ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, July 2, 2014

'ክርስትና የዋህንን በአድርባይነት መርዝ እየወጉ እና እየተሽሞነሞኑ የሚኖሩበት ሕይወት አይደለም'' በክርስትና ስም ''አትናገሩ'' ለማለት ለሚዳዳቸው የበግ ለምድ ለባሾች ምላሽ ትሁንልኝ


ዛሬ  (ስሙን አልጠቅሰውም) ማንነቱን የማላውቀው ግን ፋይሉ አናት ላይ ነጠላ ለብሶ የተነሳ ፎቶ በትልቁ የለጠፈ የፌስ ቡክ ገፄ አባል እንዲህ የሚል መልዕክት በውስጥ መስመር ላይ ለጠፈለኝ። '' አይ ክርስትና-----ቤተክርስቲያንን ማገልገል አይሻልህም? '' ወዘተ የሚሉ ቃላት ይዟል።ግለሰቡን ከእዚህ በፊት ስለማላውቀው ፋይሉን ከፍቼ ማየት ጀመርኩ።ፕሮፋይሉ ላይ በትልቁ ነጠላ ለብሶ የተነሳውን ፎቶ ለጥፏል።ከወደ አናቱ የሀገራችን ክፍል መሆኑን ፋይሉ ይናገራል።ወደውስጥ ገባሁ።አንዱ ክፍል ላይ አቶ መለስን ፎቶ በትልቁ ለጥፎ የአምላክ ያህል ''ውዳሴ መለስ'' ድርሰት ብጤ ለጥፏል።ቀጠልኩ መጎርጎሬን  በሌላ ቀን አቶ ኢሳያስን ለጥፎ ከውክሊክ ያገኘውን ታሪካቸውን ተርጉሞ ምንጭ ውክሊክ ብሎ አያይዞታል።በተለይ በእዚህኛው ክፍል ላይ አቶ ኢሳያስ ''በነፃ ምርጫ የተመረጡ በዲሞክራሲ የሚያምኑ'' የሚል ጨምሮበታል። እናም ቀደም ብዬ ከቅንነት ሃሳብ የሰጠ የመሰለኝ ሰው አሳዘነኝ እና ለእርሱ እና በቤተክርስቲያን ስም ለሚያጭበረብሩ ሁሉ እንዲህ ማለት ፈለኩ።

ለወዳጄ እና ለመሰሎችህ (የማስታወሻዬ አርዕስት ነች)  
ክርስትና የማጭበርበርያ ጉረኖ አይደለም።ክርስትና እንደ እባብ እየተቅለሰለሱ የዋሃንን የሚነድፉበት የሸለምጥማጦች ጅራፍ አይደለም።ሰው በክርስትና ውስጥ ሲኖር ፍርሃት፣አድርባይነት፣ጥቅምን ማስቀደም እና እኔ ብቻ 'ደረቴ ይቅላ ሆዴ ይሙላ' የሚል ከሆነ ክርስቲያን ባይሆን ይመረጣል።ክርስቲያን በመንግስት ዘረኝነት ሲታወጅ ከንፈር እየመጠጠ ዘረኝነትን የሚጠየፈውን መፅሐፍ ቅዱስ ይዞ ሕዝብ ከሚያታልል እራሱን ወደ ትልቅ ባህር ቢወረውር ይሻለዋል።ክርስቲያን የሰው ዘር በሙስና እና በአድልዎ ሲሰቃይ መቃወም ካልቻለ ባይፈጠር ይበጀዋል። ክርስቲያን ሰዎች ሲሰደዱ ያሰደዳቸውን ቡድን ከመውቀስ ይልቅ በቤተ ክርስቲያን ስም በስዱዳን ቁስል  ላይ የመርዝ እንጨቱን ከላከ ፍርዱ አይቀርለትም።ክርስቲያን ሰዎች ሲታሰሩ ለታሰሩት መጮህ ካልቻለ እራሱን በራሱ በሰይጣን የጥቅም አሽክላ እንደተበተበ እና ቤተክርስቲያን እየሄደ የዋሃንን የሚሸነግል ይሁዳ ቢባል ሲያንሰው ነው።

በሀገራችን ዘረኝነት ነገሰ በክርስትና ስም እንዳላዩ ያለፉ ቃል ላልተነፈስን ወዮልን፣
በሀገራችን የዋሃን ንፁሃን ምንም የተደበቀ አጀንዳ የሌላቸው መውጫ መግቢያቸው የሚታወቅ  (ዞን 9 መጥቀስ ይቻላል) በግፍ ታሰሩ።በክርስትና ስም እኛ የቤተክርስቲያን ነን እያልን ቃል ያልተነፈስን ወዮልን!
በሀገራችን ሰዎች በዘራቸው እና በቋንቋቸው ብቻ እየተለዩ ከኖሩበት ስፍራ በግፍ ተባረሩ (ሐረር፣ወለጋ፣ጉርዳፈርዳ፣ጅጅጋ፣ወዘተ) አይናችን እያየ በክርስትና ስም እኛ የቤተክርስቲያን ነን እያልን ቃል ያልተነፈስን ወዮልን!
የሀገራችን ድንበር እየተቆረሰ ለባዕዳን በሙስና እና በሀገር ክህደት ተቸበቸበ።በክርስትና ስም እኛ የቤተክርስቲያን ነን እያልን ቃል ያልተነፈስን ወዮልን! 
ኢትዮጵያውያን በባዕዳን እየታሰሩ በእየቦታው ሲንገላቱ ''ታስሬ አልጠየቃችሁኝም'' የምትለዋን ቃል ወደጎን ትተን በክርስትና ስም እኛ የቤተክርስቲያን ነን እያልን ቃል ያልተነፈስን ወዮልን! ለታሰሩት፣በዘር እና በቋንቋ አድልዎ እየተደረገባቸው ለተንገላቱት፣በኢትዮጵያዊነታቸው እየተለዩ ለሚታሰሩት መጮህ ክርስትና ነው። ክርስትና በሙስና ፊታቸው ለሚያብለጨልጩ እና በዘረኝነት ለሰከሩ እና ሃገራቸውን ለጥቅም ለሸጡ ወንጀለኞች በመቆም ወይም በአድርባይነት ዝም በማለት አይገለጥም።ክርስትና የዋህንን በአድርባይነት መርዝ እየወጉ እና  እየተሽሞነሞኑ የሚኖሩበት ሕይወት አይደለም።

ጉዳያችን 
ሰኔ 25/2006 ዓም (ጁላይ 2/2014)

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...