ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, May 2, 2014

በአምቦ እና በሌሎች ከተሞች በተማሪዎች እና በነዋሪዎች ላይ የተፈፀመው አሳዛኝ ግድያ በፅኑ እየኮነንን - ዛሬም ለሁላችንም ከጎሳ ፖለቲካ ይልቅ ኢትዮጵያዊነት መጠለያችን መሆኑን አበክረን እንናገራለን። (የጉዳያችን አጭር ማስታወሻ)



ኢህአዲግ የጎሳ ስሜቶችን በቻለው መጠን ለማራገብ መመሞከሩን እንደ ትልቅ ድል ሲቆጠረው ዓመታት አስቆጥሯል።''ከመቶ ዓመታት በፊት ጡት ተቆርጦ ነበር'' በሚል ከ ሃያ ሚልዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ  በአርሲ ሃውልት መመረቁን ኢቲቪ ሲነግረን እና በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ላይ የስርዓቱ ደጋፊዎች መሆናቸው የሚናገሩ ግለሰቦችም የቀደሙ የኢትዮጵያን መሪዎች እየነቀፉ የሃውልቱ መሰራት ''የኢህአዲግ የጎሳ ፖለቲካ ድል'' እንደሆነ ሲነገሩን ገና ሳምንታት መቆጠራቸው ነው።  

ኢህአዲግ በአምቦ ባዶ እጃቸውን ለጥያቄ ሰልፍ የወጡ ወጣቶችን በጠራራ ፀሐይ ሲገድል ፍትሃዊ እንደሆነ ሊነግረን ይሞክራል።ይህ በእውነት በኢትዮጵያዊነታችን እጅግ የሚያም ነው።አሁንም ሁኔታዎች ሁሉ የሚያረጋግጡት የኢህአዲግ የጎሳ ፖለቲካ  በሚቃወሙት ዘንድ ብቻ ሳይሆን ተመሳሳይ የጎሳ የፖለቲካ  ዓላማ ለሚያራምዱትም  በቂ ምላሽ ሲሰጥ አለመቻሉን ነው።

ይህ ብቻ አይደለም ኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያዊውን ከኢትዮጵያውነቱ የተለየ ስም በመስጠት ለማስፈራርያነት የሚጠቀሙት ፅንፈኛ የጎሳ ፖለቲከኞች ከኢህአዲግ አስተሳሰብ ብዙም ባልዘለለ መልክ ነገሮችን ጫፍ ከመውሰዳቸውም በላይ የኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ትግል እንደግመል ሽንት ወደኃላ እንዲሄድ ሲያደርጉት እንደነበረ ሁሉ አሁንም ጥያቄዎችን በኢትዮጵያዊነት ስሜት ከማቅረብ ይልቅ የመረጡት የጎሳ ፖለቲካ የትም  ሊያደርስ አይችልም።ሕዝብ በአምባገነንነት ስቃዩን እያየ ከመቶ ዓመት በፊት የነበረ ታሪክ ላይ መከራከር እና አሁንም ከመቶ ዓመታት በፊት የነበሩ ንጉስን በዘፈኑ አሞገሰ እያሉ አንድን ዘፋኝ ላይ ዘመቻ ከፍቶ 'ያዙኝ ልቀቁኝ' የሚሉ ፖለቲከኞች ድሮም ለኦሮሞ ሕዝብ አስበው ነው ብሎ መናገር በራሱ በፖለቲካ መቀለድ ነው።

ሰሞኑን በተለያዩ የሀገራችን ከተሞች እና በተለይ በአምቦ የተፈፀመውን ግድያ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች አውግዘውታል።በመጪው ሰኞ ደግሞ ''ደማችን ደማችሁ ነው'' በሚል መፈክር ስም በዋሽግተን ዲሲ ኢትዮጵያውያን ሰልፍ እንደሚወጡ ተነግሯል። የኢህአዲግን የተዛባ የችግር አፈታትን እና የጎሳ ፖለቲካውን ስንቃወም አብረን ማስተዋል የሚገባን ታሪክ ትናንትም ዛሬም ያረጋገጠልንን  ቁም ነገር ነው። ይሄውም ለሁላችንም ከኢትዮጵያዊነት ሌላ መጠለያ የለንም።

ጉዳያችን 
ሚያዝያ 25/2006 ዓም 



No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።