ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, July 23, 2014

የመርሐ ቤቴ ሕዝብ በተነሳበት ደረጃ የአዲስ አበባ ቂርቆስ ነዋሪም ተነቃንቆ ነበር።የኢትዮጵያ ሕዝብ ግፍን በመረጠው መንገድ ለመመከት እድሉ እጁ ላይ መሆኑን ከመቼውም ጊዜ በላይ የተረዳበት ጊዜ ላይ ነን። (የጉዳያችን ልዩ ዘገባ)



ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ የመርሃቤቴ ሕዝብ አድሎ የተመላበትን እና በሙስና የታጀለ ስርዓትን የሚሸከምበት ትከሻ እንደሌለው በኃይል በታገዘ ተቃውሞ መግለፁ ዓበይት ዜና ሆኖ መክረሙ ይታወቃል።ጉዳዩ የመብራት ኃይል ማከፋፈያ ትራንስፎርመሮችን  ነቅሎ ድርጅቱ ሊያዞረው ወደ ፈለገው ማለትም በዜና ዘገባዎች መሰረት ወደ ትግራይ እንደ ''አውራምባው'' ዳዊት  አገላለፅ ደግሞ ወደ ''ሰሜን ወሎ'' (ሰሜን ወሎ ወደ ትግራይ ከዞረ ሁለት አስር ዓመታት መሆኑን እያስታወስን) ሊወሰድ መወሰኑ የመርሐቤቴን ሕዝብ 'አሁንስ በዛ!' ያስባለው ወቅታዊው ምክንያት ነበር።
ጉዳዩ የወቅቱ ምክንያት ይሁን እንጂ ለ23 ዓመታት ሲነዛ የነበረው የዘረኝነት እና የሙሰኞች አገዛዝ የአካባቢውን ሕዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚያንገበግበው ጉዳይ እንደነበር ሳይታለም የተፈታ ነው።ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ህዝቡ በየቦታው ተቃውሞውን መቀጠሉን፣'ትራንስፎርመሩን አንወስድም' የሚል ቃል ከአካባቢው የኢህአዴግ/ወያኔ ሹማምንት ተደጋግሞ ቢገለፅም ወደ ስፍራው እየጎረፈ ያለው የኢህአዲግ/ወያኔ ሰራዊት በቀጣይ ቀናት በነዋሪው ላይ ጥቃት ለመፈፀም የታሰበ ሊሆን እንደሚችል የብዙዎች ግምት በመሆኑ ህዝቡ አሁንም በንቃት ከመጠበቅ አልፎ በርካቶች ወደ አካባቢው በረሃዎች እንደወረዱ ለማወቅ ተችሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በያዝነው ወር መጀመርያ ላይ በተመሳሳይ መንገድ የአዲስ አበባ ቂርቆስ ነዋሪዎች (ከለጋሃር ባቡር ጣብያ ጀርባ) የመብራት ኃይል ሰራተኞችን አግተው ማሳደራቸው ለማወቅ ተችሏል።ጉዳዩ እንዲህ ነው።የመብራት አገልግሎት የቆመበት ሕዝብ ደጋግሞ ለመብራት ኃይል ይደውላል።ምሽት ጠብቀው መሄድ ትርፍ ክፍያ እንደሚኖረው የሚያውቁት መብራት ኃይሎች ከምሽቱ 3 ሰዓት ገደማ ይመጣሉ።የሚገርመው መብራት የቆመበትን ምሰሶ ወጥቶ ለማየት የእጅ ባትሪ አልያዙም።ህዝቡ ባትሪ ፈልጎ እንዲያመጣ አዘዙ።ባትሪው መጣ።ሰራተኞቹ በመሰላል ወጥተው መጎርጎር ጀመሩ።የአካባቢው ሕዝብ ከየቤቱ ወጥቶ ዙርያውን ተኮለኮለ። ሰራተኞቹ ከምሰሶው ላይ ወረዱ እና ችግሩ'' የ 'ፍዩዝ' መቃጠል ስለሆነ ከመስርያቤት ነገ ፈልገን እንተክላለን'' ብለው ወደ መኪናቸው ሊሄዱ ሲሉ ህዝቡ ''ፈፅሞ ሳትገጥሙ አትሄዱም ስንት ቀን ካለመብራት ኖርን?'' መንገዱን ዘጋው። ሰራተኞቹ ተማጠኑ።ይብሱን ብዙ ሕዝብ ጎዳና ወጣ።ሰራተኞቹ ወደ መስርያቤት ደውለው አድኑን ብለው ቢማፀኑም የሚሆን አልሆነም።ምሽቱ ገፋ እኩለ ሌሊት ሆነ።ህዝቡ አልተኛም አለ።የፖሊስ ኃይል ተልኮ ለመደራደር ሞከረ።ህዝቡ ''ሕይወታችን ያልፋል እንጂ ፈፅሞ መብራቱ ሳይቀጠል አናድርም'' ብቸኛ እና ቁርጥ መልሱ ነበር።ሕዝብ በተራ እየጠበቀ ሰራተኞቹ ታግተው አደሩ።ፖሊስም ሕዝቡን እንደፈራ አደረ።

በማግስቱ ሌላ የፖሊስ ኃይል ተላከ ህዝቡ ''ለፀብ ዝግጁ መሆኑን እና ህይወቱ ያልፋል እንጂ መብራቱ ሳይቀጠል ወዴትም እንደማይሄድ'' ገለፀ።ብዙ ድርድሮች ተደረጉ።በመጨረሻ ሽማግሌዎች ሃሳብ አቀረቡ።ይሄውም ከሕዝቡ ተወካዮች እና ከመብራት ኃይል ሰራተኞች ጋር ሆኖ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሊሄዱ እና እዝያ በቶሎ እንደሚጠገን የሚገልፅ የማስገደጃ ውል እንዲፈረም የሚል ሃሳብ ቀረበ።በሃሳቡ ህዝቡ ተስማማ።ይህ ሲሆን ሰዓቱ ከረፋዱ 5 ሰዓት ሆኖ ነበር።ሰራተኞቹ ከታገቱ ከ12 ሰዓታት በላይ ሆኗል።
በመጨረሻም የህዝቡ ተወካዮች፣የመብራት ኃይል የታገቱት ሰራተኞች እና ፖሊስ ወደ ፖሊስ ጣብያ ሄደው የመብራት ኃይል መስመሩን በቶሎ እንደሚጠግን የሚገልፅ ውል ፈርሞ እገታው ተጠናቀቀ።እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ግን መስመሩ እንዳልተጠገነ መረጃዎች ያሳያሉ።ጉዳዩ ግን አንድ ነገር ያሳያል።ሕዝብ በጉልበቱ የማስፈፀም አቅሙን የማስመለስ ኃይል እንዳለው።ሕዝቡ መሮታል።የኢትዮጵያ ሕዝብ ግፍን በመረጠው መንገድ ለመመከት እድሉ እጁ ላይ መሆኑን ከመቼውም ጊዜ በላይ የተረዳበት ጊዜ ላይ ነን። 

ጉዳያችን 
ሐምሌ 16/2006 ዓም (ጁላይ 23/2014)

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...