ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, December 25, 2013

ከትዝታዬ


ከትዝታዬ የሚሉ በጣም አጫጭር ጽሁፎች አልፎ አልፎ ጣል ለማድረግ ማሰቤን ልግለጽና ለዛሬ ይህችን ላካፍላችሁ። በደርግ መውደቅያ ዘመን አካባቢ አዲስ አበባን የምናውቃት በታክሲ ውስጥ፣በትምህርት ቤት፡ መምህራን፣ ካፌ ቤት፣ሰራተኞች ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር  በነጻነት (ሌላውን ነጻነት ትተን) በትግርኛ፣ኦሮምኛ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ይናገሩ ነበር።

ከሚኒባሱ ጋቢና የተቀመጠ ሰው ከኋላ ለተቀመጠ ወዳጁ በትግርኛ ድምጹን ከፍ አድርጎ ያወራ ነበር።በአውቶቡስ ውስጥም ኦሮምኛ ሆነ ጉራጊኛ ህዝቡ ካለ አንዳች መሳቀቅ ይናገር ነበር። ሁሉም ተከባብሮ ይኖር ነበር።ሌላ ቋንቋ ለመናገሩ አንዳች መሳቀቅ አይሰማውም።

ዘመኑ በደንብ ትዝ ይለኛል 'ጋሽ ተስፋ ጽዮን' የሚባሉ የሳይንስ መምህር ትምህርት ቤታችን ውስጥ ቮሊቮል መጫወት ይወዱ ነበር።ሲጫወቱ በትግሪኛ እያውሩ ነበር ኳሱን የሚሰርቡት... ጋሽ መገርሳ የእስፖርት አስተማሪያችንን አልረሳቸውም ኦሮምኛ የሚችሉ ልጆች ጋር በኦሮምኛ ይቆጧቸው ነበር፣ ኮሜርስ ስገባ ጎይቶም የሚባል በጣም የማዝንለት ጓደኛ ነበረኝ።ጎይቶም የአክሱም ልጅ ነው።አባቱ በህወሃት እስር ቤት መሆኑን ከእናቱ ጋር ወደ አዲስ አበባ መምጣቱን ይነግረን ነበር።ጎይቶም ትግሪኛ ሲናገር ባይገባንም ጓደግኞቹ የተለየ ንግግ ር የተናገረ ያክል አይሰማንም።እርሱም ደስ ብሎት አውርቶ ቀጥሎ ወደ እኛ ዞሮ አማርኛ ያወራናል... አዲስ አበባ ንግድ ስራ ኮሌጅ ሬጅስትራር ክፍል ስንሄድ ኦሮምኛ የሚናገሩ ሰራተኞች ብዙ ነበሩ።ይህ ቢሮ ውስጥ ነው የማወራው። ማንም ቅር አይለውም።ልዩነትም የለውም።

... መከላከያ ፊት ለፊት ያለው ትልቁ ኢትዮዽያ ንግድ ባንክ ለስራ ልምምድ ስላክ ብዙ አለቆች የእረጅም ጊዜ የስራ ልምድ ያላቸው የተከበሩ አባቶች የሚባሉ የትግራይና የኤርትራ ተወላጆች ነበሩ።በሻይ ሰኣት ሁሉም ዘና ብለው በትግሪኛ ያወራሉ ይጫወታሉ።ሁላችንም 'ጋሼ እትዬ' ብለን የታዘዝነውን እንሰራ ነበር... ብላቴ ስንሄድ ብዙ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች በየቋንቋቸው ይናገሩ ነበር።
ይህ ውበት ዛሬ ኢትዮዽያ የራቃት ይመስለኛል። ህዝቡን ጎሰኞች ስለ ጎሳ ብዙ በማውራት አሳቀቁት። ዛሬ ስለ ጎሳ አብዝቶ የሚያወራው መንግስት ከመጣ ወዲህ ወገኔ ተሳቀቀ።ነቀምት ሲገባ አማርኛ መናገር፣ጉራጊኛ ማውራት ተሳቀቀ።አዲስ አበባ ሲገባ ከ አራዳ ቋንቋ ሌላ ማውራት የሚያሳቅቀው ሆነ። የጎሳን ነገር  መንግስት ቤተ መንግስት አስገብቶ እንደፈለገው አብኩቶ ህዝቡን አሳቀቀው።ህዝቡ የእራሱ የሆነ የመከባበር ዘይቤው ጠፋው።ዘረኞች ፋታ አገኙ።ህዝቡን ናኙበት።ዛሬ በነጻነት ድምጹን ከፍ አድርጎ የሚያወራው አዲስ አበባ ላይ  በስደት ላይ የሚገኙ ሱማሌዎች ብቻ ሆኑ።እነርሱ ታክሲ ውስጥም ጮክ ብለው ያወራሉ።ሌላው አፈረ።ይህች ነች የብሔር ብሄረሰብ መብት? ሕዝብ መከፋፈል ለስልጣን ጥበቃ።

ታህሳስ 16/2013 ዓም 


No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...