ስደተኛ መሆን ምን ማለት ነው?
ስደተኝነት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ላለፉት አርባ አመታት ልብሳችን አድርገነው የኖርነው ክፉ ዕጣችን ነው። አንድ ሰው ከአገሩ የሚሰደደው በሚደርስበት የመንግስት ወይንም የሌላ አካል ጥቃት ሳቢያ ሊሆን ይችላል።በኢትዮጵያ በተለይ በአማራ እና የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ላለፉት 25 ዓመታት ስደት ማለት ከአገር ውጭ ብቻ ሳይሆን እዚያው በአገራቸው እና በገዛ መሬታቸው ሲሆን ተመልክተናል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በጎንደር እና ጎጃም በተነሳው ሕዝባዊ አመፅ ሳብያ የስርዓቱ አገልጋይ ሆነው ይልቁንም በሕዝብ ላይ ግፍ የፈፀሙት ላይ በተለየ ጥቃት መፈፀሙ ተነግሯል።ይሄውም በጎሳ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን አማራም ሆነ ቤንሻንጉል እያለ ሳይለይ በኢህአዴግ ጋር ባላቸው ተሳትፎ እና በሕዝብ ላይ ባደረሱት በደል መጠን ከህዝብ ጋር አይጥ እና ድመት ´የሆኑ ባለስልጣናት ንብረት ላይ አደጋ መድረሱ ተሰምቷል።በጎሳ ላይ የተመሰረተ ጥቃት ግን አልተፈፀመም።ለእዚህ አብነት የሚሆነው የወልቃይት ኮሚቴ አባል አንድ ወቅት የተናገሩት ነው።እንዲህ ነበር ያሉት
´´ጎንደር ቀበሌ 18 ያለውን ፎቅ የሚያህል የለም ባለቤቱ የትግራይ ሰው ናቸው።እርሳቸው ለፍተው ጥረው ነው ያገኙት አንድ የነካባቸው ሰው የለም።እኔ እራሴ የወልቃይት ኮሚቴ አባል ነኝ አያቴ ትግራይ ናቸው።ይህንን ወሬ የሚያወራው እራሱ ወያኔ ነው።ሕዝብ ማጣላት ልማዳቸው ነው´´ ነበር ያሉት።
ይህ ብቻ አይደለም ጉዳዩን ያጣራው የክልሉ ቃል አቀባይም ምንም አይነት ዘርን እና ቋንቋን ያማከለ ጥቃት አለመፈፀሙን እና በጎንደር ከተደረሰው አደጋ ከ80% ያማያንሰው በእራሱ በክልሉ ተወላጅ ላይ የደረሰ መሆኑን ለአሜሪካ ራድዮ በሰጠው መግለጫ ገልጧል።
በጎንደር ዩንቨርስቲ የሚማሩ የትግራይ ተወላጆችን ማን በግድ ጠራቸው?
ህወሓት ግን የትግራይ ተወላጆችን ማስደንበር ቀጥላለች ለእዚህም ማስረጃ የሚሆነው የጎንደር ዩንቨርስቲ የሚማሩ የትግራይ ተወላጆችን በድንገት ዩንቨርስቲውን ለቀው እንዲወጡ በሚስጥር በመንገር እና ልዩ ትራንስፖርት በመመደብ እንዲሄዱ ያደረገችው ሥራ ነው። ተማሪዎቹ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ሲነገራቸው በሚስጥር ከመሆኑም በላይ የዩንቨርስቲ መልቀቅያ ሳይወስዱ በቀጥታ ትግራይ እንዲገቡ እና ትምህርት እንዲቀጥሉ ነው የተደረገው።ይህ በእራሱ ለተማሪዎቹም ግራ ያጋባ እና ለምን ትሄዳላችሁ ሲባሉ ´´እኛ ምን እናድርግ ኑ ተብለን ነው ´´ የሚል ምላሽ ሲሰጡ ለእራሳቸውም እየገረማቸው ነበር።ምክንያቱም የዩንቨርስቲው ማኅበረሰብ በእራሱ ምንም አይነት ችግር የሌለበት ይልቁንም የእራሱ የሆነ ልዩ የአብሮነት መንፈስ ያዳበረ ግቢ ነውና ምንም የሚያሰጋቸው ጉዳይ የለም።በእዚህ ጉዳይ የጎንደርም ሆነ የመቀሌ ሕዝብ አይታማም።የሁለቱም ከተሞች ሕዝብ እንግዳ እግር አጥቦ ያለውን አብልቶ የእራሱን አልብሶ የሚያሳድር እንጂ እንደ አራሙቻ የህወሓት ካድሬ ነገር ሲያጠነጥን የሚኖር ሕዝብ አደለም።ህወሓት ግን ወጣቶቹን በለጋ አእምሯቸው ልክ ትልቅ ችግር እንደተፈጠረ ወደ ትግራይ እንዲመጡ ልዩ ትዛዝ አስተላለፈ።
በመቀጠል በመተማ ሕዝብ ላይ ከትናትን በስትያ ጥቃት ለመፈፀም ሲዘጋጅ በመጀመርያ ያደረገው ነገር ቢኖር የትግራይ ተወላጆችን ማስደንበር ነበር።ህወሓት ቀድሞ ሲቪሉን ሕዝብ ለመፍጀት ስላሰበ እና ጅምላ ጨራሽ ሂደቱን በሚስጥር በተደረገ ስብስባ ስለወሰነ ትግርኛ ስለተናገሩ ብቻ ከውልደታቸው ጀምሮ የሚያውቁትን መተማን ለቀው እንዲወጡ በመዋቅሩ አደረገ።በነገራችን ላይ በመተማ እና በጎንደር ትግርኛ ተናጋሪዎች ህወሓት እራሷ ገና በረሃ ሳትገባ የተወለዱ የተከበሩ የአገር ሽማግሌዎች የሚኖሩባቸው ቦታዎች ናቸው። ይህ ብቻ አይደለም ትግርኛ ተናጋሪ የኤርትራ ተወላጆችም አሁንም በፍቅር የሚኖሩባቸው ከተሞች ናቸው። ከእዚህ በላቀ ቁጥር ደግሞ ባህርዳር ከተማ ከአነስተኛ ንግድ እስከ ከፍተኛ ሆቴሎች ድረስ አሁንም ትግርኛ ተናጋሪዎች ከሕዝቡ ጋር ተከባብረው የሚኖሩባት ሌላዋ ከተማ ነች። ነገር ግን ሕዝብ እንደ ሕዝብ አልተባረረባቸውም።
የሰሜን ጎንደሩ የተለየ ጉዳይ
ከእዚህ ሁሉ በተለየ የህዝብ መገፋፋት የታየው በሰሜን ጎንደር ሁመራ እና ወልቃይት ነው።እነኝህ ከተሞች ላይ ከጥንት ጀምሮ ትግርኛ ተናጋሪ እና አማርኛ ተናጋሪው ተከባብሮ የኖረበት ይልቁንም የሰሊጥ ምርት ሲደርስ ከደቡብ ኢትዮጵያ ጭምር ለሰልሊጥ ምርት ለቀማ የሚሄዱበት እና የአዝመራ ጊዜው ሲያልፍ ሕዝብ ወደቦታው የምመለስባቸው ቦታዎች ናቸው።ህወሓት በረሃ እያለችም የምዕራባዊው ትግራይ ሕዝብ የሽሬ ከተማን ጨምሮ ህወሓት ´´አማራ ጠላታችን´´እያለች ስታወራ የትግራይ ሕዝብ በስብሰባ ´´ከጎንደር ሕዝብ ጋር አታጣሉን እናንተ ካድሬዎች ዛሬ ለፍልፋቹ ወደ ጉረኗቹ ትመለሳላችሁ እኛ ቅዳሜ ገበያችን ጎንደር ሐሙሲት ነው።በፍቅር እንደኖርን ተዉን ´´ ማለቱን አሁን ድረስ የአካባቢው ሰው ደጋግሞ የሚያነሳው ወግ ነው።
ይህ የሰሜን ጎንደር አካባቢን ግን ህወሓት የአዝመራ ወቅት ብቻ የመጡ የነበሩ ገበሬዎች ሳይሆኑ ከህወሓት የተቀነሱ ወታደሮች እና ከምዕራብ ትግራይ መሬታቸው የተራቆተባቸው ገበሬዎችን ወደ ሁመራ እና ወልቃይት እየወሰደ ማስፈር ሲጀምር እና ነባር ነዋሪው ግን አገሩን መልቀቁ የግጭቶች መነሻ ሆን።ስለሆነም የወልቃይት ግጭት ሲነሳ እነኝህ ከሰፈሩ ብዙ አመታት ያላስቆተሩ ገበሬዎች በእራሳቸው ስጋት አካባቢውን እየለቀቁ መሄዳቸው ተሰምቷል። ይህ ትግግል ነው ማለት አይደለም። ለችግሩ ግን ዋነኛ መነሻ የህዝቡ ተግባብቶ የመኖር አቅም ማጣት ሳይሆን ህወሓት በነባራዊው የህዝቡ የጋራ አኗኗር ስርዓት ውስጥ ታልቃ በመግባት ፖለቲካዊ ቃና ስለፈጠረችበት ነው። ምክንያቱም ህዝቡ ግጭት ቢፈጠር እንዴት በሽማግሌ እና በሃይማኖታዊ መንገድ እንዴት እንደሚፈታ ያውቅበታል።
ባጠቃላይ ህወሓት በትግራይ ሕዝብ ላይ ቁማር መጫወቷን ማቆም አለባት።የትግራይ ህዝብም ይህንን ቁማር ቀድሞ ተረድቶ ያልተፈጠረ ነገር እያራገቡ ለዘለቄታ የህዝቡ ጥቅም ላይ የምቀልዱትን ካድሬዎች በቃችሁ ሊላቸው ይገባል።አሁንም በጎንደር፣ባባህርዳር፣በመተማ፣ደባርቅ በርካታ የትግርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን የህወሓትን ማስደንበር አጣጥለው በማህበራዊ፣ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶች ከተሳሰሩት ሕዝብ ጋር አብረው እየኖሩ ነው። ህወሓት ዘለቄታው ውርደት ወደሆነው የውርደት ገደል ለሚከታት ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ በቆሙ ካድሬዎች ሕዝቡን ማስደንበሯን ቀጥላለች።ዛሬ በማኅበራዊ ድረ ገፅ ላይ የምናየው ድራማም የእዚሁ የህወሓት የማስደንበር አካል ነው።ይህ ማለት ግን አንዳንድ በስሜታዊነት እየተገፉ ህዝብን የሚጎዳ ሥራ የሚሰሩ ይጠፋሉ ማለት አይደለም።እነርሱን ግን በሽማግሌ እያስመከሩ ሕዝብ ዘለቄታውን ከህወሓት ውድቀት በኃላ የምትኖረውን ኢትዮጵያ አሻግሮ መመልከት አለበት።መንግስት በከፋፋይነት የቆመባት አገር ሆነን እስካሁን ሕዝብ እንደ ሕዝብ አለመጫረሱ አገሩ ኢትዮጵያ ስለሆነ ነው እንጂ እንደ ህወሓት መርዛማ ሥራ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ተባልተን ባለቅን ነበር።
ህወሓት ሕዝብ ለመከፋፈል ቢሮ ከፍቶ ባለሙያ ቀጥሮ የሚሰራ የእኩይ እኩይ የሆነ መንግስት ነው።ስለሆነም የትግራይ ሕዝብ በህወሓት የማስደንበር ወጥመድ ሳትገባ እራሱ ህወሓትን በመቃወም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አጋርነትህን ማሳየት የወቅቱ ጥያቄ ነው። ደግሞስ በአንዳንድ ቦታዎች ጎረቤት ከጎረቤት በጎሳ ምክንያት ግጭት ቢነሳ ማነው መወቀስ ያለበት።የኢትዮጵያ ሕዝብ የእዚህ አይነት ጠባይ ነበረው? የትግራይ ህዝብስ በፓርላማ ደረጃ የጎሳ ፖለቲካ በማወጅ ሕዝብ ከህዝብ የለያየውን ህወሓትን መታገል እና መውቀስ ነው ያለበት ወይንስ የጎሳ አባት የሆነውን ህወሓትን እሹሩሩ ማለት አለበት? የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የሚኖር የጋራ አብሮነት ጥቅም ይበልጣል? ወይንስ ነገ ብል የሚበላው የህወሓት የዛገ ታንክ ነው የሚበልጠው? በደንብ መታሰብ ያለበት ጉዳይ ነው።
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
No comments:
Post a Comment