ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, April 27, 2014

የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን መተግበር ሌላ፣ ኦሮምኛ ተናጋሪ ገበሬዎችን በግፍ ከመሬታቸው መንቀል ሌላ ፣ኦሮምኛ ተናጋሪ ገበሬዎችም ከኢትዮጵያ ሌላ ሀገር የላቸውም።

አዲስ አበባ ዙርያ ገበሬዎች በእርሻ ላይ 

አዲስ አበባ ከ 3.5 ሚልዮን ሕዝብ በላይ ውሎ ያድርባታል።ከተማዋ አሁን ካላት የህዝብ ብዛት በላይ እንደምትጨምር ሳይታለም የተፈታ ነው።ገጠር ወደ ከተማነት እየተቀየረ ይመጣል እንጂ ከተማ ወደ ገጠርነት ሊቀየር አይችልም።ዕድገት ባለፈ ታሪኩ ያስመሰከረው ይህንኑ ነው።

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማን ለማስፋፋት ከተያዘው ማስተር ፕላን አንፃር ከተማዋ በኢህአዲግ አከላለል መሰረት ከ 'ኦሮምያ' ክልል መሬት ለመውሰድ በነበረው ሂደት ውስጥ በርካታ ገበሬዎች መሬታቸውን እንደሚለቁ በመታወቁ ተቃውሞዎች በክልሉ ቢሮዎች እና ከዩንቨርስቲ ተማሪዎች ተሰምቷል።

በመሰረቱ ኦሮምኛ ተናጋሪ ገበሬዎች ሌላ ሀገር የላቸውም።ተወልደው ያደጉባት አፈር ፈጭተው ውሃ ተራጭተው ያደጉባት መሬት ኢትዮጵያ ነች።ከቀያቸው ''ተነሱ!'' የሚል ቀጭን ትእዛዝ ማስተላለፍ በራሱ ሃሳፊነት የጎደለው ተግባር ነው።አንድ ሰው ከመሬቱ ለመነሳት ቢያንስ ከሁለት አንዱ መስፈርቶች መሟላት አለባቸው።
አንደኛው በፈቃዱ ወደ ሚፈልገው ቦታ ሲሄድ እና ሌላው ከለመደው ቦታ ለመሄድ የበለጠ ጥቅም የሚያስገኘለት ክፍያ ሲሰጠው ነው።ከእዚህ ውጭ  በዜግነትም ሆነ ለሀገር በማሰብ በምንም በማይበልጠው ሃብታም ቦታው መወሰድ አለበት ማለት በእራሱ የአስተሳሰብ ድህነት ነው።ለኢትዮጵያ ሀብታምም ሆነ ድሃ እኩል አይን ሊታዩ ይገባል።ሀብታሙ መሬቱን ከፈለገ ድሃውን የሚያማልል ልዩ ጥቅም በህጋዊ ሰነድ አረጋግጦ መስጠት አለበት።በከተሞች የቀድሞ ይዞታ የሆኑ ቦታዎች ሲወሰዱ መሆን ያለበትም ይህ ነበር። እየሆነ ያለው ግን ሀብታሙ  ወደድሃው ሲመጣ የመንግስትን ጡንቻ ይዞ መሆኑ ነው ጉዳቱ።

በአዲስ አበባ ዙርያ ያሉ የኦሮምኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን ለዘመናት ከኖሩበት ቦታ ሊወረወሩ አይገባም።የሚነሱ ከሆነ በሚያማልል ጥቅም እነርሱም አምነውበት ከሆነ ብቻ መሆን ይገባዋል።በአንድ ወቅት ከከተማ እርቆ የነበረ ቦታቸው  ከተማው ሲለጠጥ ደረሰባቸው እና የመሬታቸውን ተፈላጊነት አናረው።ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።የመሬታቸው ዋጋ ሲጨምር ጉልበተኛ ተገቢውን ክፍያ በሚያማልል መልክ ሳይሰጣቸው ፈድራል ፖሊስ ይዞ እያስፈራሩ አርቆ ማስፈር ምን አይነት ፍትሃዊነት ሊሆን ይችላል? ይህንኑ ጉዳይ የተቃወሙ የዩንቨርስቲ ተማሪዎችን መደብደብ እና ማሰርስ ምን ያህል የዜጎች የመጠየቅ መሰረታዊ መብትን መጋፋት ነው? ማናቸውም ፕሮጀክቶች በቅድምያ ከፕሮጀክቶቹ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ ማሳመን ይጠይቃል።ከእዚህ ውጭ ከጋምቤላ እስከ ቡራዩ  እና አምቦ መስመር የፕሮጀክቶች ግልፅነት የማነስ ጥያቄን እና በቂ ምላሽ የመስጠት አቅም ማነስን  በፌድራል ፖሊስ የመፍታት አባዜ እጅግ አደገኛ አካሂያድ ነው።

እዚህ ላይ የማስተር ፕላኑን ትግበራ ከንፁሃን ገበሬዎች መፈናቀል ጋር በተያየዘ እንጂ አዲስ አበባ እራሷ ''የምንስትሶ'' ነች እና ማስተር ፕላኑ የማስፋፋት ትግበራ ሊያዝ አይገባም የሚሉት የተሳሳተ እና ደካማ አስተሳሰብ እንደሆነ እረዳለሁ።''ገብረ ጉራቻ የምንትስ ደብረብርሃን የእገሌ'' ስለሆነ በሚል ስሌት የገበረዎቹን መፈናቀል የሚቃወሙ በራሳቸው የተሳሳተ ተምኔት ገብተው የምስኪን የኦሮምኛ ተናጋሪ ወገኖቻችንን ችግር ለሕዝቡ እንዳይደርስ ያደረጉበት ብሎም ከቀሪው ሕብረተሰብ ጋር በመጋጨት እና በማጋጨት የሚደክሙ መኖራቸው ይታወቃል።ይህ እንግዲህ ቀላሉን ጉዳይ  በአጉሊ መነፀር ለማየት እስከሚያዳግት ድረስ ያጠበቡበት የጥበት ደረጃ ተቀባይነት ሊያገኝ አይችልም።

ጉዳዩን ያነሱ ተማሪዎችም ይፈቱ! ፕሮጀክቶችም ህዝብን አሳታፊ እና የህዝቡን ይሁንታ ሳያገኙ አይተግበሩ።

ጉዳያችን
ሚያዝያ 19/2006 ዓም


No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...