ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, November 7, 2016

የኢትዮጵያ የወቅቱ የተቃውሞው የፖለቲካ ሜዳ ተስፋ አስቆራጭ አይደለም።ይልቁንም በብዙ ተስፋ የተሞላ ነው። (የጉዳያችን አጭር ማስታወሻ)


  • የሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች እና ስብስቦች ፍላጎት ምንድነው? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ አንድ ነው። 
  • የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ተስፋ ሰጪ እና ወደፊት ሲሄድ እንጂ ወደ ኃላ እየሄደ አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል።
  • በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥም በሁሉም ወገን የሚታዩ ፅንፈኞች ይኖራሉ።
ኢትዮጵያን አንዳንዶች በአንዳንድ መድረኮች ላይ በተነገሩ ንግግሮች ወይንም የተንሸዋረረ የግለሰቦች የፖለቲካ እና ታሪካዊ ትንተና አንፃር እየተመለከቱ ተስፋ አስቆራጭ ደረጃ እንደደረሰች የሚገምቱ አሉ።ይህ ግን የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው።ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበት የፖለቲካ ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ አይደለም። ተስፋ አስቆራጭ አድርጎ የሚያቀርበው ስልጣኑን የሙጭኝ ብሎ ሕዝብ እየገደለ እና እያሰረ የሚገኘው ሕወሓት ነው።ይህ ማለት ግን ከሁሉም ወገን ስልጡን አካሄድ መሄድ አይጠበቀም ማለት አይደለም።

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ሶስት  ቀናት ውስጥ በባህር ማዶ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ክንውኖችን በአጭሩ በማሳታወስ የወቅቱን የፖለቲካ ሁኔታ የተራራቀ የመሰለን ግን በአንድ መስመር የሚሄዱበት በርካታ እድሎች መኖራቸውን በቀላሉ ማሳየት ይቻላል።እያንዳንዱ ክስተቶች የእራሳቸው ተቃራኒ ሃሳቦች ተነስተውባቸዋል።

የመጀመርያው የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ የተሰኘው በአርበኞች ግንቦት 7፣የአፋር ፓርቲ፣ሲዳማ ንቅናቄ እና ኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር የተመሰረተው ንቅናቄ ነው።ንቅናቄው እንደመግለጫው በርካታ ስራዎች የሚቀሩት መሆኑን ቢገልጥም በኢትዮጵያዊነት ስር መንቀሳቀስ ወሳኝ መሆኑን ገልጧል።የእዚህን ንቅናቄ የሚተቹት በአማራውም ሆነ ኦሮሞ ብሔርተኝነት ስም የሚገኙ ናቸው።የአማራው ብሔርተኝነት በተለይ እራሱ በአግባቡ አለመወከሉን ይገልፅና የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ውስጥ የተወከሉት ግለሰቦች በ1980ዎቹ ውስጥ በአርሲ እና ሐረር ጨምሮ ለተፈፀሙት ግድያዎች ተሳትፎ አላቸው ይላሉ። በአንፃሩ በኦሮሞ ማሕበረሰብ በኩል የእነ አቶ ሌንጮ እና ዶ/ር ዲማ ከአንድነት ኃይል ጋር ንቅናቄ አባል መሆናቸው እንደ ስህተት ይቆትሩባቸዋል።እዚህ ላይ ኦነግ የሚለውን እንቅስቃሴ የጀመሩት ውስጥ እኔ ዶ/ር ዲማ መሆናቸውን ሁሉ ዘንግተው ከማን ጋር መሆን እንዳለባቸው ሊመክሯቸው ይሞክራሉ።ይህ ሁሉ ወቀሳ ግን የተለያዩ አስተሳሰብ ጥጎች ናቸው እንጂ ክፉ ክስተቶች አይደሉም። ዋናው ኢትዮጵያዊ አጀንዳ እስካልተጣለ ድረስ ሊስተካከል የሚችል ቀላል የሂደት ጥያቄ ነው።

ሁለተኛው የእዚህ ሳምንት መጨረሻ ክስተት የኦሮሞ ሚድያ ኔትዎርክ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ ከዶ/ር ፀጋዬ አራርሳ እና ኢታና ጋር በተደረገ ውይይት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር በቅርብ የተመሰረተች መሆኗን ከአንድ ሰዓት በላይ በረዘመ ቃለ መጠይቅ ላይ ሲነገር ተሰምቷል።ሌላው ቀርቶ የሚለበሰው ´´የሀገር ልብስ ሳይቀር የዐማራ ባህል ተፅኖ ነው´´ የሚል አገላለጥ ተሰምቷል።በተለይ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል በቅርብ የመጣ ነው የሚለው አነጋገር የሚያጣቅሰው ማስረጃ ሳይኖር በደፈናው አቢሲንያ ትባል ነበር ሲባል ተሰምቷል።ሌላው ቢቀር የኢትዮጵያ ነገስታት ከጥንት ጀምሮ የተፃፃፉት ደብዳቤ፣በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት የተፃፈው ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል ሁሉ ገደል የከተተ ስንኩል አቀራርብ ነበር።

ሶስተኛው ክስተት በትናንትናው ማለትም በጥቅምት 27፣2009 ዓም በሲያትል የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አዳራሽ የተጠራው እና ምሁራን፣የታሪክ ሰዎች፣የሃይማኖት አባቶች እና አክትቪስቶች የተገኙበት የዐማራ ማኅበረሰብ የጋራ ግብረ ኃይል የተጠራ ስብሰባ ነበር። 

በስብስባው ላይ የምጣኔ ሐብቱ ባለሙያ ዶ/ር አክሎግ እና ድምፃዊ ሻምበል በላይነህን ጨምሮ በርካቶች ታድመውበታል።በስብሰባው መጨረሻ ላይ የጋራ ምክር ቤት በመመስረት ተፈፅሟል።
ከእዚህ በተጨማሪ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በአማካሪነት እንዲሰሩ ጥቆማ ቀርቧል።ጉባኤው ከሞላ ጎደል የዐማራው ማኅበረሰብ በሕወሓት ስርዓት ውስጥ ዘርን ያማከለ ጥቃት መድረሱ፣ጥቃቱ ከሌሎች ፅንፈኛ አካላትም መሰንዘሩ፣ ኢትዮጵያን እና እምነቷን ለማጥፋት የዐማራው ማኅበረሰብ ኢላማ መሆኑ እና እነኝህን ችግሮች ለመፍታት የዐማራው መደራጀት አስፈላጊ መሆኑ ተደጋግሞ ተወስቷል።

ከላይ የተመለከትናቸው ክንውኖች በሙሉ እንቅስቃሴን፣መፍትሄ ፍለጋን እና አለመተኛትን የሚያሳዩ እንጂ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተስፋ አስቆራጭ መሆኑን አያሳይም።አሁን በስልጣን ላይ ላለው ስርዓት ግን በእየዘርፉ እና በአይነት የጠመዱበት የመሳርያ አይነቶችን ያሳያል።ከብሄር ስብስብ እስከ ኢትዮጵያዊነት መገለጫነት በእየመልኩ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚስማሙበት አንዱ እና ዋናው ነጥብ የሕወሓት መንግስት ስልጣኑን ለሕዝብ ማስረከብ እንዳለበት ነው። በሌላ በኩል ከላይ የሚታዩት የፖለቲካ አቀማመጦች መልክ ለመስጠት ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ስብስቦች በሙሉ እውነትኛ ችግሮችን እየነቀሱ እና በእርሱ ላይ ብቻ እያተኮሩ መፍትሄ መስጠት እና ወደ አንድ መድረክ መምጣት እንዳለባቸው አመላካች ጊዜም ነው ወቅቱ።ከሁሉም ግን በተለይ በማኅበራዊ ሚድያ ላይ የሚሰጡ ሃሳቦች ከስድብ እና አጉራ ዘለል ንግግሮች እንዲጠሩ እና በጨዋነት ላይ የተመሰረቱ ቃላትን መጠቀም የግድ ይላል።ማንም የፈለገውን አይነት ሃሳብ ይኑረው ማክበር እና ሃሳብን በጥሩ ቃላት መግለፅ መልመድ ተገቢ ነው።

ከእዚህ በተረፈ ግን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ተስፋ ሰጪ እና ወደፊት ሲሄድ እንጂ ወደ ኃላ እየሄደ አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል።ምናልባት ኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነች ብለው የሚናገሩት ወደ ኃላ እየነዱን እንደሆነ እናስብ ይሆናል። እውነታው ግን በተቃራኒው ነው።ምክንያቱም የእዚህ አይነቱ አባባል በእራሱ  ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያነቃ እና ፅንፍ የያዙት ኢትዮጵያን የሚያጥላሉበት ደረጃ የት ያህል እንደሆነ ያነቃል፣ያዘጋጃል።

በመጨረሻም የሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች እና ስብስቦች ፍላጎት ምንድነው? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ አንድ ነው። እርሱም በመጪዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ዋስትና ማግኘት የሚል ነው። የኦሮሞ ማኅበረሰብም ሆነ የዐማራ ማኅበረሰብ እንዲሁም ሌላው ሁሉ በነገዋ ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱ በዳይ ሌላው ተበዳይ እንዳይሆን ዋስትና ይፈልጋሉ።ይህንን ዋስትና እንዴት አስተማማኝ ማድረግ ይቻላል? ዋናው እና ቁልፉ የፖለቲካ ኃይሎች ሊመልሱት የሚገባ ቁልፍ ጥያቄ ነው።ይህንን ማስተማመኛ ዋስትና ቢኖርም የማይቀረው ግን የፅንፈኞች ጫፍ የያዘ ሃሳብ እስከመቼውም የማይቀር የፖለቲካ እንክርዳድ ነው።እንክርዳድ እንዳይኖር ማድረግ አይቻልም ዋናውን ስንዴ ሳይጎዱ መንቀል ግን ይቻላል።ለመንቀል ግን ትግስት እና ጥበብ ይፈልጋል።በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥም በሁሉም ወገን የሚታዩ ፅንፈኞች ይኖራሉ።ሆኖም ግን ሃሳባቸውን እንደ ሃሳብ እየሰሙ እና ተገቢ ከስድብ የራቀ ምላሽ መስጠት ከእዚህ ባለፈ ግን በኃይል ሃሳባቸውን ለመጫን ሲሞክሩ እንደ እየአመጣጣቸው በሕዝብ ምላሽ እንዲሰጥ ህዝብን ማንቃት ተገቢ ነው።ኢትዮጵያ አሁን የተጫናትን የሕወሓት አገዛዝ ማስወገድ ከቻለች መጪው ብሩህ ተስፋ እንደሆነ ቅንጣት ታህል መጠራጠር አይገባም።
==============================================
አንዳንዴ የጋራ ዕሴቶቻችን ላይ አለማተኮር ለምሳሌ ኪነ ጥበብ ልዩነታችን የበዛ ያስመስለዋል።ኦሮሞው ቢናገር፣ ዐማራው ቢደራጅ፣ሱማሌው ቢቃወም፣ ደቡብ ቢወቅስ  መርሳት የሌለብን ሁሉም ያገር ልጅ መሆኑን ለትውልዱ ደጋግሞ መንገር ተገቢ ነው።የጋራ የሆኑ ዕሴቶችን እያነሳን መኮርኮር የኅብረታችን መገለጫ ነው።ለሕዝብ ተስፋን ማሳየት ለዲሞክራሲ መብቱ የሚያደርገውን ትግል ሁሉ ያጠነክረዋል።

ድምፃዊት ፍሬ ሕይወት ስለሺ
  ´´ዘመድ ያገሬ ልጅ´´
ያገሬ ልጅ  (ሰሜን ያለው፣ደቡብ ያለው፣ ሱማሌ ያለው፣ወለጋ ያለው) 
አብሮ አደጌ እንዴት ነህ ቃናዬ .....


ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...