ኢቲቪ ከአለቆቹ ተዘጋጅቶ የቀረበለትን ቪድዮ ለሁለተኛ ጊዜ አሳይቷል።ፊልሙ ከ አስራ አምስት ጊዜ በላይ ከመቆራረጡ በላይ ባጠቃላይ አንዳችም የተለየ መረጃ ስርዓቱ አለማግኘቱን በትክክል ያሳያል።የተጠቀሱት ስሞች በሙሉ ዓለም ዓቀፍ ሚድያውም የሚያውቃቸው ግለሰቦችን ነው።ከእዚሁ ጋር ተያይዞ ግን ፊልሙ ሲጀምር ከአቶ አንዳርጋቸው ድምፅ ጀርባ በግርፋት ላይ ያለ ሰው የሲቃ ድምፅ በዕርቀት ይሰማ ነበር።ይህ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ ድርጅቶችም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን እንደ ማስረጃ አድርገው ለዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ማሳየት የሚችሉበት ማስረጃ ነው።ለምሳሌ ድምፁን ለብቻው መለየት እና በዓለም አቀፍ ሚድያዎች እንዲሰማ ማድረግን ይጨምራል።አሁን ወደ ሁለቱ ነጥቦች ልመለስ የቪድዮው ዓላማ እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሰጠው ትርጉም -
1/ የቪድዮው ዓላማ
የቪድዮው ዓላማ ሁለት ናቸው -ሀ/ የኢህአዲግ/ወያኔ ደጋፊዎችን ለማፅናናት
የመጀመርያው አላማ የኢህአዲግ/ወያኔ ደጋፊዎችን ለማፅናናት ነው።ይህ ማለት ለኢህአዲግ/ወያኔ ደጋፊዎች መረጃ እያገኘን ነው ብሎ ባላገኙት መረጃ ለማፅናናት ነው።በተለይ ለየመን መንግስት የተከፈለው በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር ጉዳይ እራሱ በኢህአዲግ/ወያኔ ባለስልጣናት መካከልም መተማመን አልፈጠረም።ከኢህአዲግ/ወያኔ ባለስልጣናት መካከል ማን ማን ነው? የሚለው ጥያቄ ውጅንብር እርስ በርስ ፈጥሯል።ለምሳሌ የኮምፕዩተር ፓስ ዎርድ ለኢትዮጵያ ሕዝብ a b c d ብሎ የመጥቀስ ጉዳይ በየትኛውም ዓለም ተሰምቶ የማይታወቅ ግን መረጃ ሳያገኙ ''አገኘን'' ብሎ ለማሳመን ''እናቴ ትሙት አግኝቻለሁ እመኑኝ'' ብሎ ደጋፊዎችን ለማሳመን የተሞከረ ሙከራ ነው።ይህኛው ዓላማ ሙሉ በሙሉ አልተሳካም።
ለ/ ሕዝቡን ''እባካችሁ ወደ ትጥቅ ትግል አትግቡ'' ለማለት
ሁለተኛው አላማ ሕዝቡን ለማስፈራራት ነው።አቶ አንዳርጋቸው ከተያዙ ወዲህ የኢትዮጵያ ህዝብ ለትግል መነሳሳት ከፍተኛ መሆን ለኢህአዲግ/ወያኔ ትልቅ ስጋት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።ይህንን ለመግታት ደግሞ የተለያየ ስነ-ልቦናዊ ጦርነት ለማድረግ የሚረዳው አቶ አንዳርጋቸው የትጥቅ ትግል 'አድካሚ' መሆኑን ሲናገሩ ማሳየት ነው።እዚህ ላይ ኢህአዲግ/ወያኔ ያልተረዳው ነገር ግን ይህ ጉዳይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አዲስ ነገር አለመሆኑን እና ቀድሞ የሚያውቀው መሆኑን ነው።አዎን!የትጥቅ ትግል አድካሚ ነው።አቶ አንዳርጋቸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ''ጀግና'' ብሎ ያወደሰበት አንዱ አግባብ እራሱ እኮ ከባዱን የትጥቅ ትግል ከሰላሳ ዓመት የአውሮፓ ኑሮ በኃላም ለሀገራቸው መስዋዕት ለመክፈል መነሳታቸው ነው።ይህ ማለት ኢቲቪ አቶ አንዳርጋቸው ሲናገሩ ባያሳይም ህዝቡ ቀድሞ ያውቀዋል።እናም የፊልሙ ዓላማ እዚህም ላይ ሙሉ በሙሉ አልተሳካም።
2/ ቪድዮው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሰጠው ትርጉም
ኢህአዲግ/ወያኔ ትልቁ ክሽፈቱ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከሃያ ሶስት ዓመት በኃላም አለማወቁ ነው።ለእዚህም ጉልህ ማሳያ የሚሆነን ኢቲቪ የህዝቡን ስነ-ልቦና አገኘሁ ብሎ የሚሰራው ፕሮፓጋንዳ እና ኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚያሳድረው ተፅኖ ግን በተቃራኒው የበለጠ የስርዓቱን ደካማነት መሆኑን ስንመለከት ነው።በእዚህ ቪድዮ ላይም ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሰጠው ትርጉም ኢህአዲግ/ወያኔ ካሰበው ተቃራኒ መሆኑን በሚከተሉት ሶስት ነጥቦች ማየት እንችላለን።ቪድዮው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሰጠው ትርጉም -
ሀ/ ግንቦት 7 ጠንካራ ድርጅት መሆኑንፊልሙ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳየው አንዱ ነገር ግንቦት 7 አደረጃጀቱም ሆነ የሰው ኃይሉን ጥንካሬ ነው።ለእዚህም ማስረጃው አቶ አንዳርጋቸው ከጠቀሱት ውስጥ ድርጅቱ በመረጃ ቴክኖሎጂ (አይ ቴ)ሙያ የተቀላቀሉት ግለሰቦች በ ፒ ኤች ዲ ደረጃ መሆናቸውን ነው።በመረጃ ቴክኖሎጂ ፒ ኤች ዲ ደረጃ የደረሱ ባለሙያዎች ምን ያህል ጥራት ያላቸው ባለሙያዎች መሆናቸውን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች የሚመሰክሩት ይህንኑ ነው።የኢትዮጵያ ህዝብም የሚረዳው ከእዚህ የተለየ አይደለም።ህዝቡ ''ለካ ኢህአዲግ/ወያኔ በመረጃው ዘርፍም ተበልጠሻል'' የሚል ሃሳብ ብልጭ ሲልበት አስተውሉ።
ለ/ በሀገር ውስጥም እራሱን አደራጅቶ ስርዓቱን መዋጋት እንደሚችል
በቪድዮው ላይ ህዝቡ እራሱን በሕቡ ማደራጀቱ ከአቶ አንዳርጋቸው አንደበት ተቆራርጦም ቢሆን መስማቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገር ውስጥ በሕቡም የመደራጀት አስፈላጊነትን አመላክቷል።ነፃነት የሚፈልግ ሕዝብ ነፃነት ስለማጣቱ ማንም ሊነግረው አይችልም።ላለፉት 40 ዓመታት ኢትዮጵያ ያለፈችበት የፖለቲካ ታሪክ የሚያሳየን ይህንን ነው።በሕቡ መደራጀት ኢህአዲግ/ወያኔም እራሱ የኖረበት ነው።ይህንን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀዋል።ዛሬ ግን ኢቲቪ ለሕዝቡ በአቶ አንዳርጋቸው አማካይነት በማሳሰቡ ጥሩ አጋጣሚ ነው።
ሐ/ ''አሸባሪ'' የሚለው የወል ስም ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ መሰጠቱን
ሕዝብ እኮ አስተዋይ ነው።በደንብ ይመለከታል፣ያጤናል በመጨረሻም ፍርዱን ይሰጣል።እስካሁን ኢቲቪ እና ጌቶቹ ''አሸባሪ'' ሲሉ የተሰሙት በትጥቅ ትግል የሚዋጉትን ብቻ አይደለም።ጋዜጠኞችን፣ደራስያንን፣የሃይማኖት ሰዎችን፣ብሎገሮችን፣ተማሪዎችን፣መምህራንን፣ገበሬዎችን እና የከተማ ሰላማዊ ነዋሪዎችን ሁሉ ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ከእነኝህ ሁሉ ውጭ አይደለም።ይህ ማለት በኢህአዲግ አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ ''አሸባሪ'' ተብሎ ተፈረጀ ማለት ነው።ስለዚህ አቶ አንዳርጋቸውን እና ዓላማቸውን ሕዝብ የበለጠ እየወደደው፣እያከበረው እና እየተቀላቀለው ይመጣል።በመሆኑም የፊልሙ ዓላማ ሙሉ በሙሉ ከሽፏል።ህዝቡ ኢህአዲግ/ወያኔን ''አሸባሪ'' የሚለው እራሱ ነፃነት ያጣውን ሕዝብ በሙሉ መሆኑ የታወቀ ነው።ሕዝብ በሙሉ ''አሸባሪ'' ሲባል ደግሞ ያለው አማራጭ አንድ ነው።ነፃነቱን ከአሸባሪ መንግስት መንጭቆ መውሰድ።ይህ የማይቀር መጪው ክስተት ነው።
በመጨረሻም አንዲት ነገር ሳላነሳ አላልፍም በእዚሁ ፊልም ላይ አቶ አንዳርጋቸው ከተናገሩት ለኢህአዲግ/ወያኔ ያልገባው ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተዋለው ጉዳይ።አቶ አንዳርጋቸው ዶ/ር ታደሰን ዛሬም ወያኔዎች ፊት ''ታዴ!'' ነው ያሏቸው።ይህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያሳየው ነገር አለ።የዓላማ ፅናታቸው በጊዜ እና በቦታ አለመወሰኑን።
ጉዳያችን
ሐምሌ 21/2006 ዓም (ጁላይ 28/2014)
No comments:
Post a Comment