ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, May 28, 2015

የዛሬ 24 ዓመት ኢህአዴግ አዲስ አበባን ባይቆጣጠር ኖሮ ዛሬ የኢትዮያ እድገት ከብራዚል ጋር ይስተካከል ነበር።(የጉዳያችን ማስታወሻ)


====================================
ደርግ 17 ዓመታት ሙሉ በህወሓት እና ሻብያ የተከፈተውን ጦርነት ሲዋጋ እንደነበር እና ጦርነቱ በቀን ብቻ በሚልዮን የሚቆጠር ብር ያስወጣ ነበር።በመቶሺዎች የሚቆጠር ሰራዊት መግቦ፣ታንክ እና ብረት ለበስ ተሽከርካሪ ነዳጅ 
እና ግዥ ፈፅሞ ማደር በራሱ ከፍተኛ ወጪ ነበር።ይህ ገንዘብ እንዳሁኑ የእርዳታ እና የብድር ገንዘብ ሳይሆን ህዝቡ ለእናት ሀገር እያለ ከሚያዋጣው እንደነበር ይታወቃል።በእርግጥ የሩስያ እርዳታ እና ብድር እንዳለ ሆኖ።

በአንድ ወቅት ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርይም የሰሜኑ ጦርነት ባይኖር በጥቂት አመታት ውስጥ ኢትዮጵያን ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ በባቡር ማገናኘት በተቻለ ነበር።ሲሉ መደመጣቸው ይታወሳል።በተለይ ህወሓት በዋነኛነት ድልድዮች እና መንገዶችን ማፍረስ ስራዬ ብሎ ይዞ ስለነበር እነርሱን ተከታትሎ መጠገን ሌላው ሥራ ነበር።የመከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅት (መኮድ) የተሰኘው ድርጅት አንዱ ስራው ህወሓት ያፈረሰውን 
ድልድይ እና መንገድ መልሶ መጠገን ነበር።

በደርግ የመጨረሻ አመታት ታድያ ኮ/ል መንግስቱ የመንግስታቸውን ቅርፅ ለመቀየር ወስነው ነበር።ቅይጥ ኢኮኖሚ ታወጀ።ሚኒስትሮች በአዲስ መልክ ተሾሙ።ብዙዎቹ በምዕራብ ዓለም የተማሩ ነበሩ።ኢኮኖሚውም ሆነ ፖለቲካው ለቀቅ ያለ መስሎ ነበር።በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ዕድል እንዳላቸው ምህረት እንደሚደረገም ተወራ።ፕሮፌሠር መስፍን ወ/ማርያምን ጨምሮ ሌሎች ምሁራን ከአመታት በኃላ እንደገና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን የማናገር፣በሀገሪቱ መፃኢ ዕድል ላይ የመነጋገር ዕድል አገኙ።

በወቅቱ በተያዘው መልክ የሀገሪቱ ሰላም ቢረጋጋ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ የህወሃትን የጎሳ ፖለቲካ እና የሻብያ ኤርትራን የመገንጠል አጀንዳ እንደመጥላቱ በነበረው ሕብረት ቢቀጥል ኖሮ፣በውጭ ይኖር የነበረው ሕብረተሰብ ወደሀገር ቤት ገብቶ የመስራት፣በሀገር ውስጥ ያለው ካለ ምንም የጎሳ ክፍፍል የመስራት እና ትላልቅ ኩባንያዎችን የመመስረት እድሉ ሰፊ ነበር። ዛሬ ኤፈርት እና ጥቂት ባለ ሀብቶች የሃገሩትን ሀብት ሁሉ እንዲህ ጠቅልለው ሚልዮን ኢትዮጵያውያን በድህነት ውስጥ አይዳክሩም ነበር።

አሁንም በተጀመሩ የሽግግር ሂደት ደርግ ስልጣኑን ቢለቅ እና የሽግግር መንግስት ተመስርቶ ቀጥሎም ወደ እውነተኛ ምርጫ ኢትዮጵያ ሄዳ የእራሷ የሆነ መንግስት ቢኖራት ኖሮ ዛሬ ከ 24 ዓመታት በኃላ ኢትዮጵያ ካለምንም ጥርጥር ብራዚል ከደረሰችበት የእድገት ደረጃ የመድረስ ዕድል ነበራት።እዚህ ላይ ብራዚል ቀደም ብላ በውጭ ኃይሎች የመገዛቷ እና በርካታ የባህል ተቃርኖ ቢኖርም እኛ ካለን የባህል ሀብት ጋር በምጣኔ ሀብት ደረጃ እና በፈጠራ እንዲሁም በአዲስ ቴክኖሎጂ ክህሎት ሁሉ በእጅጉ የምንራመድበት የመነቃቃት አመታት ነበሩ።በእነኝህ 24 አመታት ውስጥ ከተባለው ደረጃ ለመድረስ እንችል እንደነበር እንደማሳያ የምረዳኝን  ኢትዮጵያ ሊኖሯት እና ላይኖሯት የሚችሉት ነገሮች ሁለት ክፍል ከፍዬ ለማሳየት እና እነኝህ ጉዳዮች ማለትም ኢትዮጵያ ሊኖሯት የሚችሉት ነገሮች ምን ያህል ወደፊት እንደሚያራምዱን እና ላይኖሩ የሚችሉት ደግሞ ምን ያህል ወደኃላ እንደወሰዱን ለመመልከት ይረዳናል።እነኝህን ነጥቦች ለመንደርደርያ አነሳሁ እንጂ ጠለቅ ያለ ጥናት ቢደረግ ብዙ ጉዳዮችን ሊያሳየን እንደሚችል መረዳት ይቻላል።

ኢትዮጵያ ባለፉት 24 ዓመታት ውስጥ ሊኖሯት የሚችሉት 

 1/ የባንክ ኢንዱስትሪያችን ቢያንስ በ 5 የአፍሪካ ሁለት የመካከለኛው ምስራቅ እና አንድ አውሮፓ እንዲሁም 3 በአሜሪካ ቅርንጫፍ ከፍተው ግዙፍ የፋይናንስ ተቋም በሆኑ ነበር፣

2/ እነ ጣና በለስ የመስኖ ልማት በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ ሞደል የተባለ ምርቶቹ ከኢትዮጵያ አልፈው ለመላው ዓለም የሚልክ በአውሮፓ የስቶክ ኤክስቸንጅ ገበያ የሚገባ ኩባንያ ይሆን ነበር፣

3/ ኢትዮጵያ ከሻብያ ጋር በኤርትራ ጉዳይ ባትግባባ ቢያንስ በአሰብ ጉዳይ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራድራ ወደቧን ታስከብር ነበር።በሌላ በኩል እንደ ህወሓት በመሃል ሀገር የሚኖሩ ትውልደ ኤርትራውያንን ከሀገር ስለማታስወጣ በሂደት እነኝሁ ትውልደ ኤርትራውያን የኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ መኖር ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ በሆኑ ነበር።እዚህ ላይ በደርግ ዘመን ከፍተኛ ተደማጭ የነበሩ የኤርትራ ቆላው ተወካዮች የነበራቸውን ተሰሚነት ማሰብ ይገባል።እነኝህ ሁሉ በህወሓት ስሳደዱ እና ሲገፉ 24 ዓመታት ተቆጠሩ።

4/ ኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይሏ ጠንካራ ስለነበር በደቡብ ሱዳን ጉዳይም ሆነ የሱማልያ አልሸባብ ፈፅሞ ስጋት ሊሆኑ አይችሉም ይልቁንም በአካባቢው ሃያል ሀገርነቷ እስከ ግብፅ እና መካከለኛው ምስራቅ ድረስ ይናኝ ነበር።የአይኤስ ኤስ ጥቃት መፈፀሙ በተሰማ በ24 ሰዓታት ውስጥ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከደብረ ዘይት ተነስተው የሱዳንን የአየር ክልል ጥሰው በርካታ የአሸባሪው ይዞታዎችን ሊብያ ውስጥ ያጠቁ ነበር።በእዚህም ሌሎች ተቀናቃኝ ሀገሮችን ሊያስደምም ይችል ነበር።

5/ በጦርነት ውስጥ የነበረ ኢኮኖሚ ያንን ያህል የስራ ዕድል ለወጣቱ መፍጠር ከቻለ ከጦርነት በኃላ ላለፉት 24 ዓመታት ውስጥ ቢያንስ ከ አስር ያላነሱ ከባድ የብረት ኢንዱስትሪዎች፣የነዳጅ ማውጣት ሥራ (ሱዳን ባቅሟ ነዳጅ ስታወጣ ኢትዮጵያ በሙስና ያልባለገ መንግስት ቢኖራት ኖሮ እስካሁን የነዳጅ ምርት በጀመረን ነበር)፣ 

6/ በኢትዮጵያ ተጀምረው የነበሩት የመካናይዝድ እርሻ ልማቶች በሰፊ ይስፋፉ ነበር።ኢትዮጵያ ጤፍ በብዛት በማምረት ለዓለም ብቸኛ አምራች እና ላኪ ሀገር ትሆን ነበር።

7/ የበርካታ ሃገራት ትላልቅ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋለ ንዋይ ለማፍሰስ ይጎርፉ ነበር።በተለይ ደርግ የወደቀበት ወቅት የምስራቅ አውሮፓ ሃገራት ገና ከሩስያ ተፅኖ እየወጡ፣በርካታ የአፍሪካ ሀገራትም እየተነቃቁ ስለነበር ከወቅቱ ጋር የሚሄድ የድርጊት መርሃ ግብር እና ከሙስና በተቻለ መጠን የፀዳ መንግስት ስለሚኖር ኩባንያዎቹ ከማንም የአፍሪካ ሃገራት ኢትዮጵያን እንደሚመርጡ ሳይታለም የተፈታ ነበር።ይህም ባለፉት 24 ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ከብራዚል እኩል የምትጠራ ሀገር ትሆን ነበር።

8/ ናዝሬት የተጀመረው የትራክተር መገጣጠምያ ፋብሪካ ምርቱን አሻሽሎ በሌሎች ቦታዎች ማምረት እና የኢትዮጵያን ገበሬ በከፊልም ቢሆን ከበሬ አስተራረስ ዘዴ እንወጣ ነበር።

9/ ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ማሳደጊያ እና መንከባከቢያ ማዕከል ''ሕፃናት አምባ'' በሁሉም ክፍለ ሀገሮች ተመስርቶ እናት አባት የሞቱባቸውን በተለይ ባለፉት 24 ዓመታት ቁጥራቸው በመቶ ሺዎች የሆኑትን ሕፃናት ወደ ማዕከሉ አስገብቶ ኃላፊነት የሚሰማቸው ትውልድ ማፍራት ይቻል ነበር።የማዕከሉም አስተዳደር በባለሥልጣን ደረጃ ተዋቅሮ ኢትዮጵያውያን በወር ከደሞዛቸው እያዋጡ በርካታ እናት አባት ያጡ ሕፃናትን ሕይወት መታደግ ይቻል ነበር።ኢህአዴግ ማዕከሉ የነበሩ ሕፃናትን የደርግ ልጆች ብሎ በምሽት እንዳባረራቸው እና ማዕከሉን አንዴ የካድሬ ማሰልጠኛ ሌላ ጊዜ የግብርና ማሰልጠኛ እያደረገው መሆኑ ይታወቃል።


ኢትዮጵያ ባለፉት 24 ዓመታት ውስጥ ላይኖሯት  (ላይሆንባት) የሚችሉት 

1/ ሀገሪቱ በጫት እንዲህ አትበከልም ነበር።ወጣቶቿ በስፖርት እና በልዩ ልዩ ሙያ ላይ እንጂ የጫት ተገዢ አይሆኑም ነበር፣

2/ ከሶስት መቶ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን እህቶቻችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለግዳጅ ሥራ አይጋዙም ነበር፣

3/ የጣና በለስ ፕሮጀክት አይፈርስም ነበር፣

4/ ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት ሀገር አትሆንም ነበር፣

5/ ኢትዮጵያ በጎሳ የተደራጀ ፓርቲ አይኖራትም ነበር።ሀገሩም በጎሳ የተከፋፈለ አስተዳደር አይኖራትም ነበር።
6/ ኢትዮጵያውያን ጎሳቸው ሳይሆን ኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ በፈለጉት ቦታ ሄደው የመስራት መብት ይኖራቸው ነበር፣

7/ ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም ክብራችን ዝቅ ተደርጎ እንዲታይ አይደረገም ነበር። አንድ ችግር ሲገጥመን ወደ ኤምባሲያችን ሄደን ችግራችንን እንፈታ ነበር፣

8/ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ለሁለት የተከፈሉ አባቶች አስተዳደር አይኖራትም ነበር፣

9/ ከ11 ቢልዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ከሀገር በሕገ ወጥ መንገድ አይወጣም ነበር፣

10/ የብሔራዊ ባንክ በቀትር ፀሐይ ወርቁን ለሌቦች አስረክቦ አርተፍሻል ወርቅ አይቀበልም ነበር፣

11/ የተማረ የሚከበርባት እና ሥራ የምያገኝባት እንጂ ኮብል ስቶን ተራቢ እንዲሆን አይደረገም ነበር፣

12/ የሕፃናት አምባ ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ሕፃናት በምሽት በኢህአዴግ ወታደር አያባረሩም እና ሴቶች ለሴተኛ አዳሪነት ወንዶቹ ለጎዳና ተዳዳሪነት አይዳረጉም ነበር።

13/ ኢትዮጵያ ሕፃናቶቿን በጉዲ ፈቻነት በመሸጥ በአፍሪካ ቀዳሚ አትሆንም ነበር።

ባጠቃለይ ኢትዮጵያ በህወሓት አገዛዝ ስር እሩብ ክ/ዘመን (25 ዓመታት) ሊሞላት አንድ ዓመት ብቻ ቀራት።ሃያ አምስት አመታት በርካታ ሃገራት ወደ መካከለኛ ገብ ደረጃ የደረሱበት ነው።የዛሬ 24 ዓመት አንጎላ ጦርነት ላይ ነበረች።ዛሬ አንጎላ በከፍተኛ እድገት ላይ የምትገኝ ሀገር ነች። የዛሬ 24 ዓመት ቦትስዋና ብዙም የምትደነቅ ሀገር አልነበረችም ዛሬ ቦትስዋና የአልማዝ አምራች ሀገር ነች።የዛሬ 24 ዓመት ጋና ስሟ እምብዛም አይነሳም። ዛሬ ጋና በዲሞክራሲያዊ ምርጫ መንግስት የምትቀይር እና የነዳጅ ሀብት ባለቤት የሆነች ሀገር ነች።ሃያ አራት ዓመት እንደ ኢትዮጵያ ላለ ጠንካራ ሰራተኛ ሕዝብ፣በብዙ ውጣ ውረድ ላለፈ ሕዝብ እና በርካታ እድሎች ከፊቱ ላሉት ሕዝብ ዛሬ ብራዚል ለደረሰችበት ደረጃ የመድረስ አቅም ነበረው።ነገር ግን በጎሰኛ መንግስት ተጠልፎ የጥቂቶችን የተንደላቀቀ ሕይወት እየተመለከተ እንዲኖር ተፈርዶበታል።አሁንም ከነገ ዛሬ ይቀድማል እና ለኢትዮጵያ ነፃነት አንድነታችንን እናጠናክር።ከጎሰኞች ማዶ ለምትመሰረተው የሁላችንም ኢትዮጵያ የበኩላችንን እናድርግ። 


ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ግንቦት 20/2005 ዓም (ሜይ 28/2015)

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...