ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, July 5, 2022

የወለጋው የንፁሃን እልቂት የሚገታበት መንገድ አንድ እና አንድ ብቻ ነው።ቅሉን መስበር! ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ቅሉን ስበሩት ወይንም ኢትዮጵያንም እርስዎንም እስኪሰብርዎ ተቀምጠው ጠብቁት።

ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ
===============
ጉዳያችን /Gudayachn
===============

የሁለት ወር ህጻን ተኩሶ የሚገድል፣እርጉዝ በስለት የሚወጋ፣አዛውንት እና ባልቴቶችን በዘራቸው እየለየ የሚገድለው ከኦሮምያ ምድር የበቀለው የዘመናችን የናዚ ቡድን በምን ያህል ደረጃ  በህዝብ ላይ ጥላቻ እንዳለው አሳይቷል። የገዳዩ መጋቢ አዳማም፣ነቀምትም አዲስ አበባም ተቀምጦ በንፁሃኑ ሞት እየሳቀ ነው።አቶ ታዬ ደንዳ የኦሮምያ ብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የሰላም ሚኒስቴር ዴታ ችግሩ የገዘፈ እንደሆነ እና ከራሱ ከኦሮምያ ክልል አስተዳደር ውስጥ ችግር እንዳለ በገለጸበት የማኅበራዊ ሚድያ ጽሑፉ ላይ ተጠያቂነት እንዲኖር አሳስቧል።የኦሮምያ ክልል ውስጥ እየተፈጸመ ያለው ጭፍጨፋን ''እሰይ!'' የሚሉ ከኦሮምያ ልዩ ኃይል እስከ የክልሉ አንዳንድ ባለስልጣናት ድረስ አሉ። በእነርሱ እሳቤ ይህ ጭፍጨፋ የስልት ማስፈጸምያ አድርገው ያዩታል።በሻገተ አዕምሮ ውስጥ ሆነው እራሳቸውን እንደ ታላቅ ሴረኛ እየቆጠሩ በህዝብ ደም የሚቀልዱ ናቸው።

የሱማልያ ክልል የፀጥታ ችግር ለሁሉ ምሣሌ በሚሆን ደረጃ የተረጋጋ ሲሆን የኦሮምያ ክልል በእዚህ ደረጃ የህዝብ ደም እንደ ጎርፍ እንዲፈስ የተተወው ብቻ ሳይሆን ክልሉ በመቶዎች በአንድ ጀንበር የሞቱበት የማይመስለው ለምንድን ነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።በኢትዮጵያ ምድር የሁለት ወር ህጻን ጨምሮ የመግደል ስነ ልቦና ከኦሮምያ ምድር መብቀሉ ስለሚያሳፍራቸው እና በተወለዱበት የኦሮምያ ክልል ቀድሞ ባልተጨበጠ ታሪክ ''ከመቶ ዓመታት በፊት ጡት ተቆርጧል'' ብለው የቂም ሃውልት ይሰራልን ብለው ያዙን ልቀቁን ያሉ ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከሁለት ወር ህጻን እስከ እርጉዝ የሚገድል አረመኔያዊ ድርጊት ፈፃሚ መነሳቱን ሊሸፋፍኑ የሚሞክሩ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ጭፍጨፋው የፈሪነት መገለጫ ብቻ ሳይሆን ለዓመታት የተተረከ ትርክት ውጤትም ነው።

አሁን ብዙ ፍልስፍና የሚደረደርበት ጊዜ አይደለም።ህዝብ የሚጨፈጭፈው የኦነግ ቡድን በኃይል እንደመጣ የሚመለሰው በኃይል ብቻ እንጂ ጀዋር አለስልሶ እንደሚናገረው በድርድር አይመለስም።በኃይል ለመመለስ ደግሞ የኦሮምያ ክልል በውስጡ የተቦካካ እና ለኦነግ ስስ ዓይን ባላቸው የልዩ ኃይል አባላት እና አንዳንድ ባለስልጣናት ቸልተኝነት የተሞላ ስለሆነ እስካሁን አመርቂ ውጤት አላስገኘም። ስለሆነም አሁን አዲስ አቅጣጫ መያዝ አለበት።

በቅርቡ በኢትዮጵያ የሚነሱ የጸጥታ ችግሮች የኋላ መነሻ እና የአሁኑ ተዋናዮችን ትተን ለምን መፍታት አልተቻለም? የሚለውን አንኳር ጥያቄ መመለስ እና በተለይ አሁን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ መንግስት በቆራጥነት ሊወስዱት የሚገባው እርምጃ ምንድነው? የሚለው ላይ ብቻ ለማትኮር እሞክራለሁ።የሱማሌ ክልል ግዙፍ የጸጥታ ችግር ያውም ከጎረቤት ሱማልያ ሽብርተኞች  የሚርመሰመሱበት ሆነው እያለ የሱማሌ ክልል ያለው አስተዳደር እንደ ኦሮምያ ብልጽግና በሴራ ስላልተተበተበ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልል በተሻለ የጸጥታውን ሁኔታ አስከብሯል።

አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሲያከብሩት ወይንም ሲጠነቀቁለት የኖሩት እና በሂደት ይፈታል ብለው የጠበቁት የክልሎች የጋራ የጥምረት የጸጥታ አጠባበቅ ሂደትን ወደፊት በማምጣት የጎሳ ቅሉን አሁን የመስበርያው ጊዜዎ ነው። የጎሳ ፖለቲካን እንደ እንቁላል ቢንከባከቡት የመጨረሻው ውጤቱ በገማ እንቁላል ሰውነትን ማበላሸት ነው። አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የጎሳ ቅሉን ከመስበር ሌላ አማራጭ የለም።ቅሉ እንዲሰበር የኢትዮጵያ ህዝብ በጉጉት እየጠበቀ ብቻ ሳይሆን ህይወቱንም ለመስጠት ዝግጁ ነው። ይህ የጎሳ የፖለቲካ  ቅል የመስበር ሥራ ዛሬ ባይሆን ነገ  በሁሉም በሰላም ወይንም በኃይል እንደሚሰበር በሁሉም ዘንድ ይታወቃል። ቅሉ እንዳይሰበር በሁሉም መልክ ካሉት የጎሳ ፖለቲካ አድናቂዎች በኩል ዘመቻ ለመክፈት ይሞክራሉ። ይህ ግን ከኢትዮጵያ ህዝብ አቅም አይበልጡም። ይህ ቅል እራስዎም ላይ በመስቀል አደባባይ የግድያ ሙከራ ከመፈጸም እስክ ብዙ ሴራዎች ሰርቶብዎታል።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር 

የዛሬዋ ኢትዮጵያ በአንዱ ቦታ የተነሳ የጸጥታ ችግር በሌላው ጫፍ ያለው ኢትዮጵያዊ ደርሶ እንዳያግዝ ተደርጋ የተሰራች የህወሃት ስሪት የሆነች ኢትዮጵያ እጅግ አደገኛ ሁኔታ ላይ ነች።ይህ አደጋ ግን ቅሉን በድፍረት በመስበር ይስተካከላል። ቅሉን መስበር የሚጀመረው በአንዱ ጫፍ ያለ ኢትዮጵያዊ በሌላ ጫፍ ያለ ኢትዮጵያዊ ደርሶ እንዳያድነው ተደርጋ የተሰራችበትን ስሪት አሁን መሰበር አለበት።ይህ እንዳይሆን እና ይህ የእርስ በርስ መተጋገዝ በተለይ በክልሎች መካከል ቢኖር ኢትዮጵያ ትፈርሳለች የሚሉን የኢትዮጵያን ህዝብ የማያውቁት የህወሃት ውላጆች እነ ጀዋር ናቸው። ኢትዮጵያውያን ልዩ ህዝብ ናቸው።በአክቲቪስቶች ስነ ልቦና የምትመራ አይደለችም። መሬት ላይ ያለው እውነታ ሌላ ነው።

አሁን ሃቅን እና እውነትን መጋፈጥ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን።ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ይህንን ቅል ሳይሰብሩ መሻገር ቢቻል ጥሩ ነበር። ቅሉን ከመስበር ትንሽ መዘግየት ቢቻልም ሸጋ ነበር። ነገር ግን አይቻልም። ዛሬ እነጀዋር እና ሌሎች የኢትዮጵያውያንን ተነጣጥሎ መመታት የሚያስደስታቸው ኃይሎች ሁሉ የሚነግሩን የኦሮሞ እና የአማራ ህዝብ በጸጥታ ጉዳይ ላይ ተጋግዘው ክልላቸው ሰላም እንዲሆን ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ክልሎችም የሁለትዮሽ እና ከእዚያም በላይ እየሆኑ የጋራ ስምምነት እያደረጉ የጎሳ ፖለቲካ ሊግቱን የሚፈልጉትን ኃይሎች ሁሉ በጋራ የመቅጣት አቅም የሚዳብረው ክልሎች በጥምረት ህግ የማስከበር ሥራ እንዲጀመር ማድረግ ይህም ብቻ ኢትዮጵያን የሚያድን መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ህዝብ በቆረጠ መልኩ መግለጽ አለባቸው። በአማራ ክልል ሽብርተኛው ህወሃት ባደረገው ወረራ ላይ ከኦሮምያ እስከ ሱማሌ የነበረ የክልል ልዩ ኃይል እንደዘመተ ሁሉ ወለጋ ለገጠማት ፈተና ከአማራ ክልል ይሁን ከአፋር የሚዘምት ኢትዮጵያዊ ከጠፈር ላይ የመጣ ሳይሆን ወንድሙ መሆኑን ለህዝብ ማሳየት ቅሉን በድፍረት መስበር ማለት ነው።

ቅሉን በእዚህ ወቅት ማለትም ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ውጥረት ላይ እያለች፣የአባይ ግድብ ሊሞላ በተቃረበበት ጊዜ እና ከህወሃት ጋር ያለው ጉዳይ ባልተቋጨበት ሁኔታ ቅሉን መስበር ይቻላል ወይ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ለጥያቄው ምላሽ የሚሆነው ግን ሌላ ጥያቄ በማንሳት ነው። ይሄውም የአክቲቪስቶችን ልፈፋ እየሰሙ የጎሳ ቅሉን ተሸክሞ በመሄድ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ተቃቅሮ መኖር እና አገር ወደ አደጋ መምራት ይሻላል? ወይንስ ድሮም ለውጡን ተስፋ ያደርገው ህዝብ የጎሳ ቅሉ ይሰበራል ብሎ የጠበቀውን ህዝብ ልቡን ቅሉን በመስበር መግዛት እና የህዝብ ኃይል ይዞ ኢትዮጵያን ወደፊት ማስፈንጠር? ከሁለቱ አማራጩ የጎሳ ፖለቲካውን ቅል በድፍረት መስበር ብቻ እና ብቻ ነው ያለው አማራጩ። ይህ ደግሞ በልምምጥ አይመራም።መራር እርምጃ ቆራጥ ውሳኔ ጠቅላይ ሚኒስትር ይጠበቅብዎታል።ከእዚህ በላይ ቅሉን ተሸክማ የምትሄድ ኢትዮጵያ የለችም። ቅሉን እርስዎ ባይሰብሩት ሌላ ይሰብረዋል።ዕድሉ ባያመልጥዎ ግን ይመረጣል።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ወደ ስልጣን የመምጣትዎ ትሩፋት አድርጎ ህዝብ የጠበቀዎት የጎሳ ቅሉን ይሰብራሉ ብሎ በታላቅ ተስፋ እንደነበረ ያስታውሱ።ይህንንም በንግግርዎ እና በተግባርዎ ብቻ ሳይሆን በጻፉት የመደመር መጽሓፍም ሁሉ የጎሳ ቅሉን እንደሚሰብሩ በግልጽ ስለተናገሩ ነው። አሁን ከጎሳ ቅሉ ጋር የቆመ የኦሮሞ ብልጽግናም ሆነ የአማራ ብልጽግና፣ የአፋርም ሆነ የትግራይ በምንም ዓይነት በሳሳ ዓይን ሊመለከቱት አይገባም። የጎሳ ቅሉ እንዲሰበር ፊሽካውን ይንፉልን።ህዝብ ይነሳል።ወለጋን መታደግ የአማራውም፣የአፋሩም የሱማሌውም ኃላፊነት መሆኑን በተግባር እናሳይ።አንዳንድ ነገሮች ከታሰበቡበት ጊዜ በፊት የሚጀመሩበት ጊዜ አለ።አንዳንድ ነገሮች ደግሞ ከአሁን በኋላ መዘግየት የለባቸውም የሚባሉ ተግባራት አሉ።የጎሳ ፖለቲካ ቅሉን የመስበርያው ጊዜ ግን ነገ ሳይሆን አሁን ነው።ይህ የኢትዮጵያን ህዝብ የቅሉን ተንከባካቢዎች ለመፋለም እንዲነሳ ያደርገዋል።ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ቅሉን ስበሩት ወይንም ኢትዮጵያንም እርስዎንም እስኪሰብርዎ ተቀምጠው ጠብቁት።ሁለተኛውን ምርጫ እንደማይመርጡ እርግጠኛ ነኝ።
==================////===========


No comments: