ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, April 4, 2022

በመንግስት ውስጥ ያለ መንግስት አከል ኃይል በቶሎ ካልተቀጨ አደጋ አለው።

አዳማ

===============
ጉዳያችን / Gudayachn
===============

መንግስት ውስጥ ግልገል መንግስት አይታሰብም።በአፍሪካ ግን ከቅኝ ግዛት ማብቃት ተከትሎ የቀድሞ ቅኝ ገዢዎች ይገዙት በነበረው ሃገር ውስጥ መንግስት አከል ግልገል ኃይሎች ያደራጃሉ። እነኝህ መንግስት አከል ግልገል ኃይሎች በተለያየ ቅርጽ የሚከሰቱ እና አደረጃጀታቸውም አንድ ዓይነት አይደለም።አንዳንዶቹ ሃገሮች ውስጥ የሃገሩን ምጣኔ ሃብት አልያም የወታደሩን የተወሰነ ክፍለ ጦር ወይንም በህቡዕ የሚያደራጁት ታጣቂ መንግስት አከል ግልገል ኃይል ሆነው ከመንግስት በበለጠ ህዝብ የሚሸበርባቸው ኃይሎች ናቸው።

በዑጋንዳ ከፕሬዝዳንቱ እና ከመደበኛው ጦር በላይ የፕሬዝዳንቱ ወንድም የግል ወታደሮች እና እርሳቸው በሽርክና ያሉበት ኩባንያዎች ከሕግ በላይ ናቸው።በመሆኑም በዑጋንዳ በፕሬዝዳንቱ ወንድም ወታደሮች የተፈጸሙ ወንጀሎች እንደወንጀል ሳይወሰዱ አልፎ አልፎ ደፋር ጋዜጦች በሃገሪቱ ታዋቂ ጋዜጦች ማለትም ''ኒው ቪዥን'' እና ''ዘ ሞኒተር'' ላይ ከማጋለጥ እና በሕዝቡ ከመደነቅ ያለፈ ሥራ መስራት አልቻሉም።መንግስት አከል ግልገል ኃይሎች በብዙ የአፍሪካ ሃገሮች በውጭ ኃይሎች በገንዘብ፣በምክር እና በስልጠና ሁሉ ይደገፋሉ። በእዚህም ምክንያት ባዕዳኑ እራሱ መንግስት ለእነርሱ እንዲታዘዝ በእነኝህ ህገወጥ ቡድኖች አማካይነት ይጠቀማሉ። ለምሳሌ በናይጄርያ፣ኮንጎ፣አንጎላ፣ሴራልዮን እና ሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች ውስጥ የሚገኙ ማዕድናት ባዕዳን በቅናሽ ክፍያ ለመቆጣጠር መንግስት አከል ግልገል ኃይሎችን ጉቦ እየሰጡ ሲፈልጉ እንዲበጠብጡ ይልኳቸዋል።ጥቅማቸው ሲጠበቅ ደግሞ በገንዘብ ጉርሻ ዝም እንዲሉ ያደርጓቸዋል። 

በመንግስት ውስጥ ያለ መንግስት አከል ኃይል የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ነው። ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ በሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች የታዩት መንግስት አከል ኃይሎች በተለይ በሲቪሉ ሕዝብ መሃከል ሆነው በመግደል እና ሕዝብን በማፈናቀል የሚሹለከለኩ ኃይሎች እረብሸዋት አያውቁም። ይህ በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ጦርነቶችን አይጨምርም። ምክንያቱም ጦርነት በጦርነት ሜዳ የሚደረጉ እንጂ በሲቪሉ ውስጥ የሚደረግ መንግስት አከል ኃይሎች እራሱ መንግስት እንጂ ሌላ አልነበረም። አሁን በኢትዮጵያ የሚታየው  በመንግስት ውስጥ ያለ መንግስት አከል ኃይል በተለየ መልኩ በኦሮምያ ክልል ካቆጠቆጠ ሰነባብቷል።ይሄው ኃይል ሸኔ፣ኦነግ እየተባለ ስም ቢሰጠውም በጽንፈኛ ቡድኖች  በሙስና በበሸቀጡ ክፍልፋዮች የሚታገዝ ነው።ይሄው ክፍልፋይም በመንግስት ልዩ ልዩ መዋቅሮች ውስጥ ሆኖ የመንግስት አከል ኃይሎች ጥይት እና መረጃ አቀባይ ሆኗል።በእዚህም ሳብያ በርካቶች ተገድለዋል፣አያሌዎች ከመኖርያቸው ተፈናቅለዋል።

ይህ የተቀናጀ በዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ወንጀል ጥልቅ የደህንነት እና የጸጥታ ስራ ይጠይቃል።የደህንነት መስርያቤቱ፣ከከተማ እስከ ገጠር ያለው የጸጥታም ሆነ የአስተዳደር መዋቅር አልጸዳም።በእዚህም ዜጎች ደህንነት አይሰማቸውም ብቻ ሳይሆን በመንግስት ውስጥ ያለውን መንግስት አከል ኃይል ከመፋለም ውጭ አማራጭ እንደሌለ ሕዝቡ እየደመደመ እንደሚሄድ ለመረዳት ሊቅ መሆን አያስፈልግም።አሁን ጥያቄው ሁሉም የመንግስት አካል በጽንፈኛ ስር አይደለም እና ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግስት የጸጥታ አካል በመንግስት ውስጥ ያለውን መንግስት አከል ኃይል እራሱ መንግስት መንቀል ካልቻለ የእርስ በርስ ጦርነት በሃገሪቱ ሲነሳ ተቀምጦ የመመልከት ያህል ነው።
===========////=========

No comments:

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታላቅ ተልዕኮ የሚኖረው ሀገራዊ የምምክር ኮሚሽን በተመለከተ ምን ያህል እናውቃለን?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባካተተ መልኩ አዋቅሯል። በእዚህ ጽሑፍ ስር የሚከተሉት ነጥቦች ምላሽ ያገኛሉ፡  ኮሚሽኑ እንዴት ተመሰረተ?  የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመ...