ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, April 11, 2014

የኢትዮጵያ የውጭ ብድር በ 2001 እና በ 2005 ዓም መካከል ባሉት ዓመታት ብቻ በ156 % ወደ 11.17 ቢልዮን ዶላር ማደጉን ያሳያል በተቃራኒው ''ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ 16.5 ቢልዮን ዶላር ከሀገር ወጣ''


ኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት በለየለት የገንዘብ ዘረፋ ላይ መሰማራታቸውን እራሱ መንግስትም ያመነው ጉዳይ ነው።አንዳንድ ባለሥልጣናቱንም ዘብጥያ ማውረዱ ይታወቃል።ሆኖም የኢትዮጵያ አንጡራ ሃብት በቢልዮን የሚቆጠር ዶላር አሁንም እየተመነዘረ መውጣቱ የዓለም ዓቀፍ ጥናቶች አመላክተዋል።የሚገርመው ነገር ግን እንደተጠበቀው የሙስና ዘመቻ ሲባል የነበረው የውሃ ሽታ ሆኖ መቅረቱ ነው።አሁን የሙስና ኮሚሽን መኖሩን የሚያስታውሱት ምናልባት በለጋሃር በኩል ሲያልፉ ህንፃውን ከተመለከቱ ብቻ ነው።

ጥቂቶች በናጠጡበት፣ ሙስና ከሃይማኖት ድርጅት እስከ ቁንጮ ባለስልጣናት የተካኑበት ተግባር ነው። ጉዳዩ የበለጠ የእያንዳንዱን ሰው ትኩረት የሚሻ መሆኑን የምንረዳው ሀገሪቱ በገፍ ከውጭ ከሚቀርበው እርዳታ በተጨማሪ በከፍተኛ መጠን እየገባችበት ያለው የብድር ዕዳ ነው።በአግባቡ በፓርላማ የማይመከርባቸው፣ ፓርላማ ላይም ቢነሳ ሁሉም አጨብጭቦ የሚወጣበት ፓርላማ ከመሆኑ አንፃር ብድሩን የሚያፀድቀው አካል ምን ያህል ኃላፊነት እየተሰማው ነው? የሚለው ሌላው አጠያያቂ ጉዳይ ነው።ዕዳው ለልጅ ልጅ የሚቀመጥ እየተቀመጠልን መሆኑን አለመዘንጋት ጠቃሚ ነው።

የኢትዮጵያ የገንዘብ እና ኤኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ድረ-ገፅ እንደሚያመለክተው በ 2001 እና በ 2005 ዓም መካከል ባሉት ዓመታት ብቻ  የኢትዮጵያ የውጭ ብድር በ 156 % ማደጉን ያሳያል።ይሄውም በ 2001 ዓም 4.35 ቢልዮን የነበረው ብድር በአምስት ዓመታት ውስጥ ወደ 11.17 ቢልዮን ዶላር መመንደጉን ያሳያል።ባጠቃላይ የቅሌት መዝገባችን ወደ 16.11 ቢልዮን ዶላር ደርሷል። አብዛኞቹ በመንግስት የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ዋና ምንጫቸው የውጭ ብድር ነው።ብድር አትራፊ ለሆኑ አዋጭ ፕሮጀክቶች ከሆነ ሙሉ በሙሉ አይወቀስም ነገር ግን ተበድሮ ለሙስና እና ለጥቂቶች ኪስ ማድለብያ ሲሆን ወንጀሉን ያከብደዋል።

ትናንት ሚያዝያ 2/2006 ዓም የ ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ባቀረበው የአምስት ዓመት ትራንስፎርሜሽን ክንውን ላይ ከተባለው ግብ ኢትዮጵያ መድረስ አለመቻሏን አምኗል። የምክር ቤቱ ብቸኛ ተቃዋሚ አቶ ግርማ ''ቀድሞውንም ዕቅዱ በአግባቡ ያልታሰበበት ለመሆኑ አሁን ላለበት ውጤት መብቃቱ በራሱ ምስክር ነው'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ከፖሊሲ ችግር በተጨማሪ ቅጥ ያጡ የኢህአዲግ ባለስልጣናት ሙስና ዋነኛው ምክንያት ለመሆኑ አያጠራጥርም። ከእነርሱ ጋር አብረው የሚዘርፉ ግን ሀገሪቱ አድጋለች እያሉ ሪፖርት ለማውጣት የሚሽቀዳደሙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን እዚህ ላይ መዘንጋት አይገባም።

 ከላይ መግስት እራሱ  ያመነውን የብድር መጠን ካወሳን ቀጥለን ለሙስናው ማስረጃ ባለፈው ዓመት ግንቦት ላይ መሰረቱን ዋሽግተን ላይ ያደረገው ''ግሎባል ፋይናንስ እንተግርቲ'' ከኢትዮጵያ  ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ 16.5 ቢልዮን ዶላር ከሀገር ወጣ ይላል።(Ethiopia lost 16.5 Billion to illegal smuggling of cash out of the country in 10 years) ለትውልድ ከሚቀመጥ ብድር ላይ ከተሞች ሲብለጨለጩ እናይ ይሆናል።ግን ሀገሪቱ ከተበደረችው መጠን አንፃር እየተሰራ ነው ወይ? ስንል ትልቅ ጥያቄ ይጭራል። ጥያቄውን ይህንን ያህል ብድር የተበደረች ሀገር ዋና ከተማዋ ነዋሪ ከ25% በላይ የሚሆነው ውኃ ማግኘት አልቻለችም ይህም ቁጥሩ ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጋ ሕዝብ ነው ስንባልስ?።

ጉዳያችን
ሚያዝያ/2006 ዓም  

No comments: