የተመድ ሰ/መ/ም/ቤት ስብሰባ ጀኔቫ ሲደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ ከቱርክ ፕሬዝዳንት ኤርጋዶን ጋር
ውይይት ላይ ነበሩ።የቱርክ አፍሪካ ጉባኤ ዛሬ በአንካራ ተከፍቷል።
ፎቶ = ታኅሳስ 8/2014 ዓም (ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ትውተር ተወስዶ ለጉዳያችን እንዲሆን ሆኖ የቀረበ)
==============
ጉዳያችን ልዩ ሪፖርት
==============
በዛሬው ታህሳስ 8/2014 ዓም የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ንግግር ካደረጉት የሃገራት ተወካዮች ንግግር ውስጥ አብዛኞቹ ህገሮች በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና በተመድ የሰብዓዊ መብት ካውንስል በጋራ የተደረገው ምርመራ አወድሰዋል።የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መከበር እንዳለበት አስምረውበታል።
ከተናገሩት ውስጥ የ19ኙ ሃገሮች ያሉት ዋና ገዢ ሃሳቦች ከስር ቀርበዋል።ስብሰባው የተደረገው በጄኔቭ የተመድ ስብሰባ አዳራሽ ሆኖ ተናጋሪዎች በኮቪድ ወረርሽኝ ሳብያ በቀጥታ የቪድዮ ስርጭት ነበር የቀረቡት።ስብሰባው በሁለት ክፍል ከምሳ በፊት እና በኃላ የነበረው ስብሰባ በተመለከተ የተባለውን ከእዚህ በታች ቀርበዋል።
በክፍል አንድ ስብሰባ
በጧቱ ስብሰባ ላይ 19 ሀገሮች ተወካዮች ያሉት ዋና ጭብጦች የሚከተሉት ናቸው።
በጄነቭ የኢትዮጵያ ባለሙሉ አምባሳደር ዘነበ ከበደ ኢትዮጵያ የቀረበው ረቂቅ ፖለቲካዊ መሆኑን እንደምታምን እና ይልቁንም በህወሓት የተፈፀሙት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ችላ መባላቸው ላይ አስምረው ተናግረዋል።
የእንግሊዙ አምባሳደር ኮሚሽኑ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ለየት ባለ ቶን ሁሉ አጅበው ለማቅረብ ሞክረው ትዝብት ላይ ወድቀዋል።
ፈረንሳይ የተጀመረው የኢትዮጵያ እና የተመድ የጋራ ምርመር ይቀጥል ብላለች
ኩባ የካውንስሉ ስብሰባ በአዳጊ ሃገሮች ላይ የተሸረበ ፖለቲካዊ ቃና ያለው ነው።ቅድምያ መስጠት ያለብን ለኢትዮጵያ ብሄራዊ እና አህጉራዊ ጥረቶች ነው ብለዋል።
ፓኪስታን የተመድ ካውንስል በራሱ ያለፈ ታሪኩ የሃያላንን ፖለቲካ ፍላጎት የማስፈጸም ታሪክ አለው ብለውታል።ይህ ስብሰባ ለፓኪስታን ጥያቄ ፈጥሮባታል ብለዋል።
ኤርትራ ይህ ስብሰባ ፍትሃዊ አይደለም፣የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት የሚጻረር እና በህወሃት የተሰራውን ወንጀል ለመሸፈን የሞከረ ነው።ወደ ትግራይ ሄደው የቀሩት የእርዳታ መኪናዎችንም አንስተዋል።
ቦሊቭያ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ፖለቲካዊ ሲሆን አይስማማንም ብለዋል።
ፓራጓይ ሁሉም አካላት ለተራቡት ምግብ እንዲደርስ ያድርጉ ብላለች
ናይጄርያ ይህ ስብሰባ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የተጻረረ ነው፣የአፍሪካ ህብረትንም ይሁንታ አላገኘም ብላዋለች ።
ኒውዝላንድ ህወሃት ጦርነቱን ወደ አማራ እና አፋር ማስፋፋቱን ገልጣ ዓለም አቀፍ ምርመራ ኮሚሽኑ ቢያደርግ ብላ ቀላቅላለች
አውስትራልያ የኢትዮጵያ መንግስት ምርመራውን በሚኒስቴር ደረጃ አቋቁሞ ምርመራ ላይ መሆኑን እንደግፋለን ብለዋል።
ስዊድን የጥላቻ ንግግሮች ያሳስቡናል ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በሚንስትር ደረጃ አጣሪ ኮሚቴ ማቋቋሙን አድንቀዋል።
አየርላንድ የአፍሪካ ህብረት ማደራደር እንደሚደግፉ ተናግረዋል።የጥምር ሪፖርቱ በተሰጠው አስተያየት መሰረት ክትትል ይፈልጋል፣መብት የጣሱም ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባል ብለዋል።
ኢራን ማናቸውም ጉዳይ የኢትዮጵያን አንድነት በማይነካ መልኩ በአፍሪካ ህብረት በኩል መከናወን ይገባዋል ብለዋል።
ሲሪላንካ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ካለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት ስራውን እንዲሰራ መደረግ አለበት ብለዋል።
አሜሪካ ጉዳዩ ያሳስበናል ብለው ምግብ ወደ ትግራይ አልሄደም፣የትግራይ አማጺዎችም በአማራ እና አፋር ግፍ ፈጽመዋል፣የኤርትራ መንግስትም ጣልቃ ገብነት መቆም አለበት ብለዋል።
ደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ መንግስት የጥምር ምርመራ ውጤት መቀበሉን እናመሰናለን።በእዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋትን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጠዋል።
ሩስያ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተገዢ ነች። ኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ፖለቲካዊ ተጽኖ ያለበት ማናቸውም ውሳኔ አይሰራም።ኤክስፐርቶችን ከውጭ በመላክ የሚደረግ ስራም ውጤታማ አይሆንም።
ቻይና በኢትዮጵያውያን ችሎታ እና ጥበብ ችግሮችን የመፍታት አቅም ትተማመናለች። የአፍሪካ ህብረት ተሳትፎ ታበረታታለች።
ከእዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አካባቢያዊ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች አጫጭር ዕይታዎቻቸውን አካፍለዋል።
በክፍል ሁለት ስብሰባ
በክፍል ሁለት ማለትም ከምሳ በኃላ በነበረው ስብሰባ ላይ ድምጽ ከመሰጠቱ በፊት የምክር ቤቱ አባላት እና ኢትዮጵያ ሃሳብ እንድትሰጥ በተጠየቀው መሰረት የሚከተሉት ሀገሮች ይህንን ብለዋል።
የኢትዮጵያ አምባሳደር ዘነበ ከበደ በድጋሚ ተቃውሞ አሰምተዋል።
የኤርትራ አምባሳደር የአፍሪካ ቡድን በሙሉ ውድቅ እንዳደረገው ገልጠዋል።
የሩስያ አምባሳደር ረቂቁን እንደምትቃወም እና የአፍሪካ ችግር በአፍሪካውያን መፈታት አለበት ብላለች።
ቬንዝወላ ይህ ፖለቲካዊ ቃና ያላው ረቂቅ ነው፣ኢትዮጵያ ይህንን እንደማትቀበል ገልጣለች፣ኢትዮጵያ በተመድ እና የኢሰመኮ የተደረገው ምርመራ መቀበሏን ሁሉ ገልጣ ነው ይህንን ረቂቅ እንደገና ኮሚሽኑ ያመጣው ስለሆነም ረቂቁን አንቀበልም ብላለች።
ቻይና የሰብዓዊ ሁኔታ ፖለቲካዊ ቃና ሲኖረው እንደማፅማማ፣እኛ የኢትዮጵያን ስጋት እንረዳለን ስለሆነም ድምፃችንን በመቃወም ነው የምንሰጠው ብላለች።
ፊሊፒንስ ይህ ረቂቅ ተግባራዊ እንዳይሆን ነው ድምፅ የምንሰጠው ካለች በኃላ የኢትዮጵያ መንግስት በተመድ እና በኢሰመኮ የተደረገውን ምርመራ ተቀብሎ እያለ እና በሚኒስትር ደረጃ የሚያጣራ ኮሚቴ መስርቶ እያለ ሌላ ውሳኔ አያስፈልግም።የሰብዓዊ መብት ጉዳይ የሀገር ሉዓላዊነትን ማክበር አለበት ብላለች።
በመጨረሻም የድምፅ መስጠቱ ስነስርዓት ተካሂዶ እንግሊዝ እና አሜሪካን ጨምሮ 21 ሀገሮች አዎን ሲመርጡ 15 ሀገሮች ቻይና እና ሩስያን ጨምሮ አይሆንም ብለዋል። የቀሩት 11 ሀገሮች ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል።
የስብሰባው አጠቃላይ አንደምታ እና መንግስት ማየት ያለበት መንገድ
በድምፅ ውጤቱ መሰረት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ኤክስፐርቶች በመላክ ላለፈው አንድ ዓመት የነበረውን ሁኔታ አጥንቶ እንዲያቀርብ የሚል ሲሆን ኢትዮጵያ ውሳኔውን የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የተጠናወተው መሆኑን በመግለጫዋ አስታውቃለች።ሆኖም ግን አሁንም ኢትዮጵያ የህወሓት የሽብር ቡድንን በቶሎ ለሕግ አቅርባ እስከሄደች ድረስ እና ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣውን ልዑክ ማንነት ( ውሳኔውን አልቀበልም ብላ ውድቅ ካላደረገችው) እስከመወሰን እና ቪዛ የምትሰጠው እና የማትሰጠውን እስከመወሰን ድረስ የራሷ ተግባር ነው። ሌላው የአፍሪካ ሀገሮችን አስተባብራ ዲፕሎማሲያዊ ግፊት አስደርጋ መልሳ ኮሚሽኑን በሂደት ስብሰባ አስቀምጣ ውሳኔውን ማስቀየር ትችላለች።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የተመድ ሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በጋራ በትግራይ ያደረጉት ምርመራ የኢትዮጵያ መንግስት ሲቀበለው የሽብር ቡድኑ ህወሓት አልተቀበለውም።በመሆኑም አሁንም ምርመራው ይደረግ ቢባልም በህወሓት የተፈፀመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፀሐይ የሞቀው ነው።እዚህ ላይ ማወቅ የሚገባው ግን የምዕራባውያን ፍላጎት ኢትዮጵያ ውስጥ ጉዳይ ገብቶ መፈትፈት እና በትግራይ ሕዝብ እና በተቀረው ሕዝብ መሃል ያለ ልዩነት በምርመራ ሂደት እያሰፉ በመጨረሻ ጉዳዩን ማወሳሰብ ነው።ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት የዛሬውን ውሳኔ አስመልክቶ የሩቁ ግባቸውን ተመልክቶ ለትውልድ የሚጠቅም ብልህነት ያለው ውሳኔ መወሰን ይገባዋል።
ባጠቃላይ የዛሬው የውሳኔ ሂደት የሚያሳየው የተባበሩት መንግሥታት አባል ሀገሮች መሃል ያለው ልዩነት በግልጥ መስፋቱን እና ድርጅቱ ለውጥ ካላደረገ በቀር ውሳኔዎቹ ሁሉ የውሃ ላይ ኩበት እየሆኑ መሄዳቸው እንደማይቀር ነው።የዛሬው ውሳኔ ከሩስያ እና ቻይና በተጨማሪ ፊሊፒንስ እና ቬንዝዌላ ያሰሙት የምሬት ንግግር ከምዕራቡ ጋር የደረሰው ፍጥጫ የመጨረሻ ጫፍ እንደደረሰ በደንብ የሚያሳይ ነው። በእዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ ውሳኔዎችን ባለመቀበል ለፍትህ መቆሟን በማሳየት የጀግና ጀግና ሆና በብዙ ሀገሮች አንጀት አርሳ እንደምትወጣ መመልከት ይቻላል።የመጨረሻው መጨረሻ ግን ኢትዮጵያውያን በሽብር ቡድኑ የተዋለባቸውን ግፍ በትግራይ ሕዝብ ላይ እንዳይፈፀም በጨዋነት በመንቀሳቀስ የሽብር ቡድኑን በፍጥነት መደምሰስ እና የትግራይ ህዝብንም ከመከራው አላቆ የህወሓትን ፕሮፓጋንዳ እና እኛኑ ለማጋጨት ያሰፈሰፉትን ባዕዳን አሳፍረን ችግራችንን ስንፈታ ሁሉም ያፍራል።
በዛሬው የተመድ ሰብዓዊ መብት ምክርቤት ስብሰባ ላይ ድምፅ የሰጡ የ47 ሀገሮች ዝርዝር እና የድምፃቸው ውጤት
No comments:
Post a Comment