ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, July 10, 2022

የ1966 ዓም የወሎ ረሃብን ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን እንደወጉበት ዛሬም ሊደግሙት ሲሰናዱ ህዝብ ለምን ትመቻችላቸዋለህ? ለምንድን ነው እንደህዝብ ያለፈ ስህተታችንን የምንደግመው?


ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ የክብር ዘብ ሲቀበላቸው 

======
ጉዳያችን
======

አንድን አገር እና ህዝብ ለማጥፋት፣ለመበተን እና ቢያንስ ስነልቦናው ተሰልቦ በአካል የሚጎማለል፣በስነልቦናው ግን ተሸናፊ እንዲሆን የጠላት አገር ጠበብት ተቀምጠው መክረው እንደህዝቡ ታሪክ እና ስስ ጎን እየታየ በርካታ የድርጊት ተግባሮች ተቀምመው ይላኩለታል። ይህ ደግሞ በእዚህ የማኅበራዊ ሚድያ ዘመን የተለያዩ አገር የማተራመሻ እና የህዝቡን ስነ ልቦና የሚነኩ አደገኛ ሥራዎች ይሰሩበታል። የእዚህ ዓይነቱ የተንኮል ሥራ የጠላይ አገሮች ከድህንነት ባለሙያ እስከ ሶሾሎጂስትና ታሪክ አጥኚ ድረስ ተሳትፎበት የሚዘጋጅ የተንኮል ድር ነው።በአባይ ወንዝ የምትቀናቀነን ግብፅ በእዚህ ተክናበታለች።ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን አንገት ለማስደፋት አይደለም ዛሬ ባንዳ እንደ አሸን ፈልቶ አግኝታ ቀርቶ ቀድሞም ዕድሜዋን የፈጀችው በእዚሁ የተንኮል ድር የማድራት ሥራ ላይ ተጠምዳ ነው።

የአፍሪካ አገሮች ከእዚህ የተቀናጀ የባለሙያዎች የምክክር ውጤት የሆነ ስነ ልቦናቸውን የመጉዳት እና የተሸናፊነት ስሜት እንዲያድርባቸው በእዚህ የረቀቀ እና የማናጋር ሥራ ይሰራባቸዋል።በእዚህም የአገሮቻቸው መሪዎች ሳይቀሩ እርባና ቢስ እስኪሆኑ ድረስ በብዙ የተንኮል መረቦች ተተብትበው አገራቸውን ለባዕዳን አስረክበው በስም ብቻ የአገር መሪ እየተባሉ ለመኖር የተገደዱ አሉ።የእዚህ ዓይነት ደካማ መሪዎች መኖር በድምር በአፍሪካ ኅብረት ላይ የራሱ የሆነ ጠንክሮ እንዳይወጣ የራሱ የሆነ ጥላ አጥልቶበታል።

ወደ አገራችን ጉዳይ ስንመለከት በ1966 ዓም የወሎ ረሃብ እና ፖለቲካዊ ተጽዕኖው በወቅቱ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ የነበረውን የለውጥ ፍላጎት አስታከው የኢትዮጵያ ጠላቶች በአደገኛ መንገድ የኢትዮጵያን መሰረት ለማናጋት ተጠቅመውበታል። ረሃቡ ይዞት የነበረው የሞራላዊ ጥያቄን ኢትዮጵያ ከሥሯ እንድትናጋ ለማድረግ ረሃቡን ያመጡት ብቻ ሳይሆን ችላ ያሉት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ናቸው የሚል ዘመቻ መጀመርያ በሰፊው እንዲከፈት ተደረገ።በርካታ ምሑራን አምባሳደር እና ደራሲ ሃዲስ ዓለማየው የንጉሱ ስልጣን ተገድቦ በጠቅላይ ሚኒስትር ባብዛኛው የሚዘወር መንግስት መመስረት እና ኢትዮጵያ የገነባቻቸው ተቋማት ሳይናጉ ዕድገቷን ማፋጠን አለባት የሚሉት ላይ የስነ ልቦና ውጊያው በውስጡ መርዝ የይዘ ነገር ግን ተራውን ኢትዮጵያዊ ሊያታልል የሚችል እጅግ አደገኛ አቀራረብ ነበረው። ይሄውም ረሃቡ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አሰቃቂ ስለነበር አገር አስደንግጧል። የምዕራብ ሚድያም ሆነ በወቅቱ ያቆጠቆጠው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ረሃቡን ከረሃብነት ባለፈ በንጉሱ ላይ እና በስርዓቱ ላይ ፖለቲካዊ ዘመቻ ለማድረግ እንደሚጠቅም ታምኖበት ስለነበር የረሃቡ ክርክር ከረሃብ ባለፈ የራሱ የሆነ የተሳሳተ ዕሳቤ ተስሎበት ቀረበ።

በወቅቱ በተለያዩ ሰዎች ተጽፈው ከነበሩት ጽሑፎች ለመረዳት እንደሚቻለው ረሃቡን ከአሳዛኝነቱ ባለፈ የፖለቲካዊ ቃናው ኢትዮጵያን ለማናጋት ጥቅም ላይ ሲውል አደጋው በወቅቱ ምን ያህል እንደሚተረተር የገባው ብዙ ሰው አይመስልም።በወቅቱ የነበረው የረሃቡ አቅራረብ በአጭር አነጋገር ይህንን ይመስላል። ይሄውም ''ረሃቡ የመጣው በዝናብ እጥረት ሳይሆን ንጉሱ እና ባላባቱ መሬቱን ስለተቀራመቱት ነው።ረሃቡ ሲመጣ ንጉሱ እንዳይነገር ደብቀዋል '' ካለ በኋላ '' ስለሆነም ንጉሱን ብቻ ሳይሆን መንግስት በሙሉ ይፍረስ '' የሚል ሃሳብ በህዝቡ ውስጥ ነዙ። ይህ ረሃብን ለፖለቲካ ጥቅም የተጠቀመው እና የኢትዮጵያ ጠላቶች ያቀበሉትን መንግስት የማፍረስ አጀንዳ ሲግፋበት ከመንግስት መፍረስ በኋላ ምን እንደሚመጣ አያውቅም ነበር።

ይህንን መንግስት ይፍረት ንጉሱ ናቸው ረሃቡን ያመጡት የሚለውን የሚሞግቱ በሁለት አደገኛ አቀራረብ ባላቸው የሰው ስሜት በሚነኩ ነገር ግን ግንኙነት በሌላቸው የመልስ ምት ሃሳቦች እንዲጣጣሉ ሆነው ተቀምመው ነበር።ለምሳሌ አንድ ሰው የወሎ ረሃብ አሳዛኝ ቢሆንም መንግስት ማፍረስ ግን መፍትሄ አይሆንም የሚሉ እንደ አረመኔ ህዝብ በረሃብ ሲያልቅ የማይሰማቸው፣ከሃዲዎች እና የስርዓቱ ተጠቃሚዎች ተደርገው ይሳሉ ነበር።ይህንን ለማስረዳት የሞከሩትን አብዛኛው የፖለቲካ ንቃቱ ደካማ ስለሆነ ጥቂቶች ደግሞ ሆን ብለው ለፖለቲካ ጥቅም ተጠቀሙበር። በመሆኑም ረሃቡን ከመንግስት መፍረስ ጋር አለማገናኘት በራሱ ያለማወቅ የመጨረሻ ደረጃ አድርገው የሚያዩ ብቻ ሳይሆን ስለረሃቡ አሳዛኝነት ካወሩ በኋላ መንግስት መፍረስ መፍትሄ እንደሆነ አብሮ ተሰበከ። ይህ የተሳሳተ አስተሳሰብ መሆኑን ለመረዳት ከወሎ ድርቅ በኋላ እና የንጉሱ አስተዳደር ከፈረሰ በኋላ 60 ሚኒስትሮች እና ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በታሪካችን ጥቁሩ ቅዳሜ ተብሎ በሚጠራው በኅዳር 14፣1967 ዓም ምሽት ሲረሸኑ የወሎ ረሃብ ያስራቡ ብለው ተፈረደ ያሉ የወቅቱ አብዮተኛ ተብዬዎች የሉም ማለት አይቻልም።

ከወሎ ረሃብ አርባ ዘጠኝ ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ ላለፉት አራት ዓመታት በታኝ እና ዘረኝነትን መሰረታቸውን ባደረጉ አሸባሪዎች አቀናባሪነት እና የባዕዳን የጀርባ ድጋፍ በርካታ ወገኖቻችን ተገድለዋል።እነኝህ ወገኖቻችን መገደላቸው እጅግ አሳዛኝ ቢሆንም የህዝብ የማዘንን ስሜት ተጠቅመው ፖለቲካዊ ዘመቻ ለማራመድ የሚጠቀሙበት እራሳቸው በታኝ ኃይሎች እና ባዕዳን የኢትዮጵያ ጠላቶች ሆነው እናገኛቸዋለን።ይህንን በንጽጽር ከአሁኑ ጋር እያስተያየን ማቅረብ እንችላለን።

በ1966 ዓም

በ2014 ዓም

ያኔም ሆነ አሁን ዕውነታው 

ለወሎ ረሃብ ምክንያቱ ንጉሱ እና መንግስት ነውነው

ሸኔን የፈጠረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ነው።ነው።

ለረሃቡ ንጉሱ ምክንያት አልነበሩም።ይልቁንም በቀስታ ህዝቡን እንርዳ እንጂ ለባዕዳን ማሳጣት ጠባሳ ያመጣል የሚል ሃሳብ ያላቸው ንጉሱ ነበሩ። በወቅቱ ማን ሰምቷቸው። ዛሬም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን በመስቀል አደባባይ ለመግደል የሞከረውን፣ወለጋን ዐቢይ አይረግጥም ያለውን ሸኔ ዐቢይ አውቆ ነው እያሉ ህዝቡን የሚያታልሉ አሉ።አሉ።

የወሎ ረሃብ ከመሰረቱ ለማጥፋት መንግስት መፍረስ አለበትአለበት

የወለጋ እልቂት የሚቆመው ዐቢይ ሲወርድ ነው። የሚል ዘመቻ የኢትዮጵያ ጠላቶች አጀንዳ የሚያራግቡ አሉ።እነኝህ በውጭ ተቀምጠው ኢትዮጵያ ስትፈርስ አይስክሬም የሚልሱ ናቸው።ናቸው።

ዕውነታው በ1966ም ሆነ ዛሬ ለወሎ ረሃብም ሆነ ለሽብርተኞች ጥቃት መንግስት ማፍረስ ንጉሱንም ሆነ ዐቢይን ማውረድ ነው የሚለው አባባል የጠላት ወሬ ነው።ዓላማው ኢትዮጳያን የማተራመስ የባዕዳን አጀንዳ ነው።

ወሎ እየተራበ ንጉሱ ኬክ በሉ፣ፈገግ አሉ እየተባለ ይብጠለጠሉ ነበር።

ዛሬም ዐቢይ አገር ወክሎ በውጭ አገር ስብሰባ ሲገኝ ፈገግ ሲል፣ችግኝ ሲተክል ወዘተ ህዝብ እያለቀ ፈገግ ያለው፣ችግኝ የተከለው አውቆ እልቂቱን ስለሚደግፍ ነው እያሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች ቀደም ብለው በቀመሩት ሥራ ኢትዮጵያውያንን ያውካሉ።ያውካሉ።

በንጉሱም ላይ ሆነ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላይ የተደረገው የወሬ ዘመቻ ኢትዮጵያውያንን የማወክ እና እርስ በርስ እንዲከፋፈሉ ለማድረግ የታሰበ ሴራ ነው።በንጉሱ ጊዜ ረሃቡን ለመታደግ ከመዝመት ባለፈ በረሃቡ የሌሉበትን ንጉሱን መስደብ ይበዛ ነበር።በወቅቱ የቅድስት ማርያም የሴቶች ትምህርት ቤት ተማሪ የነበረች ዛሬ ላይ ስታስታውስ ወደ ትምህርት ቤት ስንሔድ እና ስንመጣ እነኝህ የስርዓቱ ልጆች እየተባልን መንገድ ላይ መንጓጠጥ ሁሉ ነበረብን ማለቷን የእዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አድምጧል።


በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ላይ የሚደረገው ዘመቻም እንዲሁ ተመሳሳይ ነው። ዋና ገዳዩን ኦነግ ሸኔን ከኮነኑበት ይልቅ ዐቢይ ዐቢይ እያሉ የሚሳደቡ እና ጠቅላይ ሚንስትሩ ህዝቡ ላይ የተኮሰ ቀረሽ ሃሳብ ሲያራግቡ የሚውሉ እና መንግስት ይፍረስ እያሉ በድፍረት ባዶ አስተሳሰባቸውን የሚለቁ አሉ።አሉ።

ለሕዝብ የተጨነቁ መስለው ነበር መንግስት ይፍረስ ያሉት                ዛሬም ለብሄር በማሰብ መንግስት መፍረስ እንዳለበት የሚሰብኩ አሉ።ሁሉም የኢትዮጵያ ጠላቶች አጀንዳ አስፈጻሚ ሆነው ቀረዋል።


ባጠቃላይ እንደ 1966 ዓም ዛሬም ደግመን ኢትዮጵያን ለሌላ 40 ዓመት መከራ ላይ እንዳንጥላት መጠንቀቅ አለብን።
የ1966 ዓም የወሎ ረሃብን ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን እንደወጉበት ዛሬም ሊደግሙት ሲሰናዱ ህዝብ ለምን  ትመቻችላቸዋለህ? ለምንድን ነው እንደህዝብ ያለፈ ስህተታችንን የምንደግመው? ኢትዮጵያ ቀና እንዳትል ለዘመናት ስንጋተው የነበረውን መርዝ ዛሬ ላይ እንድንግተው እና በምርጫ የተመረጠ መንግስት ይፍረስ እያሉ የሚለፍፉትን በጥብቅ ልንመረምራቸው እና አጀንዳቸው የእነማን እንደሆነ ማጋለጥ አለብን።
============///=============

No comments: