይ አለመኖሩ አሳዝኖናል ማለት ነው።

በኋላም መከላከያ መቀሌን ከህውሃት ነጻ ካወጣ በኋላ በቡድን እየሆነ ሲያጠቃው ብቻ ሳይሆን አንዳንዶች ምግቡ ላይ መርዝ እየጨመሩ፣ዓይኑ ላይ በርበሬ እየረጩ ለህዝብ ነጻነት የቆመን ሰራዊት መግፋት አሳዝኖናል ማለት ነው።

በእዚ ሳምንት በትግራይ ቴሌቭዥን አንዳንድ ሲቪል እናቶች ሳይቀሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ወደ መቀሌ ከመጣ ቃል በቃል ሲሉት የተሰማው ''ዓይናቸው ላይ በርበሬ እጨምራለሁ፣ለመውጊያ መርፌ አዘጋጅቻለሁ'' የሚሉ ንግግሮች መሰማታቸው አሁንም የጥሞና ጊዜውን በአግባቡ ያልተጠቀመ መኖሩን በመመልከቴ አሳዝኖኛል ማለት ነው።

አንዳንድ የሽብርተኛው ህወሃት ደጋፊዎች መከላከያ መቀሌ አልገባም ነገር ግን አስፈላጊ ሲሆን እርምጃ እወስዳለሁ ማለቱን እንደ ሃይማኖት የሚያመልኩት ህወሃት የተረፈላቸው እየመሰላቸው ሲደሰቱ ይታያሉ።መከላከያ መቀሌ አይገባም ማለት ምን ዓይነት መከራ እንዳለበት የሚረዱት ከህወሃት ሳይሆን ከትግራይ ህዝብ ችግር አንጻር ነገሩ የሚረዱት ግን አይደሰቱም። መከላከያ መቀሌ አይገባም ማለት  - 

- የመንግስትም ሆነ የግል ድርጅቶች ሥራ አይጀምሩም ማለት ነው።

- ባንኮች ወደ ሥራ አይገቡም፣ከብሄራዊ ባንክ ጋር ያላቸው ግንኙነት አይኖርም ማለት ነው።

- ለትግራይ የሚላክ በጀት የለም ማለት ነው።

- በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶች ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቅያ ፈተና አንዳመለጣቸው ሁሉ የስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናም መፈተን አይችሉም ማለት ነው።

- በትግራይ ያሉ ትምህርት ቤቶች፣ሆስፒታሎች እና ሌሎች አካላት ሁሉ ሥራ አይጀምሩም።ሰራተኞችም ደሞዝ አይኖራቸውም ማለት ነው።

- የውጭ ጥቃት በትግራይ ላይ ቢፈፀም ለምሳሌ ከኤርትራ ወይንም ከሱዳን ቢኖር የኢትዮጵያ መከላከያ ህወሓት እያለ ለመከላከል ስለማይችል  በቅድምያ የህወሓት መወገድ ቅድመ ሁኔታ ይሆናል ማለት ነው።

- አሁን በትግራይ ያለውን የአስተዳደር መዋቅር ህወሓት በአግባቡ እየመራው አይደለም።በብዙ ቦታዎች ለምሳሌ የአክሱም ከተማን ጨምሮ ህዝቡ በራሱ አለቆች አየመረጠ ይተዳደራል አንጂ ትግራይ በአሁኑ ጊዜ ታጣቂ ሁሉ የሚዘርፍባት አንደሆነች ትቀጥላለች ማለት ነው። 

ባጭሩ ህወሓት በቀጣይ ከታሊባን የሽብር ቡድን ጋር ሳይቀር ውል አየገባ ትግራይን ለባዕዳን ለመሸጥ ለማደራደር ይሞከራል ማለት ነው።አስገራሚው ጉዳይ ህወሃትን አንደ ሃይማኖት የሚከተሉት የትግራይ ተወላጆች የትግራይን ወጣት በአፋር አና በአማራ ክልል አስፈጅቶ ቀሪውን አራሱ ረሽኖ አሁንም የቀረውን ለማስጨረስ የሚዘጋጀውን ቅምጥል አመራሩ ግን አሁንም የታሸገ ውሃ ሳይቀር አንዳይጎድልባቸው ሆነው የሚኖሩትን አመራሮች ወንጀል አየሸፈነ ለመኖር የሚሞክር መሆኑ ነው።

መንግስት በቅድምያ ሊያከናውናቸው የሚገቡ ሦስቱ ስራዎች 

መንግስት ሀገር የማቆም አና የማፅናት ትልቅ ታሪካዊ ኃላፊነት የተጣለበት ጊዜ ነው።ይህ ኃላፊነት የመንግስት ብቻ አይደለም፣ ግለሰብ አና የሕዝብም ጭምር ኃላፊነት ነው። የህወሓት የሽብር ቡድን በአፋር እና በአማራ በተለይ ወሎ በሰው ልጅ ይፈፀማል የማይባል ግፍ ፈፅሟል።ከ70 ዓመት መነኩሴ መድፈር እስከ የካህን ሚስት መድፈር፣እናቶችን ልጆቻቸው ፊት መድፈር እና ገንዘብ ቀምቶ ከቤት ገብቶ ከበላ ከጠጣ በኃላ ያበላው ያጠጣውን ቤተሰብ ገድሎ የሄደባቸው በርካታ ምስክሮች በመገናኛ ብዙሃን ስንመለከት ነው የሰነበትነው።አሁን በጦርነቱ ሳብያ የተጎዳውን ህዝብም ሆነ ምጣኔ ሃብቱን እንዲያገግም መንግስት ቅድምያ ሊሰጣቸው የሚገባቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች አሉ።እነርሱም -

1) በአማራ ክልል በተለይ በዞን እና ወረዳ ደረጃ ሕዝብ ያመነባቸው አና በጦርነቱ ወቅት በነበራቸው ብቃት አመራር እና በችሎታ የሕዝብ ቅቡልነት ያላቸው አመራሮች እንዲመሩ ማድረግ።በአማራ ክልል በታችኛው መዋቅር ላይ ያለው አመራር በጁንታዊ አስተሳሰብ የተበከሉ፣አቅም የሌላቸው እና ሕዝብ በልዩ ልዩ የስነ ምግባር ጉድለት የሚታሙ መኖራቸው ይሰማል።

2) በኦሮምያ ክልል ያለው ሙስና ቅጥ ያጣ መሆኑ ይሰማል።ከፍተኛ የስልጣን ብልግና አና ያለአግባብ መበልጠግ ላይ ብቻ የሚሰሩ አመራሮች ከብልሹ ነጋዴዎች ጋር በመግጠም ከፍተኛ ጥፋት አየፈፀሙ ነው።ይህንን መንግስት በፍጥነት አጣርቶ መፍትሄ አለመስጠቱ አሳሳቢ ነው።

3) ወደ ትግራይ ክልል የሚተላለፍ ሙሉ ደረጃውን የጠበቀ የጤናማ ፕሮፓጋንዳ ራድዮ እና ቲቪ እንዲሁም ከአየር ላይ የሚበተን ወረቀት ጭምር ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በህወሓት ስር የኖረውን ሕዝብ ላይ ሥራ መስራት ይፈልጋል።አሁን ባለበት ሁኔታ  ብዙሃን በትግርኛ የሚተላለፉ የራድዮም ሆነ የቴሌቭዥን ስርጭቶች ቢኖሩም በባለሙያ እና በቂ በጀት ተመድቦ የሚጠበቅ ውጤት ባስቀመጠ መልኩ መስራት ይፈልጋል።

ለማጠቃለል፣በኢትዮጵያ ምድር በሽብርተኛው ህወሓት አማካይነት ደም ሲፈስ፣ሕዝብ ሲሰደድ ግማሽ ክፍለዘመን አስቆጥሯል።ባለፉት አራት ወራት ብቻ በአማራ እና በአፋር ላይ የደረሰው ግፍ በፈጠረው ቁጣ እና ስሜት ወደ መቀሌ ሕዝቡም ሠራዊቱም ቢተም ምን ሊፈጠር አንደሚችል  መገመት ይቻላል።በመሆኑም መንግስት የረጅም ጊዜ የኢትዮጵያዊነት አሳቤን ግንዛቤ ባስገባ መልኩ ሰራዊቱ በድንበር ላይ ይዞታውን አስጠብቆ ትዕዛዝ እንዲጠብቅ መደረጉ ለአሸናፊ ሰራዊት ከባድ ውሳኔ ቢሆንም ቆይቶ ግን ኢትዮጵያን በመልካም ይከፍላታል። ሆስፒታላቸው የፈረሰባቸው፣ትምህርት ቤታቸው የተዘረፈባቸው እና ከተሞቻቸው አሁንም በሽብርተኛው ህወሓት የፈረሰባቸው የአፋር እና አማራ ክልል ወጣቶች የፈሰሰውን ሲጠርጉ፣የተሰበረባቸውን ለመጠገን ሲሞክሩ መመልከቱ አንጀት ይበላል።ግፍ ተፈፅሞበት በብዙ ልቀት በልጦ ወደ ሥራ የሚሄድ ወጣት ማየት በራሱ ግፍ ያደረገው በምድር ብቻ ሳይሆን ከፈጣሪም የሚታዘዝ ቅጣት እንደሚያገኝ እማኝ ይሆናል። በአማራም ሆነ በአፋር ክልል ህዝቡ ምግብ ለወራሪዎቹ ሲሰጥ አንድም ቦታ መርዝ ጨምሮ ወይንም ሌላ የተንኮል ሥራ ሰርቶ መስጠቱ አልተሰማም።ከሰኔ፣ 2013 ዓም በፊት በትግራይ ሕግ ማስከበር ሥራ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ መከላከያ ላይ ግን አንዳንድ የትግራይ ቦታዎች ብቻ ሳይሆን ጥቅምት 24፣2013 ዓም በሰሜን ዕዝ ላይ ከተፈፀመው ጥቃት ውስጥ አንዱ በመኮንኖች ላይ በራሳቸው የትግራይ ባልደረቦች የሚበሉት ምግብ ላይ መርዝ ተጨምሮ እንደነበር የወቅቱ ዘገባ ነበር።የሽብርተኛው ህወሓት እና አምላክዎቹ ያለባቸው የጥላቻ ጥግ እና የተበደለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሞራል ልዕልና ሲታይ ያለው እርቀት የትየለሌ የሚያሰኝ ነው።ይህ የሃሳብ ልዕልና የጁንታውን ስነልቦና ላይ የበላይነቱን ተቀዳጅቷል።ቀሪው ስልታዊ አፈፃፀም ብቻ ነው።

==========////============



No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...