ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, September 27, 2016

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ´´የወያኔ አገዛዝ እና የኢትይጵያ ወደፊት´´የሚለው ፅሁፋቸውን በተመለከተ የገቡኝ እና ያልገቡኝ ነጥቦች

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም 

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ሶስተኛው ትውልድ ላይ ሆነው የኢትዮጵያን ጉዳይ እድሜ ዘመናቸውን ያልተዉ እና አሁን በእርጅና ዘመናቸውም ለችግሮች መፍትሄ ያሉትን ከመስጠት የማይደክሙ ኢትዮጵያ በዘመናዊ ዘመኗ ካፈራቻቸው ጥቂት ትጉ  ምሁራን ውስጥ ናቸው።ዛሬም ፕሮፌሰሩ አሁን ኢትዮጵያ ለገባችበት የፖለቲካ ችግር መፍትሄ ያሉትን´´የወያኔ አገዛዝ እና የኢትይጵያወደፊት´´ በሚል ርዕስ በድረ-ገፃቸው ላይ አስነብበውናል።

ፅሁፉን አንብቤዋለሁ።የምስማማበት እና የማልስማማበት ወይንም የማያስኬድ ነው የምላቸው ነጥቦች አሉኝ።ነገር ግን ርዕሴን የማልስማማበት ከማለት ያልገባኝ በሚለው ማስቀመጡ የተሻለ እንደሆነ ተሰምቶኛል።ላለመስማማት ለማለት ፅሁፍ በእራሱ ሁሉንም ነገር አይገልጥም እና እርሳቸው ያዩበት የዕይታ ጥግ እና ምክንያቶቹን በደንብ ቃል በቃል እየጠየኩ የተረዳሁ ቢሆን ነበር።ሆኖም ግን ያ ባልሆነበት ሁኔታ አለመስማማት የሚለውን ያልገባኝ የሚለው አገላለፅ የተሻለ ሆኖ ተሰምቶኛል።
የፕሮፌሰር መስፍን ፅሁፍን ባጠቃላይ ዋና መልዕክቱን በሶስት ነጥቦች የሚጠቃለል ይመስለኛል። እነርሱም : -

1/ የወቅቱ ጥያቄ ወያኔን ማውረድ ነው ግን ትግራይን ካላሳተፈ ለውጡ  ውጤታማ አይሆንም፣

2/ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት የሕወሓት ባለስልጣናት ከሚመሰረተው  ነፃ የተወካዮች ምክር ቤት ዋስትና እና የኑሮ ድጎማ ማግኘት  እና

3/ የትግራይ ሕዝብ ከሕወሓት ወይንም ከኢትዮጵያዊነት አንዱን ይምረጥ።ኢትዮጵያዊነቱን ቢመርጥ ይሻለዋል።የሚሉት ናቸው።

1/ የወቅቱ ጥያቄ ወያኔን ማውረድ ነው ግን ትግራይን ካላሳተፈ ለውጡ ውጤታማ አይሆንም 

የወቅቱ ጥያቄ ወያኔን ማውረድ ነው። ትክክል ነው።ይህ እራሱ ወያኔ በተግባሩ ሕዝቡን ገፍቶ ያመጣው የኢትዮጵያ ሕዝብ የህልውና ጥያቄ ነው። ትግሉ የትግራይን ሕዝብ ማሳተፍ እና ወያኔን ማሳተፍ በሚለው መካከል ትክክለኛ መስመር ቢሰመርበት ግን ጥሩ ነው ባይ ነኝ።ምክንያቱም የትግራይ ህዝብን ችግር ከኢትዮጵያ ችግር ጋር እንዲቆላለፍ ያደረገው ሕወሓት መሆኑ እስከተገለፀ ድረስ የትግራይ ችግር ከሚባል የሕወሓት ችግር ተብሎ ቢጠቀስ የበለጠ ገላጭ ይሆናል።ይህ ማለት ትግራይን ማሳተፍ እንደ ሀገር አካል የሚለውን እሳቤ በሚገባ ያሳያል ማለት ነው።

ፕሮፌሰር በፅሁፋቸው ላይ ´´ኢትዮጵያን በትግራይ ገመድ፣ ትግራይን በኢትዮጵያ ሰንሰለት አስሮ የያዘው ወያኔ ገመድና ሰንሰለቱን እንዲበጥስና ሁለቱም ነጻ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ወይም ትግራይንም ሆነ ኢትዮጵያን ሳይጎዳ ገመዱንና ሰንሰለቱን መበጠስ የሚችል ሌላ ማን ነው?የሚል ነው፡፡´´ ይላሉ።እዚህ ላይ ሁለቱንም ነፃ ማድረግ የሚለው መፍትሄው ህወሓት ተነጥሎ ሲመታ ወይንም እራሱን ሲያከስም ነው። ለማክሰምም ሆነ ለመመታት ደግሞ የትግራይ ሕዝብ እራሱን ከሕወሓት በፈቃዱ ለይቶ ፕሮፌሰር መጨረሻ ላይ እንደጠቀሱት ኢትዮጵያዊነቱን ሲያስበልጥ እና በፖለቲካም ሆነ ምጣኔ ሀብት ለእራሱ ከማድላት አስተሳሰብ ወጥቶ  እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል እኩል ተሳታፊ ሲሆን ነው።

በወያኔ ማውረድ ጥያቄ ውስጥ ግን ሰላማዊ ትግል ነው ወይንስ የትጥቅ ትግል የሚል ብዥታ በአሁኑ ወቅት አለ ብዬ አላምንም።የሰላማዊ ትግል ሁሉንም በአንድነት በተቀናጀ መልክ ማሳተፍ ከቻለ እና ፅናትን ካሳየ አዋጭ ለመሆኑ የሚከራከር የለም። ሆኖም ግን በወራት ውስጥ በሺህ የሚቆጠር አስከሬን ለሚከምር ወያኔ የሰላማዊ ትግል ነው ወይንስ ትጥቅ ትግል የሚል ክርክር ከቆመ ቆይቷል።ስለዚህ ብዥታው አለ የሚለው አባባል አልገባኝም።በሌላ በኩል ለውጡ ትግራይን ማሳተፍ አለበት አዎን!ነገር ግን የግድ ወያኔ በየትኛውም መልክ ማለትም በፖለቲካ፣በምጣኔ ሃብት ወይንም በማኅበራዊ መልክ ለውጡ ላይ የመሪነት ሚና ሊኖረው አይገባም።ይህ የመሪነት ሚናውን ያጎላዋል የሚለው ስጋቴን የሚያጠናክረው ፕሮፌሰር በመቀጥለው ተራ ቁጥር  2 ላይ በጠቀለልኩት ሀሳባቸው ውስጥ ነው።

2/ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት የሕወሓት ባለስልጣናት ከሚመሰረተው ነፃ የተወካዮች ምክር ቤት ዋስትና እና የኑሮ ድጎማ ማድረግ   

ፕሮፌሰር በፅሁፋቸው ላይ  በሚመሰረተው ነፃ የተወካዮች ምክር ቤት ላይ ተጣርቶ የተገኘው ሀብት እንዴት እንደሚከፋፈል ሲገልፁ 
´´ተጣርቶ የተገኘው ሀብት (የማይንቀሳቀስ ንብረትን ጨምሮ) እንደሚከተለው ሊደለደል ይቻላል፡– ይህ መነጋገሪያ ሀሳብ ብቻ ነው፡–
- ለትግራይ ልማት፤
- ለሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ልማት፤
- ለትግራይ የጦር ጉዳተኞች፤ ለእያንዳንዳቸው መጠነኛ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት፣
- ለትግራይ የሟች ቤተሰቦች፤ ለእያንዳንዳቸው መጠነኛ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት፣ 
- ለሌሎች ኢት. የሟች ቤተሰቦች፤ ለእያንዳንዳቸው መጠነኛ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት፣
- ለሌሎች ኢትዮጵያውያን የጦር ጉዳተኞች፤ ለእያንዳንዳቸው መጠነኛ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት፣
- ለወያኔ መሪዎች፤ ለመኖሪያ የሚያስፈልጋቸውን ጡረታ መስጠት፤´´ ይላሉ።

እዚህ ላይ ገና ባልተሠራ ሥራ ላይ ምቀኝነት ልገልፅ አይደለም።ነገር ግን ይህ ሃሳብ ባጭሩ ወያኔ በአገር ውስጥ እና በውጭ ያለውን ሀብት በሰላም መልሶ እንደገና እንዲደለደል ይፈቅዳል ከሚል እሳቤ የመነጨ ይመስላል።እሺ! እንደተባለው ሆነ እንበል።የወያኔ መሪዎች የሚጠየቁበት እልቆ መስፈርት የሌላቸው በኢትዮጵያ ላይ እንደ አገር የተፈፀሙ ወንጀሎች ጉዳይስ? እንዲሁ በደምሳሳው ይታለፉ? አሁንም እሺ እንደተባለው ወንጀሉ ሁሉ ተትቶ ፕሮፌሰር እንዳሉት  ´´ለወያኔ መሪዎች መኖርያ እና ጡረታ መብት ተሰጣቸው´´ እንበል።ይህ ለመጪው ትውልድ  ምን ያስተምራል? ነገ ማንም በጎሰኝነት ተነስቶ የፈለገውን ያህል ዘርፎ እና አገር አጠራምሶ ጡረታ እና መኖርያ እየሰጠን እናኑረው ? ወይንስ በትክክለኛ ዳኝነት በነፃነት እና ምንም አይነት የሰብአዊ መብቱ ሳይጣስ ለፍርድ ቀርቦ ክፍት በሆነ ችሎት እንስማ እና የህሊና ዳኝነት  ወስደን የታመመውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁስል እናድን? የመፍትሄ ሃሳቡ በእራሱ አልገባኝም። ያጠፋ ሰው ገና ለፍርድ ቀርቦ ጉዳዩ ሳይታይ የጡረታ እና ድጎማ መቁረጥ ላይ ከሄድን ፍትሃዊነትን እንደናፈቅን ሌላ ክ/ዘመን ልንዘልቅ አይደለም ወይ?

በሌላ በኩል የትግራይ ልማትን ከቀሪው ኢትዮጵያ ጋር በእኩል ድርድር የቀርቡበት መንገድ ግልፅ አይደለም።የመጪዋ ኢትዮጵያ ናፍቆታችን እኩልነት የሚያስተዳድረን መንግስት የማግኘት ነው እንጂ አሁንም የኢትዮጵያ ሌሎች ክልሎችን ከትግራይ ጋር እየመዘነ  የሚያስቀምጥ መንግስት አይደለም።ለምሳሌ ተጣርቶ ከተገኘው ሀብት ሲደለደል ለትግራይ ልማት፣ብሎ ለተቀረው የኢትዮጵያ ክልል ልማት የሚለው አገላለፅ በእራሱ ግልፅ አይደለም። ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ነች።ኢትዮጵያዊነት በትግራይ ይገለፃል።ትጋራይነትም በኢትዮጵያ ይገልፃል ካልን ለምንድነው የኢትዮጵያ ሀብት እኩል ለጋምቤላውም  ሆነ ለሱማሌው ስናከፋፍል የትግራይንም በተርታ አስቀምጠን በነባራዊ ሁኔታ የማናየው? በመጪው ምክር ቤትም የትግራይ ልማት በእራሱ አንድ አጀንዳ ሆኖ ከኢትዮጵያ በተዘረፈው ንብረት  ቅድምያ ተቀምጦ የተቀረው በሚል ስማቸው ያልተጠቀሱ የኢትዮጵያ ክልሎች ተብለው መቀመጣቸው እራሱ ምቾት ይሰጣል ወይ? ይህንን አካሄድ እራሱ የትግራይን ሕዝብ ወደነበረበት የተሳሳተ የአስተሳሰብ ጥግ የሚገፋ አይደለም ወይ? ደግሞስ ላለፉት 25 ዓመታት በትግራይ የተሰራው ልማት ትግራይ ለማዕከላዊ መንግስት ባስገባችው የቀረጥ ልክ ነው እንዴ? ብሎ ሂሳብ ውስጥ የሚገባ ቢነሳ መልሱ ምን ይሆናልና ነው በመጪው ምክር ቤትም ላይ የትግራይ ልማት የኢትዮጵያ የብቻ እና ዋናው ጉዳይ ሆኖ ከሌላው ቀሪ የኢትዮጵያ ሕዝብ ልማት ጋር እኩል ሚዛን የሚቀመጠው።እዚህ ጋር እኩል ሚዛን ስል በተናጥል እንጂ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ልማት ተመጣጣኝ የሀብት ድልድል መኖር የለበትም እያልኩ አይደለም።ሚዛኑ ግን  አልገባኝም።

3/ የትግራይ ሕዝብ ከሕወሓት ወይንም ከኢትዮጵያዊነት አንዱን ይምረጥ።ኢትዮጵያዊነቱን ቢመርጥ ይሻለዋል።

ይህ ጥሩ ሃሳብ ነው።እንዲያውም የእዚህ አይነቱ ሥራ እና ምክር ላለፉት አስር ዓመታት በደንብ ተደርጎ በተለይ ለትግራይ ሀገር ወዳድ  እና ወያኔ ወለድ ምሁራን መነገር ነበረበት።ዛሬ ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ እጅ እና እግሩን በጥቅም እና ሌላው ኢትዮጵያዊ ሊያጠፋህ ነው የሚል የማስደንበርያ  ንግግር ግራ ሳይጋባ ቢሆን ባማረ ነበር። አሁንም ግን ይህ መነገር ያለበት በኢትዮጵያዊነቱ አምኖ ነገር ግን በማንነቴ በሕወሓት ተረገጥኩ ለሚለው ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን ለእራሱ ህወሃት ሕልውናዬ ነው በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ለሚባዝነው  የትግራይ ሕዝብ ነው። እዚህ ላይ ፕሮፌሰር ያስቀመጡት አማራጭ ልብ ላለው በጣም ትክክለኛ ይመስለኛል።ኢትዮጵያዊ ነትን በማፅናት እና የትግራይ ብሔርተኝነትን በትዕቢት በማቀንቀን መካከል ያለው ትርፍ እና ኪሳራ በትትክል ተቀምጧል። ፕሮፌሰር የትግራይ ሕዝብ ያለውን ሁለት ምርጫዎች ሲያስቀምጡ እንዲህ ብለዋል - 

ምርጫ አንድ፡ የትግራይ ሕዝብ እንደጥንቱ እንደጠዋቱ ታሪኩን ይዞ በኢትዮጵያዊነቱ ይቀጥላል፤ በኢትዮጵያዊነት ታሪኩ በግምባር-ቀደም ተሰልፎ በፖሊቲካም ሆነ በመንፈሳዊ ጸጋው የኢትዮጵያዊነት ግዴታውን ይወጣል፤ ይህ ምርጫ የኢትዮጵያዊነት ግዴታ ነው፤ ይህ ምርጫ ታሪካዊ ግዴታ ነው፤ ይህ ምርጫ የዜግነት ግዴታን ከጎሣ ግዴታ ማስቀደም ነው፤ ይህ ምርጫ ከጨለማው ዘመን ወጥቶ ወደሃያ አንደኛው ምዕተ-ዓመት መሸጋገር ነው፤ ከሁሉም በላይ ይህ ምርጫ የሰፊ ሀብት ባለቤትና የመቶ ሚልዮን ዜጎች ማኅበረሰብ አባል ያደርጋል፡፡
ኢትዮጵያ የትግራይ ነች፤ ስለዚህም ትግራይ ኢትዮጵያን ነች፤ ሁለቱ አይለያዩም፤ ይህንን ወያኔም በሚገባ የተረዳው ይመስላል፤ አለዚያ ከጎንደር፣ ከላስታም፣ ከራያም፣ ከጎንደርም … የሚለቃቅመው ለምንድን ነው!

ምርጫ ሁለት፡ የትግራይ ሕዝብ የወያኔ መሣሪያ እንደሆነ ይቀጥላል፤ ይህ ሲሆን ትግራይ በመሠረቱ ከኢትዮጵያ ይገነጠላል ማለት ነው፤ በትግራይ ዙሪያ ኤርትራ በሰሜን፣ በደቡብ ደግሞ ጎንደር፣ ወሎና አፋር ይገኛሉ፤ ወያኔ ሆን ብሎ ትግራይን ከኤርትራ፣ ከጎንደር፣ ከወሎና ከአፋር ጋር አጋጭቶ ደም እንዲቃቡ አድርጓል፤ (በትግራይ ዙሪያ ያሉትን ብቻ ለማንሳት ነው እንጂ ከጂጂጋ እስከጋምቤላ፣ ከወሎ እሰከሲዳሞ ቦረና የግፍ ጠባሳዎች አሉ፤) ስለዚህም ትግራይ በወያኔ ስር ሆኖ ከአነዚህ ከከበቡትና በጠላትነት ከተፋጠጡት ሕዝቦች ጋር ዘለዓለም ሲቆራቆዝ ሊኖር ነው፤ ዙሪያውን ካሉት ሕዝቦች ሁሉ ጋር መቆራቆዝ የትግራይን ሕዝብ ያደኸያል፤ የትግራይ ሕዝብ መሸሻ ስለሌለው በአጥንቱ እየሄደ የወያኔ አገልጋይ ይሆናል፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ በምሥራቅ በአሰብ በኩል፣ በምዕራብ በጎንደር በኩል የልማትና የጋራ ደኅንነታቸውን ይመራሉ፤

ባጠቃላይ ፕሮፌሰር ያቀረቡት ሃሳብ ከብዙ አስተሳሰቦች አንፃር አንዳንድ አከራካሪ ነጥቦች ቢኖሩበትም ለትግራይ ሕዝብ ምናልባት የኢትዮጵያን የነፃነት እና የእኩልነት ጥያቄ  ላይ ከምሩ ማሰብ እና ሕወሓት አይኑን አስሮ ወደሚመራው ገደል መግባት እንደሌለበት የሚያሳየው ሌላው ትልቅ የደውል ማንቂያ ነው። የትግራይ ሕዝብ በሆይ ሆይታ በታጠቀው መሳርያ የትቢት ፕሮፓጋንዳ የሚነዙለት ሕወሐቶች የስልጣን ወንበራቸው ሲያጋድል  እንዴት ጥለውት እንደሚሄዱ እና የሚቀረው ነገር ከቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ያጋጩት ቁርሾ ብቻ እንደሚሆን ማወቅ አለበት። ዛሬ ወንበር ላይ ተቀምጠው የምናያቸው እነ አባይ ፀሐዬ፣ አባይ ወልዱ ሳምሶናይታቸውን ይዘው ትተውት እንደሚሄዱ የትግራይ ሕዝብ ካላመነ ከታሪክ አልተማረም ማለት ነው። ኮ/ል መንግሥቱም አገር ትተው ይሄዳሉ ብሎ የሚያምን የቀድሞ ሰራዊት አባልም ሆነ ኢትዮጵያዊ አልነበረም። ግን ሆኗል።በመሆኑም የትግራይ ሕዝብ ፕሮፌሰር የጠቀሱትን ምርጫ አንድ ማለትም ኢትዮጵያዊነትን ተቀብሎ  በኢትዮጵያዊነት ታሪኩ በግምባር-ቀደም ተሰልፎ በፖሊቲካም ሆነ በመንፈሳዊ ጸጋው የኢትዮጵያዊነት ግዴታውን መወጣት የወቅቱ ጥያቄ ነው።እዚህ ላይ ግን የትግራይ ሕዝብ አለመሳተፍ የትግሉን ዋጋ ያንረው እንደሆነ እንጂ  በማንኛውም ወጪ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነቱን ይቀዳጃል።ይህ እንደማይቀር ህዝቡ የቆረጠበት ደረጃ በእራሱ አመላካች ነው። የናዚዎች ፈቃደኝነት የዓለምን ሕዝብ ለነፃነት እንዳላበቃው ሁሉ የጥቂት ሕውሐት አመራሮች እና አቀንቃኞቻቸው ፍቃደኛ አለመሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ በነጻነቱ ድል ከማድረግ አያግደውም።


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...