ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, March 30, 2021

የኢትዮጵያን ፀጥታ ለማረጋገጥ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ከሽ.ነ.ድ. መጠበቅ አለባቸው።

  • የውጪ ባዕዳን እና በውስጥ ያኮረፉ ከሊቅ እስከደቂቅ ያለው ኢትዮጵያዊ ላይ ሊዘምቱበት የሚዘጋጁት በሽነድ ነው።

ኢትዮጵያ በጥገናዊ ለውጥ ውስጥ ከገባች ነገ መጋቢት 24/2013 ዓም ሦስተኛ ዓመቷን ትይዛለች።በእነኝህ ሦስት ዓመታት ውስጥ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።ይህ ለውጥ ባይመጣ ኖሮ ኢትዮጵያ ዛሬ እጅግ አደገኛ ብቻ ሳይሆን ሕልውናዋም ጥያቄ ውስጥ የማይገባበት ምክንያት አይኖርም።ምክንያቱም የነበረው የውስጥ ቅራኔ ውስብስብ ከመሆኑ አንፃር በቀጥታ የእርስ በርስ ጦርነት አይኖርም ማለት አይቻልም።አንዳንዶች ይህ ሲባል ዛሬ ያለችው ኢትዮጵያ ከሦስት ዓመት ከነበረችው የባሰ ነው ብለው የሚናገሩ በማኅበራዊ ሚድያ የሚገልጡ ከአጠቃላይ ኢትዮጵያ የነበረችበት የችግር ጥልቀት ያልተረዱ ናቸው።ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች በሙሉ ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል፣ስደተኞች ወደ ሀገራቸው በነፃ መግባት መውጣት ችለዋል፣በሺህ የሚቆጠሩ እስረኞች ተፈትተዋል፣የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት በአንፃራዊ መልኩ የተሻለ ነው፣የትምህርት ፖሊሲ በአዲስ መልክ ተዘጋጅቷል፣የኢትዮጵያ ምድር ኃይል እና አየር ኃይል መዋቅር ማሻሻያ ተሰርቷል፣የፍትሕ፣የፖሊስ እና ሌሎች መዋቅሮች ማሻሻያ ተጀምሯል፣የዓባይ ግድብ ፕሮጀክት በአዲስ መልክ ተከልሷል፣በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መሃከል ሰላም ተፈጥሯል ሌላም ስራዎች ተሰርተዋል።እነኝህ እያንዳንዳቸው ቢተነተኑ ብዙ ገፅ ማብራርያ የሚፈልጉ ናቸው።

ከላይ በመጠኑ የተጠቀሱት ስራዎች እና ሌሎች ያልተጠቀሱት ተግባራት የተሰሩ እና እየተሰሩ ቢሆኑም በሌላ በኩል ደግሞ የሕዝብ መፈናቀል፣የጎሳ ግጭቶች እና የእምነት ቦታዎች መቃጠል የተፈፀሙ አሳዛኝ ድርጊቶች ናቸው።ይህ ሁሉ ሆኖ ግን አጠቃላይ ሂደቱን ስንመለከት ኢትዮጵያ ከግዙፍ ችግሮቿ ለመውጣት ከትናንቱ እጅግ በላቀ መስመር ላይ እንዳለች መረዳት ይቻላል።ሆኖም ግን በቀጣይ ወራት ኢትዮጵያ ከምትተገብራቸው ሁለት ግዙፍ ስራዎች ማለትም የአባይ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ መሙላት ተግባር እና የብሔራዊ ምርጫ አንፃር የኢትዮጵያን መነሳት የሚያሰጋቸው ባዕዳን እና በውስጥ ያኮረፉ በውጭ እና በሀገር ውስጥ ያለውን ኢትዮጵያ ከሊቅ እስከደቂቅ ሊዘምቱበት የሚዘጋጁት በሽነድ ነው።

ሽ.ነ.ድ ኢትዮጵያን ለማጥቃት የኢትዮጵያ ጠላቶች ቀደም ባሉ ዓመታት ሲጠቀሙበት የነበረ ድርጅት ነው።ቃሉ ለመጀመርያ ጊዜ የሰማሁት የአንድ ዓመት የኮሌጅ ተማሪ ሳለሁ የዛሬ 30 ዓመት የኢትዮጵያ ኮሌጆች እና ዩንቨርስቲዎች ወደ ብላቴ የአየርወለድ ማሰልጠኛ ሲዘምቱ በሄድኩበት ወቅት ወደ አስር ሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች ውስጥ ተማሪዎቹን ለማሸበር የሚወሩ ወሬዎችን ተማሪው የሰጠው ስም ነበር።ሽነድዎች በጣም ጥቂት ሲሆኑ የጠላት ተልዕኮ ይዘው በወቅቱ የነበሩት ሽምቅ ተዋጊዎች ለማግነን የታሰበ  የውሸት ወሬ እየፈጠሩ የሚያወሩ ናቸው።እነኝህን ኃይሎች ተማሪው ወድያው ስለነቃባቸው በግዙፉ የብላቴ ተራራ ላይ አስር ሺህ ተማሪ በተሰበሰበበት ነው ሽነድ የሚለው ስም በይፋ የተሰጣቸው።ሽ.ነ.ድ ማለት ሽብር ነዥ ድርጅት ማለት ነው።

ሽ.ነ.ድዎች ዛሬ የት ናቸው ?

ሽነድዎች በብላቴ ተማሪውን በተለያየ ወሬ ለመረበሽ ሞክረው እንደነበር ሁሉ ዛሬ ሽነድዎች የኢትዮጵያን ሕዝብ ከታች ሊስትሮ እስከ ጠጅ ቤት፣ከገጠር ጠላ ቤት እስከ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል፣ከታክሲ ተሳፋሪ እስከ ቦይንግ 767፣ከቤተ መቅደስ እስከ መስጊድ፣ከዩንቨርስቲ እስከ ቀበሌ ፅህፈት ቤት፣በውጭ ደግሞ በዩቱብ መስኮት ላይ ተንጠላጥለው ይገኛሉ።

ዛሬ ሽነድዎች ሸነድ መሆናቸውን የሚያውቁ እና የማያውቁ ተብለው በሁለት ይከፈላሉ።  
 
ሽነድዎች እንዲሆኑ የሰለጠኑ እና መሆናቸውን የሚያውቁ የመኖራቸውን ያህል ሽነድ መሆናቸውን ሳያውቁ የሽነድን ሥራ የሚሰሩ አሉ።ሽነድ መሆናቸውን የሚያውቁ ሆን ብለው ህዝቡ መሃል ሆነው ከቤተሰባቸው ጀምሮ በቀን ውሏቸው ያገኙአቸውን ሁሉ በተሰጣቸው የውሸት ወሬ ሁሉ ላገኙት ሲያሰራጩ የሚውሉ ናቸው።ጧት ከባላቸው ወይንም ከሚስታቸው ቀጥሎ ጎረቤቶቻቸውን ሁሉ  ኢትዮጵያ እንዲህ ልትሆን ነው፣አዲስ አበባ ልትጠፋ ነው፣አንድ ሰው ሞተ ሲባሉ አንድ መቶ ሰው ሞተ እያሉ የሚያወሩ ናቸው። ሽነድ መሆናቸውን የሚይውቁ ሰዎች እንዳይታወቁ የሚጠነቀቁ ናቸው።የውሸት ወሬ አከፋፋይ እና አመንጪ ስለሆኑ እነርሱ የውሸቱን ወሬ የመለኮስ ሚና እንጂ ማቀጣጠሉን እራሳቸው ሽነድ መሆናቸውን ለማያውቁ ማቀበሉ ላይ ነው የሚተጉት።

ሽነድዎች አንዱ ተግባራቸው ሕዝብ ተስፋ እንዲቆርጥ የሚያደርጉ ማናቸውንም ወሬዎች ማውራት ነው።በጣም አሰቃቂ ነገር ሲፈፀም ይፈነጥዛሉ።ሕዝብ በመንግስት እና በመሪዎቹ ላይ ተስፋ እንዲቆርጥ በዋናነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በሌሎች ኢትዮጵያን ብለው በሚሰሩ ባለሙያዎች ላይ ሁሉ የውሸት ወሬ ይከፍቱባቸዋል።በእዚህም ሕዝብ ውሸት ሲደጋገምለት ያምናል በሚል ስራዬ ብለው ሕዝቡን ማሸበር ላይ በመስራት ላይ ናቸው።ሌላው ቀርቶ ዛሬ ኢትዮጵያ በመጪው ዓመት ካሜሮን ላይ ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍዋ አናዷቸዋል።በማኅበራዊ ሚድያ ሰሞኑን በሚያወሩት ወሬ እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ላይ በከፈቱት የውሸት ዘመቻ ሕዝቡን ያስተከዙት እና ተስፋ ያስቆረጡት መስሏቸው ባለበት ሰዓት ከመቅፅበት ከአይቨሪኮስት የተሰማው የኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ሕዝብ አውራ ጎዳና ላይ ወጥቶ ማስጨፈሩ ሽነድ የደከመበትን ሕዝቡን የማስተከዝ ሥራ ገደል መክተቱ አናደዳቸው።

ሸነድዎች በቀጣይ ሊሄዱበት ያሰቡበት መንገድ ያልላካቸውን እግዚአብሔር እንደላካቸው እያደረጉ በክርስትናውም ሆነ በእስልምናው መምህራንን በገንዘብ እየገዙ ትንቢት ተገለጠልን እያሉ ማውራት ነው።ዘመኑ ደግሞ የዩቱብ ዘመን ስለሆነ በቀላሉ ህዝቡ ጋር እንደሚደርሱ ያስባሉ።ሽነድዎች ጥቂት በመሆናቸው በወሬ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማሸበር አቅም የላቸውም። ነገር ግን ሽነድ መሆናቸውን ሳያውቁ የሽነድዎችን የሐሰት ወሬ የሚያሰራጩ መብዛታቸው ወሬው እንደፈለገ እንዲዞር እረድቷቸዋል።

በውጭ ሀገርም ሆነ በሀገር ቤት እጅግ ቅኖች፣ለሀገር አሳቢዎች እና የኢትዮጵያን ከፍ ማለት የሚፈልጉ ብቻ ሳይሆን በተጠሩበት ሁሉ ቀድመው ለሀገራቸው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስለ ኢትዮጵያ ከሽነድዎች በሚሰሙት የውሸት እና የተጋነነ ወሬ ተጨንቀው ሌሎችን በማስጨነቅ ሳያውቁት የሽነድ ቫይረስ ያስተላልፋሉ።ሽነድዎች ዋና ዓላማቸው ይህ ነው።ሕዝብ እንዳይረጋጋ፣እንዳይደሰት እና ተስፋ እንዳይታየው ማድረግ ስለሆነ ሽነድ መሆናቸውን ሳያውቁ የሽነድን ሥራ የሚሰሩትን ከቤተሰብነት እስከ መልካም ወዳጅ ቀርበው የውሸቱን ወሬ ይነዙባቸዋል።

ባጠቃላይ በቀጣይ ወራት ኢትዮጵያን ለመረበሽ በጦር ሜዳ ያልተሳካለት የውስጥም ሆነ የባዕዳን ኃይሎች የቀራቸው ብቸኛ መንገድ ሽነድ ( ሽብር ነዥ ድርጅት) ነው።መንግስትም ሆነ ሕዝብ ከጠጅ ቤት እስከ ሸራተን ባር፣በሞባይል ልስክ ከሚለቀቅ የውሸት ወሬ እስከ የዩቱብ የውሸት ወሬ ነዥ ተናበው ነው የሚሰሩት።ሸነድ በተራ መንደር ውስጥ ብቻ የሚገኙ አይደሉም።በመንግስት መስርያቤት እና በመንግስት መገናኛ ብዙሃንም ሳይቀሩ የሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ላይ የረቀቁ የስነ ልቦና ዘመቻ የምትከፍት ቃላት በመሰንቀር ወይንም መልካሙን ዜና በመደበቅ ካልተቻለ ቆርጦ በማስተላለፍ ሁሉ ሸነድ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ይሰራል።ስለሆነም ከሀገር ቤት እስከ ባሕር ማዶ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከቤተሰብ እስከ ጎረቤት፣የቅርብ እና የሩቅ ወዳጅ ሁሉ ሳያውቀው የሸነድ አስተላላፊ እንዳይሆን ነቅተው እና ተግተው እራሳቸውንም ቤተሰባቸውንም መጠበቅ አለባቸው። 

========================//////================

 ********************************
ማስታወቂያ /Advertisement 
====================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 
  

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...