ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, April 28, 2022

ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው ቡድኖች የየዋህ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞችን የእምነት ስሜት ቆስቁሰው ወደ ግጭት ሊመሩን ሲሞክሩ ልንታለል አይገባም።

ኢትዮጵያውያን ታዳጊ ሙስሊም እና ክርስቲያን አዲስ አበባ ሙዚየም በር ላይ 
Photo = Adam Jones
  • በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ወደ ውጭ የፈረጠጠው ''የሸኔ የውስጥ አርበኛ'' ከሽብርተኛው የህወሃት ቡድን ጋር ከፈረጠጠባቸው አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ ሃገሮች ውስጥ ሆኖ የሰሞኑን በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች እና ሙስሊም ወገኖቻችን መሃከል ግጭት እንዲፈጠር ሲያስተባብር ነበር።
===============
ጉዳያችን / Gudayachn
===============

በኢትዮጵያ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ለማጋጨት ሙከራ ሲደረግ ዛሬ አዲስ አይደለም።ለ27 ዓመታት ህወሃት ኢትዮጵያን ሲመራ ሆን ብሎ የሃይማኖት ግጭቶች እንዲነሱ ሰርቷል። ክርስቲያኖች የጥምቀት በዓል ሊያከብሩ አንድ ቀን ሲቀራቸው ሙስሊሞችን የደገፈ የመሰለ መግለጫ ሲወጣ፣ የሙስሊም ወገኖቻችን ድምጻችን ይሰማ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የሙስሊም መንግስት ይመስረት እያሉ ነው የሚል የሃሰት ወሬ በክርስቲያኖች መሃከል ይዘራ ነበር።ህዝብ ከህዝብ ጋር የሚነጋገርበት የራሱ ልዩ ቋንቋ ስላለው ይህ ሁሉ ከንቱ ሙከራ ሆኖ አልፏል።

ሰሞኑን መንግስት በሸኔ ላይ የጀመረው በድሮን የታገዘ መጠነ ሰፊ ዘመቻ በራሱ በመንግስት ውስጥ ሆነው የሸኔን እና የሸኔ መመታት የህወሃት አንዱ ክንፍ መመታት መሆኑ ያስበረገጋቸው ሁሉ አንድ ዓይነት ግርግር ካልፈጠሩ በቀር የውድቀታቸው መጨረሻ እንደሆነ ገባቸው። በእዚህ ደግሞ ከውጭ ያሉ የባዕዳን አዝማቾቻቸው ጭምር የውስጥ ተላላኪዎቻቸው ላይ የሚወሰደው እርምጃ አስደንግጧቸው ከርሟል።ባዕዳኑ በከፍተኛ ደረጃ ኢትዮጵያን ከማወክ ባለፈ ይበትንልናል ብለው በቅደም ተከተል ያስቀመጡት ቀዳሚው ሽብርተኛው ህወሃት ሲሆን በማስከተል የቤንሻንጉል እና የኦነግ ሸኔ እንቅስቃሴዎች ናቸው። ህወሃት በህዝብ ክንድ ተመትቶ ወደ ጎሬው ሲገባ በሎጀስቲክ እና በምክርም ጭምር ከተረፈው የህወሃት ቡድን ጋር አቀናጅተው ኢትዮጵያን ለማወክ ተስፋ ያደረጉበት ሽኔ ከበርካታ ቦታዎች ሰሞኑን በመከላከያ ሰራዊት እየተመታ ሲጠራረግ አንዳንድ የቡድኑ ደጋፊዎች ወደ ውጭ ሃገር መፈርጠጣቸው የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም።

ይህ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ወደ ውጭ የፈረጠጠው የሸኔ የውስጥ አርበኛ ከሽብርተኛው የህወሃት ቡድን ጋር ከፈረጠጠባቸው አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ ሃገሮች ውስጥ ሆኖ የሰሞኑን በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች እና ሙስሊም ወገኖቻችን መሃከል ግጭት እንዲፈጠር ሲያስተባብር ነበር።ለግጭቱ የገንዘብ ድጋፍ የተገኘውም ሆነ በየዋሃን እምነታቸውን በሚያከብሩ ክርስቲያን እና ሙስሊም ወገኖቻችን መሃከል የተደራጁ በወገናቸው ደም የሚነግዱ ተከፋዮች መዋቅራቸውን አንዳንድ የክልል ባለስልጣናት ቢሮ ውስጥ ሁሉ በገንዘብ ኃይል ለመዘርጋት የሞከሩ ሲሆን የሰሞኑ የጎንደርም ሆነ የዛሬው በወራቢ የደረሱት ጥቃቶች የእነኝህ ተከፋዮች ስውር እንቅስቃሴ ውጤቶች ናቸው።በጎንደር ባብዛኛው ሙስሊም ወገኖቻችን ሲጠቁ፣በወራቢ ደግሞ ክርስቲያን ወገኖቻችን ተጠቅተዋል። በሁለቱም ቦታዎች ቤተክርስቲያን እና መስጊድ ላይ ጥቃት ተፈጽሟል። የጥቃቱ አነሳሾችም ሆኑ ጥቃት አድራሾቹ ላይ መንግስት ግልጽ በሆነ መንገድ ለፍርድ ማቅረብ እና ቅጣታቸውም ህዝብ አስተማሪ መሆን ይገባዋል።

በሙስሊም ወገኖቻችን መሃከል ሆነው ክርስቲያኖችን የሚያስቆጡ ድርጊቶች መፈጸም፣ በክርስቲያን ወገኖቻችን መሃከል ሆነው ሙስሊም ወገኖቻችንን የሚያበሰጭ እና የሚያጋጭ ተግባር እንዲፈጸም ማድረግ እና በሚያስገኙት የደም ማስፈሰስ ስፋት እና ጥልቀት እየታየ በልዩ ልዩ መንገዶች የሚከፈላቸው የራሳችን ወገኖች ተልዕኮ የሰሞኑ ክስተት ውጤት ነው። ድርጊቱን ደግሞ የኢትዮጵያ ባላንጣ የሆኑ የቅርብ ሃገሮች በስለላ መዋቅሮቻቸው ከጀርባ የሚደግፉት እና ያገኙትን ቀዳዳዎች ሁሉ በመጠቀም የማባባስ ስራዎች ላይ ተጠምደው ከርመዋል። ተከፋይ አጋጮች መሬት ላይ የሚሰሩት ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ ሚድያ የሚያጣሉ እና አንዳንዶቹ በክርስቲያንም ሆነ በሙስሊም ስም ዩቱበር እና ፌስቡክ ከፍተው ሁለቱም ላይ የሚያጋጩ ጽሑፎች እየለጠፉ ሕዝቡን ለማባላት የሚጥሩ ናቸው። ለእዚህ ነው ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ዝም ብለው የነበሩ በክርስቲያንም ሆነ በሙስሊም ወገኖቻችን የሚታወቁ ተከፋይ የሃይማኖቱ አስተማሪ ተብዬዎች ቁስል እየፈለጉ እና ያሉ መለስተኛ አለመግባባቶችን እያሳበጡ ለመቀስቀስ ከየጠፉበት ብቅ እያሉ መሆናቸውን መመልከቱ በቂ ማስረጃ ነው።እነኝህ ተከፋዮች መምሕራን ተብዬዎች በመገናኛ ብዙኃን የተሰሙ መለስተኛ ግጭቶች የሕዝቡን ስሜት እንዲነኩ አድርገው እየጮሁ እና ስሜት እንዲኮረኩር አድርገው በመንገር አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳ ስልታዊ በሆነ መንገድ ይቀሰቅሳሉ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የተንኮል ዓይነቶቹን መለየት አለበት። መሬት ላይ ያለው እውነታ የጽንፍ አስተሳሰቦች አሉ።ሆኖም ግን ብዙኃኑ ክርስቲያንም ሆነ ሙስሊም ወገናችን በየራሱ ውስጥ ያሉትን የጽንፍ አስተሳሰብ አራማጆች ፈጽሞ አይቀበላቸውም።ይልቁንም ከሁሉም የመንፈሳዊ አገልግሎቶች ከጽንፍ ባለፈ የፖለቲካ አስተሳሰብ አራማጆችን በቻለው አያቀርብም፣ይከላከላል።ሆኖም ግን እነኝህ ተከፋይ አጋጮች ትንሽ የመግቢያ ቀዳዳ የሚያገኙት መለስተኛ ግጭቶች ታይተው የህዝብ ስሜታዊነት በሚያይልበት እና እነርሱም የጥላቻ ቅስቀሳቸውን በሚያቀጣጥሉበት ጊዜ ነው።ባጭሩ ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው ቡድኖች የየዋህ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞችን የእምነት ስሜት ቆስቁሰው ወደ ግጭት ለመምራት ሲሞክሩ ልንታለል አይገባም።ከአንደኛው ክ/ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ የኖረው ክርስትናም ሆነ ከ6ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ ያለው የእስልምና እምነቶች ዛሬ በተከፋይ የፖለቲካ ከሳሪዎች እንደእንግዳ አይተያዩም።እንንቃ!
=================////==============

No comments:

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታላቅ ተልዕኮ የሚኖረው ሀገራዊ የምምክር ኮሚሽን በተመለከተ ምን ያህል እናውቃለን?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባካተተ መልኩ አዋቅሯል። በእዚህ ጽሑፍ ስር የሚከተሉት ነጥቦች ምላሽ ያገኛሉ፡  ኮሚሽኑ እንዴት ተመሰረተ?  የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመ...