ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, May 23, 2014

በሕግ አምላክ! የኢትዮጵያን ታሪክ የቆነፀላችሁበት እና ያደበዘዛቹበት አቀራረብ ይስተካከል።የመንግስት የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ድረ-ገፅን ይመለከታል።
'ስለ ኢትዮጵያ' በሚለው ስር ''ታሪክ''  አምድ ላይ 'የመንግስት የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች' ድረ-ገፅን ኢትዮጵያን ያቀለለ ወረድ ሲል ደግሞ ያጣመመ የታሪክ አቀራረብ ይታይበታል።
ለመጨረሻ ጊዜ ድረ ገፁ የታረመው በ 2011 ዓም እ አ አቆጣጠር ነው ይላል ከድረ-ገፁ ላይ የሚነበበው የቀን ፅሁፍ።ያኔ አቶ በረከት አርመው አሳልፈውት ከሆነ ዛሬ በታሪክ ባለሙያዎች እንደገና መታየት አለበት።ድረ-ገፁ ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቅበት አገላለፅ 'ውስጠ ወይራ' ነች።

ይህ ገፅ ማለት ለውጭ ሃገራት ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርጉት ማናቸውም ግንኙነት በተለይ በሚድያ ዘርፍ ላሉት እንደ ዋና በር የሚታይ ነው።ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ጋዜጠኞች መሙላት የሚገባቸው ፎርም ሁሉ የሚገኘው በእዚሁ ገፅ ላይ ነው።ስለ ሀገራችን በውጭ ሃገራት የትምህርት ተቋማት ሁሉ ''ኦፊሻል''  የመንግስት ድረ-ገፅ ስለሆነ የተፃፈው ሁሉ ለማጣቀሻነት ሊቀርብ ይችላል ማለት ነው።ለእዚህ ነው ድረ-ገፁ የሚለው ነገር ሁሉ አነሰም በዛ አዲስ ለሚወለዱትም ሆነ ለውጭ ሀገር ዜጎች የሚሰጠው ፋይዳ የበዛብኝ እና ኢትዮጵያዊ አቀራረቡ የኮሰሰብኝ።

እነኝህን አንብቡ እና ቁንፅልነቱን እና የትኩረት አቅጣጫውን ታዘቡ።የመጀመርያዎቹ መንግሥታት በሚለው ስር እንዲህ ይላል።

''የመጀመሪያዎቹ መንግስታት''
''በ፰፻ ዓመተ ዓለም አካባቢ ደአማት የሚባል መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያና ኤርትራ ተቋቋመ በሰሜን ኢትዮጵያ የምትገኘው የሀ የደአማት ዋና ከተማ ነበረች። በየመን የሚኖሩት ሳባውያን በደአማት ላይ ተፅዕኖ እንደነበራቸው የሚታመን ሲሆን ይህ ተፅዕኖ ምን ያህል እንደሆነ ግን በእርግጥ አይታወቅም። ወደ ፬፻ ዓመተ ዓለም አካባቢ የደአማት መንግስት ከስልጣን ሲወድቅ በትናንሽ መንግስቶች ተተካ። ከነዚህ ትናንሽ መንግስቶች አንዱ አክሱም ሲሆን አካባቢውን እንደገና በአንድነት ለመግዛት ችሎ ነበር።''
በኢትዮጵያ እና ''በኤርትራ ተቋቋመ'' ሲል በወቅቱ ኤርትራ የምትባል ሀገር መች ነበረች? ብላችሁ ብትጠይቁ ልክ ብላችኃል። ታሪክ በወቅቱ በነበሩት የቦታ ሁኔታዎች ወይንም ደግሞ  ''አሁን ኤርትራ ተብላ በምትጠራው'' ብሎ መፃፍ አንድ ነገር ነው። ''በኢትዮጵያ እና በኤርትራ'' የሚለው አፃፃፍ ግን ፈፅሞ ስህተት ነው።

በሌላ በኩል ንግስት ሳባም ሆነች ሳባውያን እንዲሁም የሳባ ፅሁፍ መነሻው ኢትዮጵያ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳናል።''የሳባ ታሪክ ከየመን ይነሳል'' የሚሉ የታሪክ መሰረት የሌላቸው ፅሁፎች የሚነዙት ከየመን ነው።መቀመጫዋም ኢትዮጵያ መሆኑ ተፅኖ የነበረው ከኢትዮጵያ ሳባ ነው እንጂ ከየመን አይደለም።

በስድስተኛው ክ/ዘመን የቅዱስ ያሬድ ታሪክን ቀጥሎም የመሐመድ ቤተሰቦች ወደ ኢትዮጵያ መምጣትን እና በ12ኛው ክ/ዘመን የነበረው የቅዱስ ላሊበላ ታሪክን በሙሉ ይዘል እና  15ኛው ክ/ዘመን ላይ እንዲህ ይላል -''

በ፲፭ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ ኢትዮጵያ ከአክሱም ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአውሮፓ ጋር ግንኙነት ጀመረች'' ይላል።
ኢትዮጵያ ከአክሱም መንግስት መውደቅ በኃላ ከውጭ ሃገራት ጋር የነበራት ሌሎች ግንኙነቶች አልነበሩም?

ይቀጥላል -----

አፄ ቴዎድሮስ መውደቅ ምክንያቱን ሲናገር ''የሰሜን አሮሞዎችና ትግሬዎች አመፅና የግብፆች ተደጋጋሚ ድንበር መጣስ የአፄ ቴዎድሮስ ስልጣን እንዲዳከም አደረጉት።''
እዚህ ላይ ፀሐፊው ወይንም አራሚው  በአራዳ ልጆች አባባል ''እራሱን አስፎገረ'' ተመልከቱ ''በዘር የተቃኘች ማሲንቆ'' ስትመታ።ለአፄ ቴዎድሮስ መውደቅ ምክንያቱ የዘር ጉዳይ ነው? እርግጥ ነው እንግሊዞችን እየመሩ መቅደላ ድረስ በማምጣት በኃላ አፄ ዮሐንስ ተብለው የነገሱት (በቀድሞ ስማቸው ደጃች በዝብዝ ካሳ) ይሁኑ እንጂ አፄ ቴዎድሮስን ከዳር ሃገሩ ሕዝብ አጠገባቸው ያለው የመሃል ሀገር ሕዝብ ብዙ ችግር ፈጥሮአል።ለመሆኑ ''የሰሜን ኦሮሞ'' የሚባል በኢትዮጵያ ታሪክ አለ?

ዝቅ ስትሉ ኢትዮጵያ በእንግሊዝ እና በአርበኞች ጣልያንን እንዳሸነፈች ይናገር እና ግን ጣልያን ስታሳዝነው ፈፅሞ እዚህ ቦታ የመግባቱ ፋይዳ እስከማይገባችሁ ድረስ ጣልያኖች እንዴት ሽምቅ ይዋጉ ነበር ለማለት እንዲህ ያላል - ''ግን እስከ 1943 እ.ኤ.አ. ድረስ አንዳንድ ጣልያኖች በደፈጣ ያለ ስኬት ይዋጉ ነበር።'' ጉዳዩ ውግያ ነው ከድል በኃላ አንዳንድ ተባራሪ ጣልያን እንደሚኖር ይታወቃል። ታሪክ ላይ ግን መክተብ እና ሽምቅ ይዋጉ እንደነበር ለመፃፍ መዋተቱ የኢትዮጵያን ድል ማድረግ ላያደበዝዘው የመጨነቁ  ፋይዳው ምንድነው?

ይቀጥላል----

የሱማሌ ጦርነትን ''የኡጋዴን ጦርነት'' ይላል ድረ-ገፁ።በእዚህ ጦርነት ከ 300 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ሚሊሻ ከአባት ጡረተኛ ጋር ዘምተው የሀገራቸውን ድንበር ማስከበራቸውን አንዳች ነገር ሳይተነፍስ ሙሉ በሙሉ በውጭ ኃይል ኢትዮጵያ እንዳሸነፈች ሊነግረን ይሞክራል።ሌላውን ዋሹን ግን ይህንን ታሪክ የሚነግሩን አባቶች ዛሬም በሕይወት አሉ እና አትዋሹን፣ታሪኩን አታደብዝዙ።
አዎን የውጭ እርዳታ ነበር የኩባ ወታደሮችም ተራድተውናል ግን ''የኢትዮጵያ መንግስት'' የተባለ የቃል አቀባዩ ቢሮ የፃፈው የኢትዮጵያ ታሪክ ሙሉ በሙሉ የሀገሩ ሰማዕታትን ክዶ በውጭ ኃይል ነው ያሸነፍነው ብሎ መፃፍ ምን አይነት ሞራላዊ ሥራ ነው?
 ስለ ሱማሌ ወረራ ድረ-ገፁ የፃፈው ይህንን እና ይህንን ብቻ ነው።
''በ1977 እ.ኤ.አ. ሶማሊያ ኦጋዴንን በመውረሯ የኦጋዴን ጦርነት ተነሳ። በሶቪየት ሕብረት፣ ኩባ፣ ደቡብ የመን፣ ምስራቅ ጀርመንና ሰሜን ኮሪያ የመሳሪያ እርዳታ እንዲሁም ወደ 15 ሺህ በሚቆጠሩ የኩባ ወታደሮች ድጋፍ አማካኝነት ደርግ ኦጋዴንን እንደገና መቆጣጠር ቻለ።''
በመሰረቱ ጦርነቱ የደርግ ጦርነት አይደለም።የኢትዮጵያ ጦርነት ነው።15 ሺህ የኩባ ወታደርን ለመጥቀስ የተጋ ብእር ምነው በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሚሊሻዎችን እረሳብን?

ድረ - ገፁ የኢትዮጵያን ታሪክ ''የቅርብ ጊዜ'' በሚል ስር ማጉላት የፈለገው ዋናውን አላማውን የሚያመላክት ነው። ልብ በሉ የቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ ይልና የሚናገረው ስለ ኤርትራ ነው። እንዳለ ላስነብባችሁ።

''በቅርብ ጊዜ''

''በ1993 እ.ኤ.አ. በተካሄደውና የተባበሩት መንግሥታት በታዘበው ሕዝበ ድምፅ፣ ከ99 ከመቶ በላይ የሚሆነው የኤርትራ ሕዝብና በውጭ ሀገር የነበሩ ኤርትራውያን ከኢትዮጵያ መገንጠልን መርጠዋል። በሜይ 24፣ 1993 እ.ኤ.አ. ኤርትራ ከኢትዮጵያ ነፃነቷን አወጀች።
በሜይ 1998 እ.ኤ.አ. የድንበር ውዝግብ እስከ ጁን 2000 እ.ኤ.አ. ወደቀጠለው የኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት አምርቶአል። ይህ ጦርነት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን ጎድቶአል''

 እዚህ ላይ የቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ  የኤርትራ ከኢትዮጵያ መነጠል ከተፈፀመ ከ20 ዓመት በኃላ በ 2011 ዓም እ አ አቆጣጠር ለመጨረሻ ጊዜ የታረመው እና የኢትዮጵያን ታሪክ የፃፈው የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ድረ-ገፅ የሚነግረን ሌላ ነው።99% ከኢትዮጵያ መነጠላቸውን ለመተረክ ከመሮጥ ለምን የታሪኩን መነሻ አትነግሩንም?
በመንግስት ቢሮክራሲ ውስጥ ገብተው የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያጣምሙትን ማጋለጥ ይገባል።ታሪካችን በኢትዮጵያውያን ይፃፍ!

ጉዳያችን 
ግንቦት 15/2006 ዓም/ሜይ 23/2014 

No comments: