ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, March 3, 2022

ዩክሬን፣ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ እና ወቅቱ የሚጠይቀው ኢትዮጵያን እና መንግስትን የማገዝ ሃገራዊ ፋይዳው

 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የተመድ ሊቀመንበር አንቶንዮ ጉቴሬዝ

===========
ጉዳያችን ልዩ ወቅታዊ 
==========

የዓለማችን ሁኔታ ከኮቪድ ወረርሽኝ በመጠኑ መቀነስ ተከትሎ እና የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ገቢ መቀነስ፣የምዕራቡን ዓለም የሚገዳደሩት የቻይና፣ሩስያ እና ቱርክ እንደገና ማንሰራራት ውጥረቶች እየጨመሩ መጥተዋል።ይህም የዓለምን ሥርዓት እንደገና እንዲከለስ ያስገድዳል። ሥርዓቱ ደግሞ በደፈናው አይከለስም።አንድ ዓይነት የጉልበት መፈታተሾች ተካሂደው ወይንም ግልጥ ከሆነ ጦርነት በኋላ የኃይል አሰላለፍ ልዩነት እንደሚኖር አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ ግልጥ እየሆነ መጥቷል።

ዩክሬን እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ

አሁን በዩክሬን ላይ የዘመተው የሩስያ ጦር ድንገት ደራሽ አይደለም።ቢያንስ ላለፉት አስር ዓመታት በዩክሬን ጉዳይ ላይ ውዝግቡ ተጧጡፎ ነበር።የሶቬት ኅብረት መፍረስን ተከትሎ የራሳቸውን መንግስታት ካወጁት ከስቶንያ ጋር በጦር መሳርያም ሆነ በስንዴ ምርቷ የምትታወቀው እና ከ40 ሚልዮን በላይ ህዝብ ያላት የዩክሬን መሄድ በሩስያ ተቀባይነት አላገኘም።ስለሆነም ወረራው እንደማይቀር ግልጥ መሆኑን በርካታ የዓለም አቀፍ ጸጥታ ጠበብት ሲናገሩ ነው የሰነበቱት። ሩስያ ለእዚህ እንዲመቻት ክረምያን ከደቡብ ዩክሬን በኩል ባህሩን ተሻግራ የያዘችው። ይህ ዩክሬንን የመክበብ ሥራ ነበር።የምዕራቡ ዓለምም ይህንን ቀድሞ አውቋል።ጥያቄው ፑቲን መቼ ነው የሚገቡት? የሚለው ነበር።

''የሩስያ ዘመቻ ለረጅም ጊዜ የታቀደ ነበር'' ይህንን ያሉት የኔቶ ዋና ሰው እና የቀድሞው የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር የንስ ስቶንስበርግ ናቸው። እንደ ባለስልጣኑ አገላለጥ ቀድሞ የታቀደ ለመሆኑ የክሬምያ በሩስያ መያዝ አንዱ ማስረጃ ነው። የምዕራቡ ዓለም ፑቲንን ከመጀመርያው ጀምሮ አመጣጣቸው አላማረውም።ሰውየው ከሩስያው የስለላ ድርጅት ጀምሮ የነበራቸው ልምድ እና በድንገት ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በላይ የስልጣን ዘመናቸውን እያራዘሙ መምጣታቸው ሁሉ አንድ ሊያሳኩት የሚያስቡት ጉዳይ እንዳለ ጥርጣሬ ነበር። የመጀመርያ የምዕራቡ ስልት የሚመስለው ፑቲንን ማቅረብ እና በምጣኔ ሃብቱ መስመርም ቢሆን ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽንን) እንዲቀላቀሉ ያሰበ ይመስላል። ለእዚህ ማሳያው ደግሞ የሰባቱ በኢንዱስትሪ የበለጠጉ ሃገሮች ጋር ሩስያ ስምንተኛ ሆና አንድ ሰሞን አብራ ትሰበሰብ ነበር። ሆኖም ይህ ሁኔታ ብዙም አልቀጠለም።የሶርያው ጉዳይ የምዕራቡ እና የሩስያ አስተሳሰብ አንድ አይደለም።ፑቲን በአንድ የቡድን ስምንት ስብሰባ ላይ ''ሶርያ ኢራቅ አይደለችም'' የሚለው አነጋገር የመለያያ ዓረፍተ ነገር ነበረች።በእዚህም ምክንያት ፑቲን የሶርያውን ባሽር አልአሳድን ደግፈው የምዕራቡ ዓለም ደግሞ ተቃዋሚዎቻቸውን ደግፎ ቆመ።

በመቀጠል ሩስያ ክሬምያን ስትወር የአውሮፓ የጸጥታ ሁኔታ አደጋ ላይ ሊወድቅ ነው በሚል ትልቅ ተቃውሞ ተነስቶ ነበር።ይህንንም ተከትሎ የምዕራቡ ዓለም የኢኮኖሚ እቀባ በሩስያ ላይ ጣለ።እቀባው ግን ያን ያህል ውጤት አላመጣም። የባለፈው እቀባ ቀርቶ ባለፈው ሳምንት የተደረገው እጅግ የመረረ የተባለው እቀባ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሳይቀር ተተችቷል።
ትራምፕ በትናንትናው ዕለት በአንድ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር የባይደን አስተዳደርን ''ደደቦች ናቸው'' በማለት ቃል በቃል ነው የነቀፏቸው።በእዚሁ ንግግራቸው ላይ ትራምፕ -
'' ትራምፕ ከፑቲን ጋር ነው እያሉ የውሸት የዜና ድርጅቶችን እየሰማችሁ ከረማችሁ።አሁን የእኛ መሪዎች በሩስያ ላይ እቀባ እቀባ ይላሉ።ፑቲን 'ስማርት ነው።አዎን ስማርት ነው።የእኛ መሪዎች ግን ደደቦች ናቸው '' ያሉት ትራምፕ በመቀጠል ''እቀባ የሚሉት ላለፉት ዓመታት እቀባ ምን ለውጥ አመጣ? ከእቀባው የሚያተርፈው ፑቲን ነው።በእዚህ ውጥረት የነዳጅ ዋጋ ጨመረለት።ስለሆነም ፑቲን አስልቶታል'' በማለት ትራምፕ በወቅቱ የአሜሪካ አስተዳደር ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገልጠዋል።ንግግራቸው በጭብጨባ የታጀበ ነበር።

እንደእውነቱ ከሆነ የነዳጅ ዋጋ በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ በበርሜል ወደ 114 ዶላር አሻቅቧል።በእየቀኑም እየጨመረ ነው።ይህም ሆኖ ግን የምዕራቡ እቀባ በሩስያ ላይ ከእዚህ በፊት ተሰምቶ በማይታወቅ ደረጃ ነው እየገፋበት ያለው።ለምሳሌ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሃገሮች ላይ ሲጣል ያልታየው የባንክ ስዊፍት ማስተላለፍያ ከመዝጋት ጀምሮ የሩስያ የሆኑ ሹፌሮች እንዳይንቀሳቀሱ እስከማድረስ ደርሷል።የሩስያ ባለሃብቶችም በአንጻሩ የራሳቸውን መንገድ እየተከተሉ ያለ ይመስላል።ለምሳሌ በትናንትናው ዕለት ሩስያዊው የቼልሲ ክለብ ባለቤት ሮማን አብራሞቪች፣ክለቡን እንደሚሸጡ ገልጠዋል።ሰሞኑን እቀባውን አስመልክቶ ለቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት አስተያየቱን የሰጠ የሩስያ ጉዳይ አጥኚ እንደገለጡት የሩስያ ኩባንያዎች እና ህዝቡ በሩስያ ባንኮች ከ50 ቢልዮን ዶላር በላይ ተቀማጭ አለ።ህዝቡ የውጭ ምንዛሪውን በሃገሩ ባንክ ሲያስቀምጥ እንደነበር አብራርተዋል። ይህ ማለት ግን ከበረራ እቀባ እስከ የባንክ ማስተላለፍ እገዳ የዘለቀው የምዕራቡ እቀባ ሩስያን ምንም አይጎዳም ማለት አይቻልም።ሆኖም ግን በእዚህ ዓይነት ከቀጠለ ፑቲን ጦርነቱን ወደ የተቀረው አውሮፓ ወይንም ከናቶ ውጭ ወደ ሆነ ሌላ ሃገር በድንገት ሊያስፋፉት ይችላሉ።ለእዚህም የእቀባው መስፋት እንደ አንድ ምክንያት ተወስዶ ሩስያ በኢኮኖሚ ከመድቀቅ የኢኮኖሚ መድቀቁን ወደ ምዕራቡ ማስፋፋት አለብኝ ያለኝ አማራጭ ይህ ብቻ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ እንዳይወስዳት ያሰጋል።ስለሆነም የምዕራቡ ዓለም እቀባውን ሙሉ በሙሉ ወደ መዝጋት መሄዱ ሰላም ላያመጣ እንደሚችል መገመት ይቻላል። በእዚህ ሁሉ መሃል ግን መከራውን የሚያየው የዩክሬን ህዝብ ነው።ህዝቡ በአሁኑ የሩስያ ጥቃት የስደተኛው ቁጥር ከአንድ ሚልዮን በላይ ሆኗል። ስለሆነም ሰላም በቶሎ መምጣቱ እጅግ አስፈላጊ ነው።

ኢትዮጵያን እና መንግስትን የማገዝ ሃገራዊ ፋይዳው

ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችም ሆነ ሃገራዊ ሁኔታው የሚያሳየው ኢትዮጵያን እና ለመጪው አምስት ዓመታት የተመረጠውን መንግስት ከማገዝ እና የሚስተካከለው እንዲስተካከል ከማገዝ ውጭ ምንም ዓይነት አፍራሽ አካሄድ ለኢትዮጵያ አይበጅም።ዓለም አቀፋዊ ሁኔታው በቶሎ ተለዋዋጭ እንደሆነ እና ይህም ሁኔታ እንደሚቀጥል ግልጥ እየሆነ ነው።የሩስያ ዩክሬንን መውረር መልዕክቱ ቀላል አይደለም። አንድ ሉዐላዊ ሃገር በሌላ ሃገር ተወረረ ማለት ነው።በእርግጥ ይህ ዛሬ የተጀመረ አይደለም።ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ በርካታ ወረራዎች ተደርገዋል።ይህም ሆኖ ግን እያንዳንዱ ወረራ የሚያሳየው የዓለም ህግ መጣሱን ነው። የዓለም ህግ መገለጫ ትልቁ ተቋም ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ነው።በቀጣይም ሩስያን ተከትሎ ወረራዎች ሌሎች ሃገሮች በሌሎች ላይ ወረራ አያደርጉም ማለት አይደለም። በእዚህም የዓለም ትኩረት በዩክሬን ጉዳይ ላይ ስለሆነ ቶሎ ትኩረት አይስብም።

በመሆኑም በአፍሪካ ቀንድ በተለይ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግበት ጊዜ ነው።በሩስያው ጉዳይ ቀዳሚ የስልታዊ ቦታ ትኩረት ያለው የአፍሪካ ቀንድ ላይ ነው።በያዝነው ሳምንት መጀመርያ ላይ የሰባቱ በኢንዱስትሪ የበለጠጉ ሃገሮች አምባሳደሮች ሱዳን፣ግብጽ እና ኢትዮጵያ የሩስያ ጦር ወደ ዩክሬን መግባትን እንዲቃወሙ የቀጥታ ጥያቄ ማቅረባቸውን የዲፕሎማሲ ምንጮች ተናግረዋል።ሱዳን ሩስያን ደግፋ ቆማለች።የሱዳን አዲሱ የወታደራዊ መንግስት ባለስልጣናት በያዝነው ሳምንትም ሞስኮ ጉብኝት ላይ ናቸው።ከእዚህ አልፈው የባህር በራችን ለሩስያ ክፍት ነውም ብለዋል። ኤርትራ በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ሩስያን አስመልከቶ ለተደረገው ስብሰባ ሩስያን ደግፋ ድምጿን ሰጥታለች። ትናንት በተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ላይ ድምጽ ከመሰጠቱ በፊት የኤርትራው አምባሳደር ንግግር ሲያደርጉ የምዕራቡ ዓለም በሩስያ ላይም ተመሳሳይ እቀባ ማድረጉን ጭምር ፍትሃዊ አይድለም እያሉ ሲናገሩ የተባበሩት መንግስታት የቀጥታ ስርጭት ወደ ሌላ ጋዜጣዊ መግለጫ አዞረው።ይህም ሆኖ ኤርትራ ሩስያ ላይ የሚደረገውን ውሳኔ ተቃውማ ድምጿን ሰጥታለች።

የአፍሪካ ቀንድ ሃገሮች ፖለቲካ ወሳኝ ሃገር ኢትዮጵያ ነች።ከ110 ሚልዮን በላይ ህዝብ እና እጅግ ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት ያላት ኢትዮጵያ የምትይዘው አቋም ወሳኝ ነው። እዚህ ላይ ኢትዮጵያ ከንጉሱ ከስልጣን መውረድ ጀምሮ የነበራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት መዘባረቅ አሁንም እንዳይገጥማት እና ካለፈው ተምራ በጥንቃቄ እና በገለልተኝነት መጓዝ ያለባት ጊዜ አሁን ነው።በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ አንዱ ውስጥ ጭልጥ ብሎ መግባት ያለውን ወጪ እና ኪሳራ ከኢትዮጵያ በላይ የሚያውቅ የለም።የኢትዮጵያ መንግስትም በዩክሬን ጉዳይ እየያዘው ያለው መንገድ ተገቢ እና ድካም ቢኖርበትም መጨረሻው ጥሩ እንደሚሆን መገመት ይቻላል።ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስት የትናንቱ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ ድምጽ አልሰጠችም።በዛሬው ዕለትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያወጡት የሩስያ እና የዩክሬንን ጉዳይ አስመልክተው ያወጡት መግለጫ ላይ በእንግሊዝኛ ባወጡት መግለጫ ላይ ''...Ethiopia urge all parties to exercise restraint in the Ukraine crises'' ''ኢትዮጵያ በዩክሬን ቀውስ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ በሙሉ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ታሳስባለች'' ነው ያሉት።

አሁን ወቅታዊውን የዓለምን ሁኔታ በሚገባ መረዳት ኢትዮጵያ በጥንቃቄ የምትሄድበት ልጆቿም ከአላስፈላጊ ንትርክ ወጥተው የኢትዮጵያን አንድነት የመጠበቅ ሃላፊነት የሁሉም የኢትዮጵያውያን ሃላፊነት መሆኑን በደንብ የመረዳቱ ፋይዳ ነው ጠቃሚው ጉዳይ።
ስለሆነም ኢትዮጵያን ለመደገፍ ማዕከላዊ መንግስት በተረጋጋ መልክ ስራውን እንዲሰራ ማገዝ ከዜጎች ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን አስፈላጊ ነው።መንግስት ስህተቶቹን እንዲያርም በባለቤትነት መገፋፋት እንጂ በህገወጥ መልክ የመንግስት ለውጥ ለሚያቀነቅኑ ዕድል መስጠት ኢትዮጵያን ለማጥፋት ያሰፈሰፉ እና የአሁኑን የዓለም ሁኔታ ለመጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማጥቃት እንዳይሞክሩ ውስጣዊ መረጋጋት እጅግ አስፈላጊ ነው። በእርግጥ ከባዕዳን ጋር ሸርበው ኢትዮጵያን ለማጥፋት ከሚሸርበው ከሽብርተኛው ህወሃት ጋር መቼም መቼ የህግ ማስከበር ሥራ እንደሚቀጥል ይህም በአስገዳጅ ሁኔታ መሆኑን መረዳት ይቻላል።ይህም የተሻለ አማራጭ ካለው አብሮ የሚቀርብበት ሁኔታ ዝግ ሳይሆን ማለት ነው። ኢትዮጵያ በአሁኑ ተለዋዋጭ የዓለም ሁኔታ በጥበብ ካለፈችው ነጥራ የመውጣት ብቻ ሳይሆን የማደግ ዕድሏ አብሮ የቀረበበት ጊዜ ላይ ነን።ይህንን ግን መንግስት ብቻ ሳይሆን ህዝብም ሲገባው ነው ለውጥ ማምጣት የሚቻለው።

ለማጠቃለል የዩክሬን ሩስያ ግጭት ወደ ሰፊው የዓለም ግጭት የማምራት አደጋው በግልጥ ይታያል።ለእዚህ ማሳያው የምዕራቡ ዓለም በሩስያ ላይ የጫነው የእቀባ መጠን እና ስፋት ከኢኮኖሚ እቀባ ቀጥሎ ጦርነት እንደሚከተል ሆኖ የተያዘ አያያዝ ነው።ኢኮኖሚ ማድቀቅ እና ፕሮፓጋንዳ የሚከተለው ጦርነት ነው። የሩስያ እጅ የት ድረስ እንደሆነ አሁን ለማወቅ ከባድ ሆኗል።በሱዳን ወታደራዊ መፈንቅል ውስጥ የሩስያ እጅ አለበት የሚሉ የተሰሙት በቅርቡ ነው።አንዳንድ ግልጥ ያልሆኑ ጉዳዮች እንዳሉ አመላካች ነው።በየትኛውም መንገድ ግን ኢትዮጵያ የያዘችው የገለልተኛነት መንገድ (አስቸጋሪ ቢሆንም) በመጨረሻ ፍሬ ያፈራል።በእርግጥ በአንዳንድ ጉዳዮች እትዮጵያ ወደ አንዱ የምታደላበት ጉዳይ ሊፈጠር ይችላል።በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ ህንድ አንድ ጥሩ የገለልተኛ ምሳሌ ነች።ገለልተኛ የሚለው ስም በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜም ወደ አንድ ጎራ የገቡ ሁሉ የገለልተኛ ሃገሮች ማኅበር ውስጥ ገብተው ነበር።በተግባር የነበሩት ጥቂት ናቸው።ኢትዮጵያን ግን አሁን ሁሉም ይፈልጓታል። ግብጽንም ሁሉም ይፈልጓታል።ኢትዮጵያውያን ያለውን መንግስት ስህተቶች አብረን በባለቤትነት እያረምን ለልማቷ ባለን አቅም ከሰራን እና ይህንን ዓይነት ፖለቲካዊ ከባቢያዊ ሁኔታ በሁሉም መስክ መፍጠር እስከቻልን ድረስ በእዚህ ሁሉ ውስጥ ኢትዮጵያ ነጥራ ትወጣለች።የመጨረሻው መጨረሻ ዓለም ወደ አሁኑ ዓይነት የጦርነት አደጋ ውስጥ ሲገባ ኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት መንገታገት እንደማንኛውም ሃገር አይገጥማትም ማለት አይደለም።የኢትዮጵያ ህዝብ ሃላፊነትም ስለሃገር ሲባል ይህንንም አብሮ መጋፈጥ ይጨምራል።ለእዚህ ደግሞ ጋዜጠኞች፣የሃይማኖት ተቋማት፣ነጋዴዎች ሁሉ ሃላፊነታቸውን ሲወጡ ነው።

==================/////==========


No comments: