በሃያ አንደኛው ክ/ዘመን ውስጥ ሆና በ4ኛው ክ/ዘመን አስተሳሰብ ውስጥ ባሉ መሪዎች የምትመራው አዲስ አበባ፣ከተመሰረተች 130 ዓመታት ለመድፈን ቀናት የቀሯት አዲስ አበባ በኢትዮጵያ የቀደመውም ሆነ የወቅቱ ፖለቲካ ትኩሳት ውስጥ እራሷን የቻለች ፍልስፍና ነች።ከሁሉም የአገሪቱ ክፍል በአንድነት ተሰብስቦ የሚኖርባት አዲስ አበባ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ የህወሓት የመከራ ዶፍ ከወረደባቸው የአገራችን ክፍሎች ውስጥ አዲስ አበባ በቀዳሚ ከሚጠቀሱት ውስጥ ነች።አዲስ አበባ ከጋዜጠኛ እስከ ከፍተኛ ምሁር፣ከቀን ሰራተኛ እስከ ለምኖ አዳሪ፣ከትላልቅ ለፍተው ጥረው ሀብት ካፈሩ ቱጃሮች እስከ ጉልት ቸርቻሪ ድረስ በህወሓት እስር፣ግድያ እና እንግልት ያየች ከተማ ነች አዲስ አበባ።
ያስለቀሷት አዲስ አበባ
አዲስ አበባ ከሳቀች ቆይታለች።ምናልባት እኔ በዕድሜዬ አዲስ አበባ ሳቀች የምለው እንደ ከተማ (ሕዝብ ሳቀ አገር ሳቀ ነውና) የሳቀችው የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ እግር ኩአስ ጫወታ ኢትዮጵያ ያሸነፈች ጊዜ ነው ብዬ አስባለሁ።ይህም በደርግ ዘመን መሆኑ ነው።ከእዛ ወዲህ አዲስ አበባ ከሳቀችው ይልቅ ብዙ ጊዜ አልቅሳለች።የአዲስ አበባ እናቶች መንገድ ለመንገድ በልጆቻቸው ስቃይ ለብቻቸው የምያወሩባት ከተማ ሆናለች በህወሓት ዘመን።የአዲስ አበባ ለቅሶ የጀመረው በጧቱ ገና ህወሓት አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ነበር። ከተማዋ የመጡት የአልባንያ ሶሻሊስቶች መሆናቸውን ከማንኛውም የአገሪቱ ክፍል ነዋሪ ቀድማ ያወቀች ነበረች።በመሆኑም ግንቦት 20፣1983 ዓም ህወሓት ያረጁ ሶቭየት ሰራሽ ታንኮቹን በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ እያቅጨለጨለ ሲገባ የአዲስ አበባ ሕዝብ ሆ! ብሎ አልተቀበለም።በሃዘን ከቤቱ ተቀምጦ አሳለፈው እንጂ። የአዲስ አበባ ለቅሶ ህወሓት አዲስ አበባ በገባ በሳምንቱ በለቅሶ ቤት ፍንዳታ ለዓለም ከፍ ብሎ ተሰማ። ምን ይሄ ብቻ የሸጎሌ ፋብሪካ ቃጠሎም ሌላው ሃዘን ነበር። ቀጥሎ አዲስ አበባ ከገጠማት ሃዘን ውስጥ ሌላው በ1997 ዓም ከነበረው ምርጫ ተከትሎ ከ200 በላይ ልጆቿን በህወሓት አጋዚ የጥይት አረር ያጣችው አዲስ አበባ ትልቅ ሃዘን ላይ ወድቃ ነበር።እናቶች ልጆቻቸው እንደወጡ ቀሩ፣ጧት ያዩት ልጅ ምሽት ላይ በጨካኞቹ የህወሓት አጋዚዎች አስከሬን ሆኖ መጣ።አቶ መለስ በለቅሶ ባዘነው ሕዝብ ላይ በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ ብለው ደነፉበት።የሰዓት እላፊ አወጁበት።
አዲስ አበባ ፍልስፍና ነች
በኢትዮጵያ የወቅቱ የፖለቲካ የአስተሳሰብ ዘውጎች ውስጥ የአዲስ አበባ እራሱን የያዘ አንድ እና ልዩ ምናልባትም የብዙውን የኢትዮጵያዊ ሕልም እና ምኞት የያዘ ነው።ይህ ሕልም ኢትዮጵያ መሆን ይገባታል ብሎ የአዲስ አበባ ሕዝብ የሚያልመው የእራሱ ፍልስፍና አለው።ይህ የአዲስ አበባ ፍልስፍና ሰውን በኢትዮጵያዊነቱ የሚለካ ብቸኛ መስፈርት ነው።ፍልስፍናው በህወሓት የተረጨው የጎሳ መርዝ ሊበጣጥሰው ያልቻለው የአዲስ አበባ ፍልስፍና ይሄው የህወሓት ወጣት ልጆችንም ውጦ ያስቀረ እና የማረከ ከመሆን አልፎ ወጣቶቹ በወላጆቻቸው ኃላ ቀርነት በአዲስ አበባ ብሔር አልባ ፍልስፍና መስታወትነት እንዲመለከቱ አደረገ። የቆዩት ህዋታውያን ከጎጥ ፖለቲካ ያፈነገጡ የመሰላቸውን አባሎቻቸውን ''የአዲስ አበባ ውሃ እየቀመሱ'' የምትል አሽሙር ይወረውራሉ።
አዲስ አበባ አንድ ሰው በአማራነት ወይም በጉራጌ አልያም በሱማሌነት የተለየ ክብር ላግኝ ብሎ የተለየ መንገድ ቢያሳይ በአዲስ አበባ ፍልስፍና ይስተካከላል።ሕዝብ በእራሱ የሚያገልበት የማህበራዊ ቅጣት አለው።ከመስመር ወጥቶ በጎሳው ሊኩራራ የሚፈልግ ያለው አማራጭ በቶሎ በአዲስ አበባ የጋራ አገራዊ ኢትዮጵያዊ መስመር መግባት ነው።አዲስ አበባ ጎረቤት ተከራይቶ ሲገባ የት ተወለደ? ከየት መጣ ሳይሆን የሚባለው ጥሩ ሰው ይመስላል፣አይመስልም ነው ጥያቄው።አዲስ አበባ ላይ እንደ ሰው ሆኖ መኖር እንጂ ወላጆቹ ባላስመረጡት ቦታ የት ተወለደ አይደለም ጥያቄው። ለእዚህ ነው የአዲስ አበባ ሕዝብ 25 ዓመት ሙሉ የህወሓት የጎጥ ፖለቲካ ያንገሸገሸው። የአዲስ አበባ ፍልስፍና በእየጊዜው የሚነሳው ጊዝያዊ የጎሳ ስሜቶች አይደሉም።ዘለቂታው እና ዘመን አሻጋሪ ለሆነው ኢትዮጵያዊነት ትዋደቃለች።ኢትዮጵያዊነት ለአዲስ አበባ የኦሮሞው ሞት ሞቴ ነው ማለት ነው።ኢትዮጵያዊነት ማለት ለአዲስ አበባ አማራ በኖረበት አገር ባለስልጣን ተብዬ ሲሰደብ እኔ ልሰደብ ብሎ መነሳት ነው።ኢትዮጵያዊነት ለአዲስ አበባ የሱማሌው፣ጋምቤላው፣ሲዳማው፣አፋሩ ሁሉ ሳይከፋው በገዛ አገሩ በነፃነት የመኖሩ ፋይዳ ነው። አዲስ አበባ ፍልስፍናዋ ዘመን የተሻገረ፣ተሞክሮ ነጥሮ የወጣ ያጎፈረ አብዮተኛ ነኝ ባይ ሁሉ እንደፈለገ በክላሽ የማይቀይረው ጠንካራ ፍልስፍና ነው።
አዲስ አበባ ህወሓት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለፈፀመው ወንጀል መቀጣት አለበት የምትለው ይህንን መሰረታዊ የአገር ፍልስፍና ከኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ እና ክብር ጋር በዓለም አደባባይ ስላዋረደ ነው።አዲስ አበባዎች ፍልስፍናቸውን ይዘው ለኢትዮጵያ በአደባባይ ወጥተው የሚዘምሩበት ቀን ደርሷል።በሕብረታቸው እና በፍቅራቸው ታሪክ የሚሰሩበት ጊዜ ደርሷል።ለዓመታት ያለቀሰች አዲስ አበባ ከመራራ ትግል በኃላ በአደባባዮቿ የጎጥ ፖለቲካን ከትቢያ ላይ ጥላ የምትዘምርበት ቀን እሩቅ አይደለም።
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
No comments:
Post a Comment