ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, April 19, 2022

ኦነግ ሸኔ ከኦሮምያ ክልል በቶሎ ካልተወገደ ፋኖ መላው የአማራ ክልልን ሊቆጣጠር ይችላል።ሸኔ በኦሮምያ ፋኖ በአማራ ተሰማርተው ኢትዮጵያ የጦር አበጋዞች አገር እንዳያደርጓት ጥንቃቄ ያስፈልጋል።

ፋኖ፣ፋኖን ከ50 ዓመታት በፊት ያዜመው ድምጻዊ  ካሣ ተሰማ 
  • አሁን ያለንበት ከስጋቱ ሁሉ በጣም ጧት ላይ ነን።ሆኖም ግን አስፈላጊው ስራ በመንግስትም ሆነ በህዝብ በትብብር ካልተሰራ ቀትርም ምሽትም ይመጣል።
===============
ጉዳያችን / Gudayachn
===============
አገር ከብሔራዊ የጦር ኃይሏ ውጭ ምንም ዓይነት አደረጃጀት ቢኖረው ሌላ በሺህ የሚቆጠር የጦር ኃይል እንዲንቀሳቀስ የማንም አገር ሕግ አይፈቅድም።የማንኛውም መንግስት አንዱና ዋናው ግዴታውም ሰላም እና ጸጥታ ማስከበር ነው።ጸጥታን ማስከበር ድህነት በተስፋፋበት፣የምጣኔ ሃብቱ በተጎሳቆለበት ሁኔታ በራሱ ከባድ ፈተና አለበት።ምክንያቱም በቀላል የጥቅማጥቅም ድለላ ወጣቶችን በቀላሉ ወደ ጥፋት መንገድ መምራት የሚችል ከባቢያዊ ሁኔታ ይፈጥራል።ኢትዮጵያ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሕዝቧ ወጣት ነው።ይህ ኃይል ደግሞ ከሥራ ማጣት ችግሩ ጋር ተዳምሮ ብቸኛ የሥራ መስክ ጠብመንጃ አንግቦ መንቀሳቀስ እንዳይሆን ያሰጋል።

ኦነግ ሸኔ መንግስት ባለበት ሃገር አንድ ጊዜ ከሱማሌ አዋሳኝ መንደሮች፣ካለፈው እሁድ ጀምሮ ደግሞ በሸዋ ሮቢት ዙርያ ጥቃት ከፍቷል። እዚህ ላይ የሰሜን ሸዋ የመንግስት ተጠሪዎች በተለይ በሸዋ ሮቢት ዙርያ ዳግም የተከፈተው ጥቃት በግለሰቦች ግጭት የተነሳ እንደነበር ቢገልጹም ሁኔታው ግን እንደዛ እንዳልሆነ ለማወቅ ብዙም ምርምር አይጠይቅም።የኢትዮጵያ ከተሞች በኦነግ ሸኔ በተፈናቀሉ ስዱዳን እየተጣበቡ ነው። ደብረብርሃን ለእዚህ ጥሩ ምሳሌ ነች። ደብረብርሃን በኦነግ ሸኔ በሰሜን ሸዋ ባደረሳቸው ጥቃቶች ብቻ ሳይሆን በወለጋ ባደረሰው ጥቃትም የተፈናቀሉ ደብረ ብርሃን ከተማ ከትመዋል። 

የኦነግ ሸኔ በቶሎ አለመጥፋት አሁን ባሉት አነስተኛ ከተሞች የሚደረግ ጥቃት ብቻ አይሆንም መዘዙ። በቀጥታ ወደ የለየለት የከተማ የሽብር ቡድን እራሱን አያደራጅም ማለት አይቻልም።ለእዚህ ደግሞ ዋና ምክንያቱ የሸኔ የገንዘብ፣የስንቅ እና ትጥቅ ምንጭ በስልጣን ላይ ያሉ የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት እና የጸጥታ ጉዳይ ኃላፊዎች ጭምር መሆኑ ነው። መንግስት ባሉት የጸጥታ መዋቅሩ በሚገባ የሕዝቡን የጸጥታ እና ደህንነት በሚገባ ካላስጠበቀ ሕዝብ ከውስጡ የወጡትን ፋኖ እንዲጠብቀው እና ኢመደበኛ በሆነ መልክ ሁሌም እንዲኖር ይፈልጋል።በእዚህ መሃል ደግሞ በቅንነት የቆመው የፋኖ አባል  ቀድሞ ባላሰበው መንገድ ሊገፋ ይችላል።

ጉዳዩ አደገኛ ነው። ፋኖ በተለይ በኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ያለው ታሪካዊ ዳራ እና በታሪክም ለኢትዮጵያ ነጻነት የፋሺሽት ጣልያንን ከኢትዮጵያ ማስወጣት ጀምሮ የተጻፈ ታሪክ አለው።በስሙ ሲዘፈንለት፣ግጥም ሲገጠምለት እና የራሱ ሕዝባዊ ቅርጽ ያለው ታሪክ አለው። በቅርቡ ከህወሃት ጋር በተደረገው ጦርነትም የአማራ ክልልን ከኢትዮጵያ መከላከያ ጋር በአንድነት አኩሪ ታሪክ ሰርቷል። ይህ በራሱ የጠለቀ ማኅበራዊ መሰረት እንዳለው በቀላሉ መረዳት ይቻላል።

በሌላ በኩል ኦነግ ሸኔ የኦነግ ጽንሰሃሳብ ውሉደ ውሉድ ወይንም ውላጅ ነው።ጽንሰ ሃሳቡ የጠራ የፖለቲካ ግብ አይኑረው እንጂ ጧት ማታ የሚያዜመው አማራውን፣ነፍጠኛውን ማጥፋት እና የኦሮምያ መንግስት መመስረት የሚሉት ሃሳቦች የት እንደሚያደርሱ ሳያውቅ የሚናውዝ እሳቤ ባለቤት ነው። የመናወዙ ዲግሪ ለመረዳት የኦሮምያ ክልልን ያሏትን የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች ሳይቀር የሚያወድመው ይሄው የኦነግ ውላጅ የሆነ ሃሳብ የተሸከመው ሸኔ ነው። 

ሸኔ በቀጥታ ፋሺዝም ነው። ፋኖ የቀደመ ታሪኩም ሆነ አሁን ያለበት ደረጃ ሕዝብ ተከላካይ ነው። ፋኖ በቀድሞ ታሪኩ ሂደቱ ግልጽ ነው። ይሄውም ጦርነት ሲመጣ ሴት ወንድ ሳይል ይዘምታል፣የሃገር ሰላም አስተካክሎ ተመልሶ ገበሬው ወደ ግብርና ሰራተኛው ወደ ስራው ይመለሳል።አበቃ! አሁን ባለንበት ጊዜ ሽብርተኛው ህወሃት ገና ከትግራይ ህዝብም ጫንቃ ላይ ገና አልተነቀለም፣ኦነግ ሸኔም በዘር ላይ በተመሰረተ የጥላቻ ወረራ ገና አልቆመም።ስለሆነም ፋኖ የቤቱ እና የልጆቹ ጉዳይ ካላስገደደው በግንባር ጥቂት ጊዜ መቆየቱ ጉዳት የለውም። ይህም ግን ያለው ውስጣዊ አመራር ወደ ሌላ አደገኛ መንገድ እንዳይመሩት ጥንቃቄ አያስፈልገውም ማለት አይደለም።ምክንያቱም የአገር ቀዳሚ መርሁ አንድ መከላከያ ሰራዊት ነውና።

በእዚህ ሁሉ መሃል ኦነግ ሸኔ ካልጠፋ ግን ፋኖ ወደ ቤቱ የመመለስ እድሉ ላይኖር ይችላል ብቻ ሳይሆን በሂደት የአማራ ክልልን በሙሉ የመቆጣጠር ሁኔታዎች አይፈጠርም ማለት አይቻልም።ለእዚህ ደግሞ ዋናው መሰረታዊ አመላካች ጉዳይ ህዝብ ከመደበኛ ሰራዊቱ ባላነሰ ባንዳንድ ቦታዎች ፋኖ በበለጠ ሁኔታ ይጠብቀኛል የሚል ሕዝብ እየተፈጠረ መሆኑ ነው። በእዚህ አስተሳሰብ ደግሞ በህዝቡ ላይ ልንፈርድበት ምንም ዓይነት ሞራላዊ ሁኔታ አይኖርም።ምክያቱም መንግስት የሰላም እና የጸጥታ መጠበቅ ስራውን በሚገባ መወጣቱን ማሳየት ብቸኛው አማራጭ ነውና።

ለማጠቃለል ኦነግ ሸኔ ከኦሮምያ ክልል በቶሎ ካልተወገደ ፋኖ መላው የአማራ ክልልን ሊቆጣጠር ይችላል።ሸኔ በኦሮምያ ፋኖ በአማራ ተሰማርተው ኢትዮጵያ የጦር አበጋዞች አገር እንዳትሆን ያሰጋል።አሁን ያለንበት ከስጋቱ ሁሉ በጣም ጧት ላይ ነን።ሆኖም ግን አስፈላጊው ስራ በመንግስትም ሆነ በህዝብ በትብብር ካልተሰራ ቀትርም ምሽትም ይመጣል።ለእዚህ ሁሉ መፍትሄው ችግሮቻችንን በሚገባ መረዳት ነው። የኦነግ ሸኔ አረመኔያዊ ተግባርን ከአማራ ክልል እና ከሱማሌ ክልል ባልተናነሰ በኦሮምያ ክልልም ይታወቃል። ይህ ሁኔታ ግን ወደፊት እንዳለ ላይቀጥል ይችላል። ለምሳሌ ኦነግ ሸኔ ፋታ ተሰጥቶት ከኖረ ፋኖ አገንግኖ ወጥቶ ከሸኔ የመከላከል ብቸኛ አውራ ሆኖ ለመውጣት ታሪክ በራሱ ይገፋዋል። ይህ ደግሞ ከላይ በርዕሱ እንደተገለጸው ኢትዮጵያ የጦር አበጋዞች አገር እንዳትሆን ያሰጋል።ለእዚህም ዛሬ የሚሰራው አገራዊ የጋራ ስራ ወሳኝ ነው። በእዚህ ስራ ደግሞ መተማመን የሚፈጥር አሰራሮች መንግስት በሁሉም መስክ ማስፈን፣ኦነግ ሸኔ ላይ የሚደረገው ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠሉ ፋይዳው ብዙ ነው።
============////============


No comments: