በአንድ ወቅት ላይ ያለ መንግስት የሚሰራው ስህተት ወይንም ብቃት በሌለው አሰራር ሳብያ የሚያስከትለው ችግር አሁን ካለው ትውልድ ተሻግሮ ለመጪው ዘመናትም የማይለቅ ተከታታይ ችግሮችን ይዞ መምጣቱ አይቀርም።ባለፈው ወር ላይ አዲስ አበባ ላይ በተደረገ የአፍሪካ የኃይል አጠቃቀም ላይ አንድ ምሁር ባቀረቡት የጥናት ፅሁፍ ላይ የተናገሩት በአንድ ትውልድ ዘመን ያለ መንግስት ደካማ አሰራር ምን ያህል ተከታታይ ትውልዶች ላይ ጠባሳ እንደሚያስከትል የሚያመላክት ነው።ምሁሩ ''አፍሪካ'' ይላሉ ''አፍሪካ የኢንዱስትሪው አብዮት ተሳታፊ ሳትሆን አለፋት፣ቀጥሎም የመረጃ ቴክኖሎጂ (information technology-IT) በአግባቡ ሳይደርሳት አለፈ አሁን ደግሞ አረንጓዴ ኃይል ዘርፍ ተጠቃሚ ሳትሆን እንዳያልፋት ያሰጋል'' ብለዋል። ይህ ጉዳይ ኢትዮጵያንም ይመለከታል።
የኢንተርኔት አገልግሎት ቁልፍ እና የሁሉም የምጣኔ ሀብት ዘርፎችን የማንቀሳቀስ አቅሙ ቀላል አይደለም።የኢንተርኔት ዘርፉ ቢያንስ በውጭ የሚኖሩ እና በሀገር ውስጥ ያለ የግል ዘርፉን የማሳተፍ እድሉ በእጅጉ ከመጥበብ አልፎ እጅግ አደገኛ በሆነ መንገድ እና ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ለቻይና ኩባንያዎች ስራውን እያስተላለፈ መምጣቱ ሌላው አሳሳቢ ተግባር ነው።
ጂ-4 የተባለው የአራተኛው ትውልድ ቴክኖሎጂ ሥራ ጨምሮ ቻይና ሙሉ በሙሉ እጇን በኢትዮጵያ ውስጥ አስገብታለች።ሲሶው እጅ በቻይና መንግስት ሽርክና መያዙ የሚነገርለት የቻይና የቴሌኮምዩኒኬሽን ዜድቲ ኢ (ZTE) ለኔትዎርክ ሥራ ብቻ እስከ 1.3 ቢልዮን ዶላር የሚደርስ ውል እንዲፈርም መደረጉ የሚታወስ ነው።የእዚህ አይነት ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በአግባቡ ዓለም አቀፍ ጨረታ አውጥቶ ደረጃቸውን የጠበቁ ኩባንያዎችን ከማሳተፍ ይልቅ ግልፅነት የጎደላቸው ጨረታዎች ሥራ ላይ መዋላቸው ተለምዷል።ይህ አይነቱ ድርጊት እራሳቸውን የቻሉ ተያያዥ ችግሮችን ብቻ ሳይሆን ለተከፈለው ክፍያ ተገቢው እና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመገኘቱ ዋስትና መጥፋቱ ሌላው ችግር ነው።ከእዚህ በተጨማሪ ቻይና የሀገራችንን የፖለቲካም ሆነ ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ላይ እጅ የመጠምዘዝ አቅሟን የማሳደጉ ጉዳይ ሳይረሳ ነው።
ይህ ሁሉ ሆኖም ግን የ 2013 ዓም ''ፍሪደም ሃውስ'' ዓለም አቀፍ የመረጃ መረብ እና ዲጂታል መገናኛ ዳሰሳ ሪፖርቱ መሰረት ኢትዮጵያን ከመጨረሻዎቹ ተርታ ሃገራት መካከል ፈርጇታል። የመረጃ መረብ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የዘመኑን የሉላዊነት ተግዳሮትን ለማሸነፍ ቁልፍ ከመሆኑ አንፃር ሪፖርቱ ለሀገራችን ብዙ ማለት ለመሆኑ አያጠራጥርም።ከሰማንያ ሃገራት ውስጥ የመንን ብቻ እንደምንበልጥ መስማት ሌላው እራስ ምታት ነው።በሀገርቤት በኢህአዲግ እና በኢቲቪ የሚቀርበው ሪፖርት ግን ፈፅሞ እውነታውን አያመላክትም።በነገራችን ላይ ሪፖርቱ መረጃቸው ያልተገኘ ያላቸው ጥቂት ሃገራትን አላካተተም።ከእነዚህም ውስጥ ኤርትራ ትገኝበታለች።
ሙሉውን ሪፖርት ለማንበብ ይህንን ድህረ ገፅ ይክፈቱ።
http://freedomhouse.org/sites/default/files/resources/FOTN%202013_Full%20Report_0.pdf
No comments:
Post a Comment