ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, May 3, 2014

ኢህአዲግ እና በሐገር ቤትም ሆነ በባህር ማዶ ያሉ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች የሚጠቀሙበት የጎሳ ፖለቲካ ፎርሙላ ይህ ነው።(ጉዳያችን ጡመራ)


ኢትዮጵያውያን በተሸለመ ፈረስ ሲሄዱ 

ፎርሙላ (ቀመር) አንድ 

የጎሳ ፖለቲካ ማለት በመጀመርያ ቤተሰብህን የተለዩ ፍጥረት እንደሆኑ መስበክ መጀመር ማለት ነው።እነርሱ የተለዩ መሆናቸውን በደንብ ማሰብ ሲጀምሩልህ  ደግሞ በመቀጠል የሰፈርህን እና የወንዝህን ሰዎች ልዩ መሆናቸውን በሚገባ መስበክ ነው።የሰፈርህን ሰዎች ልዩ እና የተለዩ መሆናቸውን ስትነግር ግን የአንተ ቤተሰብ ጋር እንደማይደርሱ ግን ደግሞ ከቤተሰብህ ዝቅ ባለ መልክ የተለዩ መሆናቸውን ወትውታቸው። በመጨረሻ አንተ የቤተሰብህም ሆነ የሰፈርህ ብቸኛ አለቃ መሆንህን ትነግራቸውና ከሰፈርህ ማዶ ያሉ ሰዎች ደግሞ እርኩስ፣የተለዩ፣ጥንትም አባቶችን ሲበድሉ እንደነበሩ የሆነ ያልሆነ ተረታ ተረት እየነገርክ ተራራ የሚያህል ጥላቻ እንዲያድርባቸው አድርግ።

ፎርሙላ (ቀመር) ሁለት 

ከእዚህ በኃላ  በሰፈርህ ሰዎች እና ማዶ ባሉ ሰፈር ሰዎች መካከል በአንተ የጦር አበጋዝነት ጦርነት እንዲከፈት አድርግ።ጦርነቱን ልትከፍት ስትል ትልቅ ችግር ሊገጥምህ ይችላል።ለምሳሌ ለዘመናት በክፉም  ሆነ በደግ አብረው የኖሩ ሰዎች ናቸው እና ከአንተ ሰፈርም ሆነ ከማዶ ሰፈር ያሉ የበሰሉ ሽማግሌዎች ወይንም አስታራቂዎች ነገሩን እንዳያበርዱብህ ተጠንቀቅ። ''የፍቅር ዘመቻ'' ብሎ በሰፈርህ መካከል ዘፈን ልዝፈን፣ ፍቅርን ልዝራ፣ ብሎ የሚነሳ ሀገር የወደደው ዘፋኝ ካለ ቀድመህ በቻልከው ነገር በማማሰያም ሆነ በብረት ምጣድ ደብድበህ አባረው።የስም ማጥፋት ናዳ ልቀቅበት።ዘፋኝ እና የሃይማኖት ሰዎች አንድ ናቸው።ሁለቱም ዓለም አንድ ነው፣ምናምን እያሉ አላማህን ያደናቅፉብሃል።'ቀንድ ቀንዳቸውን' በላቸው።ከሃይማኖት በፍቅር የተሰበሰቡ ማሕበራት ካሉም እግር ከእግር እየተከታተልክ አድክማቸው። ከቻልክ ዝጋቸው።

የሃይማኖት እና የኪነት ሰዎች ብቻ አይደሉም የዓላማህ ጠላቶች ጋዜጠኞች፣ብሎገሮች ሁሉ ቀድመው የሰፈርህን ሰዎች ከማዶ ሰፈር ሰዎች ጋር አብረው እንዲኖሩ ሊሰብኩ ይችላሉ እና ፈጥነህ ከእየቤታቸው ፖሊስ ልከህ ልቀማቸው! ያዛቸው! ማዕከላዊ ወስደህ አጉራቸው! ነግሬሃለሁ ጉድህን ይዘከዝኩታል።በሰፈርህ እና በማዶ ሰፈር መካከል ልታጋጭ ያሰብከውን ጉድ ሁሉ ለሀገር ይነዙልሃል።ይህ ብቻ አይደለም ቤተሰብህ ከሰፈርህ ሰው የተለየ አለመሆኑን፣አንተም በቤተሰብህ እና በሰፈርህ ሰዎች ላይ መንገስ እንደማይገባህ፣ሌላ 'በሰፈርህ እና በማዶ ሰፈር ሰዎች መካከል ልዩነት የለም በፍቅር እንኑር' የሚል ሰው መንገስ አለበት ብለው ለሕዝቡ ይነግሩብሃል።እናም ፍጠን! እሰራቸው!ልክህን አሳያቸው!።

ፎርሙላ (ቀመር) ሶስት 

ይህንን ሁሉ ከጨረስክ በኃላ አንተ እና ቤተሰብህ ጥንቱንም የተለያችሁ ፍጥረቶች መሆናችሁን በተለይ አዲስ ለሚወለዱት ልጆች እየሰበክ በሰፈርህ ሰዎች እና በማዶ ሰፈር ሰዎች መካከል  እረጋ ብለህ ቡናህን  እየጠጣህ ጦርነት እንዲከፈት ማዘዝ ትችላለህ።ተቀናቃኝህን ሁሉ እንደሆነ እስር ቤት ሰደሃቸዋል።የዘፋኙንም ስም ከማዶ ሰፈር ካሉ መሰሎችህ ጋር ሆነህ ስሙን አስጠፍተሃል። ከእዚህ በኃላ ማዶ ያሉ መሰሎችም ሆኑ አንተ አንድ አይነት ጫወታ ላይ ገባችሁ ማለት ነው።መንደር ከመንደር እየቆጠረ ህዝቡ ሲባላ እነርሱ በውስኪ አንተም በኮኛክህ መዝናናት ፈታ! ማለት ነው።

ፎርሙላ (ቀመር) አራት 

ጦርነቱ  ሲደረግ አንተ በሰፈርህ ሰዎች ላይ ንጉስ  ሆነህ ''ካለእርስዎ አመራር የት እንደርሳለን?'' ስትባል  ጀነን፣ጎምለል ማለት ነው።አሁን ጥሩ ጊዜ መጣልህ የሀብት መጠንህ ይጨምራል።ምክንያቱም የሰፈርህንም ሆነ የማዶ ሰፈር ሰዎችን ገንዘብ ወደ ኪስህ እየከተትክ አለምህን መቅጨት ትችላለሃ!። በመካከል ታድያ ሥራ አትፍታ እዛኛው ማዶ የራሱ የሰፈሩን ሰዎች የመሰሉ ሰዎች ሰው እየላክ ''የእዝህኛው ሰፈር ሰዎች እናንተን ይጠላሉ ተጠንቀቁ!'' ማለት ለእራስህም ሰፈር ሰዎች እንዲሁ ተመሳሳይ ነገር ጣል ማድረግ።ግጭቱ በደንብ አልጋጋልም  ካለህ ቀድሞ ከመቶ ዓመት በፊት የነበሩ የአንተ ሰፈር ሰዎች ''የሰሩት ኃጢያት አለ'' የሚል የሐሰት ታሪክ ማዶ ሰፈር ካለው መሰልህ ጋር በሚስጥር ተነጋግረህ  ''ማስታወሻ'' በሚል ስም የቂም ሐውልቶችን በየሰፈሩ መደርደር በተለይ ሴቶች ስሜታቸው የሚነካ የሰውነት ክፍል ለምሳሌ ጡት እና ጣት የመሳሰሉ የሰውነት ክፍሎች ተቆርጠው ነበር ብለህ ሃውልት መስራት።ያኔ ወጪ ወራጁ ''ህም! ድሮ እንዲህ አድርገዋል አሉ'' እያለ ከንፈር እንዲነክስ ማገዝ።አዎ ማገዝ።

ፎርሙላ (ቀመር) አምስት 

የሰፈርህ እና የማዶ ሰፈር ሰዎች አንድ መሆናቸውን ሊሰብኩ የሚነሱ ከመከከልህ ከተነሱ ወይንም ደግሞ የእዚህ አይነት አስተሳሰብ አላቸው የምትላቸውን ገልሰቦችም ሆነ የሃይማኖት ሰዎች ማኅበራት በሙሉ ተለጣፊ ስም መስጠት   ''አጎብዳጆች፣አሸባሪዎች፣የሰፈሬን ሰዎች ሰላም የሚያናጉ፣ዥንጉርጉር አብዮት ሊያስነሱ ያቀዱ'' እያልክ  ማሰር እና መግደል።

መደምደምያ 

በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት እና በባህር ማዶ እና በሀገር ቤት በጎሳቸው ላይ እራሳቸውን ያነገሱ እና ኢትዮጵያዊነትን የሚያጥላሉ ሁሉ ሲጠቀሙበት የሰነበቱት የጎሳ ፖለቲካ ፎርሙላ  ይሄው ነው።ኢትዮጵያ በእናንተ ዘመን አልተፈጠረችም እንዴት እንደምትኖር ታውቅበታለች።ግዴላችሁም ይህች ሀገር አምላክ አላት። በኢትዮጵያዊነት ላይ ጥላቻ ያደረበት ለጥላቻውም አስር ምክንያት ቢደረድር በመንግሥትነትም ሆነ በተቃዋሚነት ቢሰየም፣የቂም ሐውልቶችን እንደ አሸን ቢያፈላም ሆነ በነፃነት ስም ከመቶ ዓመት በፊት ይህ ትውልድ ላልኖረበት ዘመን እየጠቀሰ ለስልጣን መወጣጫ ሊጠቀም ቢሞክርም  ከህዝብ ፍርድ አያመልጥም።አሁንም ግዴላችሁም ይህች ሀገር ጎሳ እና ብሔር የማያውቁ ለሰው ልጆች በሙሉ የሚፀልዩ ቅዱሳን እና የሚሰማቸው አምላክም አሏት።አሁንም ኢትዮጵያዊነት የጋራ መጠለያችን ነው።የጎሳ ፖለቲካ ፎርሙላ-ቀመራችሁ  ተነቅቶበታል።

ጉዳያችን
ሚያዝያ 25/2006 ዓም
(ከጉዳያችን ጡመራ ለሚወስዱት ፅሁፍ ምንጩ ጉዳያችን መሆኑን መጥቀስ ጨዋነት ነው)

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።