ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, December 19, 2013

ሰበር ዜና-በደቡብ ሱዳን የሪክ ማቸር ኃይሎች ውግያ ጀመሩ። ትናንት ምሽት ቁልፏን ከተማ ቦርን ተቆጣጠሩ።ኢትዮጵያና ዑጋንዳ በደቡብ ሱዳን አንፃር (ጉዳያችን አጭር ዘገባ ታህሳስ 10/2006 ዓም)


ደቡብ ሱዳን ቦር ከተማ (photo Reuters)

በደቡብ ሱዳን የተቃዋሚ ኃይሎች ከሀገሪቱ ዋና ከተማ ጁባ በ 200 ኪሎሜትር  እርቀት ላይ የምትገኘውን 'ቦር' የተሰኘችውን ቁልፍ የደቡብ ሱዳን ከተማ ተቃዋሚ ኃይሎች መቆጣጠራቸውን የከተማዋ ከንቲባ ንሂሃል ማጃክ ለቢቢሲ ረቡዕ ታህሳስ 9/2006 ዓም አስታውቀዋል።
ፊሊፕ አጐር የተሰኙ የመንግስት የጦር ኃይሉ ቃል አቀባይ በሌላ በኩል ''ወታደሮቻችን በከተማዋ የነበራቸውን የበላይነት ለሪክ ማቸር ኃይሎች አስረክበዋል'' ብለዋል።ሪክ ማቸር የቀድሞ የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት እና በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተሳትፈዋል ተብለው በሱዳን መንግስት እየተፈለጉ መሆናቸው ይታወቃል።

በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ከትናንት በስትያ በተሞከረ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ እንደ ተባበሩት መንግሥታት ዘገባ 500 ሰዎች ሲገደሉ ከ 20 ሺህ የማያንሱት ከመኖርያ ስፍራቸው ተፈናቅለው በተባበሩት መንግሥታት ግቢ ውስጥ እንዲጠለሉ ያደረገ ሲሆን ቁጥሩ ከእዚህም እንደሚልቅ ይገመታል።

በደቡብ ሱዳን ካሉት ትልልቅ ጎሳዎች ውስጥ የኑዌር እና ዲንቃ ጎሳዎች ሲጠቀሱ። የመፈንቅል ሙከራውን ያደረጉት ሪክ ማቸር የኑዌር ጎሳ ሲሆኑ ከመንግስት በኩል የተሰለፉት አብዛኞቹ የዲንቃ ጎሳ መሆናቸው ይነገራል።ጎሳዎቹ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ሰሜን ምዕራብ ኬንያ እና ሰሜናዊ ዑጋንዳ ጋር ድንበር ከመጋራት አልፎ ተመሳሳይ ጎሳዎች ከመኖራቸው አንፃር ሲታይ ጉዳዩ የአካባቢው ፖለቲካ ላይ የሚኖረው አንደምታ ቀላል ላይሆን ይችላል።

 በዑጋንዳ ካምፓላ የሚታተመው ትልቁ የዑጋንዳ ጋዜጣ ''ዘ ኒው ቪዥን'' በዛሬ ማለዳ እትሙ ላይ የዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሰቬኒ የደቡብ ሱዳንን ግጭት እንዲሸመግሉ የተባበሩት መንግሥታት መጠይቁን ዘግቧል።በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ከሁሉ በተሻለ ተፅኖ የመፍጠር አቅም የሚኖራት ምናልባትም በጉዳዩ ላይ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ እጇ ሊኖር ይችላል ተብሎ የሚገመተው ዑጋንዳ ነች።የዑጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ አሁን ውግያ ለጀመረው የርክ ማቸር ኃይል መጠለያ ለመስጠትም ሆነ ስንቅ እና ትጥቅ ለማቀበል ብቸኛ አማራጭ የመሆናቸው ዕድል ትልቅ ነው።

የኢትዮጵያን ሚና ስንመለከት ግን መንግስት በሁለት አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ይመስላል። በአንድ በኩል የሰሜን ሱዳን ወዳጅነት እንዳይደፈረስ በሌላ በኩል በደቡብ ሱዳን ያለው ጥቅም እንዳያመልጥ።የኢትዮጵያ አየርመንገድ በረራን ጨምሮ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጁባ ቅርንጫፍ እስከ መክፈት ድረስ የደረሰ የንግድ ግንኙነት ያላት ኢትዮጵያ የአሁኑን ሁኔታ በጥንቃቄ የምታየው ብቻ ሳይሆን ኢህአዲግ በሌለው ብቁ የአካባቢያዊ ፖለቲካ ትንተና ሁኔታ አንፃር  በነገሮች ላይ ውሳኔ የመስጠት ዘገምተኝነት እና የተንዛዛ የውሳኔ አሰጣጥ ሰንሰለት መርዘም ሊኖር እንደሚችል መገመት ይቻላል።

በአቶ መለስ ጊዜ ውሳኔዎችን እራሳቸው ስለሚሰጡ እና ግልፅ መስመር በማሳየት  በኩል የተሻለ ሁኔታ በአካባቢያዊ ዲፕሎማሲ ላይ ይታይ የነበረ ለመሆኑ የማይታበል ሀቅ ነው።የሱማሌው ጉዳይ ላይ አቶ መለስ የአሜሪካንን ፍላጎት የሚያረካ አቅጣጫ  የ1997 ዓም ምርጫ ማጭበርበር አንፃር ለተነሳው ሕዝባዊ አመፅ የአሜሪካንን ድጋፍ ያገኙበት መሆኑ የሚታወቅ ነው።

በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ላይ የብዙ ጥቅም ተጋሪ የሆኑት የኢህአዲግ የጦር ሹማምንት እና አንዳንድ ባለስልጣናት ውሳኔውን ከንግድ ጥቅማቸው አንፃር ብቻ እንዳይመዝኑ እና ሃገርን ለባሰ ጉዳት እንዳይዳርጉ የብዙዎች ስጋት ነው።ከሰሜን ሱዳን ጋር ያለውን ወዳጅነት ለማቆየት ብዙ ለም መሬት በመስጠት የሚታወቀው ኢህአዲግ ደቡብ ሱዳን ላይ የሚይዘው አቅጣጫ በቅርቡ የሚታወቅ ይሆናል።

እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ግን ምንም አይነት የመንግስት ለውጥ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ቢፈጠር ወይንም ያለው መንግስት ለተወሰነ ጊዜ እየተንገዳገደም መቆየት ቢችል ኢትዮጵያ ከሰሜን ሱዳን ወይንም ከደቡብ ሱዳን አንዳቸውን የመደገፍ አዝማምያ ለማሳየት ባትፈልግም የምትገደድበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።አሜሪካ አንዳንድ ጊዜ ብዙም ሀብት እና ስትራተጅያዊ ጥቅም የላቸውም ላለቻቸው ለትልልቅ የህዝብ ስደት እና ግጭቶች ጆሮዋን የማትሰጠው ን ያክል ለደቡብ ሱዳን በከፍተኛ ባለሥልጣኗ አማካይነት በጉዳዩ ላይ ሃሳቧን ሰጥታለች።

አሜሪካ ለጊዜው ጉዳዩ ላይ በቀጥታ መግባት ባትችልም የአካባቢው ሃገራትን '' 'ቀኝ እጄን ሰጥቻለሁ'  እንደእኔ ሆነህ ይህንን አድርግ'' የምትለው ሀገር የሚታዩዋት ምናልባት ኢትዮጵያ እና ዑጋንዳ ብቻ ናቸው።ኢትዮጵያ ደግሞ በአሜሪካ ፍቃድ ብቻ ላለመሄድ የሚያደርጋት የሱዳን ፊት አለ።ሱዳን ተፅኖ ለመፍጠር በኤርትራ የሚገኙ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎችን መሸጋገርያ እንዳትሰጥ ያሰጋል።በመሆኑም ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ጉዳይ እንደ ሱማሌው ችግር ሙሉ በሙሉ የመግባቷ አዝማምያ እምብዛም አይታይም።ለዑጋንዳው ዩዌሪ ሙሰቨኒ ግን ሰርግ እና ምላሻቸው ነው።

ጉዳያችን ታህሳስ 10/2006 ዓም
የጉዳያችንን ዘገባ በድህረ ገፅዎ ላይ ሲያወጡ ያገኙበትን ምንጭ  መግለፅ ጨዋነት ነው።

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...