ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, July 10, 2014

መንግስታዊ ሽብርተኝነትን የሚሸከም ትከሻ አይኖረንም!!! We cannot Tolerate TPLF/EPRDF’s State Terror! ''ከዚህ በኋላ ለምናደርጋቸው ሀገር አቀፍ ንቅናቄዎች መላው የሀገሪቱ ህብረተሰብ በንቃት ተዘጋጅቶ እንዲጠብቅ ጥሪውን እያስተላለፈ ለዚህም ቁርጠኛ አመራር ለመስጠት ዝግጁነቱን ለመግለፅ ይወዳል'' ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ (English version is also attached)

We cannot Tolerate TPLF/EPRDF’s State Terror! (click  here to read English version)


Press Release by Blue Party Ethiopia / Semayawi Party- Ethiopia/
ሀምሌ 3/2006ዓ/ም
የህወሓት/ኢህአዲግ አገዛዝ በኢትዮጵያ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ዜጎችን በማፈንና በማሰቃየት ብሎም በመግደል የአፈና አገዛዙን ለረጅም ጊዜ ሲያራምድ መቆየቱ ዓለም የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡ በተለይም ባለፉት 10 ዓመታት የህዝብን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማፈን እስራትና ግድያውን ህጋዊ ለማስመሰል የተለያዩ አፋኝ አዋጆችን አውጥቷል፡፡ እነዚህን አዋጆችንም ተገን አድርጎ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችንና አባለትን፣ ጋዜጠኞችንና ጦማርያንን፣ እንዲሁም የእምነት ተቋማት መሪዎችን እና በአገዛዙ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎችን ማሰሩን፣ ማሰቃየቱንና ግድያውን ተያይዞታል፡፡ በህገ መንግስቱ የተካተቱ የሰብዓዊ መብቶችንና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በሙሉ የሚጥሰውና የአምባገነንነት ስልጣኑን ለማራዘም ሲል ያፀደቀው የፀረ-ሽብር አዋጅ ከፀደቀበት እለት አንስቶ ኢህአዴግ ለስልጣኔ ያሰጉኛል የሚላቸውን ፍፁም ሰላማዊ ታጋዮችንና ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው በድፍረት የፃፉ ጋዜጠኞችን ብሎም የእምነት ነፃነታችን ይከበር ብለው የጠየቁ የሀይማኖት መሪዎችን በጠራራ ፀሃይ ያለምንም ወንጀል በዚሁ ህገ ወጥ አዋጅ ‹‹የፀረ ሽብር ግብረ ሀይል›› በሚባል ማንነቱ በማይታወቅ የጨለማ ቡድን ወደ እስር ቤት እያጋዘ ይገኛል፡፡
ይህን የሚያጋልጡ ሚዲያዎችንም ለማፈን እስር ቤቶችን ጨምሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እያፈሰሰ የአየር ሞገድ ያውካል፤ በዚህ ሳያበቃ በሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን የሚያሰሙ ፖለቲከኞችን ለማሸማቀቅ እንደ ኢሳት ያሉ ሚዲያዎችን የአሸባሪ ልሳን ብሎ በመፈረጅ ሚዲያውን የሚጠቀሙትን ደግሞ ከአሸባሪዎች ጋር ንክኪ እንዳላቸው አድርጎ መወንጀሉን ቀጥሎበታል፡፡ እንደሰማያዊ እምነት ማንም አካል መልእክት የሚያስተላለፍበትን የሚዲያ ተቋም ሊመርጥለት እንደማይችል መንግስት እንዲገነዘበው ከዚህ በፊት በግልፅ ያሳወቀ ሲሆን አሁንም ፓርቲው በዚሁ የፀና አቋሙ እንደሚቀጥል በድጋሚ ይገልፃል፡፡
ባጠቃለይ የዚህን ገዢ አካል የእውር ድንብር ሀገር የማስተዳደር ጉዞ ለመታገል በርካቶች በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም በህወሓት/ኢህአዲግ ግፍና መከራ ተገፍተው ስርዓቱን በሃይል እናስወግዳለን ብለው ሀገር ጥለው የተሰደዱ ዜጎችም እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የህወሓት/ኢህአዲግ ማናለብኝነትና የስልጣን ጥመኝነትም በግለሰቦች ላይ ከሚያስከትለው ማህበራዊ ቀውስ በላይ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ አለመረጋጋትን አስከትሏል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ይህ ገዢ ፓርቲ የፈጠረው ስርዓት የሀገሪቷን ሰላማዊ የፖለቲካ ምህዳር በማጥበብ ሀገራችንን ወደ አልተፈለገ አለመረጋጋትና ቀውስ እየመራት ይገኛል፡፡ፓርቲያችንም እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም በቅርቡ እየተፈፀሙ የሚገኙ ህገ ወጥ ድርጊቶች ስላሳሰበው ይህን መግለጫ ለማውጣት ተገዷል:-
1. ሰኔ 16 2006 ዓ.ም የየመን መንግስት የዓለም አቀፍ ስምምነቶችንና ድንጋጌዎችን በመጣስና በሰው ሀገር የውስጥ ጉዳይ በመግባት የአማፂ ቡድን ግንቦት ሰባት ዋና ፀሃፊ የሆኑትን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን መያዟ ይታወሳል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ለህወሓት/ ኢህአዴግ ተላልፈው መሰጠታቸውን ከ16 ቀናት በኋላ መታወቁና ይህንንም ሁለቱ ሀይሎች ማመናቸው ተሰምቷል፡፡ ነፃነት በሌለበት ሀገር ዜጎች ሰብዓዊ ክብራቸውን ለማስጠበቅ የሚያደርጉት ጥረት የሌሎች ሀገር መንግስታት የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት በዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ሆነ በተለይ በሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ጥላ የሚያጠላ መሆኑን ግንዛቤ አለመወሰዱ እጅግ የሚያሳዝን ድርጊት ነው፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ከተያዙ በኋላ ላለፉት 16 ቀናት በምን አይነት ሁናቴ እንደቆዩ ህዝብና ቤተሰቦቻቸው እንዲያውቁት አለመደረጉ፤ ስለ አያያዛቸው ሁኔታም በማህበረሰቡና በፓርቲያችን ውስጥ ከፍተኛ ጥርጣሬ እንዲኖር አድርጓል፡፡ሰማያዊ ፓርቲ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ሰብዓዊ አያያዝ እያሳሰበው ህወሓት መራሹ የኢህአዴግ አገዛዝ አያያዛቸውን ግልፅ እንዲያደርግ ሰብዓዊ ክብራቸውም እንዲጠበቅ በጥብቅ ያሳስባል፡፡
2. በዚሁ ሳምንት ገዢው ፓርቲ ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ የአምባገነኑን መንግስት ህወሓት/ኢህአዲግን ሲታገሉ የነበሩ ፖለቲከኞችን በስመ አሸባሪ ከያሉበት እየለቀመ ህገ-ወጥ እስራት መፈፀሙ ይታወቃል፡፡ ህወሓት/ኢህአዲግ ይህ ግብታዊ ተግባሩ ምንም እንኳን አዲስ ባይሆንም በአሁኑ ወቅት ለውጥን ለማምጣት በቆራጥነት እየታገሉ ያሉ ሰላማዊ ታጋዮችን ማሰሩ በሀገር ውስጥ በህጋዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ፓርቲዎችን ከአማፂ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ያላቸው በማስመሰል ሰላማዊ ትግሉን ለማዳከምና መጪውን 2007 ዓ/ም ምርጫ ያለ ተቀናቃኝ ለማለፍ የሚደረግ ህገ ወጥ እንቅስቃሴ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ የፓርቲያችን ብ/ም/ቤት ምክትል ሰብሳቢ የሆነው አቶ የሺዋስ አሰፋ በሰላማዊ ትግሉ በቁርጠኝነት እየተሳተፈ ባለበት ሁኔታ ለእስር መዳረጉ፤ የአንድነት ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው፤ የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ምክትል ሀላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከፍተኛ የህዝብ ንቅናቄን በመፍጠር ላይ ያለው የአረና /ትግራይ/ ፓርቲ አመራር አባል የሆኑትን አቶ አብረሃ ደስታ ለእስር መዳረጋቸው ህወኃት/ኢህአዴግ የመጨረሻው መጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ያረጋግጣል፡፡ በመሆኑም አገዛዙ እያካሄደ ያለውን መንግስታዊ ሽብር አቁሞ ለሀገርም ሆነ ለራሱ የሚበጀውን መንገድ እንዲከተል እያሳሰብን የታሰሩት የፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንጠይቃለን፡፡
በመጨረሻም ፓርቲያችንን መንግስት እያደረገ ያለው ሽብርን የመንዛትና ህግን የመጣስ ተግባሩ መቼም ቢሆን ከሰላማዊ ትግሉ እንደማያቆመውና ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በአፅንኦት እየገለፀ እነዚህንና ከላይ የተጠቀሱትን የገዢውን ፓርቲ መርህ አልባነት፣ ህገ-ወጥነት እና የለየለት አምባገነንነትን አሁን ካለው ነባራዊ እውነታ ጋር አጣምሮ የትግል ስልቱን ደረጃ ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ማሸጋገር እንዳለበት አምኗል፡፡ በመሆኑም ከዚህ በኋላ ለምናደርጋቸው ሀገር አቀፍ ንቅናቄዎች መላው የሀገሪቱ ህብረተሰብ በንቃት ተዘጋጅቶ እንዲጠብቅ ጥሪውን እያስተላለፈ ለዚህም ቁርጠኛ አመራር ለመስጠት ዝግጁነቱን ለመግለፅ ይወዳል፡፡በዚህ አምባገነንነትን ለመታገል በሚደረገው ንቅናቄም በሀገር ውስጥ የሚገኙ ህጋዊና ሰላማዊ ፓርቲዎች፤አለም አቀፍ ተቋማት፤የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፤ሲቪክ ማህበራት፤መላው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሰላማዊ ትግሉ ጎን በጋራ እንድንቆም እንጠይቃለን፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር
ሰማያዊ ፓርቲ
ሀምሌ 3/2006ዓ/ም

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።