4ኛው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች በከፊል
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአንድ በኩል በፓትርያሪኩ እና በሙስና እና ሃይማኖት ቅሰጣ የተሰማሩ ግለሰቦች በሌላ በኩል ሙስናንና የሃይማኖት ቀሳጮችን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ለመንቀል በቆረጡ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ መካከል ያለው ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ በጉዳዩ ላይ ተከታታይ መረጃ የሰጠው ''ሐራ ተዋህዶ'' የተሰኘው ድረ-ገፅ ሰሞኑን በተከታታይ ባወጣው ዘገባ አስታወቀ።
በተለይ ዛሬ ግንቦት 23/2007 ዓም 4ኛው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ባለ 18 ነጥቦች የአቋም መግለጫ በማውጣት መጠናቀቁን እና አቡነ ማትያስን ለማነጋገር በጉባኤው የተወከሉ አባቶች እና ተሳታፊዎች ላይ ፓትሪያርኩ በር መዝጋታቸውን ዘግቧል።በድረ-ገፁ ላይ ከወጡትን ዘገባዎች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል።
- ፓትርያርኩ ጠቅላላ ጉባኤው በላካቸው ብፁዓን አባቶች እና ተሳታፊዎች ላይ በራቸውን ዘጉ
- የፓትርያርኩን ዳተኝነት በማጋለጥ ፍትሕን የሚጠይቁ የዐደባባይ ሰላማዊ ሰልፎች ይካሔዳሉ
- በአማሳኞች እና በተሐድሶ መናፍቃን ላይ የሚደረገው ተጋድሎ በየአጥቢያዎቹ ይቀጣጠላል
- ማስረጃ የተገኘባቸውን አማሳኞች በአገሪቱ ሕግ ለመጠየቅ የባለሞያዎች ቡድን ተቋቁሟል
፬ኛው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ባለ18 ነጥቦች የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፤ ከመግለጫው ነጥቦች ውስጥ የሚከተሉት ይገኛሉ፡-
- በአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ የቀረበው ጥያቄ የኹሉም አህጉረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤያት የጋራ አቋም በመኾኑ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠው ተጠይቋል፤
- የቤተ ክርስቲያን ሀብት እና ንብረት ለግል ጥቅማቸው በማዋል የቤተ ክርስቲያንን አቅም የሚያዳክሙ አማሳኞች ማስረጃ ተጠናቅሮ በአገሪቱ ሕግ መሠረት ለፍርድ እንዲቀርቡ ተጠይቋል፤
- አንዳንድ የገዳማት እና አድባራት ሓላፊዎች ‹‹የተሳሳተ አመክንዮ›› ሳቢያ በሰንበት ት/ቤቶች ላይ እየደረሰ ያለው እስር፣ እንግልት እና ወከባ እንዲቆም ተጠይቋል፤
- የመንግሥት የፍትሕ አካላት ከአጥፊዎች ጋራ በመተባበር የሰንበት ት/ቤት አባላትን ከማሰር እና ከማንገላት እንዲቆጠቡ ይደረግ ዘንድ ተጠይቋል፤
- በቤተ ክርስቲያን ተልእኮ አፈጻጸም ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረ ያለውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ለማጋለጥ ከሀገር አቀፍ አንድነት እስከ አጥቢያ ማስረጃ የማሰባሰቡ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል፤
- ማስረጃ በቀረበባቸው ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲሰጥ እና ውሳኔውንም ተግባራዊ ለማድረግ ኹሉም የቤተ ክርስቲያን አካላት አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ ተጠይቋል፤
- ከ25 በላይ አማሳኝ የአድባራት አለቆች እና ጸሐፊዎች ላይ በቂ ማስረጃዎች ተሰብስበዋል
- የተሐድሶ አራማጅ ሰባክያንን የሚጋብዙ አለቆችና የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች ተለይተዋል
- የደብረ ናዝሬት ቅ/ዮሴፍ፣ የመካነ ሰማዕት ቅ/ቂርቆስ እና ጃቲ ኪዳነ ምሕረት ተጠቅሰዋ
- የሀ/ስብከቱ ሥ/አስኪያጅ የሰንበት ት/ቤቶቹን አመራሮች ‹‹እኔ ራሴ አሳስራችኋለኹ›› አሏቸው
- ‹‹እንቅስቃሴው ይቀጥላል፤ የመላው የአ/አ ሰንበት ት/ቤቶች እና የአንድነቱ የጸና አቋም ነው››
በድረ-ገፁ ላይ ተከታታይ መረጃዎች አሁንም እይተለቀቁ ሲሆን ስለ ጉባኤው ዝርዝር ለማንበብ ይህንን ይጫኑ
ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ግንቦት 24/2007 ዓም (ጁን 1/2015)
No comments:
Post a Comment