ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, August 10, 2016

ወይ ባልዘፈንሽ፤ ከዘፈንሽ ባላሳፈርሽ (የፓትርያርኩ መግለጫ) በዲ/ን ኢንጅነር ዓባይነህ ካሴ


በዲ/ን ኢንጅነር ዓባይነህ ካሴ 
ትናንት ነሐሴ ፫ ቀን ፳፻፰ በፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የተሰጠው መግለጫ ከወቅታዊነቱ ይልቅ ወገንተኛነቱ ያየለበት እንደኾነ በገሃድ ይነበባል፡፡ ብዙ ጊዜ አሳፍረውናል አሁንም ያው መንገድ እንደተስማማቸው ያሳያል፡፡ ከአንድ ፓትርያርክ የሚጠበቀው ሰብእና እንደዚህ ባለ አስጨናቂ ጊዜ ከማንም ያልወገነ ማዕከላዊ ሀሳብ ይዞ ግልግል ውስጥ መግባት ነው፡፡ በዚህ መለኪያ ፓትርያርክ ማትያስ የሰጡት መግለጫ ሲመዘን ብዙ የሚነሳ የሚጣል ጉድ አለበት፡፡ ይህንን መለኪያ መከተል ካልቻሉ (በልባቸው ምን እያሰቡ ዝም ሊሉ እንደሚችሉ ብናወቅም) ዝም እንዳሉ ቢቀሩ ይሻለን ነበር፡፡
በአበው ብኂል ወይ ባልዘፈንሽ፣ ከዘፈንሽ ባላሳፈርሽ ይባላል፡፡ የማይችል ሰው ስለማይችል አርፎ መቀመጥ ይገባዋል፡፡ እችላለሁ ካለ ደግሞ ጉዳዩ በሚጠብቀው ደረጃ በቅቶ መገኘት አለበት፡፡ ከሁለቱም ያጣ ኾኖ እችላለሁም ብሎ ዕድሉንም አግኝቶ ባገኘው ዕድል ሳይጠቀም ከቀረ ሮቤላዊነት ይኾናል፡፡ (መቼም ሮቤል በተባለ ወጣት “ዋናተኛ” ሪዮ ኦሎምፒክስ ላይ የብዙ ጀግኖች አትሌቶቻችንን ወርቃማ ታሪክ የሚፃረር አሳፋሪ እና አዋራጅ ድርጊት መፈጸሙን ከቀደመው አብረቅራቂ የኦሎምፒክ ገድላችን በፍጹም ተቃርኖ ያስመዘገብነውን አሳፋሪ ኩነት የማያውቅ የለምና) ለእኔ ሁለቱም አንድ ናቸው፡፡
ለሁለቱም ታሪክ በር ከፍታ መድረክ አመቻችታ ተቀበለቻቸው፡፡ አንችልም ብለው ከመድረኩ መራቅ ሲገባቸው በማይችሉበት መድረክ እንደሚችሉ ኾነው ብቅ አሉ፡፡ ያ መድረክ እጅግ በጣም ቢያንስ ከተዋናዮቹ የሚጠብቀው ሚኒማ አለ፡፡ ከሚኒማው በጥቂቱ መውረድም ብዙ አያሳማም፡፡ አፈጻጸሙ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ከኾነ ግን አዋራጅ ይኾናል፡፡ ከጀርባ ያለው ባንዲራ ነውና፡፡ ውድቀቱ በእነርሱ ብቻ አይቆምም ሀገርንም ያሳፍራል፡፡
የፓትርያርኩ መግለጫ ከወገብ በላይ ታቦት ከወገብ በታች ጣዖት የኾነ ግራ የገባው ኾኖ ይነበባል፡፡ ጸልዩ አስተምሩ የሚሉት እንደታቦት የሚታዩ ናቸውና፡፡ መግለጫ ሰጡ ሲባል መደንገጤ አልቀረም ደግሞ ምን ብለው አዲስ የቤት ሥራ ይሰጡን ይኾን በማለት ከልቤ ተጨንቄ ነበር፡፡ የኾነው እና ያስጨነቀኝ ተገጣጠሙ እናም አሳመመኝ፡፡
በተለይ በተራ ቁጥር ሁለት እና ሦስት ላይ የተቀመጡት ሀሳቦች ምን ማለት እንደፈለጉ ያሳብቅባቸዋል፡፡ 
2. በየአካባቢው የሚገኙ አዛውንቶችና ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና አባወራዎች እንዲሁም እማወራዎች ልጆቻቸውንና የአካባቢው ወጣቶችን በመምከርና በማስተማር የሰው ሕይወትን ከጥፋት፣ የሀገር ሀብትን ከውድመት እንዲታደጉ ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች፤
በዚህ ሀሳብ ውስጥ ገላጋይነት ፈጽሞ ስፍራውን እንደለቀቀ ይታያል፡፡ የሚመከረው አንዱ ወገን ብቻ እንደኾነ ያሳያል፡፡ በእርሳቸው ሀሳብ ሌላ የሚመከር አካል የለም፡፡ ወጣቱ አጥፊ መኾኑን ጠቅሰው ምክር እንደሚያስፈልገውም ጠቁመዋል፡፡ በእርግጥ ቦታቸው ይህ ነበርን? አይደለም፡፡ በመካከል ኾነው ቢያንስ ቢያንስ አንተም ተው አንተም ተው በማለት ቃለ ተግሣጹን ለሁሉም በማዳረስ እኔ ልሸምግል ማለት በተገባቸው ነበር፡፡ ጨርሶ ወደ አንዱ አዘንብሎ ከቀሩ የተነሡበት ዓላማ ወይ አልተሳካም ወይ ከጅምሩ ዓላማቸው ሌላ ነበር፡፡

3. ሁሉም ወገኖች አለን የሚሉትን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ፣በውይይትና በምክክር እንዲሁም በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ በመጓዝ ችግሩን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ያደርጉ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን ታሳስባለች፡፡
በዚህ መግለጫ ውስጥ “ጥያቄ አለን የሚሉት ወገኖች . . . በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ በመጓዝ ችግሩን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ያደርጉ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን ታሳስባለች” ይላሉ፡፡ “ችግሩን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት” የሚለውን ስንመለከተው የተጀመረ ጥረት መኖሩን ያሳያል፡፡ የተጀመረ ጥረት ለመኖሩ ምን ያኽል እርግጠኛ ሊኾኑ ናቸው? ካለስ የቱ? አልነገሩንም፡፡ መንግሥት ጉዳዩ ከውጭ ኃይሎች ጋር የተዳመረ መኾኑን ገልጦ እየተናገረ ነው፡፡ ከየትኞቹ የውጭ ኃይሎች ጋር በዚህም በመንግሥት በኩል ምን የተጀመረ ነገር አለ? ካለ ተስፋ ሰጪ ነውና ቢጠቁሙ ሠናይ በኾነ፡፡ አለበለዚያ አለ ብሎ መናገሩ ግምት ውስጥ ይጥላል፡፡

ሌላው በዚሁ መግለጫ ውስጥ “በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ” የምትለው አባባል ወጣቱን በሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ አልሄድህም ተብላ የምትተረጎም ናት፡፡ ወጣቱ በተባለው መንገድ ሄደ ሲባል ሌላውስ አካል? ነው ወይስ በዘወርዋራው መንግሥት ሕጋዊ ሲኾን ወጣቱ ሕገ ወጥ ነው መባሉ ነው? እንደዚህ ከኾነ ደግሞ አንዱን አጽድቆ ሌላውን መኮነን ስለኾነ ከገላጋይነት ይልቅ ወገንተኝነት አለበት፡፡
ራሱ መግለጫው “በሀገር ውስጥ አለመግባባት ሲፈጠር አንዱን ካንዱ ሳትለይና ሌላውን ሳታገል ሁሉንም በእኩልነትና በልጅነት መንፈስ በማየት ስትመክር፣ ስታስተምርና ስታስማማ የነበረች፣ አሁንም ያለች፣ ለወደፊትም የምትኖር የቁርጥ ቀን እናት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡” በማለት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሚና ደግሞም መለኪያ ሚዛን አስቀምጦ የተነሣ ነው፡፡ ይኸው መሥፈርት ወይም መዳልው ወይም ሚዛን ወይም መለኪያ በሁለቱ ሀሳቦች ውስጥ አለመገኘቱ ግራ ያጋባ፡፡ አንዱን ካንዱ ሳትለይና ሳታገልል ከተባለ እና አሁንም ያንን ታደርጋለች በሚል ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ከሰበከ በኋላ ይህ ሀሳብ ወዴት እንደመነነ ሳይታወቅ አንዱ ወገን ላይ ብቻ ማትኮር ተገቢነት የለውም፡፡ ለዚህም ነው ወይ ባልዘፈንሽ ከዘፈንሽ ባላሳፈርሽ የተባለው፡፡


ምንጭ= ዲ/ን ኢንጅነር ዓባይነህ ካሴ ፌስ ቡክ ገፅ (https://www.facebook.com/abayneh.kassie.5/posts/1003781496407994) 

ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

No comments:

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሃራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሐራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)