በአማራ ክልል ታዳጊዎችን ለጽንፍ ተግባር የሚመለምሉ አሉ።
===============
ጉዳያችን / Gudayachn
===============
ጽንፈኝነት ዘር የለውም። የእገሌ ጎሳ ሲሰራው ስህተት እና ወንጀል፣የእንቶኔ ጎሳ ሲሰራው ትክክል ሊሆን አይችልም። ነጩን ነጭ፣ጥቁሩን ጥቁር ብሎ ኢትዮጵያዊነት ከሁሉም አቅጣጫ ገንኖ እንዲወጣ ማድረግ በምንም ዓይነት ድርድር ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም።ኢትዮጵያ ዘመናትን ተሻግራ ዛሬ ላይ የደረሰችው በጎሳቸው እያሰሉ ፍትሕ የማይሰጡ እውነተኛ መሪዎች ስለነበሯት ነበር። ህዝብን ወደ እልቂት የሚመራ ማናቸውም ዓይነት ተግባር ከየትኛውም ጎሳ ቢመጣ ኢትዮጵያን የሚል በሙሉ ሊቃወመው የሚገባ ነው።
ይህ በእንዲህ እያለ በአማራ ክልል ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 19 ዓመት የሆናቸው ታዳጊዎችን በተለያዩ ሰዋራ ቦታዎች ወታደራዊ ስልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን መረጃዎች ወጥተዋል።ስልጠና እንዲሰጡ የሚያደርጉት ደግሞ የጽንፈኝነት እንቅስቃሴ ለማራመድ ዕቅድ በያዙ አካላት መሆኑን መረጃው ያሳያል። እነዚህ በታዳጊዎች ህይወት ቁማር ለመጫወት የቆረጡ ሰዎች በተጠቀሰው የእድሜ ክልል ብቻ የሚገኙ የአማራ ተተኪ ትውልዶች እንዲመለምሉና ጫካ ገብተው የትጥቅ ትግል እንዲጀምሩ በወሰኑት መሰረት በርካቶች እንደ እሳት እራት በከንቱ መስዋዕት ለመሆን እየተዘጋጁ ይገኛሉ፡፡ ይህ የአማራ ክልል ወደ እርስ በርስ ግጭት እንዲገባ ብቻ ሳይሆን ክልሉ ለኢትዮጵያ ካለው ጉልህ ሚና አንጻር የእዚህ ዓይነት የጽንፍ እንቅስቃሴዎች ለኢትዮጵያ ትልቅ አደጋ አለው።
የኢትዮጵያ የቅርብም ሆኑ የሩቅ ጠላቶቿ በአሁኑ ጊዜ ትልቁ ፍላጎታቸው በኢትዮጵያ የእርስበርስ ጦርነት እንዲነሳ በቻሉት መንገድ በተለያየ መንገድ ያኮረፉ ግለሰቦች በገንዘብ በመደገፍ ወደ ጽንፍ እንቅስቃሴ እንዲገቡ ማድረግ ነው። የሚገርመው ታዳጊዎችን የመመልመሉ ተግባር ከአልሸባብ ጭምር መማር አለብን የሚል አቋም ማንጸባረቁ አስገራሚው ጉዳይ ነው።በእዚህ እኩይ ተግባር የተሰማሩ ነገ ክልሉን ማባርያ ወደ የሌለው እልቂት ከትተው ሕዝቡን ወደ የማይወጣው ማጥ ውስጥ ብቻ የሚከቱ ሳይሆኑ እርስ በርሱ ተከባሮ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ ወደ የባሰ ግጭት ከትተው መጪውን የኢትዮጵያውያንን ሕይወት የሚያጨልም አደገኛ አካሄድ በመሆኑ ከወዲሁ ህዝብ አውቆ ነቅቶ እና ተግቶ መቀመጥ አለበት።
ይህ በእንዲህ እያለ የትግራይ ወጣቶችን ያስጨረሰው ሽብርተኛው ህወሃት የትግራይ እናቶች ልጆቻችን የት አሉ? ብለው ሲጠይቁ ''የትግራይ ወጣቶችን ቆጥሮ ያስረከበኝ የለም '' የሚል የትዕቢት መልስ ከሰጠ በኋላ የትግራይ እናቶች በቤታቸው በድብቅ ከማልቀስ ሌላ አማራጭ አላገኙም።በኢትዮጵያ ያለውን የትግራይ ወጣት ያስጨረሰው ሽብርተኛው ሕወሃት ወደ ሱዳን ዘልቆ ታዳጊዎችን መመልመል ሥራ ላይ ተጠምዶ ሰንብቷል።ይህ በእንዲህ እያለ ግን በህወሓት ውስጥ የሁለቱ ቡድን ማለትም ድርድር እናድርግ የሚለው እና ጦርነቱን እያረዘምን እንዋጋ በሚሉት ቡድኖች መሃከል ውጥረቱ ከሯል።ጦርነቱን እንቀጥል የሚሉት የቡድኑ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች የሱዳኑን እንቅስቃሴ በዋናነት እንደሚመሩት የሚነገር ሲሆን፤ ድርደር ይሻለናል የሚለው ጎራ የእነዚህን እንቅስቃሴ በጥርጣሬ ከማየት ባሻገር ውስጣዊ ሽኩቻውን ከፍ እንዳደረገው በስፋት እየተሰራጨ ነው፡፡
በእነዚህ ሃይሎች የሚዘወረው ሱዳንን ማዕከል በማድረግ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የህወሓት ሽብር ቡድን በተደጋጋሚ በአልፋሽጋ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ለመግባት ሙከራ አድርጓል፡፡ በድንበር አካባቢ ሰርጎ ለመግባት በሚደረገው ሙከራ በርካታ የትግራይ ወጣቶችን ህይወት እንደዋዛ እየቀጨ የአካል ጉዳተኛ እያደረገ ከንቱ ምኞት ሆኖ ቢቀርም፤ ቡድኑ ለትውሉዱ ደንታ ቢስ መሆኑን በሚያሳይ መልኩ ትንኮሳውን ቀጥሏል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም መጨረሻ በአልፋሽጋ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ የቡድኑ ታጣቂዎች ውስጥ በርካቶች በኢትዮጵያ የፀጥታ አካላት በወተሰደ እርምጃ ተገድለዋል፡፡ ብዛታቸው ያልታወቀ የቡድኑ ታጣቂዎች ቆስለው በሱዳን ጦር ወታደራዊ ካምፕ ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛል።
ቡድኑ በሱዳን የሚገኘውን የህወሃት ክንፍ ለማጠናከር የተለያዩ ስራዎች እያከናወነ መሆኑንም ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ በዚህ መሰረት የሰው ሃይል ከመመልመል አንፃር ዶክተር መኮነን፣ ብ/ጄኔራል ግደይ ሃይሉ (ወዲ ፊውዳል)፣ ኮሎኔል ዕኮት፣ ኮሎኔል ሃይለ፣ ኮሎኔል ወዲ አማረ የተባሉ እና በየደረጃው የሚገኙ የቡድኑ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች በተለያዩ የስደተኛ መጠለያ ካምፖች በመዘዋወር የትግራይ ተወላጆችና ታጣቂዎችን ለመቀስቀስ ኮሚቴ በማዋቀር እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
በዚህ መሰረት የሰው ሃይል ከመመልመል አንፃር ዶክተር መኮነን፣ ብ/ጄኔራል ግደይ ሃይሉ (ወዲ ፊውዳል)፣ ኮሎኔል ዕኮት፣ ኮሎኔል ሃይለ፣ ኮሎኔል ወዲ አማረ የተባሉ እና በየደረጃው የሚገኙ የቡድኑ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች በተለያዩ የስደተኛ መጠለያ ካምፖች በመዘዋወር የትግራይ ተወላጆችና ታጣቂዎችን ለመቀስቀስ ኮሚቴ በማዋቀር እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። የምልመላ ስራውን ለማሳካትም በጄኔራል ወዲ ፊውዳል የሚመራ ኮሚቴ ገዳሪፍ በሚገኘው የስደተኛ መጠለያ ካምፕ የሚገኙ ወጣቶችን ለመመልመል እንደተሰማራ ተጠቁሟል። በተመሳሳይ ኮሎኔል አጽረጋ እና ዶክተር መኮነን በተባሉ ግሰለቦች የሚመራ ኮሚቴ በካርቱምና አካባቢው የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ቡድኑን በመቀላቀል ወደ ስልጠና እንዲገቡ የመመልመል ስራዎችን እየሰሩ ነው። ሱዳንን ማዕከል በማድረግ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የህወሓት ሽብር ቡድን የሰው ሃይል አቅሙን ለማጠናከር የሚያደርገውን የቅስቀሳና ታጣቂዎችን የመመልመል ስራ አጠናክሮ ከመቀጠሉ ባሻገር ወታደራዊ ስልጠና እየሰጠ መሆኑ ታውቋል።አሸባሪው ቡድን በዚህ መልኩ የትግራይ ወጣቶችን ከመቀሌ እስከ ሱዳን እግር በግር እየተከታተለ መከራቸውን ለማራዘም እየሰራ ሲሆን፤ ይህ የማያባራ ሰቆቃ የሚጋብዝ እኩይ ሴራ አንድ ቦታ ሊቆም ይገባል፡፡ ቡድኑ በቃህ ሊባል ይገባል፡፡
በሌላ በኩል የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከሸኔ የጸዳ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ በህዝቡ መሃከል እየተወራ ነው። ለእዚህ መነሻነት በርካታ ጉዳዮች እየቀረቡ ነው።ከእዚህ ውስጥ አንዱ ድርጅቱ በቅርቡ ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ የአቋም መግለጫ ላይም ሆነ በኋላ ያወጣው መግለጫ ላይ አንድም ቦታ ሸኔ ያላወገዘ ብቻ ሳይሆን ከፓርቲው ጋር ቁርኝት ያላቸው አባላቱ በማኅበራዊ ሚድያ ሳይቀር ሽኔን ሲያሞካሹ ታይተዋል። ኦፌኮ ሸኔን በተመለከተ አለማውገዙ ብቻ ሳይሆን መንግስት እንዲደራደር የሚያግባባ መግለጫ ከማውጣቱ በላይ አመራሮቹ የሚሰጧቸው የተለያዩ መግለጫዎች የሚያሳዩት ይህንኑ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።
ባጠቃላይ የጽንፍ እንቅስቃሴዎች በአዲስ መልክ በአማራ ክልል፣በመሃል ሃገር በኦሮምያ ብልጽግና ውስጥ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሸኔ አሁን በኦፌኮ ውስጥ አለ ተብሏል።በሌላ በኩል ሽብርተኛው ህወሓት ውስጡ እንደገና ከመከፋፈሉ በላይ ወደ ሱዳን ተሻግሮ ለአቅመ አዳም እና ሔዋን ያልደረሱ ልጆች እየመለመለ ነው። ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ለመክተት የሚደረግ የሃገር ውስጥም ሆነ የባዕዳን ሴራ ሁሉ ውጤት እንደሆነ ለማወቅ ሊቅነት አይጠይቅም። ኢትዮጵያውያን ጸንተው በመቆም ኢትዮጵያን ወደ የትኛውም የጽንፍ እንቅስቃሴ የሚገፉ ኃይሎች ከየትኛውም ክልል ቢነሱ ህዝብ እንደ ህዝብ ሊቃወመው ይገባል።ይህ የአሁኑ ትውልድን ማዳን ብቻ ሳይሆን መጪውን ትውልድም የማዳን ስራ ነው።
===============////============
No comments:
Post a Comment