ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, August 4, 2016

የጎንደር የበሰለ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ እንቅስቃሴ ህወሃትን ''ከካሮት እና ዱላ'' አንዱን እንዲመርጥ አስገድዶታል ። (የጉዳያችን ማስታወሻ)


አንድ ወቅት አንድ የፖለቲካ ተንታኝ (ስማቸው ይቆየን) ህወሃትን በተመለከተ  ለምንድነው ይህንን ያህል ሕዝብ እየገደለ፣እያሰረ እና እያሰደደ ስልጣን ላይ ለመቆየት የቻለው? ሲሉ ከጠየቁ በኃላ መልሱን ሲመልሱ እንዲህ ማለታቸውን አስታውሳለሁ። 
'' ህወሓት የገጠሙት ተቃዋሚዎች በሙሉ የህወሃትን ተንኮል የሚመጥኑ አይደሉም። ፕሮፌሰር አስራትን ተመልከት።ፕሮፌሰሩ እድሜያቸውን ሙሉ በሽተኛ ሲያድኑ የኖሩ ሰው ናቸው።እንዴት ብለው 17 ዓመት ሙሉ ሰው ሲገድል ከነበረ ህወሓትን የሚመጥን የትግል ስልት እንዴት ይቀይሱ? ሌሎች ተቃዋሚዎችን ተመልከቱ።ግማሾቹ ዳኞች፣የሕግ ሰዎች፣የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ናቸው።እነኝህ ሰዎች ደግሞ ሕግ እና ስርዓት ጠብቀው እንጂ እንደ ህወሓት ሕግን አፈር ድሜ እያስጋጡ አይታገሉም።ስለሆነም ህወሓት የሚመጥነው ተቃዋሚ ያስፈልገዋል።'' ነበር ያሉት።

አሁን ላይ ሆነን ስንመለከት፣የምሁሩን ሃሳብ ማቃለል አይቻልም።ህወሓት ከቅንጅት በፊት ስርዓቱን የተቃወሙ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበርን፣ ነፃውን ሚድያ፣የ1997 ዓም ምርጫ እንቅስቃሴ እና ከእዚያ በኃላ የታሰሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች ተቃውሞ ሁሉ ህወሃትን የሚመጥነው ተቃዋሚ አለማግኘቱን አመላካች ድርጊቶች ሆነው አልፈዋል።ድሮስ ሕግን የሚያውቅ በሕግ ትሞግተዋለህ።እንደ ህወሓት ላላ የሰራውን ሕግ በመደፍጠጥ ለሚታወቅ ስርዓት አብዝቶ ስለ ሕግ በማውራት ህወሓት ኢትዮጵያን በጎሳ ፖለቲካው እንዳይረግጣት ለማድረግ አልተቻለም።በአዲስ አበባ በ1997 ዓም ከ200 በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሲገደሉ፣ጋምቤላ  ላይ ኢትዮጵያውያን መሬታቸውን ሲነጠቁ፣ከ500 በላይ የኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ለምን ተሰለፋችሁ በሚል ብቻ ከገደለ በኃላ ፣በመቶዎች የሚቆጠሩ የሲዳማ ሕዝብ ሲገደል ሁሉ የነፃነት ትግሉ፣የህወሃትን ትዕቢት የተሞላበት ንቀት የሚመጥን ትግል ያለህ እያለ  ነበር።

ካሮት እና ዱላ 

አቶ መለስ ህወሓት አስጨንቆ የሚታገላት እንደሚያስፈልጋት በምፀት መናገራቸው ይታወሳል። የሰላማዊ ትግልን ያናናቁት አቶ መለስ የትጥቅ ትግል የሚፈልግ ካለ ''መንገዱን ጨርቅ ያድርግለት'' የሚል መልክት አስተላልፈው ነበር።መልክቱ ''እኛ በመጣንበት መንገድ ኑ!'' መሆኑ ነው።ከሰሞኑ በጎንደር የተነሳው ተቃውሞ በህወሓት የአገዛዝ ዘመን ፈፅሞ ያልታየ እና በዓይነቱም ልዩ ነው።የወልቃይት ጠገዴ አማራነት የያዘው የአቤቱታ ኮሚቴ ጥያቄውን በአግባቡ እስከ ፈድሬሽን ምክርቤት እና የተለያዩ የመንግስት አካላት በግንባር  ላቀረበው ጥያቄ ከህወሓት የተገኘው ምላሽ በትዕቢት ''ወልቃይት ትግራይ ነው'' የሚል ''ምን ታመጣላችሁ'' ምላሽ ነበር።

የጎንደር ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በአይነቱ ልዩ ነው።ልዩ ያደረገው የህዝቡ ሕብረት ብቻ አይደለም።ደረጃውን የጠበቀ የፖለቲካ አቀራረብ የያዘ መሆኑም ብቻ አይደለም።መላው ኢትዮጵያውያንን ቁስል እና ህመም የዳሰሰ ብቻ ስለሆነም ብቻ አይደለም።እንቅስቃሴው አላማውን የሚያሳካው ካሮት እና ዱላ ለህውሃት በማቅረብም ጭምር ነው።ህወሓት በኃይል ለመጠቀም ሲሞክር ይህ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ዱላ ያቀርባል።ህወሓት ሰላማዊ ለመሆን ሲሞክር ደግሞ ካሮት ያቀርባል።በእዚህም መሰረት ህወሓት ሐምሌ 5 ቀን ኮ/ል ደመቀን ለመያዝ ጦር ሲሰብቅ እንቅስቃሴው ጦር ሰብቆ መጣ።በሐምሌ 24/ 2008 ዓም ከግማሽ ሚልዮን ሕዝብ በላይ በተሳተፈበት ሰልፍ ላይ ህወሓት ሰልፉ አለመፈቀዱን በራድዮ ፋና እና ኢቲቪ ሲያስነገር ዋለ።የጎንደሩ እንቅስቃሴ ግን ካሮት እና ዱላ ይዞ ሰልፉን አካሄደ።በካሮት ሰላማዊ መልኩን አቅርቡ።በዱላው ከኃላ የሚጠብቅ ታጣቂ በማሰለፍ ህወሃትን አስገድዶ ሰልፍ ለማድረግ የቻለ እና በአይነቱ ልዩ ነበር።እንቅስቃሴው በእዚህ አላበቃም ከእሁዱ ሰልፍ በኃላ ሐምሌ 26/2016 ዓም እንቅስቃሴው ለህውሃት ግልፅ ደብዳቤ ፅፏል።የጎንደር እንቅስ ቃሴ ካሮት እና ዱላ አቀራረብ ህወሓትን ከማንቀጥቀጥ አልፎ የስልጣን መሰረቱን አናግቶታል።''በአህያ ቆዳ የተሰራ ቤት፣ፍርስርስ ይላል ጅብ የመጣ እለት'' እንዲሉ በጎጥ ላይ የተመሰረተ የህውሃት ፖለቲካ በቻለው መጠን ሕዝብ በሕዝብ ላይ ለማስነሳት ቢሞክርም ባለመቻሉ የሚይዘው የሚጨብጠው ጠፍቶታል።ህወሓት አሁን የሚመጥነው የትግል ምርጫ ቀርቦለታል።ከካሮት እና ዱላ መምረጥ የህወሓት ምርጫ ነው።




ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...