ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, March 14, 2022

አስቸኳይ! የተፈናቃዮችን ችግር ለመፍታት እና በከተሞች የሰራተኛው ኑሮ ለማሻሻል መንግስት ቀላል የሆኑ 3 ቁልፍ ሥራዎችን በፍጥነት ይስራ!

አስቸኳይ! 
===========
የጉዳያችን መልዕክት
===========

ኢትዮጵያ ያለፈውን፣አሁን ያለችበትን እና መጪውን በሚገባ ፈትሻ ወደፊት ለመሔድ የመንደርደርያዋ ጊዜ አሁን ነው። ፖለቲካ መንግስትን መቃወም ብቻ አድርጎ የሙሉ ጊዜ ሥራ መሆን የለበትም።መንግስትም የስልጣን ወንበር ላይ በመቀመጡ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ነው፣ኢትዮጵያ ፀሓይ በፀሓይ ነች የሚል ንግግሮች መቀነስ አለበት።

የድኅነት መጠኑ ቀላል አይደለም። በቀላሉ ስሌት ሁሉ ነገር እንዳለ ሆኖ ቢሆን እንኳን ህዝቡ ያለበት ቀላል የኑሮ ትግል አይደለም።በኢትዮጵያ ግን ነገሮች ሁሉ እንዳሉ አይደሉም።ከባድ የጦርነት እና የኮቪድ ወረርሽኝ ውስጥ አልፈናል። በኢትዮጵያ የሚሰሩ ፈጣን ተግባራት የሃገሪቱን መጪ ዕጣ የሚወስኑ ናቸው።በመቶ ሺዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ሌሎች መቶ ሺዎች ስጋት አለባቸው።ሚልዮኖች ሥራ አጥ ናቸው።በተለይ በከተሞች ያለው የሥራ አጥ ችግር በቀላሉ የሚታይ አይደለም።ለእነኝህ ሁሉ ችግሮች ብዙ ምክንያቶች መዘርዘር ቢቻልም አንዱ እና ዋናው የክልል እና ብሄር ተኮር አጥሩ ወጣቶች ተንቀሳቅሰው በፈለጉት ክልል እንዳይሰሩ ማድረጉ እና የምርት ገበያ ፍሰቱ የተሳለጠ አለመሆኑ የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።ይህ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ አይችልም።በውስጥ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ከፍተኛ የማቴርያል እና የገንዘብ እንዲሁም የሙያ ድጋፍ የሚያገኙ በኢትዮጵያውያን ጊዜያዊ ችግሮች በማስፋት ሃገሪቱ እንዳትረጋጋ የሚጥሩ ሃይሎች ኢትዮጵያን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይወስዷት መንግስት መስራት ያለበት ወሳኝ ተግባራት አሉ።

ወቅታዊ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት ማድረግ ያለበት 3 ተግባሮች

በኢትዮጵያ ያለውን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከትግራይ እስከ ወለጋ፣ከቤኒሻንጉል እስከ ባሌ የተፈናቀሉ ወገኖችን ችግር ለመፍታት እና ወቅታዊውን የከተሞች የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ የሚከተሉትን ሦስት ተግባራት መከወኑ እንደሃገር ጥቅም አለው።

1) የተፈናቃዮች አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ በፍጥነት መመስረት 
  • ተፈናቃዮች እየገጠማቸው ያለው ችግር የዕለት ተደራሽ እርዳታ ብቻ አይደለም።ጉዳያቸውን ከሌላ የመንግስት ሥራ በተለየ የሚመለከት ባለስልጣን እና ቢሮ የማጣት ግዙፍ ችግርም ጭምር ነው። ይህ ትልቅ ስብራት ነው።ጎዳና የወጣ ዜጋ ቢያንስ የሚያደምጠው ሰው ሊያጣ አይገባም።ለእዚህ በቅርቡ ከወለጋ የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ከአዲስ አበባ እስከ አርሲ እና ደብረብርሃን የተንከረታተቱበት ሂደት በሃገር ውስጥ መገናኛ ሁሉ የተዘገበውን መመልከት ይቻላል። የሚያደምጣቸው የለም።ሃላፊነት የሚወስድ የለም።
  • በመሆኑም ይህ ብሔራዊ ኮሚቴ የማስፈጸም አቅሙ በቶሎ በህግ ተሰጥቶት ሊንቀሳቀስ እና በሁሉም ክልሎች ከትግራይ የመጡትን ጨምሮ የአጭር ጊዜ ፕሮግራም አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባት አለበት።
  • ኮሚቴው ከሙሰኝነት የጸዱ እና ብሄራዊ ሃብት በማዕከል የሚያሰባስቡ ታማኝ ሰዎች መያዝ አለበት።
  • በስራው ላይ የመከላከያ አባላት መሳተፋቸው የሰው ኃይል እንቅስቃሴው ፈጣን ያደርገዋል።በህዝቡ እና በመከላከያ መሃል ያለውን ግንኙነትም ያጠነክራል።
2) የከተሞች የኑሮ ውድነትን ችግር ለመፍታት የሚከተሉት 2 ተግባሮች መስራት ይችላል።

እነርሱም 
        ሀ) ለመንግስት እና የግል ሰራተኞች የሰራተኛ ማኅበራት ለሰራተኛው መሰረታዊ ፍላጎት በቅናሽ በጅምላ ሸቀጦችን እየገዙ እንዲያከፋፍሉ ማድረግ።

አሁን ባለው ሁኔታ የሸማቾች ማኅበር ለህዝቡ የሚያከፋፍለው በትክክል ለባለ ተጠቃሚው እንዳይደርስ የሆነው ነጋዴው በጉቦ ስለሚሸምት እና መልሶ በትርፍ ስለሚሸጥ ነው። ይህ ማለት በከተማ ያለውን ትክክለኛ ተጠቃሚ ለማኘት ቢያንስ የመንግስት ሰራተኞች እና የግል ሰራተኞች በቅናሽ የሚያገኙበት መንገድ በሰራተኛ ማኅበሮቻቸው በኩል ቢመቻች ቀሪው ለፍቶ አዳሪን የሚሻማው ሳይኖር የማግኘት ዕድሉ ይጨምራል።የመንግስት እና የግል ሰራተኞች የቤተሰብ ብዛት እያስመዘገቡ የመሰረታዊ ሸቀጦች ማድረስ በሚልዮን የሚቆጠር ቤተሰቦቻቸው ስለሚጠቅም ቀላል የዋጋ ለውጥ አያመጣም።

    ለ) መንግስት ፈጣን ቤቶች እየሰራ በኮንትራት ለሰራተኞች ማከራየት መጀመር አለበት።

ይህ መንግስት በሁሉ ቦታ እየገባ የሚለው የኢኮኖሚ ፍልስፍና እራሱ የፍልስፍናው ሰሪዎችም አይጠቀሙበትም።ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮች የሚፈቱት ከህዝብ በተሰበሰበ ቀረጥ ነው።ይህ የቀረጥ ገንዘብ ደግሞ ያለው መንግስት ጋር ነው።በእዚህ ዓይነት መንግስት ወደገበያው ሲገባ የግል የቤት ኪራይ ይቀንሳል።ገበያውን ያረጋጋል።አሁን ባለው ሁኔታ መንግስት ከአዲስ አበባ ወጣ ያሉ አካባቢዎች ላይ ፈጣን ቤቶች በመስራት የትራንስፖርት ሁኔታ ማመቻቸት ይችላል።

 3) ወቅታዊ (Seasonal) የእርሻ የስራ ዕድሎች ለከተማው ወጣት መፍጠር 

በኢትዮጵያ ሁለት የዝናብ ወቅቶች አሉ።በእነኝህ ጊዜዎች የከተማ ነዋሪ ወጣቶች በከተማ ሥራ መፈለግ ላይ ብቻ ሳይሆን ለአንድ ዓመት ተከራይተው የመረጡትን የሰብል ዓይነት ዘርተው በአንድ ዓመት ሰብስበው እና ሸጠው ወደ ከተማ የሚመለሱበት መንገድ ማመቻቸት ይቻላል። ይሄውም በከተማ በማኅበር ተደራጅተው የሥራ ዕድል እንደሚፈጠረው ሁሉ ከከተሞች ውጭ የሆኑ ባዶ ቦታዎች ለተደራጁ ወጣቶች ለአንድ ዓመት ወይንም በበለጠ ጊዜ በማከራየት እና ብድር እንዲያገኙ በማድረግ ሰብል አምርተው ሸጠው በአንድ ዓመት ውስጥ እንዲመለሱ ማድረግ ነው።ይህ ማለማመድ ወጣቶች የግብርና ምርት ምን ያህል ሃብት እንደሚያስገኝ ሲያውቁ እንዲገፉበትም መንገድ የሚያመቻች ነው።

ይህ ስራ ለምሳሌ በመጪው ዓመት ወደ ኮሌጅ የሚገቡ ወጣቶች የ12ኛ ክፍል መልቀቅያ ፈተና ከወሰዱ በኋላ ወደ ኮሌጅ ከመግባታቸው በፊት የተወሰነ ገንዘብ አግኝተው ወደ ከተማ የሚመለሱበት ሥራ ሊሆን ይችላል።በእዚህም በከተማ ያለውን የሥራ አጥ ቁጥር በተወሰነ ደረጃ ያቅልላል።ወጣቶች ግብርናው ምን ያህል ሃብት እንደሚያፈራላቸው ሞክረው እንዲረዱ ያደርጋል።የተሳካላቸው ወጣቶች ደግሞ ምሳሌ ሆነው ሌሎችን ይስባሉ። እዚህ ላይ ወጣቶቹ ለሚወስዱት ብድር እና ለእርሻቸው የመድን ዋስትና እንዲገቡ በማድረግ መተማመናቸው እንዲጨምር ያደርጋል። ለእዚህም ክልሎች የእርሻ ቦታዎችን እና ለወጣቶቹ የመኖርያ ቦታ ማዘጋጀት ይችላሉ።ይህ ሥራ ወደ መስኖ ሥራ ሲገባ የሚያወጣው ውጤት ቀላል አይደለም።ከእዚህ ጋር አብሮ የሚታየው የቀላል ኢንዱስትሪ ማስፋፋት ሥራ አብሮ የሚቀጥል ይሆናል።ከተሞች ላይ ያሉ አስፈላጊ ዕቃዎች ወጣቶቹ በቀላል ኢንዱስትሪ የማምረት ሥራ በማስፋፋት ከግብርናው ጎን ሊያስኬዱት ይችላሉ።

ለማጠቃለል አሁን መንግስት በተፈናቃዮች አንጻር የሚታየውን የተዝረከረከ አሰራር ለመፍታት በብሔራዊ ደረጃ በተቋቋመ ኮሚቴ መመራት፣የከተሞችን የኑሮ ችግር ለመቅረፍ የመንግስት እና የግል ድርጅቶች ሰራተኞች ላይ ያተኮረ ሥራ መስራት እና ወቅታዊ የግብርና ሥራ ላይ ወጣቶች እንዲሰማሩ የዝናብ ወቅቱ ሳያልፍ ከአሁኑ ማደራጀት ላይ መስራቱ ጠቃሚ ነው።ይህንን እና የመሳሰሉት ተግባራት ላይ ማትኮር ካልተቻለ የሕዝብ አለመረጋጋት ወደ የሰላም መደፍረስ ሊያመራ ይችላል።የኢትዮጵያ ጠላቶች ደግሞ የሚፈልጉት ኢትዮጵያ ወደ ነበረችበት የውጥረት ሜዳ እንድትገባ ነው።ስለሆነም እርምጃዎቹ ጠቃሚዎች ናቸው።
=============///==========



  



No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...