ከአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ፕሮግራም ጋር በተያያዘ ሃሳባቸውን የሚገልፁም ሆኑ ምንም አይነት ሃሳብ ሳይገልፁ የኢትዮጵያን ውድቀት ከዳር ሆነው በማየት የህሊና እረፍት የሚያገኙ የሚመስላቸው ሁለቱም ነገሮችን የሚያዩበት ጥግ የእየራሱ ቦይ አለው።እርግጥ የሁሉንም መብት መከበር አለበት።እኔን መሰሎች ፍቅረ ኢትዮጵያ ይዞናል።''ይህ ጠቃሚ ነው ፣ይሄኛው ደግሞ እንደ ሀገር ጎጂ ነው'' እያልን የምንናገር እና ጥጋችን ፍቅረ-ኢትዮጵያ ብቻ የሆንን የምንለው አሁንም ሚዛን ደፍቶ የሚገኘው ከጊዜ በኃላ መሆኑ ይገርመኛል።
እኛ የምናነሳውን ከአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ፕሮግራም ጋር የተያያዙት የነገሮችን አመጣጥ ቀድመው ቢያውቁትም ለተራው ሕዝብ ግን አይነግሩትም።ምክንያቱም ፖለቲካ ነው እና ብዙ ቀመር ይወጣለታል ወይንም ጊዜው አሁን አይደለም ይባላል።ከእዚህ ውጭ ግን ያለው ሌላው አባዜ (የእኔ አስተያየት ነው) ይሉኝታ ያጠቃው ፖለቲካ ነው።ለምሳሌ የሰሞኑ በኦሮምኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን ላይ የተፈጠረው ችግር አድራጊው ኢህአዲግ ይሁን እንጂ የችግሩ ምንጮች ግን ሁለት ናቸው።
1ኛ/ የመጀመርያው የኢህአዲግ የተሳሳተ ቋንቋን መሰረት ያደረገ የፌድራል ስርዓት።
የመጀመርያው ችግር የኢህአዲግ የተሳሳተ ጎሳን መሰረት ያደረገ የፌድራል ስርዓት ነው። ይህ ፅንሰ ሃሳብ ኢህአዲግ/ወያኔ ገና በጫካ ሳለ ሲኮነን የነበረ።ኢትዮጵያን የበታተን ዕድል ያለው መሆኑ የተመሰከረለት። በአንፃሩ ኢህአዲግ ደግሞ ''የለም እንደ ብረት አንድነታችንን እያጠነከረው ነው'' እያለ ሲዋሸን የነበረ ጉዳይ ነው።ከእዚህ በፊት ዜጎች ከኖሩበት ቀዬ እየተባረሩ እንዲሄዱ፣ጎሳ በጎሳ ላይ እንዲነሳ እና እንዲጋደል ያደረገ፣ድሮ በሀገራት መካከል ይነሱ የነበሩ የድንበር ፀቦች በኢህአዲግ ዘመን ጎሳ ከጎሳ ድንበር ጋር መጋጨት እና ጦርነት የከፈቱበት (ለምሳሌ በሱማሌ እና በኦሮሞ መካከል እና በጉጂ እና በኦሮሞ መካከል የተነሱት ግጭቶች) ሁሉ ምክንያት ይሄው የ ኢህአዲግ ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌድራሊዝም ተብዬው ነው።2ኛ/ ሁለተኛው ለዘመናት ኢትዮጵያን ለማመስ ሲያደባ የነበረው የፅንፈኛ የእስልምና እንቅስቃሴ በኢህአዲግ የጎሳ ፖለቲካ ማዳበርያነት ዳብሮ የኢትዮጵያን ችግር ለማወሳሰብ ከመቼውም ጊዜ በላይ አመቺ ጊዜ ማግኘቱ።
ወቅቱ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንዳትቀጥል የሚፈልጉ በርካታ ሃገራት የእየራሳቸውን አጀንዳ ይዘው የተሰለፉበት ወቅት ነው።ለእዚህም በዘመነ ኢህአዲግ ሁለት አመቺ ሁኔታዎች ተፈጥረውላቸዋል።አንደኛው ለዘመናት ዕድል ያላገኘው ፅንፈኛው የእስልምና ኃይል በብሄር ስም ተደራጅቶ የኢህአዲግ አጋር ድርጅት ተብሎ ወደ ክልሎች እና አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ስልጣን መምጣት መቻሉ ሲሆን ሁለተኛው ይሄው ኃይል በገንዘብ፣በቁሳቁስ እና በሰው ኃይል ሀገርቤት ውስጥ እራሱ ኢህአዲግ ውስጥ የጠነከረ እንዲሆን መቻሉ ነው።በተለይ ይህንን ኃይል የሚደግፉት እና በኢንቨስትመንትም ሆነ በተለያየ ድርጅት ስም ሀገርቤት የገቡ የቅርብም ሆኑ የሩቅ ከኢትዮጵያ መዳከም እንደሚጠቀሙ የሚያስቡ ኃይሎች ለቡድኑ ከፍተኛ ሽፋን እራሱ ኢህአዲግ ውስጥ ሆነው እየሰጡ ይገኛሉ።አሁን ጥያቄው የኢትዮጵያ የአንድነት የፖለቲካ ኃይሎች እነኝህ ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት ነገሮች አንጥረው መቃወም እና ሕዝቡን ከጎናቸው ማሰለፍ ሲገባቸው እነርሱ ግን ግዝያዊ ወይንም ስልታዊ ሥራ እየሰሩ እየመሰላቸው ሁለት የተሳሳቱ ተግባራትን ሲሰሩ ይታያሉ።
አንደኛው በኦሮምያ እና በሌሎች ቦታዎች የተነሱት የጎሳ ግጭቶች መሰረቱ የኢህአዲግ የተሳሳተ ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌድራሊዝም መሆኑን ሳይፍሩ መናገር አለባቸው።የተወሰኑ ጎሳዎች ስሜት ይነካል ተብሎ ዘላቂ አሸናፊውን ሃሳብ ወደጎን ማድረግ አርቆ ማየት አይመስለኝም።
ሁለተኛው ፅንፈኛው የእስልምና ኃይል (ኢህአዲግ የእስልምና ጉዳዮች ኮሚቴዎችን የሚከስበትን ማለቴ አይደለም) ኢትዮጵያን ለዘመናት ሲያተራምስ የኖረ መሆኑን እያወቁ ሰሞኑን በኦሮምያ በተነሳው ችግር ላይም እጁን እንዳስገባ እያወቁ ለስልታዊ አቀራረብ ነገሩን ወደጎን ትቶ ማለፍ ተገቢ አይደለም። አዎን! በፌድራል የተገደሉት ኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ሞትን መቃወም ተገቢ ነው።ነገር ግን ሁለት አደገኛ ኃይሎችን መቃወም ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ነው።እነርሱም የኢህአዲግን ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌድራልዝም እና በጉዳዩ ላይ በኦሮሞ ሕዝብ ስም መነገድ የሚፈልገው ፅንፈኛው አክራሪ ኃይልን።
በነገራችን ላይ ሁለቱ ማለትም ኢህአዲግ/ወያኔ እና ጎሳ ውስጥ ለመወሸቅ የሚውተረተረው ፅንፈኛው ኃይል እርስ በርስ እየተመጋገቡ መሆኑን ማየት ይቻላል።ሁለቱንም አንድ የሚያደርጋቸው ነጥቦች አሏቸው።ሁለቱም የኢትዮጵያን ያለፈ ታሪክ ጥላሸት መቀባት ይፈልጋሉ፣ሁለቱም የኢትዮጵያ አንድነት በፍቅር እና በሕብረት ከሚሆን ይልቅ ሁሉም በየጎሳው እንዲያስብ ይጥራሉ።ለእዚህም በብዙ ነገሮች ተገልጧል።ባለፈው አርሲ ላይ በ20 ሚልዮን ብር የተሰራው ሃውልት ላይ ሁለቱም ሲዘፍኑለት ሕዝብ ግን ጥቅሙ ምንድነው? እያለ ስጠይቅ ነበር።አሁንም በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ላይም ሲደጋገፉ እናያለን ትናንት ሚያዝያ 28/2006 ዓም አንድ የኢህአዲግ ደጋፊ እና በስርዓቱም ውስጥ ቦታ ያለው ዳንኤል ብርሃነ የተሰኘ ጦማሪ ጀዋር መሐመድን የገለፀበት ቃል እንዲህ ይላል ‹‹ጃዋር እኮ ታጋይ ነው - ዝም ብለህ አትማው፡፡ ይሄ የሰሞኑ ወሬው ከቀኝ ሀይሎች ድጋፍ ለማግኘት ብሎ እንጂ ለክፋት አይደለም›› መመጋገብ ማለት ይህ ነው።
ዛሬ ለሕዝቡ ትክክለኛውን ጉዳይ መናገር ካልተቻለ ነገ ኢትዮጵያን የማትወጣበት አዘቅት ውስጥ እየከተትን መሆኑን ማሰብ ይገባል። ይሉኝታ ያጠቃው ፖለቲካ ኢትዮጵያን የትም አያደርሳትም።ሁሉንም ባንዴ መናገር አይቻልም የሚሉት ስልት ለእንደዚህ አይነቱ ተግባር አዋጪ አይደለም።
ጉዳያችን
ሚያዝያ 29/2006 ዓም
No comments:
Post a Comment