ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, May 27, 2015

ኢህአዲግ/ወያኔ በዋናውም ሆነ የከተሞች ''ምክርቤት'' ውስጥ አይልም እንጂ ግማሽ ያህል ወንበር ለተቃዋሚዎች ሰጥቻለሁ ቢልም ኢትዮጵያ ውስጥ ለፈጠረው የፖለቲካ ችግር አንዳች መፍትሄ አይሰጥም (የጉዳያችን ማስታወሻ)

Picture source - Pampazuka news (Pan-African voice for freedom and justice) 

አንዳንዶች ላለፉት 24 ዓመታት ኢትዮጵያ አሁን በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት ሳብያ የገባችበትን ውስብስብ ችግር በጥገናዊ ለውጥ የሚስተካከል ይመስላቸዋል።ይህ ግን ፈፅሞ የማይታሰብ ነው።ሌሎች ደግሞ ሁል ጊዜ 100% ከመጠበቅ የመጣ አባዜ ስለያዘን እንጂ ስርዓቱ የተወሰነ የፓርላማ ወንበር ከለቀቀ ቢያንስ ብዙ ነገር ማስተካከል ይቻላል የሚል ''የመለስተኛ ፕሮግራም'' አቀንቃኞች አሉ።ይህ አስተሳሰብ ግን በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ አለ ማለት አይደለም።በሆነ ጥቅም ከስርዓቱ ጋር በተሳሰሩት እና ከወያኔ ውጭ ያለች ኢትዮጵያን ፈርተው ከሚመለከቱ አንዳንድ የዋሃን በቀር የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን ያለበት የፖለቲካ ብስለት ደረጃ ጥሩ የሚባል ይመስለኛል።እርግጥ ነው በኑሮ ውጣ ውረድ፣ልጆቹን ለማሳደግ እና በልቶ ለማደር መታተሩ በራሱ የፈጠሩበት እጅግ ፈታኝ የሆነ መስሎ የማደር እና ነገሮች በጣም ጫፍ እስኪደርሱ የመጠበቅ አዝማምያ አይኖርም ማለት አይቻልም። 

አሁን ግን ትንሽ ማለት የምፈልገው በተሻለ ኑሮ ላይ የሚኖሩ ሀገራቸውን የሚወዱ ግን ደግሞ ወያኔ በኢትዮጵያ ላይ እያደረሰ ያለው፣ያደረሰው እና ወደፊት ያቀደውን ዕቅድ በሚገባ ያልተረዱ፣አልያም ተረድተው ግን የሆነች የቸልታ አይሉት የኑሮዬ አልያም የግል ፕሮግራም እንዳትነካ ብቻ ነገሮች እንዳሉ ቢቀጥሉ የሚፈልጉ፣ ግን ትንሽ የመደለያ የለውጥ እርጥባን ከስርዓቱ ቢወረወር እና ''ይህንን ሕዝብ የሚያስታግስ ነገር ቢኖር'' ብለው  የሚመኙ ሁሉ ነገ ወያኔ/ኢህአዴግ ለተቃዋሚዎች ትንሽ ወንበር በእርጥባንነት ቢወረውር በሀገሪቱ የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ለውጥ ይመጣል ብለው በእየካፌው ለማውራት የተዘጋጁ ናቸው።

ግራም ነፈሰ ቀኝ ግን ወያኔ/ኢህአዴግ በውሸት ጀምሮ በውሸት ባለቀው ምርጫ ተብዬው ግርግር በኃላ ለተቃዋሚዎች ግማሽ የምክር ቤት ወንበር ለቅቅያለሁ ቢልም አንዳች ለውጥ ኢትዮጵያ ላይ አይመጣም።ለምን? 
ይህንን በሚከተሉት ማስረጃ ነጥቦች መግለፅ ይቻላል።

1ኛ/ የተወካዮች ምክር ቤት በመንግስት መዋቅር ውስጥ በስመ 'ሕግ አውጪ' ስም ቢሰጠውም በተግባር ግን የህወሓት ማዕከላዊ ምክር ቤት የወሰነለትን እንዲቀበል እና እንዲያጨበጭብ ብቻ የተፈጠረ አካል ነው።

እዚህ ላይ የሀገር ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር ያደረገችውን ስምምነት ቀድሞ በጉዳዩ ላይ መወያየት፣ማጥናት እና መወሰን ሲገባው አቶ ሃይለማርያም ከተፈራረሙ በኃላ ነው ለምክርቤት የቀረበው።የግብፅ እና የሱዳን ምክር ቤቶች ግን ተወያይተዋል አንቀፅ በአንቀፅ ተመልክተውታል።ይልቁንም ምሁራን በመገናኛ ብዙሃን ሁሉ ሃሳብ ሰጥተውበታል።የኢትዮጵያ ምክርቤት ግን የውሉን ይዘት ለማግኘት የግብፅ ''አልሃራም ኦን ላይን'' ድረ-ገፁ ላይ እስክፅፍ መጠበቅ ነበረበት።ይህ ውል የምክር ቤቱን ጥርስ አልባነት የሚያሳይ ትልቅ ምሳሌ ነው።ምክር ቤት የሚል ስም ለመስጠት የምጎሉት በርካታ ነገሮች እንዳሉ ስለማስብ እዚህ ላይ በእዚህ ደረጃ መጥራቱ ተገቢ እንዳልሆነ እረዳለሁ።

2ኛ/ የምክር ቤቱ ተወካዮች በሀገሪቱ ፖሊሲ ላይ ምንም አይነት ሃሳብ የማመንጨት መብትም አቅምም የላቸውም።

3ኛ/ የምክር ቤቱ ተወካይ አባላት በእራሳቸው ከእስር ቤት ባነሰ ፍርሃት ውስጥ ነው ያሉት።ማንም የወያኔ/ኢህአዴግ ካድሬ ሊነዳቸው ይችላል።

ሌላም ብዙ ብዙ መጥቀስ ይቻላል።ባጭሩ ተቃዋሚ ምክር ቤት መግባቱ የሚያመጣው አንዳች ለውጥ የለም።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ነፃነት፣አጠቃላይ የፖሊሲ እና የፖለቲካ፣ምጣኔ ሀብት እና ወታደራዊ አደረጃጀት እና  መዋቅር ለውጥ ነው።

አንዳንድ ጊዜ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግርን ከእስረኞች መፈታት፣ከምርጫ ሂደት፣ከጋዜጣ ህትመት መፈቀድ እና ሃሳብን ከመግለፅ መብቶች ጋር ብቻ አያይዞ መመልከት እና ይህንን እንደ መጨረሻ ግብ መመልከት በእራሱ አደጋ አለው።ይህ ማለት እነኝህ ቁልፍ ጉዳዮች አያስፈልጉም ማለት አይደለም።ነገር ግን እነኝህ ጉዳዮች ወደ ግብ መድረሻ ስልት ናቸው እንጂ ዋና የኢትዮጵያን ችግር ፈተው የሚጨርሱ አይደሉም።እንበል ነገ ወያኔ/ኢህአዴግ እስረኞችን ሁሉ ቢፈታ፣ጋዜጦች ቢታተሙ ወዘተ በቃ ነገር አለሙ አበቃ ማለት ነው? አይመሰለኝም።ከኢህአዴግ/ወያኔ የሚጠበቀው መሰረታዊ የፖሊሲ ማለትም ከጎሳ ፖለቲካ መውጣት፣የስልጣን ሽግግርን ግልፅ እና ታማኝነት ባለው መንገድ መከወን፣የሀገርን እና የህዝብን ጥቅም ካለምንም ማዳላት ማስጠበቅ፣የምጣኔ ሀብት ድልድሉን እና አደረጃጀቱን ከአንድ ጎሳ እጅ አውጥቶ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል ዕድል መስጠት እና የወታደራዊ መዋቅሩን  አሁንም ከአንድ ጎሳ እጅ አውጥቶ ኢትዮጵያዊ ማድረግ የሚሉት የመጀመርያ ደረጃ እና ካለምንም ቅድመ ሁኔታ መከናወን ያለባቸው ናቸው።

እነኝህ ከላይ የተጠቀሱት ቁልፍ ጥያቄዎች ሳይመለሱ እስረኛ ፈታ፣ጋዜጣ ፈቀደ፣ጥርስ አልባ ለሆነው ምክርቤቱ ሰላሳ ወንበር ፈቀደ ወዘተ ለኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር ላይ ለጊዜው ነገሮችን ያረገቡ ይምሰሉ እንጂ አንዳች የሚፈይዱት ነገር የለም።ስርዓቱን ስንቃወም መሰረታዊ ፖሊሲውን እና ዘረኛ እና አድሏዊ ሂደቱን መቀየር እንዳለበት እያተኮርን እንጂ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ብናተኩር ማናልባት ለስርዓቱ እድሜ ይጠቅም እንደሆነ እንጂ አንዳች አይፈይድም። መሰረታዊው የሕዝብ ጥያቄ የሚመልስ እና የኢትዮጵያን አቅጣጫ  ከአናካሽ የጎሳ አደረጃጀት (ይህም በይምሰል ሳይሆን ዋስትና በሚሰጥ መልኩ) አውጥቶ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማስቀጠል አሁንም ድፍረቱ፣ፍላጎቱም ሆነ እድሉ ያለው በተቃዋሚዎች እጅ ነው።ኢህአዴግ/ወያኔ ምን ያህል ጥገና አደረኩ ቢል የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር ኢምንት ያህል የመቅረፍ አቅሙም ተፈጥሮውም የለውም።በመሆኑም ኢህአዲግ/ወያኔ በዋናውም ሆነ የከተሞች  ''ምክርቤት'' ውስጥ (አይልም እንጂ) ግማሽ ያህል ወንበር ለተቃዋሚዎች ሰጥቻለሁ ቢልም ኢትዮጵያ ውስጥ ለፈጠረው የፖለቲካ ችግር አንዳች መፍትሄ አይሰጥም።

ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ግንቦት 19/2007 ዓም  (ሜይ 27/2015)

No comments: