ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, January 8, 2014

የኢቲቪ የልደት በዓል መርሃግብሩ ላይ የተሻሻሉ እና ያልተሻሻሉ መልኮቹ


ኢቲቪ በትናንትናው የገና በዓል ላይ ከእዚህ በፊት በተሻለ አቀራረብ ቀርቧል።የዛሬ አመት ካቀረበው ደረጃውን ካልጠበቀ መርሃግብር የዘንድሮው የተሻለ በዓል አስመስሎታል።በሌላ በኩል ደግሞ የሚቀሩት መርሃግብሮችም መኖራቸውን ሳንረሳ ነው።በመሆኑም የተሻሻለ አቀራረብ እና ያልተሻሻሉ አቀራረቦች ወይንም መርሃግብሮች በሚሉት ላይ እንዲህ ልበል-

የተሻሻሉ አቀራረቦች 

1/ መርሃ ግብሮቹን የቴሌቭዥን ጣቢያው በእራሱ ከመያዝ ለማስታወቅያ ድርጅቶች ዕድል ሰጥቷል።የሰራዊት ፍቅሬ እና ሸዋፈራሁ ማስታወቅያ ድርጅቶች ተሳትፈዋል፣

2/ በመርሃግብራቸው ላይ በቃለ መጠይቅ ያቀረቧቸው እንግዶች ብዙ ስብጥር ባይታይባቸውም ጠንክሮ ስለመስራት አውርተዋል።እዚህ ላይ በአጭር መንገድ ሃብታም  እና ጄኔራል የሆኑ ሰዎች ሲደነቁ እውነታውን ያንፀባርቃል የሚል እምነት እንደሌለኝ ይመዝገብልኝ።ዝርዝሩን ለማውራት ጊዜ የለኝም፣

3/ የሰራዊት ፍቅሬ እና ሸዋፈራሁ ማስታወቂያ ድርጅቶችን ጨምሮ ለፌስቱላ ሆስፒታል ስጦታዎች ሲበረከቱ ታይቷል፣

4/ ኢትዮጵያዊነት በጋሽ ውብሸት ወርቃለማሁ ሲነገር እና ሲተረክ አምሮበታል፣

5/ የሸገሮቹ ''የእኛ'' የራድዮ ተውኔት እና በ''አቤት'' እና ''እቴጌ'' ዜማቸው የሚታወቁት አምስቱ ወጣቶች ስለሀገር እና የሴት ልጅ አቅም ላይ  የተናገሩት አስተማሪ ነበር፣

6/ የገና ጫወታ ከዘመናዊው ዳንስ ጋር ያለው ልዩነት ለማሳየት እና ባህልን ማክበር ተገቢነት ላይ ያተኮረ ትንሽ ትይንት በመጠኑ ለማሳየት ተሞክሯል እና የመሳሰሉት ሲሆኑ።

ያልተሻሻሉ  አቀራረቦች 


1/ የበዓሉን ሃይማኖታዊ ገፅታ የሚያንፀባርቅ መርሃግብር አልታየም።ልደቱ የክርስቶስ መሆኑ ተረሳ እንዴ? የጌታን ልደት ለሁለት ሺህ አመት ያከበረች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስለበዓሉ መርሃ ግብር እንዲኖራት ለሕዝቡ እንድትናገር ዕድል መስጠት ይገባ ነበር፣

2/ በጣም አስቂኝ የዘንድሮ ኢቲቪ አቀራረብ በመሃል ላይ የፈረንጆቹን የገና ክላሲካል የምታሰማ ሙዚቃ ከፍቶ በረዶ ሲንጠባጠብ እና ብልጭልጭ የገና ኮተት የሚያሳይ ምስል ብልጭ ያደርግ ነበር።ይህ በኢቲቪ 3 ላይም ደጋግማ የታየች የባዕድ ቡትቶ ነገር ነች።እኛ ሀገር እኮ በገና በረዶ የለም።አሁን በረዶ ሲንጠባጠብ እና የአውሮፓ የገና ክላሲካል በእየመርሃ ግብሩ መሃል ማስገባት ለምን አስፈለገ? የገና በዓል የሚገልፅ ሀገርኛ ዜማ ጠፋ ማለት ነው?

3/ በዋዜማውም ሆነ በዕለቱ ምሽት ላይ ዜና አንባቢው በአውሮፓ ሱፍ ከሚታይ የሀገር ባህል ልብሱን ቢለብስ ባማረበት ነበር።በእዚህ አቀራረብ ኢሳቶች ይምጡብኝ።ዜና አንባቢው በሀገር ባህል ልብስ ቂቅ ብሎ ነው የታየው።መቼም ኢቲቪን የተመለከቱ የውጭ ሀገር ዜጎች በዜና አንባቢዎቹ አለባበስ ከሀገር ቤቱ እኩል ሳያፍሩበት አይቀሩም፣

4/ የአመት በዓል መርሃግብሮችን ባብዛኛው ወጣቶች እና ታዳጊ ወጣቶች የመመልከታቸውን ያክል ታዋቂ ምሁራን እና በምርምር እንዲሁም በትምህርቱ ዘርፍ ዝናን ያተረፉ ሰዎች ከታሪካቸው ተሞክሮ ጋር ቢቀርቡ አስተማሪ በሆነ ነበር።ሁል ጊዜ የኪነት ሰዎች ብቻ መድረኩን ሊሞሉት አይገባም ባይ ነኝ።ኪነት አንዱ አስፈላጊ ዘርፍ ቢሆንም ሁሉም ሰው የኪነት ሰው ሆኖ ሀገር አያድግም።ምሁራኑን እንደ ቅቤ ጣል ቢደረጉ ጥሩ ነበር።

አበቃሁ

ጉዳያችን ታህሳስ 30/2006 ዓም 

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...