ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, March 8, 2022

የሴቶች ቀን ማርች 8 በሚከበርበት በዛሬዋ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ዩንቨርስቲዎች የሚማሩ ሴት ተማሪዎች ዩንቨርስቲዎቻቸው እጅግ አስፈሪ እንደሆኑባቸው ስንቶቻችን እናውቃለን?



    • ለክብርት ፕሪዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣
    • የትምሕርት ሚንስትር ፕሮፌሰር ብርሓኑ ነጋ፣
    • የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣
    • ክብርት የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት  መዓዛ አሸናፊ እና ሌሎች
 ይህ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ እና ወቅታዊ ነው። አፋጣኝ መፍትሄ ይፈልጋል።

==========
ጉዳያችን ልዩ ዘገባ
==========

ኢትዮጵያ አሁን ካደጉ ሃገሮች ሁሉ በተሻለ የሴቶች ትልልቅ ሚናዎች በፖለቲካም ሆነ በአመራር ደረጃ የወጡባት ሃገር ነች። እትዮጵያ ከክርስቶስ ልደት በፊት 700 ዓመት በፊት በእስራኤል የነገሰው ንጉስ ሰለሞንን ለመጎብኘት የሄደችው ኢትዮጵያዊት ንግስት ሳባ ትመራት የነበረች ሃገር ነች።የአክሱም መንግስትን ያፈረሰች እና  በ9ኛው ክ/ዘመን በኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥፋት ያመጣችው ዮዲት ጉዲትም ሴት ነበረች። በኋላም በየዘመኑ ከተነሱት ንግስት ዕሌኒ፣ንግስት ጣይቱ፣ንግስት ዘውዲቱ ሁሉ የኢትዮጵያ መሪዎች ሆነው አልፈዋል።ለምሳሌ ንግስት ዘውዲቱ በነገሱበት የ20ኛው ክ/ዘመን የመጀመርያ ዓመታት ላይ የኢትዮጵያ መሪ ሲሆኑ በአውሮፓ ብዙ ሃገሮች ሴቶች ስራ ወጥተው የማይሰሩበት እና የመምረጥ መብታቸው ብቻ ሳይሆን የመማር ዕድል በማይፈቀድላቸው ዘመን ነበር።

 ዛሬ ማርች 8 የሴቶች ቀን ነው።ቀኑ በኢትዮጵያ እየተከበረ ነው።የአከባበሩ ታሪክ የሚነሳው ወደኋላ 100 ዓመታት ይጓዛል።እንደ አውሮፓውያኑ 1908ዓም  በኒውዮርክ ከተማ ነዋሪ የሆኑ 15,000 ሴቶች የተሻሻለ የሥራ ሰዓትና የደመወዝ ክፍያን እንዲሁም የመምረጥ መብታቸው እንዲከበር ጠይቀው አደባባይ ወጡ። ከአንድ ዓመት በኋላ በአሜሪካ በብሔራዊ ቀንነት አወጀ።በዓሉ ዓለምአቀፋዊ ሆኖ እንዲከበር ክላራ ዚክተን የተባለች ሴት በ1910 ዓም እአአ በዴንማርክ ዋና ከተማ ኮፐንሃገን በተደረገ ዓለምአቀፍ ስብሰባ ላይ ሃሳቡ ቀረበ። በእዚህም ከ17 ሃገራት የተውጣጡ 100 ተሳታፊ ሴቶች በሃሳቡ ተስማሙ። በመቀጠል በ1911 ዓም እአቆጣጠር በዓሉ በኦስትርያ፣ዴንማርክ፣ጀርመንና ስዊዘርላንድ በዓሉ መከበር ጀመረ።በዓሉ በተሟላ ደረጀ ዓለምአቀፋዊ መልኩን የያዘው እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1975 ዓም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ቀንን ሲያከብር ነበር።

በኢትዮጵያ በወታደራዊ መንግስት ጊዜ ከሶሻሊዝም ርዕዮት ጋር እየትጠቀሰ መከበር ጀመረ።በወቅቱ የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር (አኢሴማ) በሚል በብሔራዊ ደረጃ ኢስከ ቀበሌ ድረስ መዋቅር ያለው ነበር።ይህ አደረጃጀት ግን ነጻ አደረጃጀት ባለመሆኑ እና የመንግስት ውሳኔ አስፈጻሚ ብቻ ሳይሆን የካድሬነት ተግባሩ ማመዘኑ እንደማኅበር ጸንቶ መቀጠል አልቻለም።

በዘመነ ህወሃት/ኢሃዲግ የሴቶች መብት ጉዳይ ይህንን ያህል የተሻለ ለውጥ አልታየበትም።ለሩብ ክፍለዘመን ያህል አንዳች ይህ ነው የሚባል ብሄራዊ የሴቶች ማኅበር የለም።አንድ በጉልህ ሥራ የሚነሳው በራሳቸው አነሳሽነት የተነሳሱ የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር የሰሩት አመርቂ ውጤት ተጠቃሽ ነው። ማኅበሩ በሺህ የሚቆጠሩ ሴቶች ነጻ የሕግ ምክር እና ጥብቅና የቆመ እንዲሁም ሴቶች የተመለከቱ የሕግ ክፍተጎች እንዲስተካከሉ ለፖሊሲ አውጪዎች በመቀስቀስ ትልቅ ሥራ ሰርተዋል። ሆኖም ግን የህወሃት/ኢሃዴግ መንግስት ማኅበሩን አላሰራውም።በሚልዮን የሚቆጠር ከበጎ አድራጊዎች ያገኘውን ገንዘብ በፍርድቤት አግዶ በክልሎች ያሉትን ቢሮዎች እንዳያንቀሳቅስ ከጉዞው ሊያደናቅፈው ሞክሯል።

ከህወሃት ወደ መቀሌ መሸሽ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍቱ እርምጃዎች ወስደዋል። የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት፣የፍትሕ መስርያቤቱ ከፍተኛ ባለስልጣን፣የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እና በሚንስትር ደረጃም ቁጥራቸው ከቀድሞው ላቅ ባለ መልክ ወደ ስልጣን እርከን መጥተዋል።

በኢትዮጵያ የሴቶች ችግሮች እጅግ ብዙዎች ናቸው።በእዚህ ጽሑፍ ግን የሚተኮርበት በኢትዮጵያ ሴት ዩንቨርስቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች ዩንቨርስቲዎቻቸው አስጨናቂዎች እና ምቹ እንዳልሆኑ ይህም በምን ያህል ደረጃ በሴቶች የትምሕርት ስኬት ላይ ተጽዕኖ እንዳለው በሚገባ አለመታየቱን መጠቆም ነው።ይህንን አስመልክቶ ጉዳያችን በአንድ ዩንቨርስቲ የደረሰ በሴት ተማሪ ላይ የደረሰ በደል ከሰማች በኋላ አንድ መጠነኛ የመረጃ ማሰባሰብ ስራ በኢትዮጵያ በሚገኙ አምስት ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ላይ ዩንቨርስቲዎቻቸው በምን ያህል ደረጃ ለሴቶች ምቹ ናቸው? በሚል ጥያቄ አቅርባ ነበር።በእዚህ መሰረት እጅግ የሚያስደነግጥ ሁኔታ ላይ እንዳለን የሚያሳይ ስዕል ለማግኘት ተችሏል።

በዩንቨርስቲዎች ውስጥ የተፈጸሙት እና በሴቶች ላይ ሽብር በሚባል ደረጃ ወንጀል እየተሰራ ለመሆኑ አመላካች ነው።በዩንቨርስቲዎቹ ውስጥ ሴቶች ከእዚህ በታች ያሉትን ማድረግ እንደማይችሉ ወይንም እንደሚፈጸምባቸው በእዚህም ሳብያ ሴት ተማሪዎች እጅግ እንደሚጨነቁ ይህም ጭንቀት ዩንቨርስቲውን ለቀው እስከሚወጡ ድረስ የስነልቦና ችግርም እንደሚያስከትልባቸው ለመረዳት ተችሏል።በሰሞኑ በተደረገው መጠነኛ ዳሰሳ በተገኘው መረጃ መሰረት የሚከተሉትን ችግሮች በዋናነት መጥቀስ ይቻላል።
  • በአንድ የታወቀ ዩንቨርስቲ ውስጥ ሴቶች መጻሕፍት ቤት አምሽተው ፈጽሞ ወደ ዶርማቸው መምጣት አይችሉም።ዩንቨርስቲው ግቢ እና ጥበቃ ባለው በእዚህ ዩንቨርስቲ ውስጥ ሴት ተማሪዎቹ የሚፈሩት ከተማሪዎች በላይ የዩንቨርስቲው ጥበቃዎችን እና የምግብ ቤት ሰራተኞችን ነው።በአንድ ዩንቨርስቲ ውስጥ የዩንቨርስቲው ጥበቃዎች ተማሪዎችን መድፈራቸው በተማሪውም በዩንቨርስቲው ሰራተኞችም ዘንድ የታወቀ ነው።
  • በአንድ ዩንቨርስቲ ውስጥ የተማሪዎች የምግብ ቤት ኃላፊ የሴት ተማሪዎችን የመመገብያ ካርድ ቀምቶ በግል ስልካቸው ላይ እየደወለ ከስነምግባር የወጣ ጥያቄ አቅርቧል። በእዚህ ተግባር የተጨነቁ ተማሪዎች የሆነውን በዶርማቸው ላሉ ተማሪዎች ሳይናገሩ እንደሚደብቁ ታውቋል።
  • በብዙ ዩንቨርስቲዎች ውስጥ ሴት ተማሪዎች ኮምፕዩተር ይዘው ግቢው ውስጥ መታየት ይፈራሉ።በግቢ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ዶርማቸው ውስጥ ኮምፕዩተራቸውን ይዘው ቢገቡ ጥበቃ የሚያደርግላቸው የለም።የሴቶች ዶርሞች ምሽት ላይ ተሰብረው ኮምፕዩተር እና ሞባይሎች ይወሰዳል። አንዳንዶቹ ጋር ፊታቸውን ሸፍነው በሚመጡ ሌቦች ነው የሚዘረፉት።
  • በብዙ ዩንቨርስቲዎች ውስጥ መምሕራን ተማሪዎችን በጾታቸው ብቻ በውጤቶቻቸው እና የመመረቅያ ጽሁፎቻቸው ላይ ተጽዕኖ ያደርሱባቸዋል።
  • ተማሪዎቹ ወደ ዩንቨርስቲ ቢሮዎች የሚፈልጉትን አገልግሎት ለማግኘት ሲሄዱ በብዙ ቦታዎች ሴቶች ተማሪዎችን በንቀት እና ሥርዓት አልባ በሆነ መንገድ የሚያስተናግዱ በርካታ ሰራተኞች አሉ።
  • ለሃይማኖታዊ ስርዓት አካባቢያቸው ወደሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ወይንም መስጊድ ለመሄድ በአለባበሳቸው ምክንያት አንዳንድ ዩንቨርስቲዎች ያሉ የጥበቃ ሰራተኞች የወጣውንም ያልወጣውንም ሕግ እንደፈለጉ እየተረጎሙ ሴቶች ተማሪዎችን ያጉላላሉ።
  • ሴቶች ተማሪዎች ዩንቨርስቲ አካባቢ ወደየሚገኙ ሱቆች ወጥተው ዕቃ ለመግዛት በጣም ይሳቀቃሉ።ምክንያቱም በሱቆቹ አካባቢ ያሉ ለደህንነታቸው ስጋት የሆኑ ወጣቶች አሉ።
  • አንዳንድ ዩንቨርስቲ የሚገኙባቸው ክልሎች የጸጥታ ኃይሎች ዋና የጥቃት ኢላማዎቻቸው ወደ ከተማው የሚመጡ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ሲሆኑ ይህ ሁኔታ ደግሞ በከተማዎቹ አስተዳደሮች እና የዩንቨርስቲ አመራሮች ጭምር የሚታወቅ ግን ምንም እርምጃ ያልተወሰደባቸው ናቸው።
በእነኝህ ሁሉ ተጽዕኖዎች ሳብያ ሴት የዩንቨርስቲ ተማሪዎች 
  • የዩንቨርስቲ ከባቢያዊ የትምህርት ሁኔታ አስጨናቂ ሆኖባቸዋል።በእዚህ ሳብያ የትምህርት ውጤታቸው የሚቀንስ ብቻ ሳይሆን የሚያቋርጡ እንደሚኖሩ መገመት ቀላል ነው። ለመኖሩ መገመት ቀላል ነው።
  • አንገታቸውን ደፍተው በዩንቨርስቲው ውስጥ መቆየት እንደ ብልሃት እየተወሰደ ነው።
  • አዳዲስ ሃሳቦችን የማፍለቅ እና ለመብት የመቆም ቆራጥ ስሜት እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል።
  • ችግሩ በዩንቨርስቲዎቹ ውስጥ በሲስተም የተሳሰረ ስለሆነ ብሶታቸውን የሚያሰሙበት እና የሚከሱበት አካል ዩንቨርስቲው ውስጥ የለም።
  • ከእዚህ በፊት በደረሰባቸው በደል ለመክሰስ የሞከሩ በእዚሁ የተሳሰረ ሲስተም ሳብያ የበለጠ መሸማቀቅ ስለደረሰባቸው ሌሎች መብታቸውን እንዳይጠይቁ አድርጓል።
ባጠቃላይ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዩንቨርስቲዎች በሴት ተማሪዎች ላይ ያለ ድምጹ ያልተሰማ በደል አለ።ይህ ችግር ወደ የልማት ችግር ሲተረጎም በኢትዮጵያ ሴት ምሑራን ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት እጅግ ግዙፍ ነው።የችግሩ አንዱ መገለጫ ደግሞ ጠንካራ የሆነ ለሴት ተማሪዎች የሚቆም ንቅናቄም ሆነ ሥር የያዘ ስራ አለመኖሩ ነው። የችግሩ ትልቁ መነሻ ግን ከዩንቨርስቲዎቹ ውጭ የሆነ ጥገኛ ያልሆነ አካል ተማሪዎች ያሉባቸውን ችግሮች በምስጢር የሚሰጡበት ልዩ የመገናኛ መስመር ከፍቶ ችግሮቹን ከስሩ ለመንቀል መስራት ነው።በእዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን አንድ ዩንቨርስቲዎች የራሳቸው ጥበቃዎች እና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ለተማሪዎቹ አደጋ መሆናቸው አሳዛኝ ነው። ይህንን ችግር ከእዚህ ጠለቅ ባለ መልክ ምርመራ ቢደረግ ብዙ ጉዳዮች ሊገኙ ይችላሉ።ጉዳዩ አንገብጋቢ ነው።

====================///=========

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...