ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, December 29, 2021

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታላቅ ተልዕኮ የሚኖረው ሀገራዊ የምምክር ኮሚሽን ተመሰረተ።ስለኮሚሽኑ ምንነት ምን ያህል ያውቃሉ? ጉዳያችን ያገኘችውን መረጃዎች ታካፍላችኋለች።  • የእዚህ ኮሚሽን መመስረት ኢትዮጵያ የተቋማት ግንባታ ላይ በሚገባ እየሰራች እንደሆነ የሚያበስር ብስራት ነው።
  • ይህንን ኮሚሽን ማጠናከር፣ማክበር አና በአግባቡ መጠቀም ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ዕድል ነው።ዜጎች ሁሉ ከፍተኛ ትኩረት እና አክብሮት ሊሰጡት ይገባል።
ETHIOPIAN MP PASS BILL TO SET UP NATIONAL DIALOGUE COMMISSION 
===================================
ጉዳያችን ልዩ ዘገባ /Gudayachn Special Report
===================================
ታኅሳስ 1፣2014 ዓም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ መሠረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች በተለያዩ ጎራዎች የተሠለፉ የፖለቲካ ልሂቃንም ሆኑ ምልዓተ ሕዝቡ ተቀራራቢና በአገራዊ አንድነት ገንቢ አቋም እንዲይዙና አካታች አገራዊ ምክክር ተግባራዊ ለማድረግ፣ ይህንኑ ምክክር በገለልተኝነት ለመምራትና ለማስተባበር የሚችል ቅቡልነት ያለው ተቋም ለማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውሳኔ መርቶት ነበር። 

በእዚህ መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታኅሳስ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፣ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር ዕይታ ለምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶት የነበረ ሲሆን በእዚሁ ውይይት ላይ  የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የፍትሕ ሚኒስትርና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎችም አካላት ተሳትፈዋል፡፡በውይይቶቹ ውስጥ ከተነሱት እና አጽንኦት እንዲሰጥባቸው ከተወሱት ውስጥ የኮሚሽነሮች አሰያየም፣ አወቃቀርና የኮሚሽኑ አደረጃጀት ላይ ያላቸውን ሥጋትና የገለልተኝነት ሁኔታዎች ጥቂቶቹ ነበሩ።ከእዚህ ሁሉ ውይይት  በኃላ ዛሬ ታኅሳስ 20፣2014 ዓም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በረቂቁ ላይ ተወያይቶ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል።

ኮሚሽኑ 11 ያለመከሰስ መብት ያላቸው ኮሚሽነሮች ይኖሩታል።በኮሚሽነሮቹ መብዛት ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሃሳብ ሰጥተዋል። የኮሚሽኑ ዋና ተግባር ልዩነትና አለመግባባት ለማርገብና ለመፍታት ሰፋፊ አገራዊ የሕዝብ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ አገራዊ መግባባት ለማምጣት የሚሠራ ነው። የኮሚሽኑ መቋቋም በኢትዮጵያ ሃገረ መንግስት የሚመሰረተው አንዱ ተቃዋሚ ሲጠፋ ነው የሚለው አስተሳሰብ በእዚህ ኮሚሽን መመስረት ይቀየራል ተብሎ ይታሰባል።ይህ ግን ሽብርተኛን እና ኢትዮጵያን ለመበተን የሚነሳ አካልን አይመለከትም።

በኮሚሽኑ መመስረት ዙርያ ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ‹‹ሰላም፣ ደኅንነት፣ ዲፕሎማሲና ልማት በኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ ምን ይደረግ?›› በሚል ርዕስ  ምሁራንን ያካተተ የፓናል ውይይት አድርጎ ነበር።በእዚሁ ውይይት ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም መምህርና ‹‹ብሔራዊ ደኅንነት በኢትዮጵያ›› በሚል የጥናት ርዕስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እየሠሩ ያሉት አቶ ዮናስ ታሪኩ ‹‹ደኅንነት›› በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ በተለይ ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ ‹‹የማንን ደኅንነት እናስጠብቅ›› የሚለው ላይ አለመግባባት መኖሩንና በዚህም ምንክያት የአገሪቱ ደኅንነት ፍትጊያ ውስጥ መግባቱን መናገራቸው ተዘግቧል። በእርሳቸው ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ እንደተገለጠው የሃገረ መንግስቱ መጠበቅ የቡድን መብት መጠበቅ ለምሳሌ በቋንቋ እና ማንንነት ላይ ያለው ከለላ ትኩረት እንዲሰጠው የሚፈልጉ የመኖራቸውን ያህል በተቃራኒው ሃገረ መንግስቱ መጠበቅ ላይ ኢትዮጵያዊነትን በሚገባ ይዞ መጓዝ እንዳለበት አጥብቀው የሚያሳስቡ እንዳሉ ገልጠዋል። አቶ ዮናስ ማብራርያቸውን በመቀጠል የሁለቱ ቡድኖች ሃሳብ እርስ በርስ የሚጋጩ አስመስሎ በማቅረብ ችግር የመፍጠር ሁኔታ መሆኑን ገልጠው ይህ ግን ወደ ግጭት ሊያመራ እንደማይገባ አብራርተዋል።

ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመው የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለእንዲህ ዓይነት የኢትዮጵያ ሁኔታዎች ዓይነተኛ መፍትሄ የሚሰጥ እንደሚሆን ይታመናል።ይህንን ኮሚሽን ማጠናከር፣ማክበር አና በአግባቡ መጠቀም ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ዕድል ነው።ኮሚሽኑ ሁለት አና ከእዚያ በላይ የሆኑ የምክክር ሃሳቦችን ሁሉ የሚያስተናግድ ሲሆን የሦስት ዓመታት ዕድሜ ይኖረዋል።ከእዚህ በተጨማሪ በሀገራዊ ደረጃ የማያግባቡ አጀንዳዎችን መርጦ በሰነድነት አዘጋጅቶ ለውይይት የሚያቀርብ አና የሚቋጩትን በመቋጨት ያልተቋጩትን ደግሞ በውይይት እንዲፈቱ የማድረግ ትልቅ ሃገራዊ አደራ ተቀብሏል። ሌላው እና የኮሚሽኑ ትውልድ ተሻጋሪ መሆኑን የሚያሳየው የኮሚሽኑ ተግባር ደግሞ የውይይት ሰነዶቹ ሂደት ጭምር ለቀጣይ ትውልድ መማርያ እንዲሆኑ በሚገባ በሰነድነት ሰንዶ ለብሄራዊ ቤተ መዛግብት የሚያስረክብ ሲሆን፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሰነዶቹን በፈለገ ጊዜ ለመመልከት እንዲችል ሁኔታዎች የሚመቻቹ መሆናቸው ነው። 

የእዚህ ኮሚሽን መመስረት ኢትዮጵያ  የተቋማት ግንባታ ላይ እየሰራች እንደሆነ በሚገባ የሚያበስር ብስራት ነው።በመሆኑም ዜጎች ለኮሚሽኑ ከፍተኛ ትኩረት እና ተገቢው አክብሮት ሊሰጡት ይገባል።የኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ አንዱ ችግር ያሉትን የተለያዩ ሃሳቦች በአግባቡ ሰንዶ እና አስተካክሎ መፍትሄ እንዲያገኙ ለውይይት እና ለህዝብ ውሳኔም ሆነ አስፈጻሚ እና ህግ አውጪ አካል አለመቅረባቸው መሆኑን ማስተዋል ይገባል።አንዳንዶቹ ቀላል የልዩነት ሃሳቦች በእየሚድያው ላይ ይንገዋለላሉ እንጂ እንዴት እና መቼ መፍትሄ እንደሚያገኙ ሃላፊነት የሚወስደው ተቋም ማን እንደሆነ ስለማይታወቅ ሁሉንም ጉዳይ መንግስት ይፍታው በሚል መጯጯህ ብቻ ጉዳዮች ሲንገዋለሉ ከርመው ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፈልጉ የውጭም ሆኑ የውስጥ አካላት ጉዳዮቹን ለሃገር መበጥበጫ ሲጠቀሙበት መመልከት የተለመደ ነው።አሁን የእዚህ ዓይነት ተቋም መኖር ለኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ልማቷም ያለው አስተማማኝ መሰረትነት የሚናቅ አይደለም።ይህንን ስራ ለሚሰሩ ብቻ ሳይሆን ሃሳቡን ላመነጩ የመንግስት አካላት ሁሉ ከፍ ያለ ክብር እና ምስጋና ይገባቸዋል።የኮሚሽኑን ውጤታማነት ደግሞ በበለጠ የምንረዳው እና የምናመሰግነው በቀጣይ በሚሰራቸው ስራዎች ይሆናል።ለስራዎቹ ስኬቶች ግን የእያንዳንዳችን አስተዋጽዖ አስፈላጊ ነው።

===================///==========No comments:

ለፕሮፌሰር መራር፣ልደቱ፣ጀዋርና ኢንጅነር ይልቃል ዘፈን ይህችን ዜማ እንምረጥላቸው።

በቅድምያ ስለ አራቱም የመግቢያ ማስታወሻና ወቅታዊ ሁኔታቸው። አራቱም ከመስከረም በኋላ መንግስት የለም ብለው ኢትዮጵያን ለእርስ በርስ ጦርነት ሊነክሯት ሞክረዋል።ዝርዝሩን፣ከእነማን ጋር መክረው እንደነበር፣ለኢትዮጵያ ደግሰው...