ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, May 22, 2015

ሰበር ዜና - ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ''የአርበኞች-ግንቦት 7'' ሊቀ መንበር ሕዝቡ ዳግም እንዳይታለል የምርጫ ካርዱን ቀዶ በመጣል ለለውጥ ያለውን ቁርጠኘነት እንዲያሳይ የሚገልፅ መልዕክት አስተላለፉ።(የጉዳያችን ጡመራ መንደርደርያ ሃሳብ እና የመልዕክታቸው ሙሉ ፅሁፍ ተያይዟል)

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የአርበኞች ግንቦት 7 የአንድነት እና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበር 

የጉዳያችን ጡመራ መንደርደርያ 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዲሞክራሲ አሰራር፣ሕግን እና ስርዓትን ለማክበር ብቃት እና ዝግጁነት ያለው መሆኑን በተደጋጋሚ ቢያሳይም በጠበንጃ ኃይል ስልጣን ላይ የተፈናጠጠው ወያኔ/ኢህአዴግ ዛሬም ሕዝቡን ማሸበሩን ቀጥሏል።የሚቀናቀኗቸውን ተቃዋሚዎች በሙሉ በአሸባሪነት በይፋ ሲኮንን ከመክረሙም በላይ ትናንት ሐሙስ የታየው ክስተት ደግሞ ከምርጫው በኃላ ምን እንደሚደረግ በይበልጥ ግልፅ ሆኗል።ሐሙስ ግንቦት 13/2007 ዓም ስርዓቱ በአዲስ አበባ የሰበሰባቸው የጥቃቅን እና የኮብል ስቶን ሰራተኞች እንዲሁም የስርዓቱ የጥቅም ተጋሪዎችን ሰብስቦ ያሳየው ትዕይንት የጦርነት ትዕይንት ሲሆን ወጣቶች ክላሽ ይዘው ሲገሉ እና ሲሮጡ የሚያሳይ ትዕይንት በአዲስ አበባ ስታድዮም መሃል ሜዳ ላይ ሲተወን ሕዝብ ተመልክቶ አዝኗል።

ይህ የሚያሳየው ምርጫ በዘመነ ወያኔ ፈፅሞ የሰላማዊ የስልጣን መሸጋገርያ እንደማይሆን ነው።ይህንኑ ጉዳይ በዕለቱ ባለ 99.6% የይስሙላ ምክር ቤት ቀርበው የተናገሩት አቶ ኃይለ ማርያም ከምርጫ በኃላ ስለሚሰሩት የቂም ተግባር በግልፅ አስቀምጠዋል።ለእዚህም ማስረጃው ሌላው ቀርቶ ባለፈው ሳምንት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር የተከራከሩትን የመድረኩ ዶ/ር መራራን ''ስርዓቱ በአድልዎ የማይሰራ ቢሆን የጤና ባለሙያው ዶ/ር ቴዎድሮስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ምን ይሰራል?'' የሚለውን የክርክር ሃሳብ ላይ ሳይቀር ስርዓቱ ቂም የያዘ እና ለበቀል እየተዘጋጀ መሆኑን በሚገልፅ መልኩ አቶ ኃይለማርያም ''አንዳንድ ተቃዋሚዎች በምርጫ ክርክሩ ወቅት ባለስልጣናትን መስደብ በመቻላቸው እንዳይኩራሩ'' የሚል  መልዕክት ማስተላለፋቸው ክርክሩን በእራሱ ''በስድብነት'' መመዝገባቸው እና ለበቀል እየተዘጋጁ መሆናቸውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በግልፅ አስታውቀዋል። 

ባለፉት 24 ዓመታት ውስጥ ለምንም ነገር መታመን ያልቻለው በጎጥ ላይ የተመሰረተው ስርዓት ያለፈ የቆሸሸ ታሪኩን ተመልክተን የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ መግለጫ ስናነብ ምን ያህል ትክክለኛ እና ኢትዮጵያውያን ካለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ነፃነታቸውን ለመቀዳጀት መቁረጣቸውን የሚያሳዩበት ታሪካዊ አጋጣሚ በውሸት ምርጫ ላይ ባለመሳተፍ የመጀመርያ እርምጃ መሆን እንዳለበት ህሊናውን የማይደልል ሰው ሁሉ የሚረዳው እውነት ነው። የመልዕክቱን ሙሉ ቃል ከእዚህ በታች ይመልከቱ።ፅሁፉን ከዶ/ር ታደሰ ብሩ ገፅ ላይ የተወሰደ ነው።

=======================================================================
ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር በድርጅታቸው እና በእራሳቸው ስም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተላለፉት መልዕክት 

የተከበራችሁ እናቶቼና አባቶቼ፤ እህቶቼና ወንድሞቼ እንዲሁም ልጆቼ የምትሆኑ ወጣቶች!!
አገራችን የምትገኝበትን አስጨናቂ ሁኔታ ሁላችንም እንረዳለን። የህወሓት/ኢሕአዴግ ፋሽስቶች ቡድን እየገረፈ፣ እያሰረና እየገደለ በካርዳችሁ መርጣችሁ የምርጫ ድግሴን ካላሞቃችሁልኝ እያለ ነው። እንኳንስ ዛሬ ታዛቢ በሌለበት፤ ታዛቢ እያለም እንኳን ወያኔ የሕዝብን ድምጽ በትክክል ቆጥሮ አያውቅም። ወያኔ ለሕዝብ ድምጽ ምንም ደንታ የሌለው የኋላቀር ወሮበሎች ቡድን ነው::
ለስንት አስርት ዓመታት ለወያኔ ባርነት እንገብራለን? ለሀያ አስምስት ዓመታት ተገዛን፣ ተገደልን፣ ተቀጠቀጥን፣ ታሰርን፣ ተሰቃየን፣ ልጆቻችን በአገራቸው ተስፋ ቆርጠው ሲሰደዱ በበረሀ ንዳድ አለቁ፤ በባህር ሰጥመው ቀሩ፤ በባዕዳን አረመኔዎች እንደከብት ታረዱ፤ ቤንዚን ተርከፍክፎባቸው ተቃጠሉ። ሀይማኖታችን ተዋረደ፤ ባህላችን ረከሰ፤ ታሪካችን ተናቀ። በልማት ስም ወልደን ከከበድንበት ተፈናቀልን፤ አገራችን አደገች እያለ ሕዝብ በኑሮ ውድነት ተሰቃየ። በልቶ ማደር ብርቅ ነው። እንደሙጫ የሚያጣብቀንን ማኅበረሰባዊ ትስስር በስልጣን ለመቆየትና ኅብረተሰቡን ለመዝረፍ ሲል ሆን ብሎ እያፈራረሰው ነው:: ይኽ ሁሉ አይበቃንምን? ይኸ ሁሉ አይመረንምን? 
ወላጆቼ፣ እህት ወንድሞቼ!ውርደት ይብቃን። የተረገጥንና የተገደልን አንሶን ፍጹም ማንንም ሊያሞኝ በማይችል የለበጣ ምርጫ ወደን የተረገጥን፤ ፈልገን የተገዛን ለማስመሰል ወያኔ የሚያደርገውን ሩጫ እናክሽፈው:: ከፊታችን ያለውን ምርጫ ባለመሳተፍ ምሬታችንን እንግለጽ። 
ዛሬ በግሌ እና በአርበኞች ግንቦት 7፡ የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ስም ጥሪዬን አቀርባለሁ። በዚህ ምርጫ አትሳተፉ። የምርጫ ካርዳችሁን ቀዳችሁ ጣሉት። እናምርር። ካላመረርን ለውጥ ሊመጣ አይችልም። ይልቅስ ለማይቀረው የመጨረሻው ትግል ራሳችንን እናዘጋጅ::
አርበኞች ግንቦት 7፣ ከትግራይ፣ ከኦሮሞ፣ ከአፋር፣ ከኦጋዴን፣ ከጋምቤላ፣ ከቤሻንጉል ድርጅቶች ጋር ትብብር በመፍጠር የአገር አድን ኃይል በመገንባት ላይ ነው። እኛ ልጆችህ በብሔርም ሆነ በሀይማኖት አንከፋፈልም። ከትግራይ እስከ ኦጋዴን፤ ከአፋር እስከ ጋምቤላ ሁሉንም የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ያካተተ ስብስብ ፈጥረን በኅብረት አገዛዙን እየታገልን ነው። ይህ ትግል ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ ትግል ነው። የትግሉም ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ነው። ክርስቲያን ሙስሊም፤ ወንድ ሴት፤ ወጣት አረጋዊ ሳንል፤ በብሔርም ሆና በቋንቋ ሳንከፋፈል ሁላችንም ይህን አስከፊ ሥርዓት በቃህ እንበለው። 
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ይህንን የውሸት ምርጫ ባለመሳተፍ ለለውጥ ያለህን ዝግጁነት አሳይ! ደግሜ እለዋለሁ - የምርጫ ካርድህን ቅደድ!!!
የጦርና የፓሊስ ሠራዊት አባላት ሆይ!
እናንተ የሕዝብ አካላት ናችሁ። በወገኖቻችሁ ላይ አትተኩሱ። ይልቁንስ አፈሙዛችሁን አገራችንን ለውርደት በዳረገውና በሙስና በተጨማለቀው ዘራፊው የህወሓት አገዛዝ ላይ አዙሩት። ታሪካችሁን ከምታበላሹ፤ ታሪክ ሥሩ። ለራሳችሁ፣ ለቤተሰቦቻችሁ፣ ለልጆቻችሁ እና ለሕዝብ የሚጠቅም አገርና መንግሥት እንዲኖረን የእናንተ የግልም ሆነ የጋራ ተነሳሽነት ወሳኝ ነው። ወያኔ ህዝቡን የሚዘርፈው በእናንተ ትከሻ ላይ ቆሞ እንደሆነ ላንዳፍታም አትርሱት:: እንደመላው ህብረተሰብ እናንተም በነጻነትና በኩራት የምትኖሩበት ሀገር እንደምትሹ አልጠራጠርም:: ስለዚህም ይህን የህወሓት የውሸት ምርጫ ተቃወሙ። ዛሬውኑ ነፃነትና ፍትህ ከጠማው ወገናችሁ ጎን ቁሙ። 
የኢትዮጵያ ወጣቶች፤ ትግላችን እስከ ነፃነት ድረስ ይቀጥላል። ነፃነታችንን በእርግጠኝነት በትግላችን እንቀዳጃለን። የምትወዷት፣ የምትኮሩባት አገር - ኢትዮጵያ - ትኖረናለች። ለዚህ ግን ዛሬ ተደራጅተን፣ ፀንተን መታገል የሁላችንም ኃላፊነት ነው። ዛሬ ሁላችንም በፍላጎትና በመንፈስ የተገናኘን ነንና ሁሉም በያለበት ትግሉን ያጧጡፍ። ውጤቱ ቀድሞ በታወቀው በዚህ ምርጫ አለመሳተፍ ለትግሉ ያለንን ቁርጠኝነት ማሳያ ነውና ለውሸት ምርጫ ያለን የመረረ ተቃውሞ በምርጫው ባለመሳተፍ እናሳይ። 
ነፃ እንወጣለን!
የኢትዮጵያ ሕዝብ የነፃነቱ ባለቤት ይሆናል!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
ብርሃኑ ነጋ
የአርበኞች ግንቦት 7:የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበር
=============================
መልዕክቱን በድምፅ ለመስማት ይህንን ይጫኑ

ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ግንቦት 14/2005 ዓም (ሜይ 22/2015)

No comments: