Wednesday, May 13, 2020

ኢትዮጵያ ተደፍራለች! አለመቆጣት የመታመም ምልክትም ነው።

ከእዚህ በታች ያለውን የእንግሊዝኛ መልዕክት በተለይ በትዊተር እና ሌሎች የማኅበራዊ ሚድያዎች ያሰራጩ።ተፅኖ የማትፈጥር ቃል በምድር ላይ እንደሌለች ይመኑ።
Here are the two messages of Gudayachn to Egypt and the USA stands regarding the Grand Ethiopian Renaissance Dam. 
>> If Egypt tries to provoke Ethiopia in any military action, it will lose the Nile as a whole
forever.
>> If the USA supports Egyptians' injustice and unfair stand in case of the Grand Ethiopian Renaissance Dam, America will lose her Africa base forever.

ሰው የሚያስደስተው ነገር ሲኖር ይደሰታል።የሚያስቆጣው ጉዳይ ላይ ይቆጣል።ከእዚህ በተቃራኒ የሚሆን ሰው የጤንነቱ ትክክለኛነት ያጠራጥራል።በሚያስቆጣው ጉዳይ አለመቆጣት ጉዳዩን በደንብ አለመረዳት  የህመም ምልክት ነው።

ግብፅ በዓባይ ግድብ ዙርያ እያለች ያለው በሚገባ የገባን አይመስልም።ግብፅ እያለች ያለችው በቤትህ ውስጥ ለምትቀዳው አንድ ኩባያ ውሃ እኔ መፍቀድ አለብኝ ነው።ኢትዮጵያ ግድቡን የምትጠቀመው የኤሌክትሪክ ማመንጫ ተርባይነሩን አሽከርክሮ እንዲያልፍ ብቻ ነው።ይህንንም ግብፆች እንዲረዱት ለዓመታት የህዝብ ዲፕሎማሲ ልዑክ ከመላክ ጀምሮ በውይይት ሱዳንን ጨምሮ በቅርቡም አሜሪካ ባለችበት ተወያየች።አሁንም ግን ግብፅ እየፎከረች ነው።

ዛሬ ብቻ የግብፁ አልሃራም ጋዜጣ በግድቡ ዙርያ ሁለት የፉከራ ፅሁፍ አውጥቷል።አንዱ ርዕሱ ''የግብፅን የሕይወት መስመር መከላከል'' ይላል ሁለተኛው ፅሁፍ ደግሞ ''የሕዳሴው ግድብ የጫወታው ፍፃሜ'' ይላል።ይህ ሁሉ ፉከራ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለ ውሃ ነው።ይህ ድንበር ጥሶ ወታደር የማዝመት ያህል ነው።አንዳንዴ ኢትዮጵያውያን በጣም በበዛ ደረጃ ሳይታወቀን ''ፍትሃዊ'' የሆንን እየመሰለን የራሳችን ውሃ ላይ ግብፅ፣ሱዳን እና አሜሪካ እያወሩ መሆኑን ሁሉ  ሳያስቆጣን መቅረቱ በራሱ አደጋ አለው።እያወራሁ ያለሁት ስለ ተራው የእኔ ብጤ ሰው ነው።ተራው ሕዝብ በደንብ ሊሰማው ይገባል።ሊቆጣ ይገባል።ሙከራው ካላናደደን፣ነገ በተግባር ሲመጣም አንቆጣም።መቆጣት ጤነኛነት ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሚድያዎች፣የኪነጥበብ ባለሙያዎች እና ባለስልጣናት ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገባው ደረጃ እንዲቆጣ ማድረግ አለባቸው።አለመቆጣት በራሱ ህመም ነው።በተለይ ሚድያዎች እና የኪነጥበብ ሰዎች ለይምሰል ከሚመስል አባባል  ወጥተው ተጨባጭ ማስረጃ የሚያሳይ ደረጃውን የጠበቀ ፕሮግራም በማዘጋጀት ህዝቡ እንዲቆጣ ማድረግ መቻል አለባቸው።ይህ የቁጣ ስነ ልቦና መድረስ ያለበት ደረጃ መድረስ አለበት። ከሚፈለገው የቁጣ ስሜት በትንሹ ካነሰ በራሱ አደጋ ነው።አሁንም መቆጣት የጤነኛነት ምልክትም መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።አለመቆጣት እና የድፍረቱን ልክ አለመረዳቱ በራሱ ግዙፍ አደጋ አለው።ግብፆች የህዝቡን የቁጣ መጠን አይለኩም ማለት አይቻልም።

ስለሆነም ኢትዮጵያውያን በሚገባ እንዲቆጡ ማድረግ ያስፈልጋል።የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት ለመቀራመት የሚፈልጉ ኃይሎች የህዝቡን የመቆጣት ልክ ይለኩታል።ስለሆነም በቤትህ በብርጭቆ የተቀዳ ውሃ ከሌላ ቦታ የመጣ ሰው ውሃውን የምትጠጣው እኔ ስፈቅድልህ ነው ስትባል እንዴት መቆጣት አለመቻልህ የጤና አለመሆኑን እራስን መጠየቅ ይገባል።ይህንን ጥያቄ ጋዜጠኛውም የኪነጥበብ ሰውም መረዳት አለበት።ስሜት የሚኮረኩሩ እና የባለቤትነት ስሜቱን የሚያስረግጡ ዝግጅቶች ከምድያዎች ያስፈልጋል።መንግስት በዲፕሎማሲው የግለት ልክ ከብዙ መረጃዎች አንፃር ሊሄድበት ይችላል።ግለቱ ከመንግስት መምጣት ያለበት የግብፅ የቀይ መስመር ደረጃ ይኖራል።ለግብፅ ሚድያፉከራ ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስት መልስ መስጠት የለበትም።ሕዝብ ግን መቆጣቱ ለግብፃውያን በደንብ መታየት አለበት። ለግብፃውያን ሲባል ብቻ አይደለም፣የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህ ጉዳይ ካላመመው እና በሚገባው መልክ ካላስቆጣው በራሱ ብዙ ነገር ማለት ነው።መታመም አንዱ ሆኖ ማለት ነው።

ባጠቃላይ የውሃው ሙሌት እስኪረጋገጥ ሕዝብ በግብፅ ጉዳይ መቆጣቱን በሚገባ ማሳየት አለበት።ቁጣው ከሚገለጥበት መንገድ አንዱ ከማኅበራዊ ሚድያም ኢትዮጵያውያን ጉዳዩ በደንብ እንዲረዱት ቅስቀሳ ማድረግ ነው። እዚህ ላይ ጉዳዩን የማያውቅ ማን አለ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል።እኔ የምለው ግን በሚገባ ደረጃ ሕዝብ ቁጣው መታየት አለበት።መናደድ አለበት ነው።ይህ በራሱ ከግድቡ ሥራ ጋር አብሮ የሚሄድ የስነ ልቦና ልእልና መገለጫ መሆኑ ሊገባን ያስፈልጋል።በተለይ፣ በተለይ በየትኛውም ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን  በትውተር እና ሌሎች የማኅበራዊ ሚድያዎች የኢትዮጵያ በውሃዋ የመጠቀም ፍትሃዊ መብት ላይ ያተኮሩ እጅግ ኃይለኛ ቃላትን የያዙ መልዕክት ያላቸው  ነገር ግን ከስድብ እና ከወረዱ ቃላት የፀዱ ዓረፍተ ነገሮች ማሰራጨት ያስፈልጋል።

February 28, 2020 Al Jazeera report on Ethiopian Grand Renaissance Dam 


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Monday, May 11, 2020

የዓባይ ጉዳይ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው።ከዓባይ ወንዝ ተጠቃሚ የገልፍ አገሮች፣ ግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት ለፀጥታው ምክርቤት ደብዳቤ የፃፈችባቸው ሁለት ዓላማዎች።

የዓባይ ግድብ 
=========   

የዓባይ ጉዳይ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው።ከዓባይ ወንዝ ተጠቃሚ የገልፍ አገሮች

ግብፅ የኢትዮጵያን የዓባይ ግድብ ጉዳይ ባላት ኃይል ሁሉ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።የውሃው ተጠቃሚ አገራት ደግሞ ግብፅ ብቻ አይደለችም።በዓባይ ውሃ እየተጠቀሙ ያሉት የመካከለኛው ምስራቅ በተለይ የገልፍ አገራት፣እስራኤል ጭምር ናቸው።ሳውዳረብያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በዓባይ ውሃ ተጠቃሚዎች ናቸው። ብዙዎች ውሃው በቀጥታ የሚሄድበትን አገር እንጂ ከጀርባ በውሃው እየተጠቀሙ ያሉ አገሮች አናስባቸውም።ይህንን ጉዳይ በሰፌው ወደፊት እመለስበታለሁ።ሆኖም ግን የአገራችን ምሑራን ጉዳዩ ከጀርባው ያሉትን የውሃው ተጠቃሚዎች በደንብ ማሳየት እና የኢትዮጵያ ህዝብም እንዲያውቀው ማድረግ አለባቸው ብዬ አስባለሁ። 

የገልፍ  አገሮች  ከአባይ የሚጠቀሙት ከመጠጥ ውሃ ሽያጭ ብቻ ሳይሆን ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ በምታመርተው መስኖ የሚገኘውን የእርሻ ምርት በቀላል የትራንስፖርት ወጪ ደጃቸው ድረስ ስለሚደርስ ነው።ከፍራፍሬ እስከ ሩዝ እና ጥጥ ምርት በዓባይ መስኖ ይመረታል።አንዳንዶቹ  ዘመናዊ የእርሻ ቦታዎች ደግሞ በገልፍ አገሮች ቱጃሮች እና ንጉሳውያን ቤተሰቦች የገንዘብ ድጎማ የተመሰረቱ ናቸው። 

ሰኔ 7/2018 ዓም እኤአ  የገልፍ ዜና አገልግሎት   የተባበሩት አረብ ኢምረት እና ሳውዲ አረብያ 12 ወራት የፈጀ ፣ከሁለቱም አገሮች 350 ባለስልጣናት እና ባለሙያዎች የተወያዩበት በ44 የጋራ ስልታዊ ፕሮጀክት ላይ ተስማሙ።ፕሮጀክቱ በሶስት ምሰሶዎች ላይ የተመሰረተ ነበር።እነርሱም የምጣኔ ሀብት፣ዕውቀት እና የሰው ኃይል እና ፖለቲካ፣ወታደራዊ እና ፀጥታ ምሰሶዎች ናቸው።
''The UAE and Saudi Arabia announced on Tuesday a joint vision for economic, developmental and military integration through 44 joint strategic projects.A total of 350 government officials from different fields prepared “The Strategy of Resolve” within 12 months. The strategy outlines three main axes: the economic axis, the human and knowledge axis, and the political, security and military axis'' Gulf news June 07,2018.
ይህ ስምምነት ሁለቱ አገሮች በግብፅ ያላቸውን ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅም ሁሉ የሚያጠቃልል ነው።የግብፅ ኢኮኖሚ ደግሞ ከዓባይ ወንዝ ውጪ ሌላ ሕይወት የለውም።በተመሳሳይ መንገድም የፀጥታ ጉዳዩን ስንቃኝ ተመሳሳይ የጥቅም መተሳሰር ይታያል።ስለሆነም የእዚህ ሁሉ ማሰርያው ''ሪሞት'' ኢትዮጵያ ጋር እንዳለ መገንዘብ ይቻላል።ኢትዮጵያ ግብፅን ብቻ ሳይሆን የገልፍ አገሮችን ምጣኔ ሃብታዊ እና ፀጥታ ሁሉ የመቆጣጠር አቅሟ በዓባይ ግድብ ሳብያ እጇ ላይ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ስለሆነም ይህ ግድብ የሞት ሽረት እና የህልውናችን ጉዳይ መሆኑን መረዳት ይቻላል።በሌላ በኩል የግድቡን አለመሳካት የሚመኙ አገሮች ስፋት እና ስብጥርም በሚገባ መረዳት ተገቢ ነው።
 ግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክርቤት ደብዳቤ የፃፈችበት ምክንያት ሁለት ጉዳዮችን ያለመ ይመስላል
ግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ መፃፍ በየቀኑ በሚባል ደረጃ በዜና ድረ ገፆች ይወጣል።ይህም አንዱ የግብፅ መረብ ዓላማ ነው። ደብዳቤውን የፃፈችበት ምክንያት ግን ሁለት ዓላማዎች እንዳለው ከሚወጡት ተደጋጋሚ ዜናዎች መረዳት ይቻላል። እነርሱም -
1ኛ) ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ ብዙ ምላሽ እንድትሰጥ እና ጉዳዩን በዓለም አቀፍ ደረጃ አጀንዳ ለማድረግ 
ግብፆች ለፀጥታው ምክርቤት የፃፉት ደብዳቤ ምንም ያህል በየቀኑ በተለያዩ ገፆች እንዲወጣ ለማድረግ ቢሞክሩም በኮሮና ወረርሽኝ ሳብያ አገሮች እና ዓለም አቀፍ ሚድያዎች ሽፋን ሰጥተው አላወሩትም።የአገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም በጉዳዩ ላይ ሃሳብ ሲሰጡ አልታዩም። በእርግጥ የአረብ ሊግ በፓርላማ አባላት ስብስብ እና ከወራት በፊት በካይሮ ከኮሮና ወረርሽኝ በፊት መግለጫ አውጥቷል።ይህ ግን የተለመደ ጭፍን ግብፅን የመደገፍ እና ኢትዮጵያን እንደ ስልታዊ ጠላት የማየት የተሳሳተ አመለካከት ውጤት ነው።ባጭሩ ግን የግብፅ ደብዳቤ ዓለም አቀፍ ትኩረት አልሳበም ስለሆነም ኢትዮጵያ እንድታጮህላት ግብፅ ትፈልጋለች።ስለሆነም ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መውሰዱ አዋጪ ነው ብላ አሰበች።ከእዚህ ጋር ተያይዞ ጉዳዩን ፖለቲካዊ እና ዓለም አቀፍ ጣልቃ ገብነት እንዲኖር የማድረግ ፍላጎቷ በዋናነት እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።
2ኛ) ሁለተኛው ፍላጎቷ በኢትዮጵያ በግንባታ ላይ ያሉ ዓለም አቀፍ የግንባታ ኩባንያዎች ለምሳሌ የጣልያኑን ሳሊኒ እና የቻያና ኩባንያዎችንም ለማስፈራራት እና አገሮቻቸው ጉዳዩ በፀጥታው ምክር ቤት እየታየ ያለ ጉዳይ አድርገው በማቅረብ በኩባንያዎቹ ላይ ተፅኖ ለማስፈጠር  ነው።ከሁለት ወራት በፊት ግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ከመፃፉ በፊት፣ የግብፅ ፓርላማ  ድንገተኛ ስብሰባ ጠርቶ ነበር።ስብሰባው ሁለት ዓላማዎች የያዘ ነበር።እነርሱም በአባይ ግድብ ላይ እየተሳተፉ ያሉ ኩባንያዎች በግብፅ ምንም አይነት ፕሮጀክት ወደፊት እንዳይሰጣቸው፣አሁንም የወሰዱት ካለ በፍጥነት እንዲዘጋ የሚል እና የዓለም አቀፍ አበዳሪ ባንኮች ለኢትዮጵያ ምንም አይነት ብድር እንዳይሰጡ ለመጠየቅ ነበር።ሆኖም የተጠራው ስብሰባ ከ24 ሰዓታት ያነሰ ጊዜ ሲቀረው  በወረርሽኙ ተሳቦ እንደተሰረዘ  ተሰማ።ሆኖም ጉዳዩ ቆይቶ በተደረገ ምክክክር ለፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን በመምራት ፓርላማው ያሰባቸውን ሁለት ጉዳዮች ማሳካት ይቻላል የሚል ምክረ ሃሳብ ተነስቶ እንደሆነ ቀጥሎ ከተደረጉት ሂደቶች መረዳት ይቻላል።ፓርላማው ጠርቶት የነበረውን ድንገተኛ ስብሰባ እና ስለ ግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማንነት ለማንበብ ይህንን ይጫኑ።
ባጠቃላይ ኢትዮጵያ የዓባይ ግድብ ጉዳይ ላይ ፈፅሞ ወደኃላ ማለት የሌለባት የሞት እና የሽረት እንዲሁም የህልውና ጉዳይ መሆኑን መረዳት አለባት። ይህ ጊዜ ደግሞ ዓለም በወረርሽኙ ሳብያ በብዙ ውስጣዊ ጉዳዮች የተወጠረበት ከመሆኑ አንፃር  ምንም ዓይነት ችግር ለመፍጠር በተቀናቃኝ መንግሥታት ቢሞከረም ጊዜው ግን ከብዙ ትግል ጋር መወጣት ከተቻለ ለኢትዮጵያ መልካም ዕድል ይዞ መጥቷል።ሕዝቡም ጉዳዩን በእዚህ ደረጃ መረዳት አለበት።
ጉዳያችን ሚድያ፣ኮሚኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት 
Gudayachn Multimedia, Communication and Consultant
Gudayachn Multimedia, Kommunikasjon og Konsultent 

Saturday, May 9, 2020

አትታለሉ! በታኝ ኃይሎች ዛሬ ቀድመው ያሉት በምርጫው ውጤት ማግስት ሊሉት የነበረውን ነው።


አዲስ አበባ Addis Ababa

የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደሰንሰለት ተያይዞ የሚመጣ ነው።ከዘመናት በፊት ኢትዮጵያን የገጠሟት ጠላቶች አዎን! ጠላቶች ናቸው መልክ፣ጊዜ፣እና ድምፅ ቀይረው የመጡት።ኢትዮጵያ የተዳከመች በመሰላቸው ጊዜ ሁሉ በግርግር ከጉዞ ምሕዋሯ አስተው እነሱ ወደሚፈጉት  የሲዖል መንገድ ሊመሯት ይፈልጋሉ።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላለፉት ሁለት ዓመታት የሄደበት ውጣ ውረድ በራሱ ጥሩ ተሞክሮ ነው።ለውጡ ከሰማይ በድንገት የመጣ አይደለም።ዛሬ አንዳንድ አክትቪስቶች የመገናኛ ብዙሃኑን ስለያዙ ብቻ ጧት ማታ እንደሚነግሩን እነርሱ ብቻ ከኮምፕዩተር ጀርባ ተቀምጠው ባደረጉት ቅስቀሳ ወይንም እስር ቤት ወርደው ስለወጡ የመጣ አይደለም። አንድ ትልቅ ዛፍ ለመጣል የዛፍ ቆራጩ እና የገመድ ሳቢው ሚና ወይንም የዛፉ ማርጀት ብቻ መተረክ ያላዋቂነት መለያ ነው። ዛፉ እንዲቆረጥ ቆራጩ ጫካውን አልፎ እንዲመጣ መንገድ የመራ አለ።ቀድሞ ዛፍ በምላጭ እንደማይቆረጥ አውቆ ብረት ከአፈር ለይቶ ያነጠረ፣በመጥረብያ መልክ የሰራ፣የሳለ፣ለመጥረብያው እጀታ ያበጀ፣መጥረብያውን ለሕዝብ ለማድረስ ገበያ ወስዶ የሸጠ ሁሉ ለዛፉ መቆረጥ አስተዋፅኦ አለው።

የኢትዮጵያ ለውጥ እንዲመጣ፣በ1985 ዓም በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ግቢ እየጮሁ ሕይወታቸው ካለፈው፣በስደት ተንከራተው በምዕራብ አገር ሄደው ለኢትዮጵያ ድምፅ ለመሆን የራድዮ እና ቴሌቭዥን ጣብያ መስርተው ስርዓቱን ካጋለጡት እስከ ኤርትራ በረሃ የትጥቅ ትግል ለማድረግ የሞከሩት፣በፋኖ ተደራጅተው ከተፋለሙት እስከ በቄሮ ተደራጅተው አደባባይ እስከወጡት፣በኢህአዴግ ውስጥ ሆነው ከታገሉት ከአሁኑ አመራሮች እስከ አገር ወዳድ እና በታማኝነት አገሩን እስካገለገለው ባለሙያ ሁሉ ለለውጡ አስተዋፅኦ ማድረጉን መረዳት ይገባል።

በታኝ ኃይሎች ይህንን ሁሉ ክደው እነርሱ መንግስት አውጪ እና አውራጅ፣እነርሱ ብቻ ለለውጥ የታገሉ፣ሌላው ጠባቂ ሆኖ የኖረ፣እነርሱ ብቻ ስልት እና ግብ የሚያውቁ ሌላው የእነርሱን ያህል ያልተማረ፣የማይመራመር እና የማይገባው አድርገው የሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ቆይቶ እራሳቸውንም አታልሏቸው አፋቸውን ሞልተው በብቸኝነት ስለለውጡ እንዲያወሩ ብዙዎች በዝምታችን ፈቅደንላቸው ኖረናል።ከአሁን በኃላ ግን ይህ መቆም አለበት።ኢትዮጵያ በክብር ከትውልድ ወደ ትውልድ እስከተሸጋገረች ድረስ እንጂ  የመበተን ዓላማቸውን ባመቻቸው ጊዜ ለማሳካት ከሚጥሩ ጋር ብዙ እርቀት መሄድ አይቻልም።

ሰሞኑን በታኝ ኃይሎች ከህወሓት እስከ ጀዋር መሐመድ፣ከበቀለ ገርባ እስከ አልሸባብ የሚናገሩት ንግግር አንድ ነው።ለሰበብ የምርጫው የጊዜ ሰሌዳ መቀየሩን እንደምክንያት ያንሱት እንጂ ዋና ግቡ ግን ቀድሞውንም ያሰቡበት ምርጫው ተደረገም አልተደረገ በኃይል አተራምሰው የኢትዮጵያን ማንነት ማጥፋት ነው። ለእዚህ ደግሞ ኢትዮጵያን ቀድሞም ለማጥፋት የረጅም ጊዜ ምኞት የነበራቸው  ባዕዳን የቆየ ዕቅዳቸውን አቧራ እያራገፉ ዛሬ ላይ ለማስፈፀም ከምንጊዜውም በላይ ተጠራርተዋል።

በታኝ ኃይሎች ዛሬ የሚያነሱት ጉዳይ ማለትም የምርጫው የጊዜ ሰሌዳ መቀየር እና እርሱን ተከትሎ ከመስከረም 30 ወዲህ የሽግግር መንግስት መመስረት አለበት የሚለው አባባል ከምርጫው በኃላም ሊያነሱት የነበረውን ጉዳይ ነው አሁን እየነገሩን ያለው። አሁን ያለው በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የሚመራው መንግስት ምርጫ እንደሚያደርግ ያስታወቀው ከ ስድስት ወራት በፊት ነው። ቀድም ብሎም የምርጫ ቦርድ በሕግ እንዲመሰረት ማድረጉ ይታወቃል።የምርጫው የጊዜ ሰሌዳ ለነሐሴ ወር ተይዞ ቢቆይም በመላው ዓለም በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ሳብያ ምርጫው በነሐሴ ሊደረግ እንደማይችል አስታወቀ።ምርጫው መደረግ የማይችልበት ምክንያት የሚያሳምን ነው።ኮሮና ወረርሽኝ ካለው አደገኛ የመዛመት አቅም አንፃር ምርጫ ማድረግ ይቻላል እያሉ እየሞገቱ ያሉ ህወሓቶች እና የቀሩት በታኝ ኃይሎች ሃሳብ በራሱ ከህዝብ ይልቅ የስልጣን ወንበራቸውን ማጠናከርን ብቻ እንደሚፈልጉ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።

በታኝ ኃይሎች ከጀዋር ጀምሮ በምርጫው ሂደት ይዘውት የነበረው ስልት ሁለት ነው።የመጀመርያው በምርጫው ሂደት ከልባቸው የሚሳተፉ መስለውመቅረብ፣ሂደቱን ማሰናከል እና በመጨረሻ የምርጫው ውጤት ለእነርሱ የማያዳለ ከሆነ በምርጫ ያሸነፈውን ኃይል አሁን እንደሚሉት ሕጋዊ መንግስት አይደለም የሽግግር መንግስት ይመስረት በሚል ሁከት መፍጠር ነው። ይህንን ሃሳባቸውን ሳያውቁት ብዙ ጊዜ ተንፍሰውታል።ለማስረጃነት ጀዋር እራሱ ከቤተመንግሥቱ የአንድነት ፓርክ ጀምሮ የኢትዮጵያ መሠረትነት የሚያሳዩ ነገሮች ጋር አንድነት የፈጠረ ሃሳብ አላቸው ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር መስራት እንደማይፈልግ ብዙ ጊዜ ተናግሯል።ይህ ማለት በምርጫ ቢያሸንፉም አሁን ከሚለው የተሻለ ነገር እንደማይል ጥሩ ማሳያ ነው።

ስለሆነም ለማጠቃለል፣በታኝ ኃይሎች ዛሬ ገና ምርጫው ሳይደረግ የሚያነሱት የግርግር መንግስት ጥያቄ ከምርጫው ማግስት ሊያነሱት የነበረ ጉዳይ እንደነበር እና የምርጫው ሂደትም ሆነ ውጤት ምንም ይሁን ምን ቀድሞም  የነበራቸው ዓላማ አገር በማተራመስ ወደ ስልጣን መውጣት እና ኢትዮጵያን እንዳልነበረች ማድረግ በመቀጠልም ለቀጣሪ ባእዳን አሳልፎ መስጠት እና  የራሳቸውን የስልጣን እና የንዋይ ፍላጎት ከማርካት ውጪ ሌላ ፍላጎት እንደሌላቸው መታወቅ አለበት።በመሆኑም በታኝ ኃይሎች ዛሬ የሚሉት ሁሉ ወደፊት ያሰቡት ተንኮል የነበረና ዛሬ በኮሮና ምክንያት ሳያስቡት የተፉት መርዝ መሆኑን ሁሉም አውቆ ኢትዮጵያ ወይንም ሞት! ብሎ ቆርጦ ሊነሳ የሚገባበት ጊዜ ነው።እርግጥ ነው፣ኢትዮጵያውያን ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ብዙ ሕዝብ ከምጣኔ ሀብት ድቀቱ ሆነ ወረርሽኙ ከሚያስከትለው ጉዳት አንፃር  ቀላል ፈተና አይደለም።ሆኖም ግን አገር የምትፈተነው በእንዲህ ያለ ጊዜ በመሆኑ ለበታኝ ኃይሎች ፈፅሞ ላለመንብርከክ እና አገርንም ለጥፋት ኃይሎች ላለመስጠት በንቃት እና በትጋት መከታተል እና መነሳት ያስፈጋል።ምርጫው የጊዜ ሰለዳው የተቀየረበት ምክንያት አሳማኝም ብቻ ሳይሆን ተገቢ ነው።ከወረርሽኙ በኃላ የሚደረገው ምርጫ የኢትዮጵያ ወሳኝ መንገድ ነው።በታኝ ኃይሎች የሚጨፍሩበት የፖለቲካ መድረክ ከሆነ ደግሞ ምርጫ አስር ዓመትም  ዘግይቶ የአገር ህልውና መከበር ቅድምያ ማግኘት አለበት።


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Thursday, May 7, 2020

የዓባይን ግድብ ጉዳይ ተከትሎ ኢትዮጵያ በመጪው ወራት ሊገጥማት የሚችሉትን ተግዳሮቶች ለመወጣት የውስጥ አንድነቷን እና ፀጥታዋን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መጠበቅ አለባት።


ጉዳያችን ልዩ አጭር ዘገባ
================
ሚያዝያ 29/2012 ዓም 
(ጉዳያችን ድረ ገፅ፣ፌስ ቡክ እና ቴሌግራም ላይ የተለጠፈ)
================
- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ለግብፅ እና ሱዳን ደብዳቤ ልከዋል፣
- ግብፅ ለፀጥታው ምክር ቤት የላከችው ደብዳቤ ዋና ይዘት፣
- ሱዳን ከአሜሪካ የምትፈልገው ዋና ጉዳይ 
===================
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ለሱዳን እና ለግብፅ ኢትዮጵያ የዓባይ ውሃን ለመሙላት ባወጣችው የጊዜ ሰሌዳ እና በሂደቱ ላይ ሁለቱ አገሮች እንዲስማሙ እና የኢትዮጵያን አዲስ ዕቅድ (ፕሮፖዛል) በደብዳቤ ልከው እንደነበር የግብፁ አልሃራም በድረ ገፁ ማምሻውን ገልጧል።ደብዳቤው የተላከው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሚያዝያ 10/2020 ዓም ሲሆን በጉዳዩ ላይ ግብፅ ባለመስማማቷ ግንቦት 1/2020 እኤአ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክርቤት ይህንኑ ደብዳቤ ያስገባችው አቤቱታ ይህንኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ደብዳቤ የሚቃወም አንቀፅ እንዳለበት ያትታል።

እንደጋዜጣው አባባል የኢትዮጵያን አዲሱን ፕሮፖዛል ሱዳንም እንዳልተቀበለች የሚገልጥ ዓረፍተነገር ግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክርቤት በላከችው ደብዳቤ ላይ ጠቅሳለች።የሱዳን መቃወም ወይንም ሱዳን ኦፊሻል ምላሽ ለኢትዮጵያ መስጠት አለመስጠቷን ጉዳያችን አላረጋገጠችም።የግብፅ ሚድያዎች በዓባይ ግድብ ዙርያ በርካታ የሐሰት ዜናዎችን በመንዛት ብዙ ጊዜ ይወቀሳሉ።

የግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክርቤት የላከችው ባለ 17 ገፅ ደብዳቤ በዋናነት ''ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግን አላከበረችም ግዴታዋን ትወጣ'' የሚል እና የውሃ ሙሊቱ ግብፅ ሳታውቀው እንዳይፈፀም የሚጠይቅ ነው።የኢትዮጵያ ውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ ኢትዮጵያ ውሃውን መሙላት በያዝነው ክረምት እንደምትጀምር እና ይህንን  ከማድረግ ምንም የሚያግዳት እንደሌለ መግለጣቸው ይታወሳል።በሌላ በኩል የግብፁ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር  ሳመህ ሹክሪ ከእስቶንያው አቻቸው ጋር በስልክ መወያያታቸውን አልሃራም ዘግቧል።የኢትዮጵያ መንገናኛ ብዙሃንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ከኢስቶንያ አቻቸው ጋር መወያየታቸውን በቅርቡ ዘግበው ነበር። ኢስቶንያ የወቅቱ የፀጥታው ምክር ቤት አባል ነች።

ይህ በእንዲህ እያለ ሱዳን ከሃያ ዓመታት በኃላ ለመጀመርያ ጊዜ ከአሜሪካን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን በማደስ ላይ እንደሆነች እና አምባሳደሯን ዋሽንግተን ላይ መሰየሟ ተሰምቷል።የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  ፖምፕዎ ትናንት ተጠይቀው በቅርቡም አሜሪካ አምባሳደሯን ወደ ካርቱም እንደምትልክ ለእዚህም እየሰራች መሆኗን ገልጠዋል።የሱዳን ዋነኛ እና ቀጣዩ ከአሜሪካ የምትፈልገው ሱዳንን ከአሸባሪ መዝገብ ውስጥ እንድትሰርዛት ነው።

ግብፅ በአባይ ጉዳይ ሱዳን ኢትዮጵያን እንድትቃወም  የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም።የሱዳን የውስጥ ጉዳይ ከመግባት እና የምትፈልገውን መንግስት ለመመስረት ከመጣር እስከ መለማመጥ የሚደርስ ሥራ ላይ ነች።በቅርቡ ሁለት የወታደራዊ አይሮፕላኖች  ለኮሮና ወረርሽ የሚረዱ መርጃ የህክምና ቁሳቁስ ይዘው ከካይሮ ወደ ካርቱም በረዋል።

የዓባይን ግድብ ጉዳይ ተከትሎ ኢትዮጵያ በመጪው ወራት ሊገጥማት የሚችሉትን ተግዳሮቶች ለመወጣት የውስጥ አንድነቷን እና ፀጥታዋን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መጠበቅ አለባት።ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ከሳምንት በፊት በምክር ቤት ባደረጉት ማብራርያ ላይ ''ኢትዮጵያ ልትወረር በምትችልበት በእዚህ ጊዜ''   የሚሉ ቃላት ከመጠቀማቸውም በላይ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ ላይም የአገር ሉዓላዊነት ጥቃት ሊደርስ የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ጠቁመዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ ነው አንዳንድ ተቃዋሚዎች በድርድር መንግስት ይመስረት የሚል አጀንዳ እያራገቡ ያሉት።ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በሰጡት መግለጫ ይህ ፈፅሞ እንደማይሆን እና መንግስት ከሕገ መንግስቱ እና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ውጪ የሚሄዱትን እንደማይታገስ እና ለእዚህም በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልጠዋል።

በምርጫው መራዘሙ ላይ ከተስማሙት ዋና ዋና የተቃዋሚ ኃይሎች ውስጥ  ኢዜማ፣ እናት ፓርቲ እና አብን ተጠቃሽ ናቸው።ኢትዮጵያውያን ይህ ወቅት በታኝ  ኃይሎችን ተጋፍጠው እና የውስጥ አንድነታቸውን አጠንክረው ኢትዮጵያን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የሚነሱበት ወሳኝ ጊዜ መሆኑን ከመቼውም ጊዜ በላይ መረዳት አለባቸው።

ጉዳያችን ዩቱብ ሰብስክራይብ ያድርጉ 



ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Wednesday, May 6, 2020

ፊደል በቆጠሩ ሰዎች በማኅበራዊ ሚድያ የሚቀነቀነው የሰሞኑ የትግራይ ''ቾቪንዝም'' ፕሮፓጋንዳ ሕዝቡን ወደ ጥፋት ይዞት እንዳይሄድ ያሰጋል።

- በፅሁፉ መጨረሻ ላይ ድምፃዊ ሙሐመድ አህመድ እና ሌሎች አርቲስቶች የተሳተፉበት ''መንቃት አንጀምርም ወይ!'' አዲስ ቪድዮ ዜማ ያገኛሉ።
============
በሮበርት ሃይደን በፒተስበርግ ዩንቨርስቲ እኤአ 1993 ዓም ሕትመት ላይ  ዩጎዝላቭያ የመበታተን አደጋ ሳይደርስባት ምሁራን የሚፅፉት ፅሁፍ በጸሃፊዎቹ ባፈለቁት ሃሳብ ወይንም ትንታኔ መሆኑ ቀርቶ የት አካባቢ ተወለዱ የሚለው ገኖ ወጥቶ እንደነበር ያትታል። በወቅቱ የብሔር ''ቾቪንዝም'' ዋና መለያ እየሆነ መምጣቱን ይሄው ሕትመት ያስነብባል (Hayden, R. M. 1993)

''ቾቪንዝም'' ቀጥተኛ ትርጉሙ ከመጠን ያለፈ የእኔ ብሔር፣ፆታ፣ባሕል ወይንም ቡድን የተለየ እና ልዩ ተፈጥሮ እና አቅም አለው ብሎ የማሰብ ምናባዊ ስሜት ነው።ቃሉ የመጣው በ1830ዎቹ እአአቆጣጠር የፈረንሳዩ ናፖልዮን ታማኝ ወታደር ኒኮላ ቾቨኒ ነው።ቃሉ በተለይ በዘመነ ናዚ፣በሴቶች የእኩልነት ትግል የወንዶች የበላይነትን ለመታገያ እና በዘመናችን የተነሱት የጎሳ አክራሪዎች መገለጫ እየሆነ ያለ ቃል ነው።

ሰዎች የራሳቸው ጎሳ ከሁሉ የበለጠ መሆኑን የሚነግሯቸውን በመጀመርያ ደረጃ ሲሰሙ እንደቀላል እና እነርሱ እንደዛ የማያስቡ ነፃ ሰዎች እንደሆኑ ይመለከቱታል።እየቆየ ግን አብሮ ከማደግ እና እየተጋነኑ የሚቀርቡት ትርክቶች በምክንያታዊነት የሚያምነውን፣የሰው ልጅ ሁሉ እኩል ነው ብሎ በዕምነቱ የፀናውን ሳይቀር እንደ ዘመኑ ኮሮና ቫይረስ ሳያውቀው ይወረዋል።ችግሩ ደግሞ እራሱ መያዙን ሳያውቀው ምልክቱን ሳያሳይ መኖሩ ነው።

በኢትዮጵያ የተለያዩ የብሔር ፖለቲካ ቡድኖች የብሔራቸውን አባላት ለመቀስቀስ ''ቾቪንዝም'' በግልጥም ሆነ በስውር አራምደዋል።ሻብያ፣ህወሓት፣ኦነግ እና በቅርቡ ደግሞ በዓማራ ዙርያ የሚያቀነቅኑ አደረጃጀቶች ሁሉ የእነርሱ ብሔር ከሌላው የተለየ እንደሆነ አድርገው ለመሳል በርካታ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አድርገዋል፣መፃህፍት ፅፈዋል፣ካድሬ አሰማርተው ህዝባቸውን ሰብከዋል።አሁን በሀገራችን የምናየው የግጭት መንስኤ አንዱ ለዓመታት የተዘራው የብሔር  ''ቾቪንዝም'' ውጤት ነው። ቅስቀሳው የአጭር ጊዜ ግብን አልሞ የተነሳ ስለሆነ ከጊዜ በኃላ ቀስቃሾቹ ለመመለስ ወይንም ለማብረድ ቢሞክሩም አይችሉም።ይልቁንም ለስልት ብለው የጀመሩት 'የብሔር 'ቾቪንዝም'' በመጨረሻ ራሳቸውን ይዞ የሚጠፋ አደገኛ መርዝ ሆኖ ይወጣል።

በተለይ ህወሓት እና ሻብያ ወጣቱን ወደ ትግል ለማስገባት ከተጠቀሙበት መንገድ አንዱ ይሄው ''ቾቪንዝም''ነው።ለምሳሌ ህወሓት  በደርግ ዘመን መቀሌን ከተቆጣጠረ በኃላ አካባቢውን ለቀው ወደ መሃል አገር ለመሄድ ብዙ ወጣት ማሰቡን እንደተረዳ ያደረገው የዘፈን ፕሮግራም እያዘጋጀ ሴቶቹ ወንዶቹ ወገብ ላይ መቀነት እንዲያስሩ በማድረግ ታላቂቱ ትግራይን ትተህ  ወዴት ትሄዳለህ እኔ ሴቷ ስዋጋ የሚል መልዕክት እንዲተላለፍ በማድረግ ብዙ ወጣት ለመሰብሰብ ችላለች። 

''ቾቪንዝም'' በዓለማችን ላይ ብዙ ሕዝብን መቀመቅ ውስጥ ከቷል።የ''ቾቪንዝም'' ቀስቃሾች ሲያረጁ የተከሉት መርዝ ቶሎ ስለማይነቀል ለትውልድ የሚቆይ ፀብ አፍርቶ ያንን 'ታላቅ ሕዝብ ነህ' ያሉትን ሕዝብ የበለጠ  ችግር ውስጥ  ከተውታል።ለምሳሌ ሂትለርን ብንመለከት  የጀርመን አርያን ሕዝብ ታልቅ እንደሆነ እና ዓለምን መግዛት እንዳለበት ሰበከ።ብዙ ጀርመኖች ለካ ታላቅ እና የተለየን ነን እያሉ ተከተሉት። የዓለም ሕዝብ በህብረት ተነስቶ ከአራት ማዕዘን ከቦ አገሪቱን ለሁለት ተከፍላ ለዓመታት እንድትቆይ ተደረገች። የ''ቾቪንዝም'' አደገኛነት ጤነኛውንም ሰው ''ታላቅ ነኝ እንዴ?'' እያለ እንዲያብድ ያደርገዋል። የስብከቱ ጥልቀት እና ብዛት ከሰውነት ያወጣል። 

ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚድያ እና በትግራይ ሚድያዎች የተጀመረው ይሄው ነው።በትግራይ ሚድያዎች የሚቀርቡ ቃለ መጠይቆች  በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጠያቂዎቹም ሆኑ መላሾቹ የትግራይ ''ቾቪንዝም'' ለማንፀባረቅ ሲሞክሩ ይታያሉ። ''ይሄ ሕዝብ ሻብያ በ 1977 ዓም መንገድ ዘግታበት አለቱን ሰንጥቆ በሱዳን በኩል መንገድ የሰራ በዓለም ላይ ልዩ የሆነ ሕዝብ ነው'' አለ አንዱ ዛሬ በአንድ የቀጥታ የማኅበራዊ ሚድያ የቪድዮ ፕሮግራም ላይ ቀርቦ።በማኅበራዊ ሚድያ በተለይ በየቀኑ የትግራይ ''ቾቪንዝም'' ላይ ብቻ የሚያወሩ የቀጥታ ስርጭቶች ቁጥራቸው እየበዛ ነው።ብዙዎቹ አቅራቢዎች  በአውሮፓ እና በአሜሪካ የሚኖሩ ቅምጥሎች እና በኑሯቸው የደላቸው የመቀሌ ሕዝብ ውሃ ማጣት ያማያውቁ፣ሽሬ እንዳስላሴ ዙርያ ያለ ገበሬ ክሊኒክ በማጣት እናቶች እየሞቱ እንደሆነ የማያውቁ ፣ ነገር ግን ትግራይ ልዩ ሕዝብ እንደሆነ ሲሰብኩ ለአፋቸው አንዴም ሳት የማይላቸው ናቸው።

'የተከበራችሁ' የትግራይ  'ቾቪንዝም'' ፕሮፓጋንዳ አራማጆች ወደ ህሊናችሁ ተመለሱ።''ቾቪንዝም'' ማንንም ጠቅሞ አያውቅም።በእዚህ በ21ኛው ክ/ዘመን በእዚህ ፋሺሽታዊ ቅስቀሳ የሚታለል ትውልድ የለም።የሚታለሉ ቢኖሩ ከቀረው ሕዝብ ጋር በሰላም እንዳይኖር ከማድረግ ሌላ የምታተርፉት አንዳች ነገር የለም።ስሜታዊነት፣የውሸት ስብከት እና የአጭር ጊዜ ግብን ብቻ ታሳቢ ያደረገ  የ''ቾቪንዝም'' ስብከት መዘዙ ለልጆቻችሁም ጭምር ነው።ከሁሉ ጋር በፍቅር፣በመከባበር እና በመተጋገዝ ለመኖር የማይችል ትውልድ ማፍራት ነገ እራሱን የሚችል ሳይሆን የበለጠ ከሁሉ ጋር ልጋጭ በማለት የራሱም ሆነ የሌላው ፈተና የሚሆን ትውልድ ነው ማፍራት የሚቻለው።ስለሆነም የትግራይ ''ቾቪንዝም'' ሰባኪዎች ይህንን ክፉ ሥራ እንድታቆሙ ትለመናላችሁ። ቀደም ብሎ የኤርትራ፣ኦሮሞ፣ዓማራ ''ቾቪንዝም'' ስብከቶች ብለውት ብለውት ደክሟቸው ሁሉም ባይተዉት እጅጉን ቀንሰዋል።የቀሩት ደግሞ እድሜ ያስተምራቸዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።የትግራይ  ''ቾቪንዝም'' ግን በግልጥ እና በብዛት ሰሞኑን እንዳዲስ አገርሽቷል።አገሩ ሽማግሌ የሌለው አስመሰላችሁት።ይህንንስ እያያችሁ ዝም የምትሉ የትግራይ አባወራዎች እና እማወራዎችስ መምከር አይገባችሁም ወይ? የ''ቾቪንዝም'' ሥራ ማንን ጠቀመ? ስንቱን ለስደት እና ለባሕር አውሬ ከመዳረግ ሌላ ምን አተረፈ? ይልቁንም ፊደል በቆጠሩ ''ቾቪንስቶች'' ህዝቡ የተለየ እየተደረገ የሚሰበከው ስብከት ለመገንጠል ቅድመ ሁኔታ እንደሆነ እንዴት አይገባንም? ነገ ከጥፋት እና እልቂት በኃላ ጉዳዩ እንዴት ተነሳ ብሎ ማጥናት እና ምክንያቶቹን ለመዘርዘር የጥናት መድረክ ማንጋጋት አይጠቅም።ይሄው ጥፋቱ ሳይመጣ ''ቾቪንዝም'' ወይንም ሞት! ያሉትን ምከሩ።



ሰዋዊ ዜማ 


ጉዳያችን ሚድያ፣ኮሚኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት 
Gudayachn Multimedia, Communication and Consultant
Gudayachn Multimedia, Kommunikasjon og Konsultent 

ማጣቀሻ

1 Hayden, R. M. (1993). The triumph of chauvinistic nationalisms in Yugoslavia: Bleak implications for anthropology. Anthropology of East Europe Review11(1 & 2), 73-78.



ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Monday, May 4, 2020

የልጅ አዋቂው ጠቅላይ ሚንስትር ዓቢይ፣ ማስተዋል ያነሳቸውን አዛውንቶቹን የህወሓት ባለስልጣናት ለፍርድ ቢያቀርብ መቀሌ በከበሮ እንደምትደምቅ አትጠራጠሩ።


የጉዳያችን ማስታወሻ 
ሚያዝያ 27/2020 ዓም
  • በፅሁፉ መጨረሻ ላይ የቴዎድሮስ ካሕሳይ የትግሪኛ አዲስ ዜማ ቪድዮ ይመለከታሉ።

የልጅ አዋቂ የሚለው አባባል በኢትዮጵያውያን ብሂል ውስጥ የተለመደ ነው።ይህ ስም የሚሰጠው ሰው የግድ እድሜው በልጅ እድሜ ክልል የሚገኝ መሆን ኖሮበት አይደለም።ጎረምሳም ቢሆን ጎልማሳ ከአዛውንቶች ያነሰ ዕድሜ  ያለው ነገር ግን አስተሳሰቡ በሳል ከሆነ የልጅ አዋቂ የሚል ስያሜ ያገኛል።ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።የለውጡ ሂደት በራሱ በብዙ የስልጣን ፍላጎቶች፣የጥቅም ውጥረቶች፣የጎሳ ስሜቶች እና የአካባቢው ጅኦ-ፖለቲካ ሹክቻዎች ብታዩበትም ኢትዮጵያን እንደአገር ከማስቀጠል አልፎ በዓለም አቀፍም ሆነ በአካባቢያዊ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ቦታ አስፈላጊ አገር የመሆኗ ዕውነታ እንደገና ጎልቶ እንዲታይ አድርጎታል።

በእነኝህ ሁሉ ሂደቶች ውስጥ ግን የህወሓት ግልጥ እና ስውር ተንኮል በኢትዮጵያ ፖለቲካም ላይ ሆነ በምጣኔ ሃብቷ እና በውስጥ ሰላም እንዲሁም በሕዝብ የእርስ በርስ ግንኙነት ሁሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት  አድርሷል።የህወሓት የደህንነት ባለስልጣናት አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ ወደ መቀሌ እና ውጪ አገራት ከመሸሻቸው በፊት በኢትዮጵያ ያሉ ስስ የሆኑ የሃይማኖት ውጥረቶች፣የብሔር ቁርሾዎች እና የጥቅም ግጭቶች ያበጡባቸውን ቦታዎች ያውቁ ስለነበር እነኝህን ሁሉ አንድ በአንድ እየቆሰቆሱ እና በገንዘብ እንዲሁም በሰው ኃይል ድጋፍ እየሰጡ ግጭቶች በየቦታው እንዲፈነዱ አድርገዋል።ለግጭቶቹ ሁሉ ህወሓት ብቻ ተጠያቂ ነው ባይባልም በቀጥታ የለሉበትን ግጭቶች ግን ባብዛኛው በሎጀስቲክ፣በምክር እና በአይዞህ ባይ ፕሮፓጋንዳ የህወሓት ባለስልጣኖች እንደተባበሩ እና የይሁንታ ምልክት ሲያሳዩ እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው።

ህወሓት በእነኝህ ግጭቶች ሁሉ አልሳካ ሲላት በምጣኔ ሃብት ሴራ ውስጥ በቻለችው ለመነከር ሞከረች፣ይህ የምጣኔ ሃብቱ ሴራ አገር ያሽመደምዳል በመቀጠል ወደ ፖለቲካዊ ቅራኔ ያድጋል ብለው ሲያስቡ የኮሮና ወረርሽኝ መጥቶ ምጣኔ ሃብቱ ወደ የአደጋ ዕዝ  ባህሪ መያዙ ሲታወቅ እና የተማመኑበት የገንዘብ አቅምም በራሱ በቀውሱ ምክንያት እንደሚሟ ሲያውቁ ሁኔታዎች አለማዋጣታቸው ግልጥ ሆነላቸው።

ይህ በእንዲህ እያለ ነበር ህወሓት በኮረና ወረርሽኝ ሳብያ የዓለም ትኩረት በመቀየሩ በአለን አቅም የአቶ ኢሳያስን መንግስት መቀየር ላይ ብንሰራ የተሻለ ነው ወደሚለው ቀድሞም ያሰቡት ግን በሁለተኛ ደረጃ ሊሰራ ያቀዱትን ሥራ በቀዳሚነት የመስራት ውሳኔ ላይ የደረሱት። ይህ በእንዲህ እያለ ደግሞ የዓባይ ጉዳይ ከግብፅ ጋር ውዝግቡ ሲባባስ ህወሓት አዲስ አጀንዳ በውስጥ ማራመድ ጀመረች።በእዚህ ጊዜው ውስጥ ትኩስ የሆነ የነገር መጫርያ አጀንዳ ባልነበረበት ወቅት የህወሓት ባለስልጣናት ትኩስ ነገር መጫርያ አጀንዳ ሲያፈላልጉ የምርጫ ቦርድ በኮሮና ምክንያት የምርጫው ጊዜ ሰሌዳ በታሰበው ጊዜ ሊደረግ እንደማይችል ገለጠ። ይህ ጥሩ አጀንዳ ሊሆን እንደሚችል የህወሓት ባለስልጣናት ገመቱ። ስለሆነም ምርጫው መደረግ አለበት፣ካልሆነ ግን ትግራይ በራሷ ምርጫ ታደርጋለች የሚል ውሳኔ የማዕከላዊው የህወሓት ኮሚቴ ወሰነ ሲሉ ሚያዝያ 26/2012 ዓም ምሽት አስነገሩ።

ህወሓት በትግራይ ምርጫ ቢያደርግ ባያደርግ ለህልውናው ይረዳዋል? ብለን ብንጠይቅ እንደ ትግራይ ክልል ምንም ለውጥ አያመጣም። ድርጅቱ አፋኝ እና አምባገነን ለመሆኑ የትግራይ ሕዝብ ከማንም የበለጠ ያውቀዋል።ምርጫውም ለይስሙላ እንደሚሆን ፀሐይ የሞቀው ነው። ህወሓት ሕጋዊ አድርጎ እራሱን ለማታለል ብቻ የሚጠቀምበት ምርጫ እንደሆነ አላፊ አግዳሚው የሚያውቀው ነው። ይልቁንም የትግራይ ሕዝብ ወደ ኤርትራ የሚወስደው መንገድ የሚከፈተው እና ሕዝብ እንደፈለገ ነግዶ እና ገዝቶ የሚኖረው  ህወሓት ከስልጣኑ ሲወገድ  እንደሆነ ያውቃል።ይህ ብቻ አይደለም በትግራይ የኑሮ ውድነቱ ዋነኛ  ምክንያት በአቦይ ስብሐት እና ቤተሰባቸው በመላዋ ትግራይ የተዘረጋው የቤተሰብ የንግድ መረብ እንደሆነ ያውቃል።ከእዚህ በተጨማሪም ህወሓት ከአሁን በኃላ ለማዕከላዊ መንግስት ያለመታዘዝ ተግባሩን ከጨመረ ከማዕከላዊ መንግስት ከበጀት ጀመሮ  እስከ መሰረታዊ ፍጆታዎች ድረስ ህዝቡ ላይ የሚደርሰው ተጨማሪ የኑሮ ውድነት ከባድ እንደሚሆን ሁሉም የሚረዳው ነው።

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን በልጅ አዋቂው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በኩል የታየው ትዕግስት፣አርቆ ማስተዋል እና አላስፈላጊ የቃላት ምልልስ ውስጥ ከመግባት ይልቅ የመንግስት የዕለት ከዕለት ሥራ ላይ ማትኮሩ ለራሱ ለትግራይ ሕዝብ እና አዛውንቶች ግርምታን እና አድናቆትን አትርፏል።በተለይ በለውጡ መጀመርያ አካባቢ ህወሓት የትግራይ ተወላጆች በሙሉ ሊታሰሩ ነው፣ነግደው መኖር አይችሉም፣እያለች እርሷ እንደሸሸችው የትግራይ ሕዝብ በሙሉ መቀሌ እንዲገባ በውስጥም በግልጥም ያደረገችው ቅስቀሳ ሁሉ ውሎ አድሮ ውሸት መሆኑ ሲታወቅ ህወሓት ክፉኛ በትግራይ ሕዝብ እንድትጠላ ሆናለች።ይህንን አባባል አንዳንዶች ውሸት አድርገው ያዩታል።ይህንን የሚሉት በተለይ በውጭ  አገር ያሉ ካድሬ በመሆናቸው በኤርትራ ስደተኞች ስም የመጡ ከህወሓት የበለጡ ህወሓቶች በማኅበራዊ ሚድያ የሚሉት መሬት ላይ ያለውን የትግራይ ሕዝብ ስሜት የሚገልጥ አይደለም።

ስለሆነም ህወሓት አሁን የመጨረሻው መጨረሻ ላይ ደርሳለች።አጀንዳዎቿ ሁሉ አልቀዋል።የግጭት ፖለቲካዋ ከጎሳ እስከ የሃይማኖት ግጭት የሞከረችው ከሸፈ።ዛሬ ኢትዮጵያ ብዙ ስራዎች ቢያስፈልጉትም ከክልል የፖለቲካ ስሞች ከተከፋፈለ ኢህአዴግ ወደ ብልጥግና በሚል የሱማሌ እና የአፋር ክልል ሳይቀሩ የፖሊሲ አውጪነቱ ኃላፊነት ደርሰዋል።ይህ ብዙ ሥራ የሚፈልግ ቢሆንም ከአደገኛ የመበታተን አደጋ ቢያንስ በመዋቅር አያያዝ የተሻለ ማዕቀፍ ተፈጥሯል። የልጅ አዋቂው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በሚገባም በማይገባ መንገድ የሚተቹት የመኖራቸውን ያህል ወደኃላ ሂደቱን ስንመለከት ግን ብዙዎቹ ሂደቶች ትዕግስት  እና ማስተዋል የተሞሉ ነበሩ።አሁን ህወሓት በደረሰበት ምርጫ ለብቻዬ አደርጋለሁ የሚለው አደገኛ የቀይ መስመር ማለፍ ሂደት ግን የልጅ አዋቂው በቀላሉ ያልፈዋል ወይ? የሚለው አጀንዳ የሰሞኑ አጀንዳ መሆኑ አይቀርም።

አጀንዳው ከመወያያ አልፎ ሕጋዊ መሰረት የሌለው እና ህገ መንግስ ይከበር እያለ በመናገር የሚቀድመው የሌለው ህወሓት አሁን እራሱ የሕገ መንግስቱ ዋነኛ ጠላት መሆኑን መቀሌ ከገባ በኃላም አረጋግጧል።የአሁን ህገ መንግስቱን መጣስ ግን የልጅ አዋቂውን የመጨረሻ ደወል እንዲያሰማ የሚያስገድድ እንዳይሆን ያሰጋል።በእዚህ በኮሮና ዘመን ዓለም ሁሉ  ትኩረቱ ወረርሽኙ ላይ ነው።የኢትዮጵያ አየር ኃይል መቀሌ ገብቶ በወንጀል ሲፈለጉ የነበሩትን በቁጥጥር ስር አዋለ የሚለውን ዜና ዓለም በዜና አርእስት  ደረጃም አያነበው።ምክንያቱም ዜናው ሁሉ ኮሮና ነው።ይህ በራሱ ለልጅ አዋቂው መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል።በሌላ በኩል የልጅ አዋቂው ዝም ብሎ ወደ እዚህኛው እርምጃ አይገባም።መጀመርያ የትግራይ ሕዝብ በራሱ በህወሓት ላይ የሚነሳበት ብዙ ምክንያቶች በአጀንዳ ላይ ተቀምጠዋል።አጀንዳዎቹ ደግሞ የልጅ አዋቂው ብቻውን አይመክርባቸውም። የአስመራው ፕሬዝዳንት (በአራዳ አነጋገር ''ኢሱ'') በትግራይ የሚፈጠረው ቀውስ ያሳስባቸዋል።

ህወሓት ከመቀሌ ቢወገድ የሚኖረው ክፍተት የህዝብ ስደት እንዳያስከትል እና ግጭት እንዲፈጠር ኢሱ የማይፈልጉበት ሁለት ምክንያቶች አሉ።የመጀመርያው ሌላ በግርግሩ ስሙን የቀየረ ህወሓት እንዳይመጣ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሚኖረው አለመረጋጋት መዘዙ ለራሷ ለአስመራም ስለሚተርፍ ነው።ስለሆነም በእዚህ ሳምንት መጨረሻ አዲስ አበባ ደርሰው ሰኞ ምሽት አዲስ አበባን የለቀቁት አቶ ኢሳያስ ዋና አጀንዳቸው ህወሓት እና ህወሓት እንደሚሆን አለመገመት አይቻልም። የሆነው ሆኖ ግን  የልጅ አዋቂው  ጠቅላይ ሚንስትር ዓቢይ፣ ማስተዋል ያነሳቸውን አዛውንቶቹን የህወሓት ባለስልጣናት ለፍርድ ቢያቀርብ መቀሌ በከበሮ እንደምትደምቅ አትጠራጠሩ።

አዲሱ የቴዎድሮስ ካሕሳይ የትግሪኛ ዜማ 




ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

The Ethiopian Orthodox Tewahedo Church is in turmoil in Athens, Greece.

His Holiness Abune Mathias I, Patriarch of the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church, met with Greece's Ambassador to Ethiopia, Antonios Sg...