ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, March 22, 2013

የአቶ አርከበ እቁባይ ሃሳቦች ለህወሓት ለምን አልተስማማውም ?ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ (Photo: William Davison/Bloomberg)


 መጋቢት ወር 2005 ዓም 

ህዳር ወር 1997 ዓም መነሻውን የመስቀል አደባባይ ያደረገው አምስተኛው የኢትዮጵያ የታላቁ እሩጫ ውድድር በጥሩ ሁኔታ ከተከናወኑት ውድድሮች የሚጠቀስ ነበር።በወቅቱ መንግስት የተወጠሩ የፖለቲካ ስሜቶችን በመጠኑም ቢሆን ማላላት የቻለባቸው ጊዜዎች ነበሩ።ከአምስት ወር በኃላ የሚደረገው አጠቃላይ ብሔራዊ ምርጫ፣ብዛት ያላቸው ጋዜጦች፣የውጭ መንግሥታት ስለምርጫው የሰጡት ተስፋ እና ተለያይተው ይሰሩ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ''ቅንጅት'' በሚል ህብረት ስር መደራጀት ወዘተ አመቱን ኢትዮጵያውያን በተስፋ እንዲጠብቁት ያደረገ ነበር።


በእዚህ መንፈስ ውስጥ ነበር የታላቁ እሩጫን ለመወዳደር ከተሰለፉት ሺዎች ጋር በመስቀል አደባባይ ሰውነታቸውን ከሚያሟሙቁት ጋር የተሰለፍኩት።በወቅቱ ታድያ አስገራሚው ትዕይንት ቀድሞ ኮ/ል መንግስቱ ከሚቆሙበት ሰገነት ላይ ይታይ ነበር። የወቅቱ የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ አርከበ እቁባይ እና አቶ መለስ ዜናዊ ውድድሩን ካስጀመረው ከአትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ጋር ቆመው የሚሮጠውን ሕዝብ በእጃቸው ሰላምታ ይሰጡ ነበር።ጨዋው እና በኢትዮጵያዊነት ስሜት የታሸው የአዲስ አበባ እና የአካባቢው ሕዝብ በተለይ አቶ አርከበ እጃቸውን ሲያነሱ በደስታ እና በእልልታ ያጨበጭብ ነበር።ይህም በልዩ ክብር እና መውደድ ይደረግ የነበረ የክብር ሰላምታ ነበር።

ለአቶ አርከበ የአዲስ አበባ ሕዝብ ለምን ክብር ሰጠ?

የአለም ከንትባዎችን ሃሳቦች በሚገልፀው ድህረ ገፅ (worldmayor.com) ላይ አቶ አርከበ ስለ እራሳቸው በገለፁበት ፅሁፍ ላይ እንድሚነበብው ከእንግሊዝ በቢዝነስ አድምንስትሬሽን የማስተርስ ዲግሪ እና ከኔዘርላንድ በአለምአቀፍ ግንኙነት ሌላ የማስተርስ ዲግሪ እንዳላቸው ይገልፃሉ።ከትምህርት ዝግጅታቸው በላይ አቶ አርከበ ለሕዝብ የተዋወቁበት ትልቁ አጋጣሚ ግን የ አዲስ አበባ ከንቲባ በነበሩበት ጊዜ ነው።አቶ አርከበ በአዲስ አበባ ከንቲባነታቸው ወቅት በሁለት ትላልቅ ሃሳቦች ውስጥ የተወጠሩበት ነበር። የመጀመርያው ቀድመው በኢህአዲግ ውስጥ ያውቁት የነበረው አካባቢያዊ ስሜት ሙሉ በሙሉ አዲስ አበባ ላይ የማይሰራ መሆኑን በመረዳት በፍፁም ፍቅር ለውጥ ለማምጣት መስራት የሚለው ሲሆን ሁለተኛው በአቶ መለስ እና በሌሎች የህወሓት አባላት ''ቀስ በል ብዙ አትሩጥ የፓርቲአችን ፖሊሲ እያየህ'' የሚለው አስተሳሰብ ነበር። በተለይ አቶ መለስ የአቶ አርከበን በሕዝብ መወደድ በታላቁ እሩጫ ጊዜም ሆነ ከእዛ በኃላ በሕዝቡ ልብ ውስጥ እየገቡ መምጣታቸው ቅር እንዳሰኛችው የታወቀው '' የአዲስ አበባ ልማት ቀለም ከመቀባት ያለፈ አደለም'' ያሉት ንግግር ሕዝቡን ካስደመመ በኃላ ነበር።

አቶ መለስ ይህንን ይበሉ እንጂ አቶ አርከበ ለአዲስ አበባ ሁነኛ ለውጥ ያመጡ ግለሰብ ሆነው ይሰሙኛል።እርግጥ ነው በ1997ቱ አገራዊ ምርጫ ኢህአዲግ በአዲስ አበባ እራሱም ያመነበት መቶ በመቶ ተሸንፏል። ይህ ግን የአቶ አርከበን ጥረት የሚያደበዝዘው ሳይሆን እንዲያውም አቶ መለስ በግምገማ ጊዜ አቶ አርከበን ለማሸማቀቅ በጣም የተጠቀሙበት ወርቃማ ጊዜ ሆኖ አልፏል።የአቶ አርከበን በሕዝቡ ውስጥ የነበራቸውን ስብእና ለማኮሰስም ጥሩ አጋጣሚ በመሆኑ አክራሪ ህወሃቶች የህዝብን ድምፅ በጉልበት ከደፈጠጡ በኃላ አዲስ ሥራ የተጀመረ ለማስመሰል (የአቶ አርከበን የስራ ፍሬ በመደበቅ) ብዙ ሲጥሩ ትዝብት ላይ ወድቀዋል።

አቶ አርከበ የአዲስ አበባ ከንቲባ በነበሩበት ጊዜ ከአከናወኗቸው ተግባራት ውስጥ-

1/ የአዲስ አበባን የቆሻሻ አወጋገድ ሥራ ዘመናዊ ማድረግ።

አሁን ባለንበት ዘመን የትላልቅ ከትሞች ቆሻሻ አወጋገድ መንገድ እና መልሶ ለምርት የመጠቀም ሂደት (recycling process)ትልቁ ሥራ መሆኑ ይታወቃል።የአቶ አርከበ ቢሮ የአዲስ አበባ ከተማ በ መንደር ደረጃ የቆሻሻ ማስወገጃ ገንዳ እንዲኖር ከማድረጉም በላይ የስራውን ሂደት የውጭ ኩባንያ በተውሰነ ገንዘብ ስራውን ለመውሰድ ያቀረበውን ኮንትራት ባለመቀበል ስራው የብዙ ሺህ ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠርያ እንዲሆን አድርገዋል።በአሁኑ ጊዜ የአገልግሎት ጥራት ጉድለት ቢስተዋልም ከየትኛውም መንደር ውስጥ የቆሻሻ ገንዳ እና ቤት ለቤት በተወሰነ ክፍያ ሕዝቡን በመጠይቅ የሚሰበስቡ ወጣቶች ስራውን ያከናውናሉ። እዚህ ላይ የስራው መጀመር ብቻ ሳይሆን ወጣቶች ይህንን ሥራ የመስራት ሞራል እንዲኖራችው የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጡ ያደረጉት ጥረት የሚዘነጋ አይደለም።እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት የቆሻሻ መሰብሰብ ሥራ እና ወደ ማዳበርያነት እና ሌሎች ምርቶች ለመቀየር ወጣቶቹን የማሰልጠን ሥራ ሌላው ተጠቃሽ ተግባር ነበር።

2/ የአዲስ አበባን ከተማ የአስተዳደር መዋቅር በማስተካከል።

የአዲስ አበባ ከተማ ቀድሞ በቀበሌ እና ከፍተኛ በሚሉ ሁለት የተዋረድ መዋቅሮች ትታወቅ ነበር። በአቶ አርከበ ዘመነ ከንቲባነት ግን ክፍለከተሞች እና ቀበሌዎች ዋና ማዘጋጃ ቤት ይሰራቸው የነበሩ ስራዎች እንዲወርዱ እና ሕዝቡን በቅርብ እንዲያገኙ ሆኗል።ለምሳሌ የመሬት አስተዳደር፣የንግድ ግብር መክፈል፣ልደት፣ጋብቻ ሰርተፍኬት መስጠት እና የመሳሰሉት የአገልግሎት ስራዎች በክፍለከተማ ደረጃ ወርደው መሰራት ችለዋል። ይህም የተቀላጠፈ እና የተሻለ አገልግሎት ለማስገኘት አስችሏል።ከእዚሁ ጋር ተጠቃሹ የውልና ማስረጃ ቢሮ ሲሆን ይህ ቢሮም በተሻለ ፍጥነት የስራ ፍሰቱን ያስተካከለ ቢሮ ነበር።

3/ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማሰባሰብ 

አቶ አርከበ የአዲስ አበባ ከንቲባ ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ በተፈጠሩት የስራ መዋቅሮች መሰረት በመጀመርያ ዲግሪ ለነበሩ ብዙ ወጣቶች ሥራ ለማስጀመር ችለው ነበር።በእዚሁ መሰረት ብዙ የዩንቨርስቲ ምሩቃን ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበር።በወቅቱ የፖለቲካ አመለካከትን መስፈርት ያላደረጉ የቅጥር ሂደቶችም ታይተው ነበር።ሆኖም ግን ከጥቂት ጊዜ በኃላ እንደ ሪፖርተር ዘገባ ከሰባ ፐርሰንት በላይ የሚሆኑት ስራቸውን ለመልቀቅ ተገደዋል።ይህ የሆነበት ምክንያት የአቶ አርከበን ሁሉን አቀፍ አመለካከት የሚቃወሙ አክራሪ ህወሃቶች የአቶ አርከበን ሂደት እግር በእግር እየተከታተሉ ከመውቀሳቸውም በላይ አዲስ የተቀጠሩትን ወጣቶች ማዋከብና ቆይተውም የተማረ ሁሉ ቅንጅት ነው በሚል እሳቤ ማንገላታት በመጀመራቸው ነበር።አንድ የኢህአዲግ ካድሬ በአንድወቅት አቶ አርከበን ''ከተማ ገባና ሥጋውንም ነፍሱንም ለአዲስ አበባ ሰጠ እኮ አበዛው'' ያሉት አገላለፅ አቶ አርከበ ምን ይባሉ እንድነበር አመላካች ነበር። ምናልባት ካድሬው ትግራይን እረስቶ የሚል ቃና ያለው ይመስላል።አንዳንድ ጊዜ ኢህአድጎች እንደዚህ የወረደ አስተሳሰብ ሲያስቡ ላይገርም ይችላል።ለመንደር ማሰብ ለህወሓት ካድሬዎች አዲስ አይደለም።

4/ እያንዳንዱን ቀበሌ እና ክፍለ ከተማ በኮምፕዩተር ኔትዎርክ ለማገናኘት የስራ ጅማሮ ነበር። 

5/ ለእያንዳንዱ ቀበሌ እና ክፍለከተማ ከስድስት ፎቅ ያላነሰ ምቹ ቢሮ መስራት በእቅድ ደረጃ የተያዘ እና በአንዳንዶች ለምሳሌ ቦሌ ክፍለ ከተማ የተከናወነ።

6/ የአዲስ አበባ ከተማን ዓለም አቀፋዊ ከተማነት ማጉላት ለእዚህም ማስረጃዎቹ 

ሀ/ የቦምባርሌን የልደት በአል በመስቀል አደባባይ ዓለም አቀፋዊ መድረክ ፈጥሮ  ልጆቹ እና የልጅ ልጆቹ ልዩ እንግዳ የሆኑበት ሲ ኤን ኤን ን ጨምሮ በቀጥታ ለዓለም የተላለፈ ፕሮግራም ማዘጋጀት፣ 

ለ/ ታዋቂዋን የአሜሪካ ቱጃር እና የጥቁሮች ተሟጋች ኦፕራን ወደሃገርቤት በመጋበዝ ስለ ኢትዮጵያ እንድትናገር በማድረግ እና 

ሐ/ ለአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች በሙሉ የእያንዳንዱን የአፍሪካ ሃገራት የመንገድ ስያሜ እንዲያገኙ እና ለሁሉም የአፍሪካ አገሮች የኢምባሲ መስርያ ቦታ በመስጠት የሰሩት ሥራ አዲስ አበባን አለመቀፋዊ ባህርይዋን አጉልተውላታል።

ማጠቃለያ 

አቶ አርከበ በከንቲባነታቸው ጊዜ ባሳዩት የስራ ፍሬ ህወሓቶች አልተደሰተም።ህዝቡ ግን ተደስቷል። ለእዚህም ነው ''አቶ አርከበ ኢህአዲግን ለቀው ይውጡ እና በግልዎ ይወዳደሩ እንምረጥዎት'' ያለው። ምንያደርጋል ለምርጫ 97 ላይ ኢህአዲግ አቶ አርከበ ቀርበው በቴሌቭዥን ለኢህአዲግ እንዲሟገቱ ያደረገው አንዱ 'አሱ የህዝብ አደለም የእኛ ነው ለማለት ነበር።'ምንም ቢሰሩም በሃገርጉዳይ ላይ ግን ቀልድ የማያውቀው ሕዝብ ምርጫውን አስተካከለ።አቶ አርከበን እየወደደ ግን ከገቡበት ጉረኖ አልወጣ ስላሉት።የሆነው ሆኖ አቶ አርከበ ምንም ያህል የህዝብ ፍቅር ቢያገኙ ለሕወሃቶች ግን አልተስማሟቸውም።አቶ አርከበ ጥሩ እንደሚሰሩ ያወቁት ህወሃቶች አቶ አርከበን መጀመርያ ወደ ከተማ ልማት ሚኒስትር ቀጥሎ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪነት አወረዷቸው።አሁን ደግሞ ከማአከላዊኮሚቴነትም ተነሱ።ምናልባት እንደሚመስለኝ ክልላዊ ሃሳብ የተጠናወተው ኢህአዲግ አቶ አርከብን ወደ ትግራይ ልማት ወይንም ለአንዱ ሀገር አምባሳደርነት አስቧቸው ይሆናል።ለሁሉም ጊዜ ይፈታዋል።ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

No comments: