ጉዳያችን/ Gudayachn
ጥቅምት 26፣2009 ዓም
================
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ወዴት እየሄደ እንደሆነ ለማወቅ በሚቻልበት ደረጃ አይደለም።በሀገር ቤት በተለይ በዐማራ እና ኦሮሞው ክፍል ለመናገር የሚዘገንን ግድያ፣ስቃይ እና ሰቆቃ በሕወሓት ወታደሮች እየተፈፀመ ነው።ይህ የኢንተርኔት እና ስልክ መስመሮችን በመዝጋት የሚፈፀመው ግድያ እና እስር በተለይ በዐማራ በኩል ከሕዝቡ እየተሰጠ ያለው ምላሽ ወደ በረሃ ወርዶ ከመፋለም እስከ እጅ በእጅ ትንቅንቅ ድረስ ሕዝቡ እየተፋለመ ነው።በእዚሁ ሳምንት መጀመርያ ላይ የባህር ዳር ነዋሪ ወጣቶች በስርዓቱ ባለስልጣናት መኖርያ ሰፈር እና በማዘጋጃ ቤት ቢሮ ላይ የፈፀሙት የቦንብ ጥቃት አንዱ የትንቅንቁ መገለጫ ሆኖአል።በሰሜን ጎንደርም መጠነ ሰፊ ጦርነት እየተካሄደ ነው።የገበሬውን መሳርያ ለመንጠቅ የዘመተው የሕወሓት ሰራዊት በሄደበት የገበሬው የጥይት አረር እያረገፈው መሆኑን የሚገልጡ ዜናዎች እየወጡ ነው።
ይህ በእንዲህ እያለ ነው በመጪው እሁድ ጥቅምት 27፣2009 ዓም ´´የዐማራ ሕዝብ አንድነት ግብረ ኃይል´´በሲያትል አሜሪካ ስብሰባ ጠርቷል።ይህ ስብሰባ በተለይ በዐማራ ዙርያ የተሰባሰቡ ድርጅቶች፣ሲቪክ ማኅበራት፣አክትቪስቶች እና ምሁራንን ሁሉ የሚያሳትፍ እንደሚሆን ተገልጧል።በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ብቻ እንደሚያሸበርቅ የሚጠበቀው ይህ ስብሰባ በዐማራው ማኅበረሰብ ዙርያ የተሰባሰቡ ሁሉ በግልፅ እና በጋራ የሚገናኙበት የመጀመርያ መድረክ ይሆናል።
ስብሰባው የሚደረግበት ዋና ምክንያት እና አጀንዳዎች ምን ምን እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።በተለያየ መልኩ የተደራጁ አደረጃጀቶች ግን አንድ አይነት የኅብረት መድረክ እንደሚፈጥሩ ይታሰባል።በስብሰባው ላይ የጎንደር ኅብረት፣ሞረሽ ወገኔ እና ቤተ ዐማራን እንደሚጨምር የተገለጠው ስብሰባ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
ባብዛኛው ወጣቶች የሚንቀሳቀሱበት የዐማራ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ሲቪክ ማኅበራት እና አክትቪስቶች በተለያዩ መድረኮች ሲገልጡ እንደሚሰማው የሁሉም መድረሻ ግብ ወያኔን ማስወገድ ብቻ ሳይሆን በዐማራ ማኅበረሰብ ላይ ከእዚህ በፊት በዘር ጥላቻ ላይ ብቻ ተመስርተው ግድያ የፈፀሙ እና ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የሚጠሉትን ሁሉ እንደሚፋለሙ ያሳስባሉ።በመጪው የእሁድ ስብሰባ ላይም እነኝህ ስሜቶች እንደሚንፀባረቁ ይጠበቃል።በዐማራ ማኅበረሰብ መደራጀት አለበት? ወይንስ የለበትም? የሚለው ክርክር በማኅበራዊ ሚድያ ላይ ይሰሙ የነበሩት ክርክሮች አሁን አሁን አይሰሙም።ከጥቂት ወራት በፊት በእዚህ ዙርያ የሚነሱት ክርክሮች የእየራሳቸውን ነጥቦች ሲያነሱ ይሰማ ነበር።
የዐማራ ማኅበረሰብ መደራጀት አለበት የሚሉት ወገኖች ሁለት ምክንያቶች ያነሳሉ እነርሱም የማኅበረሰቡ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በሕወሓት የደረሰበት ዘርን ያማከለ ጥቃት እና በሌሎች የስርዓቱ አጋሮች በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ያደረሱትን ጥቃት በአብነት ይጠቅሳሉ። ከእዚህ በተጨማሪም በመጪው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስልጣን ላይ ዐማራውን ያገለለ የስልጣን ሽግግር ፈፅሞ የማይታሰብ መሆኑን አሁንም አበክረው ይመክራሉ።
የጥቅምት 27ቱ የሲያትል፣አሜሪካው ስብሰባ ባንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከላይ የተነሱትን ነጥቦች ዙርያ የሚንፀባረቁበት መድረክ እንደሚሆን ይታሰባል።የማኅበረሰቡ ትግል እስከምን ድረስ ይሄዳል? በኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ላይስ የሚኖረው ተፅኖ ምን አይነት ይሆናል? የሚፈጠረው መድረክ እራሱን ወደ ፖለቲካ ኃይል ይቀይራል? ወይንስ ስብስብ ሆኖ ይቀጥላል? እና ሌሎች ጥያቄዎች ይነሳሉ።ከእዚሁ ጋር በተያያዘ ግን የማኅበረሰቡን የፖለቲካ አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው።
በሌላ በኩል ሳይነሳ የማይታለፈው ጉዳይ የማኅበረሰቡ ስብስቦች ላይ የሚነሱ አከራካሪ ጉዳዮች መኖራቸው ነው።ከእነዚህ ውስጥ ፍፁም ጫፍ የያዘ እና ማኅበረሰቡ ´´የእራሱ መንግስት ይኑረው´´ የሚለው ሃሳብ ድረስ ይሄዳል።የእዚህ አይነቶቹ ሃሳቦች እንደ መከራከርያ የሚያነሱት በአሁኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አክራሪ እና ፅንፍ ካልተያዘ ´´በተቃራኒ´´ በኩል ያለውን ፅንፍ መመከት አይቻልም የሚል እሳቤ ይንፀባርቃል።ሆኖም ግን ይህ አስተሳሰብ በብዙዎች ዘንድ የእራሱ የሆነ ተቃርኖ ገጥሞታል።
በሌላ በኩል ደግሞ የእዚህ አይነቱ የሃሳብ ክርክር ክስተት የአንድ ተቋም ጤነኛ ባህሪ መሆኑን የሚገልፁ አሉ። መከራከር፣የሃሳብ ፍትግያ እና ግጭቶች አስፈላጊ እና ወደ አንድ ነጥብ የሚመሩ ተፈጥሯዊ የአንድ ተቋም የመመስረት ወይንም የመለወጥ የምልክት ሂደቶች ናቸው። እነኝህ ሂደቶች በመጪው እሁድ አይነት የፊት ለፊት ስብሰባዎች መፍትሄ እንዲያገኙ ይረዳል።
በመጨረሻም የሲያትሉ ስብሰባ በቸልታ እንዳይታይ ያሚያደርገው አንዱ እና አይነተኛ ምክንያት በሺህ የሚቆጠር የዐማራው ማኅበረሰብ ብረት አንስቶ ከሕወሓት አምባገነን ስርዓት ጋር እየተፋለመ መሆኑ ነው።ስብሰባው ግን ከወጣት እስከ አዛውንት እና የሃይማኖት መሪዎች ሁሉ የሚገኙበት እና ከማኅበረሰቡ ጉዳይ እስከ ኢትዮጵያዊነት ሃገራዊ ጉዳይ እንደሚወሱበት ይጠበቃል።
በመጨረሻም የሲያትሉ ስብሰባ በቸልታ እንዳይታይ ያሚያደርገው አንዱ እና አይነተኛ ምክንያት በሺህ የሚቆጠር የዐማራው ማኅበረሰብ ብረት አንስቶ ከሕወሓት አምባገነን ስርዓት ጋር እየተፋለመ መሆኑ ነው።ስብሰባው ግን ከወጣት እስከ አዛውንት እና የሃይማኖት መሪዎች ሁሉ የሚገኙበት እና ከማኅበረሰቡ ጉዳይ እስከ ኢትዮጵያዊነት ሃገራዊ ጉዳይ እንደሚወሱበት ይጠበቃል።
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
No comments:
Post a Comment