ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, November 2, 2016

በዐማራ ፖለቲካ ዙርያ የሚታየኝ እውነት እና ስጋት (የጉዳያችን አጭር ማስታወሻ)




ጉዳያችን /Gudayachn 
ጥቅምት 23/2009 ዓም 
====================
አንድን ነገር ፈርተነው ዝም ካልን አላዋቂ እንዲመራን መንገድ መክፈት ነው።ይህንን ጉዳይ የማነሳው አዲስ የውይይት ርዕስ ለመክፈት አይደለም።በፌስ ቡክ ላይ አንድ ግለሰብ ስለፃፈ/ስለፃፈች ወይንም ሶስት እና አራት ሰዎች ሃሳባቸውን ስላሰፈሩ ሃሳቡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወይንም እንወክለዋለን ያሉት ሕዝብ ሃሳብ ነው ለማለትም አይደለም። ሃሳቦች ግን ከመጀመርያው ካልተነሱ ጊዜ በወሰዱ ቁጥር እየጠጠሩ እና ንግግሮች ሁሉ ሕግ ሆነው ሳይታወቅ ይቀራሉ።

ፖለቲካ መነሻ እና ግብ ከሌለው መውጫው ጭንቅ ነው። ፖለቲካ አስፍቶ የማየት አዕምሮ ላይ ካላረፈ አንድ ሰው ላይ ወጥታ  አጠገቧ ያለውን አንድ ቅንጣት ፀጉር ትልቅ ዛፍ አድርጋ አይታ ደን ውስጥ ነኝ ብላ እንደምታስብ ቅማልም በጠበበ መረጃ ላይ መመስረትን  ያመጣል። ፖለቲካ ልምድ እና ሙያም ይፈልጋል።ፖለቲካ በፍፁም ፍቅር እና የሰውን ልጅ ሁሉ የመውደድ ፀጋ ሳይታደሉ የሚገቡበት አይደለም።የሰውን ልጅ ሁሉ ሳይወዱ የሚገቡበት ፖለቲካ በአለማችን ላይ እንደተመለከትነው መጨረሻ ላይ የእራስን ጎሳ ወደማምለክ ይቀየርና ግቡ ´´ፋሽዝም እና ናዚዝም´´ ይሆናል። ስለዚህ ጥንቃቄ ይፈልጋል።

እውነታው  
=======
የዐማራ  ማኅበረሰብ ለሕወሐት ´እንደጠላት ተቆጥሮ በግልፅ እና በስውር ላለፉት 25 ዓመታት በተለየ መልኩ ተጠቅቷል።በሕወሓት ማኔፌሥቶ ውስጥ እንደተገለፀው በገዢ መደብነት ተጠቅሶ ቁጥር አንድ ጠላት ተብሏል።ላለፉት 25 ዓመታትም በሺህ የሚቆጠሩ በዐማራነታቸው ብቻ እና ብቻ ተጠቅሶ ተገድለዋል፣ከቤታቸው ተባረዋል፣በርካታ ስውር ጥቃቶች ተፈፅመዋል።እነኝህን ትውልድ፣ታሪክ እና እግዚአብሔር በጊዜው የሚፈርዱት ይሆናል።ይህ ማለት በሌላው ብሔር ላይ አልደረሰም ማለት አይደለም።በተለይ በዐማራው ላይ የተደረገው ግን ማኅበረሰቡን የስልጣን ስጋት ነው በሚል ብቻ ሳይሆን ከሰይጣናዊ ፍፁም ጥላቻ የተፈፀመ መሆኑ ነው።በሌላው ላይ የተፈፀመው  አንድ፣የተፈጥሮ ሃብቱን ለመቆጣጠር አልያም ለመብቱ በተነሳበት ወቅት ስልጣንን ለመጠበቅ በሚል ሕወሓት የወሰዳቸው እርምጃዎች ናቸው። በዐማራው ላይ የተወሰደው ግን ከእዚህ በተለየ ስልታዊነት ላይ የተመሰረተ ከፖለቲካ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ዘርፎች ሁሉ የማስወገድ እና በመጨረሻም ወደ ማጥፋት የዞረ ተግባር ነው። ይህ በርካታ ማስረጃዎች ያሉት ያለፉት 25 ዓመታት እውነታ ነው።

ስጋት 
====
ከላይ የተጠቀሰው እውነታ በርካቶች ስለ ማኅበረሰቡ መብት፣ነፃነት (በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ነፃነት) እና እኩልነት ድምፃቸውን እያሰሙ ነው።ይህ ክስተቱ ያመጣው ሂደት ነው።ይህ ማለት ግን ብሶት በእራሱ ፖለቲካ አይሆንም።ብሶት ቁጭት እና የንዴት ማብረጃ ብሎ ያገኘውን ዕቃ ሁሉ የመወርወር ክፉ አባዜ ያስከትላል። ስለሆነም በዐማራ ማኅበረሰብ ዙርያ የሚነሱ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች መልሶ እራሱን ዐማራውን የሚያስከፋ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይፈልጋል።የዐማራ ማኅበረሰብን ስነ ልቦና፣ብሔራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሞራል ልዕልናን ከግንዛቤ ያላስገባ ፖለቲካ መጨረሻ ላይ ፈረንጆቹ እንደሚሉት ወደ እራስ መተኮስ (fire back) ያስከትላል።ይህንን ለማለት ያስገደደኝ በማኅበራዊ ሚድያ ላይ አንድ ሰሞን በርካታ ተከታይ ስላገኙ ብቻ እራሳቸው የፖለቲካ ፕሮግራም አውጪ ቀጥለው ወክለነዋል ስለሚሉት ሕዝብ የወደፊት እጣ ለመወሰን የሚዳዱ ደፋሮች ስመለከት ነው።

ስለ ዐማራ ማኅበረሰብ እውነቱን የሚናገሩ በደሉ ስልታዊ መሆኑን በማስረጃ የሚያቀርቡ እና ይህ ለነገዋ ኢትዮጵያ አደጋ መሆኑን የሚያሳስቡ ሁሉ ክብር ይገባቸዋል።ይህንን በደልም አንስተው ቆርጠው ለመታገል የወሰኑም እውነተኞች እና ስለ ፍቅር የሚያደርጉት እንደሆነ የታመነ ነው።ከእዚህ አልፈው ይህንን ስሜት እየኮረኮሩ ስለ ዐማራ ነፃ መንግስት ለመስበክ የሚፈልጉ ግን ´´ሰከን በሉ´´ ማለት ተገቢ ነው። ፖለቲካ የዕቃ ዕቃ ጫወታ አይደለም።ፖለቲካ ሰፊ ልቦና እና አሁንም ልድገመው  በደልን ውጦ ሌላውን በፍፁም ፍቅር መውደድ ይፈልጋል።

የዐማራ ማኅበረሰብ የእረጅም ጊዜ የፖለቲካ ተሞክሮ አለው።ኢትዮጵያን ብሎ የሚኖረው ስለተመቸው እና ስላልተመቸው አይደለም።የዛሬ የሁላችንም ኢትዮጵያውያን መደህየት የነገ እንዳልሆነ ያምናል። ያጣነው መልካም መንግስት ነው።ይህንን ደግሞ በበደላችንን እያሰማን ወደ እኩል ኢትዮጵያ የሚወስደንን መንገድ እንከታለለን እንጂ በማኅበራዊ ሚድያ የሚመራን ሕዝብ አይደለንም።በእርግጠኝነት የእዚህ አይነቱ የዐማራ መንግስት የምትል አጀንዳ ማራገብ አንድ ወያኔ በውጭ ባለው ማኅበረሰብ ዘንድ ሌላ አጀንዳ ለመፍጠር ያሰባት ነች። አልያም አዲስ ነገር የፈጠሩ መስሏቸው ወይንም ጊዚያዊ የፖለቲካ አጀንዳ በማንሳት ጥሩ ስልት የፈጠሩ የመሰላቸው የሚያነሱት ነው።

ባጠቃላይ ግን ያኛውም ተባለ ይሄኛው ቁም ነገሩ የዐማራ ማኅበረሰብን ብሔራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሞራል ልዕልና ከኢትዮጵያዊነት ጋር ያለውን ቁርኝት የዐማራ መንግስት በሚል የፌስ ቡክ አጀንዳ አትጉዱት።በእርግጥ ይህ ሃሳብ በእራሱ ለመውቀስ ገና ነው ሊባል ይችላል።የእኛ ችግር ይህ ነው።ነገሮችን ከወዲሁ በእንጭጩ ሃሳቡ ካልተቀጨ ነገ የሚናገር የለም።እያየን ማለፍ መቼም ባህላችን ሆኗል።ስለዚህ ነው በደሉን አብረን እንጩህ፣ለነገዋ ኢትዮጵያ አብረን እንስራ ነገር ግን አጀንዳውን ወደተለየ መንገድ የሚወስዱትን ´´ሰከን በሉ´´ እንበል የምንለው።



ጉዳያችን GUDAYACHN

 www.gudayachn.com

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።