ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, April 7, 2014

''ከአያያዝ ይቀደዳል፣ከአነጋገር ይፈረዳል'' አሁንም ጥያቄው የኢህአዲግ/ወያኔ መንግስት የአባይን ግድብ ከልቡ ይፈልገዋልወይ? የሚለው ነው።(የጉዳያችን አጭር ማስታወሻ)

ዓባይ 

በአባይ ላይ የሚገነባው ታላቁ ''የህዳሴ ግድብ'' ከተጠናቀቀ እና መሰራት ከተቻለ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ አትሆንም የሚል ዕምነት የለኝም። የአካሄድ፣ቀድሞ ሳይታቀድ  የፕሮጀክቱ በድንገተኝነት መገለፅ፣የህዝብ ዲፕሎማሲ አመራሩ፣ከፖለቲካዊ ፍጆታ አውጥቶ የህዝቡ የማድረግ ሂደቱ ወዘተ ላይ አሁን በዝርዝር አልገባበትም።

 እኔን እየሞገተኝ ያለው ጥያቄ ኢህአዲግ/ወያኔ ከልቡ ነው ወይ 'አባይ አባይ' የሚለው? የሚለው ጥያቄ ነው።

ለሁሉም እስኪ እነኝህ ጥያቄዎች እንመልከት እና የእራሳችንን ፍርድ እንስጥ  -

 የአባይ ግድብ የኢትዮጵያ ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን መንግስት ካመነ - 

- ለምንድነው በሀገር ውስጥ ያለውን የውስጥ ፖለቲካ ለማላላት ፍቃደኝነት የማያሳየው?

- ለምንድነው እለት ከእለት ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ጋር ሲጋጭ፣ምሁራንን ስያሸሽ፣ሃይማኖትን ለመቆጣጠር ሲባዝን የሚታየው?

 - የአባይ ጉዳይ ትልቅ የዲፕሎማሲ ንቅናቄ የሚጠይቅ በተለይ የዲያስፖራውን ድጋፍ የሚፈልግ መሆኑ ይታወቃል።የዲያስፖራው ጥያቄ ደግሞ ግድቡ  አይገንባ አይደለም።ይልቁን የሰብአዊ መብት አያያዝ፣እኩል ተሳታፊነት፣ተጠቃሚነት እና የጎሳ ፖለቲካ በሃገር ዓቀፍ ፖለቲካ ይቀየር የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።የአባይ ግድብ ቀዳሚ አጀንዳዬ ነው ካለ መንግስት ለምን እነኝህን ጥያቄዎች መመለስ አልፈለገም?

-  በግድቡ ሳብያ ከውጭ የሚመጣው ተፅኖ ቀላል አለመሆኑ እየታወቀ። የውጭው ተፅኖ ደግሞ ከሀገር ውስጥ የልዩነት መስፋት ጋር ኢትዮጵያን ትልቅ አደጋ ላይ እንደምጥላት እየታወቀ ለምንድነው ዲፕሎማሲው በደካማ እና ለስራው ብዙ ልምድ በሌላቸው ሰዎች እንዲመራ የሚያደርገው? (የዲፕሎማሲ ሥራ እራሱን የቻለ ሙያ ነው የ ጤና ሙያ ያጠና ሰው ዲፕሎማሲው ላይ አምጥቶ ማሰራት ማለት ምን ማለት ነው?)

 - የአባይ ጉዳይ የኢትዮጵያ ቀዳሚ አጀንዳ ከሆነ መንግስት ለምንድነው ኢትዮጵያውያንን አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ በሚለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው?

- ለግድቡ የገንዘብ ድጋፍ ትኩረት የሚሰጥ ከሆነ -
        - ለምንድነው ለአንድ ሃውልት አሩሲ ውስጥ 20 ሚልዮን ብር የሚያወጣው? ለምንድነው ለአንድ ባለሥልጣኑ   መታከምያ ከሰላሳ ሚልዮን ብር በላይ የሚያወጣው?
        - ለምንድነው በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር በውጭ የሚኖረውን ዲያስፖራ ለመሰለያ የሚጠቅሙ ሶፍት ዌሮችን ለመግዛት የሚያወጣው?

- የአባይ ጉዳይ የኢትዮጵያ ቀዳሚ አጀንዳ ከሆነ ለምንድነው ግብፅ ከደርዘን በማያንሱ ሃገራት እየዞረች የዲፕሎማሲ ዘመቻ ስታደርግ መንግስት ጉዳዩን ለማስረዳት ልዑካንን በየሃገራቱ መላክ ያልፈለገው?

ባጠቃላይ የአባይ ጉዳይ ትልቁ የኢህአዲግ/ወያኔ የትኩረት ጉዳይ የሚመስላቸው ትንሽ ሳይሳሳቱ የቀሩ አይመስለኝም።የመንግስት ትልቁ ጉዳይ አይመስለኝም።ትልቁ ጉዳይ ቢሆንማ ኖሮ የሀገር ውስጥ ፖለቲካውን ለማረም በተነሳ ነበር።ግን ይህንን አላደረገም። በትክክል ለሀገር የሚያስብ መንግስት ለአባይ ግድብ የሚከፍለው ትንሽ መስዋዕትነት (መስዋዕትነት ከተባለ) የሀገር ውስጥ ፖለቲካውን በፍጥነት አሻሽሎ ብሔራዊ ህብረት እና እንድነትን ማጠናከር ነው።

በመሆኑም መንግስት ይህንን ለማድረግ ፍቃደኛ ባልሆነበት ሁኔታ የሚያመላክተው አንድ ነገር ግድቡን መፈለግን አይደለም።ግድቡን መጀመር ከፍተኛ ገንዘብ ማሰባሰብ፣በተሰበሰበው ገንዘብ በሚሰጡ የፕሮጀክት ስራዎች ''የእህት'' ኩባንያዎችን አቅም ማፈርጠም፣ተደናቂነትን ሀገር ውስጥ ማግኘት፣ለረጅም ጊዜ የስልጣን ገበያ የሕዝብን ሃሳብ ወጥሮ ይዞ ማቆየት የኢህአዲግ ትልቁ አጀንዳው ይመስላል። ''ከአያያዝ ይቀደዳል፣ከአነጋገር ይፈረዳል'' አሁንም ጥያቄው የኢህአዲግ/ወያኔ መንግስት የአባይን ግድብ ከልቡ ይፈልገዋል ወይ? የሚለው ነው።

ጉዳያችን
መጋቢት 2/2006 ዓም 

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...