ሚያዝያ 7/2014 ዓም
===============
ጉዳያችን / Gudayachn
===============
ከችግር የፀዳ አገር የለም።የችግር ዓይነቱ መለያየቱ እርግጥ ነው። የኢትዮጵያ ወቅታዊውም ሆነ የከረሙት ፖለቲካዊ፣ምጣኔሃብታዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች ስረ መሰረታቸው ከኋላ የሚጀምር እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የፈጠሩት በሚመስል መልክ አንዳንድ ዩቱበሮችም ሆኑ ግለሰቦች ለህዝብ እንደሚያስተላልፉት የተሳሳተ መረጃ አይደለም። ችግሮቻችንን መረዳት እና የሚፈቱበት መንገድ ላይ ከመምከር ይልቅ በመንጋ አስተሳሰብ በመዋጥ ብቻ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ በተልዕኮ የማጥላላት ዘመቻ ከከፈቱ የአገር ውስጥ እና የባዕዳን የኢትዮጵያ ጠላቶች የሚወረወርላቸውን መርዘኛ ቃላት በማወቅም ካለማወቅ ወደ ውስጣቸው እያስገቡ መልሰው የወሬያቸው ማሟሻ ሲያደርጉ መመልከት አሳዛኝ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ሲመጡ የጠበቀቻቸው ኢትዮጵያ በጎሳ ላይ የተመሰረተ ህገመንግስት ብቻ ሳይሆን ታች ወረዳ ድረስ በጥላቻ የጎሳ ፖለቲካ የተወታተበ አሰራር እና አመራር ብቻ ሳይሆን የጸጥታ አስጠባቂም ጭምር ነው። አንዳንዶች ይህንን አሰራር እና አመራር ለምን አልቀየሩትም? የሚል ጥያቄ ይጠይቃሉ። ይህ ጥያቄ ተገቢ ጥያቄ ነው።ነገር ግን ጥያቄው የለውጡን አካሄድ ካለመረዳት የሚመነጭ ችግር ነው።ይህ ለውጥ በኢትዮጵያ በ1966 ዓም እና የ1983 ዓም ለውጥ የሚለይበት በተለይ የጸጥታ አጠባበቅ ታች በወረዳ ደረጃ የተለየ ባህሪ አለው።
በ1966 ዓም የንጉሱ ሥርዓት በወታደራዊ መንግስት ከተቀየረ በኋላ ከመደበኛ ወታደሩ ውጭ ያለው ታች ያለውን የቀበሌ እና የወረዳ የጸጥታ አጠባበቅ በአብዮት ጠባቂ እና የገበሬ ማኅበር ታጣቂዎች የጸጥታ የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ወሰዱ። ወቅቱ በፖለቲካ የስልጣን ግጭት ከፍተኛ የደም መፋሰስ ቢያስከትልም የቀበሌና ገበሬ ማኅበር ታጣቂ ከስር ያለውን የጸጥታ አጠባበቅ እስከ የግለሰብ ቤት ድረስ እንዲወርድ አድርጓል።
በሌላ በኩል በ1983 ዓም የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣ ብሔራዊ ጦር ሰራዊቱን ከማፍረስ ባለፈ አሁንም በከተሞች በቀበሌ እና በገጠር ደግሞ በገበሬው ደረጃ ልክ ወታደራዊ መንግስት በአብዮት ጠባቂ እና የገበሬ ማኅበር ታጣቂ እንዳደረገው ሁሉ ህወሃት/ኢህአዴግ በከተሞች 'ሰላምና መረጋጋት' የተሰኙ ታጣቂዎች በገበሬው ዘንድም በወታደራዊው መንግስት ዘመን የታጠቁ ታጣቂዎች በአዲስ ታጣቂዎች በመቀየር ከታች ያለውን የጸጥታ አጠባበቅ በማገዝ በቶሎ ጸጥታውን ማረጋጋት ተሞክሯል። የጸጥታው አካል ግን በራሱ የቆመ ሳይሆን የፖለቲካ አካሉ በታች ወረዳ ደረጃ ስለተቀየረ በ1966 ዓም ሆነ በ1983 ዓም የተፈጠሩት የጸጥታ አካላት ከፖለቲካ አመራሩ ጋር አብረው የተፈጠሩ ስለሆኑ እንደ እጅ እና ጓንት ለመያያዝ እና ለመናበብ ችለዋል።
አሁን ያለው ለውጥ ግን በትልልቅ የኢትዮጵያ የጸጥታ አካሎችን ለምሳሌ የመከላከያ እና የደህንነት መዋቅር ለማስተካከል የደከመውን ያህል ታች ወረዳ ላይ ያለው የጸጥታ መዋቅር እና የፖለቲካ አስተዳደሩን ግን እንደ 1966 ዓም እና እንደ 1983 ዓም አልቀየረም።በመሆኑም በክልል ደረጃ እና ከዋና ከተማዋ በራቁ ቦታዎች ላይ ያለው የጸጥታ መረጃዎች በስርዓት እንዳይፈሱ ቀድሞም የነበሩ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች በከተሞችም ሆነ በገጠር የመንግስት የአስተዳደር መዋቅር ላይ ብቻ ሳይሆን በህወሃት/ኢሃዴግ ዘመን የነበሩ ለውጡ የደከመ ሲመስላቸው ከህወሃት ጋር የሚጻጻፉ ሌላ ጊዜ ደግሞ የለውጥ ሃዋርያ እየሆኑ በዘረፋ ሲጠመዱ ከርመዋል።በመሆኑም ይህ ለውጥ በጸጥታ አደረጃጀትም ሆነ ከታች ያለውን የፖለቲካ አመራር ሳይቀየር የተገባበት ስለሆነ ብዙ ነገሮች ተደባልቀው መሄዳቸው ያስከተሉት ችግር አንዱ እና ዋናው የለውጡ ችግር ነው።ይህ ሁኔታ ወደ ኦሮምያ ክልል ሲመጣ ቀድሞ ከነበረው የኦህዴድ አክራሪ ቡድን ላይ ከውጭ የመጣው የኦነግ የተለያዩ አደረጃጀቶች በክልሉ አስተዳደራዊም ሆነ የክልል ኃይል ውስጥ በቀጥታ ገቡ።ከእዚህ ሁሉ በላይ ግን ህወሃት በኢትዮጵያ ላይ አጥምዶት የሄደው ከፋፋይ የጎሳ ፖለቲካ አራማጅ ሕገ መንግስት የችግሮቹ ዋና አንቀሳቃሽ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለአክራሪ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች እንደ ጋሻ ሆኖ ለወንጀል መፈጸምያ መጠቀምያ መሆኑ የታወቀ ነው።
ይህ ለውጥ የጎሳ ፖለቲካን ተንጠላጥለው የስልጣን ጥማቸውን ለማርካት በሚራወጡ ኃይሎች እና ኢትዮጵያን የሁሉም እኩል ጠቃሚ ትሁን በሚሉ ኃይሎች መሃከል የሚደረግ ፍትግያ ውስጥ ለመሆኑ የሚጠራጠር የለም።ይህም ሆኖ ግን በብሔራዊ ውይይት ኮሚሽን ሃሳቦችን በሰላማዊ መንገድ ቀርበው ውይይት ሲደረግባቸው ብዙዎቹ ሃሳቦች መፍትሄ ያገኛሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።መፍትሄ የማያገኙ ሃሳቦች ቢኖሩ ቢያንስ ሕዝብ የበታኝ ኃይሎች ሃሳብ ምን ያህል ትውልድ እና አገር በታኝ እንደሆነ በውይይቱ ሂደት ለህዝብ መጋለጡ አይቀርም።
ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ወቅታዊ ችግርን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የፈጠሩት አይደለም። የችግሩ ስሮች ወደ ኋላ የሚወስደን ነው።ይህ ማለት ግን አሁን ላሉት ችግሮች የመፍትሔ አካል አይደሉም ማለት አይደለም።የህወሃት ደጋፊዎችም ሆኑ የጽንፍ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች አሁን ዋና ዒላማቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው። ከዩቱብ እስከ ትዊተር፣ከመንደር ጠጅ ቤቶች እስከ የገጠር ጠላ ቤት ድረስ ሁለቱም ኃይሎች ያሰማሯቸው እና ተከፋዮችን አሰማርተው የኢትዮጵያ ችግር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የሆኑ አስመስሎ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ላይ ተጠምደዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ይልቅ ኃይለስላሴ የበለጡ ኦሮሞ ናቸው የሚል ትርክት ይዘው ብቅ ካሉት ከዶ/ር መራራ ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማራ ጠል ናቸው እስከሚለው ውሸት ድረስ የምዕራባውያን ሚድያዎች ሁሉ ዋና የጥላቻ ዘመቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላይ የዘመቱ ናቸው። አንዳንዶች ከወሬው ብዛት ሳያውቁት እንዲጠራጠሩ የራሳቸውን የማገናዘብ እና ምክንያታዊ አስተሳሰብ ሲቃረኑ፣ ሌሎች ዐቢይ አማራ ጠል ሆነ ማለት ልጆቹ እና ባለቤቱን ጠላ ማለት እንደሆነ አዙረው ለማሰብ አለመቻላቸውን ለመገንዘብ ሲያቅታቸው መመልከት ያሳዝናል። ኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግል አገር አይደለችም።ሁላችንም እንደሚያገባን እና እንደምንወዳት እርሱም ይወዳታል።ምናልባት የእርሱ የመምራት ዕድሉን አግኝቷል። ኢትዮጵያውያን በወሬ ማዕበል ከመወሰድ ኢትዮጵያን ብሎ የቆመን መሪን በማገዝ ኢትዮጵያን ወደየተሻለ ደረጃ እናድርስ። የዩቱብ አሻሻጮች እየተከትልን የወሬ አዳማቂ መሆን አገር አይጠቅምም።
===============///============
No comments:
Post a Comment