ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, September 7, 2016

የህወሓት አባላት እና ደጋፊዎች አምስቱ ግለሰባዊ እና ተቋማዊ ጠባዮችህወሓት በትግል ወቅት ለእርዳታ የመጣውን እህል በጎን ስትሸጥ የሚያሳይ (ፎቶ ቢቢሲ 


መነሻ 

በእዚህ ፅሁፍ ውስጥ የህወሓት አባላት እና ደጋፊዎች ማለት እራሱን የሕዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ ብሎ የሚጠራው ድርጅት አባላት እና ደጋፊዎች ማለትም እራሳቸውን በግልፅ እና ስውር አባልነት የሚንቀሳቀሱ፣በተለያየ ጥቅሞች ሕልውናቸው ከድርጅቱ ጋር የተሳሰረ እንደሆነ የሚያምኑትን ሁሉ ያጠቃልላል። እዚህ ላይ ´´ህወሓት ማለት የትግራይ ሕዝብ ነው የትግራይ ሕዝብ ማለት ህወሓት ነው´´ የሚለውን የሳሞራ የኑስ ንግግር ተከትለው የሚያስቡ ካሉ ቢያንስ እኔ በአሁኑ ሰዓት እዚህ ድምዳሜ ላይ ስላልደረስኩ የሳሞራ እና አድናቂዎቻቸው ሃሳብ ሆና ትቆይ። በእዚህ መንገድ የሚያስቡ የማሰብ መብታቸውን እያከበርኩ ጊዜ የሚፈታው ስለሆነ በእሱ ላይ ጊዜ መውሰድ አልፈለኩም።ሆኖም ግን ይህ ፅሁፍ እራሳቸውን በቆይታ፣በስልጠና እና ባላቸው ማኅበራዊ ግንኙነቶች ሁሉ የህወሓት አባላት እና ደጋፊዎች የተላበሷቸውን አምስቱ ግለሰባዊ እና ቋማዊ ጠባዮችን  ለመግለፅ እሞክራለሁ።እነኝህ አምስት ጠባዮች ከከፍተኛው እርከን እስከ ታች ያለው ካድሬ ድረስ በመጠን እየተለያዩ የሚንፀባረቁ ናቸው።ሆኖም ግን እያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸውን በንቃት መገንዘብ እና መመልከት ይጠይቃል።

የእዚህ ፅሁፍ አቅራቢ እነኝህን ፀባዮች እንዲሁ በግምት የሚያቀርባቸው ሳይሆኑ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ ባለበት ጊዜ በሥራም ሆነ በማኅበራዊ እና ቤተሰባዊ ግንኙነት ሁሉ የተመለከተው ምልከታ ስለሆነ ፅሁፉ በተራ ግምት እና መላ ምት ላይ የተመሰረተ አለመሆኑን መገንዘቡ ተገቢ ነው። 

አምስቱ  ፀባዮች 

1. ድብቅነት 

ህወሓት አባላት፣ደጋፊዎች እና ድርጅቱ እራሱ ሕይወታቸው የተመሰረተው በድብቅነት ላይ ነው።ሀብታቸው፣ የሚሰሩት ሥራ፣ ማንን እንደሚወዱ እና እንደሚጠሉ ሁሉ በግልፅ ለእራሳቸው ሰው ካልሆነ በቀር አይገልጡም።ለምሳሌ አንድ ከእነርሱ ካምፕ ውጭ የሆነ ሰው ምን ያህል ጥሩ እና ምክንያታዊ ቢሆን ስለ ጥሩነቱ እና ምክንያታዊነቱ ከሚከራከሩት ይልቅ ቀድመው በተደበቀ ጥላቻ ውስጥ ሆነው ለሌላ ሰው ግን ጥሩነቱን ይናገራሉ።እዚህ ላይ አንዳንድ ማስረጃዎች ልጥቀስ።አቶ መለስ አቶ አዲሱን በአደባባይ ሲያሞግሱ ትሰማላችሁ።አቶ አዲሱ በአቶ መለስ ሞት ላይ አልቅሰዋል።አቶ መለስ ግን አቶ አዲሱ ከስልጣን የወረዱ ቀን ´´ኢትዮ ፈርስት´´ በአቶ አዲሱ መሰናበት ምን ተሰማዎት? ሲባሉ አቶ መለስ ´´ብዙ ሳይዘባርቅ መውረዱ ´´የሚል ቃል ሳያስቡት ተጠቀሙ (ይህ በዩቱብ መመልከት ይቻላል)። የአቶ መለስ ፈገግ እያሉ መግደል የህወሓቶች የተለመደች የድብቅነት ሕይወት አንዱ መገለጫ ነው። 

ሌላው የድብቅነት መገለጫ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ክስተቶች ውስጥ እራሳቸው ፈፅመው ሌሎች እንዳደረጉት የሚሰሩት ድራማዎች ናቸው።አሁን እየታወቀ መጣ እንጂ በአማራው ሕዝብ በደቡብ ክልሎች መሰደድ፣መገፋት ጉዳይ ሁሉ ከጀርባ የሕግ ድጋፍ ሲሰጡ የነበሩ የህወሓት ሰዎች ናቸው።ይህ የድብቅነት ጠባይ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት አንዱ ማሳያ ደግሞ ከአቶ መለስ በኃላ ውሳኔ ሰጪው አካል ተሰውሮ ውሳኔ እየሰጠ አቶ ኃይለ ማርያምን ከፊት ማስቀደሙ ነው።አሁንም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየተሰሩ ያሉ በርካታ ድብቅ ስራዎች እንደሚኖሩ ካለፉ ታሪኮች መረዳት ይቻላል።

2/ ተንኮል እና ሴረኛነት 

ተንኮል እና ሴራ በህወሓት እና በአባላቱ ዘንድ እንደ ትልቅ ዝና እና ገድል ይቆጠራል።ይመስለናል እንጂ የአቶ መለስ አድናቂዎች ህወሓቶች እና ደጋፊዎቻቸው አቶ መለስን የሚያደንቁበት ዋና ምክንያት እና እነርሱ በአደባባይ ´´ችሎታ´´የሚል ሽፋን ይስጡት እንጂ ብዙ ህወሓቶች እና ደጋፊዎች የሚያደንቁበትን መንገድ ጠጋ ብላችሁ ስትጠይቁ  የሚነግሯችሁ በህወሓት ላይ ያንዣበበው የስልጣን ተግዳሮቶች ሁሉ አቶ መለስ እንዴት በተንኮል እና በሴራ እንደተሻገሩ ሲናገሩ ትሰማላችሁ።ለእዚህም የ1997 ዓም ከቅንጅት ጋር ያደረጉት ድርድር እና ክህደር እንደ ትልቅ ገድል ሲወራ መስማት በህወሓት መንደር መስማት የተለመደ ነው። ስለዚህ ተንኮለኛ እና ሴረኛ የህወሓት አባልም ሆነ ደጋፊ እንደ ትልቅ ዝና ይነገርለታል።በጤናማው ዓለም ግን ይህ የክፉዎች ተግባር ነው።ለእዚህ ነው የሚሰሩትን ተንኮሎች እና ሴራዎች በተመለከትን ቁጥር በማኅበራዊ ሚድያ ሁሉ ሳይቀር በጤነኛ ዓለም አስተሳሰብ እሳቤ እያሰብን ስንብከነከን እንውላለን።ለሕወሐታውያን ግን ይህ ከትልቅ ጀብዱ የሚቆጠር ነው።

እስረኛ ሊያመልጥ ሲል ገደልነው፣እሳት በእስር ቤቱ ውስጥ ተነሳ፣ ታክሲ ውስጥ አሸባሪ ቦንብ አፈነዳ፣ በሀውዜን እና ሐሙሲት ገበያ ላይ አይሮፕላን ደበደበ፣ የኦሮምያ ፕሬዝዳንት አቶ አለማየሁ ኩምሳ አረፉ፣ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ እስር ቤት ለሞት የሚያደርስ ህመም ታመሙ፣ የብሔራዊ ባንክ ወርቅ ተዘረፈ፣ ይቀጥላል በርካታ ጉዳዮች የተንኮል እና የሴረኝነት ውጤቶች ብዙ ናቸው።ህወሃታውያን ደግሞ  በእዚህ ሁሉ ተንኮል ይቁራሩበታል።በግለሰብ ደረጃ ስታገኙአቸውም ተንኮልን እንደ ትልቅ እውቀት ይቆጥሩታል።

ህወሓቶች እና ደጋፊዎቻቸው ተንኮል እና ሴራ ሲሰሩ እየሳቁ ነው እንጂ በተጨማደደ ፊት አይደለም።የአገሬ እና የድርጅቴ ሰው አይደለም ባሉት ላይ ግን ተንኮል ሲያደሩ የሚጀምሩት ከቤተሰብ ነው።የመጀመርያ ኢላማቸው ቤተሰቡን መከፋፈል ነው።የህወሐቶች ሰለባ የሆኑ በርካታ ቤተሰቦች እና ወዳጆች ባላወቁት መንገድ ተቃቅረው ቆይተው ጉዳዩን ሲመረምሩት የወያኔ ሴራ እንደሆነ ይረዱታል።በህወሓት ዘንድ የምትናቅ እና የተንኮል ድር የማይደራባት ትንሽ መርፌ የለችም።በአንድ ድርጅት ውስጥ ከበር ካለው ዘበኛ እስከ የበላይ አለቃ ድረስ ተንኮል ለመሸረብ ደጋፊዎቻቸውን በማሰለፍ ታጥቀው ይነሳሉ።የኢትዮጵያ ቴሌ መስርያቤት፣ የመብራት ኃይል፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ሌሎችም በህወሓት የዘር መርዝ ተወግተው የቆሰሉ እና በርካታ ባላሙያዎችን እየወጉ እና ባላጠፉት ጥፋት እየወነጀሉ ከስራ አባረዋል፣የበይ ተመልካች ሆነዋል።በዘመነ ህወሓት  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ሥራ አስኪያጆች እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንድ ሥራ አስኪያጅ እንዴት ሥራ እንደለቀቁ  ማስታወስ በቂ ነው።የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥራ አስኪያጅ እስከ 1980ዎቹ መጨረሻ እና 90ዎቹ መጀመርያ የነበሩት በእስር እንዲማቅቁ የተደርጉበት እና ሌላው ሥራ አስኪያጅ ጧት በመኖርያ ቤታቸው ሞተው የተገኙበት ሁኔታ እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አስኪያጅ በመሆን ያገለገሉ ግለሰብ እንዴት ስራቸውን እንዲለቁ እንደተደረገ ለአብነት ማንሳቱ የህወሓትን ተንኮል እና ሴራ ግልፅ አድርጎ ያሳያል።

3/ ሰው መሳይ በሸንጎነት 

ህወሓቶች እና ደጋፊዎቻቸው የሚታወቁበት እና የትካኑባት አንዷ መንገድ በሰው ፊት እና በአደባባይ ሰው መስሎ መታየት ነው።ህወሓት በውጭ ዓለም ስሙ በክፉ ሲነሳ የሚያመውን ያህልምንም አያመውም።ግለሰቦቹም እንዲሁ ናቸው።በአደባባይ ስትመለከቷቸው የሃይማኖት ሰዎች፣ወደ እምነት ቦታዎች አዘውትረው በመሄዳቸው ቀድመው የሚታዩ፣ ፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ የክርስቲያንም ሆነ የእስልምና እምነት ዋጋ የሚሰጣቸውን ነገር ሁሉ በመለጠፍ ፍፁም ሃይማኖተኛ ለመምሰል የሚቀድማቸው የለም።በማኅበራዊ ኑሮም ቀድመው ልሙት ባይ ይሆናሉ።ይህ ሁሉ ግን ከሀዘነታ ሳይሆን ከስልት አንፃር ብቻ የሚፈፅሙት መሆኑን ቆይታችሁ ጥረዱታላችሁ።

አንዲት በፈስ ቡክ ገፅ ላይ ነጠላ ለብሳ ወይንም ስትፀልይ የምታዩአት ወይንም የምትመለከቱት የህወሓት አባል ወይንም የተባይ ተጋሪ በገሃዱ ዓለም ላይ ያላቸው እምነት ያስደነግጣል።እነኝሁ ሰዎች በአደባባይ ስለሚሞተው ሕዝብ ስታወሯቸው የሃይማኖታቸውን አማልክት በመጥራት ስለምሞተው እና ስለሚታሰረው ሕዝብ አንዳች ጉዳይ እንደሌላቸው በድፍረት ሲናግሩ አፋቸውን አያደናቅፋቸውም።

4/ ዘረኝነት 

ለህወሓት እና ደጋፊዎቻቸው የእነርሱ መንደር ብቻ የበላይ አድርጎ የሚጠቀሙበት አንድ አባባል አለ። ´´ምንትስ አስር ይውለድ´´ የምትል።በግለሰብ የህወሓት አባላትም ሆኑ ደጋፊዎች ዘንድ ከእነርሱ መንደር ውጭ ላለ ሰው መጀመርያ ሞቅ ያለ ፈገግታ ሲያሳዩ ትመለከታላችሁ።በአጋጣሚ ዘወር ካላችሁ ፊታቸው በጥላቻ ሲገላምጧችሁ ትመለከቱና ፈገግታው የውሸት መሆኑን ትረዳላችሁ። በምንም ደረጃ የሚገኝ ሰውን በሰውነቱ ብቻ መመልከት ክልክል መሆኑ በህወሓት መንደር የተከለከለ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው በጠባዩ፣ በመልካም ስራው፣ በችሎታው ሳይሆን ቀድመው የሚፈርጁት ከእነርሱ ሰፈር በመወለዱ እና ባለመወለዱ ነው። እነርሱ መንደር ከተወለደ እንደ አዋቂ፣ አስተዋይ እና የኢትዮጵያ ጠቃሚ ዜጋ እንደሆነ ያስባሉ ብቻ ሳይሆን ይደመድማሉ።ለምሳሌ አንድ መስርያ ቤት ውስጥ ሄደው ያገኙት ሰራተኛ ከእነርሱ መንደር ካልተወለደ በመስርያ ቤቱ ውስጥ የተቀጠረው የሆነ ተንኮል በህወሓት ላይ ሊሰራ እንጂ በኢትዮጵያዊነት ፍቅር ነው ብለው ላለማመን አይምሯቸውን ዘግተውታል።

የህወሓት እና ደጋፊዎቹ ዘረኝነት የሚገለፀው በተለያየ መንገድ ነው።ከእነዚህ ውስጥ ዋነኛው እና አንዱ የእነርሱ ያልሆነ ያሉትን ማግለል እና አድልዎ መፈፀም ነው።በግለሰብ ደረጃ ያገሏችኃል።በንግድ ድርጅት ደረጃ፣በእምነት ድርጅት ደረጃ፣በማኅበራዊ ግንኙነት ሁሉ ያላቸውን ትስስር የሚፈፅሙት ´´በመንደር ውልደት´´ ከሚመስላቸው ጋር ብቻ ነው።አንድ ሰው የቱንም ያህል መልካም ሰው መሆኑ በጥላቻ እና ማግለል መርዝ ከመነደፍ አያድነውም።ይልቁንም ትውልዱ እየተጠቀሰ ይነቀፋል፣ ሲብስ ደግሞ ከአሸባሪ አይ ኤስ ኤስ ጋር ሁሉ እየተነፃፀረ ይሰደባል። እራሳቸውን የተለዩ ፍጥረቶች አስመስሎ ለማቅረብ መሞከር እና መኮፈስ የሕወሃቶች እና ደጋፊዎቻቸው ዋነኛ መለክያ ነው።     

የህወሓት ዘረኝነት አይን ያወጣ እና እፍረተ ቢስ በሚባል ደረጃ የታየ ነው።የጦር ሰራዊቱን መኮንኖች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ፣የአዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ፣ከፍተኛ የመንግስት ሹሞች እና ቁልፍ ቦታዎችን፣ከፍተኛ የንግድ ስራዎችን፣በውጭ አገራት የሚገኙ ኤምባሲ ሰራተኞች እና አምባሳደሮችን ሲወርድ በአዲስ አበባ በቀበሌ ደረጃ ሊቀመንበሮች እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሻንጣ አውራጅ እና ጫኝ ድረስ ከአንድ አካባቢ የመጡ መሆናቸውን ብቻ መጥቀሱ የጉዳዩ አሳፋሪነት እና አይን አውጣነት በሚገባ ያሳያል።

5/ ስግብግብነት 

ህወሓት እና ደጋፊዎቹ የሚለዩበት አንዱ ፀባይ ስግብግብነት ነው።እነርሱ ያልቀደሱት ቅዳሴ እንደማያርግ፣እነርሱ ሃሳብ ያልሰጡበት የጥናት ወረቀት እንደማይሳካ፣ እነርሱ በሽርክና ያልገቡበት ኩባንያ እንዲፈርስ፣እነርሱን የማያወድስ ፅሁፍ አሸባሪ፣ ለእነርሱ ድርጎ ያልሰጠ ነጋዴ አጭበርባሪ በማለት ሁሉም ቦታ መግባት ይፈልጋሉ። እድር ውስጥ፣ጉልት የምትሸተውን፣የቀን ሰራተኛውን ሌላው ቢቀር እራሳቸው የሾሙትን ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይቀር ከምህዋራቸው የሚወጣ ስለሚመስላቸው ተስገብግበው ሁሉም ላይ ለመታየት ይፈልጋሉ።

በገልሰብ ደረጃ ስትመለክቷቸው እምነት ቤቱ ቀድመው ፃድቃን ለመሆን ከመስተንግዶ እስከ መዝሙሩ፣ ከእርዳታ ሰጪ እስከ ወጥ ቤት ሁሉ ፊታቸውን ማስመታት ስራዬ ብለው ይይዙታል።በተለይ የኅብረተሰቡ የጋራ መገለጫዎች እንደ እድር፣አብያተ ክርስቲያናት፣መስጊዶች፣ የንግድ ማኅበራት፣የሰራተኛ ማኅበራት፣ ሌላው ቀርቶ የቤተሰብ ማኅበራት ውስጥ ሁሉ ምን እንደሚደረግ ለማዳመጥ እንዲገቡ ይደረጋሉ። ህወሓቶች ይህንን የሚያደርጉት ከላይ የተጠቀሱት ድብቅነት፣ተንኮል እና ዘረኘነት ከማኅበረሰቡ መልካም ባህርያት ጋር ፈፅመው የተቃረኑ ስራዎች እንደሆኑ ስለሚያውቁ በከፍተኛ የራስ መተማመን እጦት እና ጥርጣሬ ማዕበል ይመታሉ። ስለሆነም  የታክሲ ሹፌሩም ሆነ ተሳፋሪው፣አስተማሪውም ሆነ ተማሪው፣ ዲያስፖራውም ሆነ የአገር ነዋሪውን ሁሉ ይጠረጥራሉ።ለእዚህ ነው አንድ ኮሽታ በተሰማ ቁጥር በእነርሱ አጠራር ጠላቶቻቸው እስከ ሚኒስቴር ማዕረግ ደረጃ ድረስ እንደ ገቡባቸው በፍርሃት እና በድንጋጤ የሚናገሩት።

ባጠቃላይ ህወሓት እና ደጋፊዎቹ ከላይ የጠቀሱትን አምስት ጠባዮች ሲይዙ በአንድ ቀን እና ምሽት የመጡ ሳይሆኑ ለእራሳቸውም ሳይታወቃቸው ቀስ በቀስ በድርጅታቸው ደረጃ እና በግለሰብ ደረጃ ያደጉ ናቸው።ይህ ግን ለእነርሱ ላይታወቅ ይችላል።ይህ ደግሞ አሁን ያደረሳቸው ደረጃ እራስን ዝቅ አድርጎ ከማየት የመነጨ አጉል ጀብዱ የተቀላቀለበት ፍፁም ጭካኔ ቀድሞ ከነበረው አድጎ እና ገዝፎ ወደ ባሰ ፋሽሽታዊ ደረጃ አሻግሯቸዋል።ለእዚህ ማሳያዎቹ ሰሞኑን በኦሮምያ፣ጎንደር እና ጎጃም የሚፈፀሙት አረመንያዊ ድርጊቶች ናቸው።ግድያዎቹ የፍርሃት፣በእራስ ያለመተማመን እና ከፍርሃትም የሚመነጩ ናቸው። አንዳንዶች ደጋፊዎቻቸው አረመንይያው ድርጊቶችን እንደ ጀግንነት ሲቆጥሩላቸው ይስተዋላል። ይህ ግን ትክክል አስተሳሰብ አይደለም።በእራስ መተማመን ያለው እና አቅም ያለው ድርጅትም ሆነ ግለሰብ የእራሱን ወገን በመፍጀት እርካታ እና ጀግንነት ሊሰማው ባልተገባ ነበር።ለእዚህ አይነቱ የህወሓት ፀባያት መፍትሄው ስርዓቱ እራሱን ጠግኖ ሌላ አውሬ እንዲሆን መፍቀድ በአገርም ሆነ በሕዝብ ላይ እንደመቀለድ ይቆጠራል። ህወሓት እንደ ድርጅት እና ደጋፊዎቹ በርካቶችን እየወጉ ገድለዋል፣በየዋህ ልቦና የቀረቧቸውን በፈገግታ መርዝ እያስላሱ አምክነዋቸዋል። ለእዚህ ማሳያ እንዲሆን አንድ ጉዳይ ብቻ አንስቼ ላብቃ።ሰሞኑን በኢትዮጵያ በህወሓት እና በቀረው ሕዝብ መካከል ያለው ግብግብ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ እና አቶ በረከትን ጨምሮ በጎንደር ሲኒማ አዳራሽ በጠሩት ስብሰባ ዱላ ቀረሽ ንግግር እና እሮሮ በመጨረሻም አዳራሹ በድንጋይ ተደብድቦ ሾልከው አዲስ አበባ መጥተው ሳለ። በሕወሓታዊ ሽሩድ አቀራረብ አቶ አባይ ፀሐዬ፣በረከት ስምዖን፣ዶ/ር ካሱ ኢላላ እና አባ ዱላ አይናቸውን በጨው አጥበው፣የውሸት ፈገግታ እያሳዩ እና እየተቅለሰለሱ ስልጣን አንልቀቅ ግን እንታደስ የሚል አጀንዳ ይዘው በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ብቅ አሉ። ህወሓቶች ማለት እንዲህ ናቸው።ያልተመቻቸው ጊዜ ስያሞግሱ ያሰሙሃል ዘወር ስትል የመውጊያ እና የጥላቻ ጦራቸውን ይስላሉ።ሕዝብ በ1997 ዓም ሆ! ብሎ ሲነሳ እንደራደር ይሉሃል።ጉዳዩ የበረደ ሲመስላቸው ´´ኢህአዴግ ሾላ አይደለም በድንጋይ የሚወርደው´´ይሉሃል። እነአቶ በረከትም ነገረ ህወሓትን በካድሬ አንደበታቸው ሊያነበንቡልህ በኢቲቪ መስኮት ቀለስለስ እያሉ የቀረቡት ለማታለል እንጂ በተመሳሳይ ሰዓት ግድያ እና እስር በንፁሁ ኢትዮጵያዊ ላይ እየተፈፀመ ነው።ህወሓት እና ደጋፊዎቹ በጋራ የምጋሯቸውን ፀባያት ከድርጅት እስከ ግለሰቦች ድረስ በጥንቃቄ መመልከት እና መከላከል የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው።ህወሓትን በሚገባ እወቁት።ደጋፊዎች ጋሻ ጃግረዎችንም ፀባይ ተረዱ።ፈፅሞ ከኢትዮጵያዊነት ባህሪ የተለየ መሆኑን ትረዳላችሁ።     

ጉዳያችን GUDAYACHN

 www.gudayachn.com

No comments: