ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, December 15, 2013

''ፖለቲካ ሀጢአት ነው ወይ? '' የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቅ አጭር እና ግልፅ ምላሽ

በሳምንቱ መጨረሻ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን ወደ ደብረዘይት ደብረ መድሃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስያን  ባዘጋጀው የመንፈሳዊ ጉዞ ላይ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ምዕመናን ተሳትፈዋል።መርሃግብሩ ላይ ከምዕመናን እና በቀጥታ በማኅበራዊ ድህረገፆች ለአባቶች የጥያቄ እና መልስ መርሃግብር ተዘጋጅቶ ነበር። ለተነሱ ጥያቄዎች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምላሽ መስጠታቸው ከማኅበሩ የፌስ ቡክ ገፅ ላይ የተገኘው መረጃ ይገልፃል።ምእመናን ከእንደዚህ አይነት መርሃግብሮች እና ከሊቃውንቱ ቀጥተኛ እና  ትክክለኛ መረጃ ማግኘታቸው  ትልቅ ዋጋ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።

ከገፁ ላይ የተገኘውን ከእዚህ በታች እንዲህ ይነበባል-

''ቀጥሎ የሚኖረን መርሐ ግብር የጥያቄና መልስ መርሐ ግብር ሲሆን ሊቃውንቱ መልአከ ታቦር ተሸመ ዘሪሁን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ አባል፤ መጋቤ ሐዲስ ደጉ ዓለም ካሣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲሳት ትርጓሜ መምህር፤ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ በቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የብሉይና የሐዲስ ትርጓሜ መምህር፤ ሲሆኑ ከምዕመናን ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ደግሞ በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ አቅራቢነት ያስተናግዳሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይመለስልን የምትሉት ጥያቄ ካላችሁ በውስጥ መስመራችንም ሆነ በ ኢ-ሜላችን ብትሉክልን እናስተናግደዋለን፡፡
……………………

ጥያቄ 2 . ቅዱስ ጳውሎስ ሀገራችን በሰማይ ነው ስላለ እኛ ክርስቲያኖች በምድራዊት ሀገራችን ላይ እንዴት እንስራ?


እግዚአብሔር ሰማይ ዙፋኔ ምድርም የእግሬ መረገ ናት እንዳለ አሁን ዛሬ ተቀምጠን የምንዘምርበት፣ የምንማርበት፣ የምናመሰግንበት፣ ይሄ ምድርም የእግዚአብሔር ፍጥረት ስለሆነ ሰው ለሀገሩም ሊሰራ ሊሞት ይገባዋል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በአድዋ ድል የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን ሱታፌ ማስታወስ በቂ ነው፡፡ መልአከ ታቦር ተሸመ ዘሪሁን የሊቃውንት ጉባኤ አባል
……………………..

ጥያቄ 4 ፡ ፖለቲካ ሀጢአት ነው ወይ?

ሰው በዚህ አለም ሲኖር ከሀጢአት በቀር በአለም ያለው ሁሉ ይመለከተዋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እነ ዳዊት፣ እነሰሎሞን ፖለቲከኞች ነበሩ ስለዚህ ሀጢአት አይደለም ሀጢአት የሚሆነው አያያዙን ማወቅ ሲያቅት ነው፡፡ ወተት መጠጣት ሀጢአት አይደለም በረቡዕ ከተጠጣ ግን ሀጢአት ይሆናል፣ ቢላዎ ባለሞያ ሴት ካገኘችው ያገለግላል ባለጌ ካገኘው ሰው ይጎዳበታል ፖለቲካም አያያዙን ካወቅንበት ሀጢአት አይደለም፡፡ መጋቢ ሐዲስ እሸቱ ዓለምዓየሁ በቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የብሉይና የሐዲስ ትርጓሜ መምህር።''
በጉባኤው ላይ ከታደሙት ምዕመናን በከፊል ምንጭ - https://www.facebook.com/mkidusanNo comments: