Friday, December 13, 2024

ኢትዮጵያ ከሞቃዲሾ ሱማልያ ጋር በአንካራ፣ቱርክ ያደረገችው ስምምነት በተመለከተ፡

በአንካራ የተደረገው የኢትዮጵያና የሱማልያ ስምምነት


  • የስምምነቱ ምንነት፣ 
  • ኢትዮጵያ የመዘዘቻቸው ካርዶች ከአስመራ እስከ ካይሮ የፈጠሩት ድንጋጤና ድንዛዜ፣
  • ኢትዮጵያ ያስከበረችው ጥቅሞቿ ምን ምንድን ናቸው? 
  • ስምምነቱ ካለፈው ይልቅ መጪውን የኢትዮጵያ አቅጣጫ ያመላክታል።
===========
ጉዳያችን ምጥን
===========

ኢትዮጵያ ከሞቃዲሾ ሱማልያ ጋር በአንካራ፣ቱርክ ያደረገችው ስምምነት ምንነት?

በያዝነው ሳምንት አጋማሽ ኢትዮጵያ እና ሱማልያ ያደረጉት ስምምነት የሚከተሉትን ነጥቦች ይዟል። እነርሱም፡
  • የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች አንዳቸው የሌላኛቸውን ሉዓላዊነት፣ ነጻነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት እና በአፍሪካ ሕብረት ደንቦች ላይ የሰፈሩ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ለማክበር ተስማምተዋል።
  • በወዳጅነት የመከባበር መንፈስ ያለፉ ልዩነቶችን እና አወዛጋቢ ጉዳዮችን ወደ ኋላ በመተው በትብብር ለጋራ ብልጽግና ወደፊት ለመሥራት ተስማምተዋል።
  • ሶማሊያ በአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ስር ሆነው በአገሯ የተሰማሩትን የኢትዮጵያ ወታደሮች መስዋዕትነት ዕውቅና ትሰጣለች።
  • የሶማሊያን የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር መተላላፊያ ማግኘቷ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ሁለቱ አገራት ዕውቅና ይሰጣሉ።
  • ሁለቱ አገራት በቱርክ አመቻቻነት በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ የቴክኒካዊ ጉዳዮች ድርድር ማድረግ የሚጀምሩ ሲሆን፣ ይህም በአራት ወራት ውስጥ የሚቋጭ ይሆናል።
  • በሉዓላዊ የሶማሊያ መንግሥት ስር ኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ዘላቂ የባሕር መተላላፊ እንድታገኝ የሚያስችል ለሁለቱም አገራት ጠቃሚ የሆኑ የኮንትራት፣ የኪራይ፣ እና ተመሳሳይ የንግድ አሠራር መንገዶችን በጋር በመሆን ለማጠናቀቅ ተስማምተዋል።
  • ሁለቱ አገራት የቱርክን ድጋፍ በመቀበል በስምምነቱ አተረጓጎም እና አተገባበር ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ልዩነቶችን በቱርክ አማካይነት በንግግር እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተስማምተዋል።
 ከካይሮ እስከ አስመራ ከአስመራ እስከ ሞቃዲሾ መሪዎቹን በድንጋጤ ያደነዘዙት ኢትዮጵያ የመዘዘቻቸው ካርዶች 
  • የኢትዮጵያ ፍላጎት ከሱማልያ አንጻር ግልጽ ነው።
    • ሱማልያ የኢትዮጵያ የጸጥታ ችግር እንዳትሆን፣
    • ሱማልያ የኢትዮጵያ ስልታዊም ሆነ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር እንዳታብር፣
    • የጋራ የምጣኔ ሃብት ትብብር እንዲኖር፣
    • ኢትዮጵያ ለሱማሌ ደህንነት በከፈለችው ዋጋ የሚመጥን ልክ ያለው ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር የሚሉት ይጠቀሳሉ።

  • ከእነኝህ ፍላጎቶች አንጻር ሱማልያ ሁሉንም በሚጻረር መልኩ ለማፈንገጥ ሙከራ ማድረግ የጀመረችው የአሁኑ የሱማልያ ፕሬዝዳንት ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ነው። በፕሬዝዳንቱ ሲመት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሞቃዲሾ ድረስ ሔደው መገኘታቸው ይታወሳል። ይህም ሆኖ ግን አዲሱ ፕሬዝዳንት ብዙ ለመዝለል ሙከራ እንደሚያደርጉ ቀድሞውንም ይጠረጠሩ ነበር።

  • ይህ መዝለል እየበዛ መጥቶ ፕሬዝዳንቱ መጀመርያ ኢትዮጵያን መጎብኘት ትተው አስመራ ሲሄዱ ኢትዮጵያ እየተከታተለች ነበር። አስመራ ሄደውም አቶ ኢሳያስ ያሰለጠኑላቸውን ወታደሮች ጎበኙ፣ ምሳ ተበላ፣ ቡና ጠጥተው ወደ ሞቃዲሾ አመሩ።
  • በእዚህ ሂደት መሃል የምስራቅ አፍሪካ የምጣኔ ሃብት ጥምረት ሃሳብ ቀደም ብሎ በቀደሙት የሱማልያ ፕሬዝዳንት በበጎ የተጤነውን ጉዳይ አዲስ ፕሬዝዳንት ቸል አሉት።

  •   በእዚህ መሃል ኢትዮጵያ በእጇ ላይ ያሉትን ካርዶች መዘዘች፣ ጫወታውን ጀመረችው። ይህንንም እኤአ ጥር 1፣2024 ኢትዮጵያ ከሱማልያ ላንድ ጋር የወደብ እና የባሕር ኃይል ጣብያ ለመትከል የመግባብያ ስምምነት ተፈራረመች። የመግባብያ ስምምነት ማለት ዝርዝር ስምምነት ይቀረዋል።ነገር ግን በመሰረተ ሃሳቡ ሁለቱ ሃገሮች ተስማሙ ማለት ነው። 

  • በእዚህ ስምምነት ላይ ከወደቡ ጉዳይ ይልቅ ሱማልያ ላንድ በሃገርነት የመውጣቷ ጉዳይ ሱማልያን አመሰ። ኢትዮጵያ ዝም ብላ ጉዳዩን ትከታተል ነበር።

  • የሱማልያው ፕሬዝዳንት ከአስመራ ካይሮ ተመላለሱ። አቶ ኢሳያስ ድግሷ እንዳማረላት ወይዘሮ ካይሮ መመላለሱን ተያያዙት።

  • ቀጥሎ የግብጹ መሪ አስመራ የአንድ ቀን ውሎ አድርገው ከሱማልያ እና ከኤርትራ ጋር የጋራ ስምመነት ተፈራረሙ።ሱማልያ በቀጣይ የአውሮፓውያን ዓመት የኢትዮጵያ ጦር በሰላም አስከባሪነት በግዛቴ አይቀጥልም ብላ የመግለጫ ጋጋታ አወጣች።ግብጽ የጦር መሳርያ ወደ ሱማልያ መላክ ጀመረች። ሽር ጉድ አበዛጭ

  • በእዚህ ጊዜም ኢትዮጵያ አላወራችም። ይልቁንም ሸምቀቆውን አጠበቀች። በመቀጠል ሁለት እርምጃዎች ወሰደች። እነርሱም የመጀመርያው የግብጽ አየር ኃይል መሳርያ የሚያቀብልባቸው የሱማልያ ዋና ዋና የአይሮፕላይ ማረፍያዎችን ተቆጣጠረች። በመቀጠል በመቶዎች የሚቆተሩ ዘመናዊ ታንኮች የያዘ ሰራዊት ካለፈው ወር ጀምሮ የበለጠ አስገባች።

  • የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሱማሌ በኩል ያላቸው ቁርጠኝነት ኤርትራን እና ግብጽን ብቻ ሳይሆን እራሳቸው የሱማሊያ ፕሬዝዳንትም እጅ በአፍ እንዲያደርጉ አስገደደ። ኢትዮጵያ የግብጽ እንቅስቃሴ በቀጥታ ከኢትዮጵያ የመልስ ምት እንደሚገጥመው ብቻ ሳይሆን የግብጽ ጦር ምን ሊያደርግ መጣ? ስንት ዓመት ሙሉ ያልረዳን ሰራዊት ዛሬ ምን ሊያደርግ መጣ? የሚሉ የሱማሊያ የጎሳ አለቆች ቁጣ አስፈሪ ሆኖ መጣ።

  • የኢትዮጵያ ሰራዊት በሱማሊያ ህዝብ ዘንድ ያለውን ተወዳጅነት እሩቡን ማግኘት ያልቻለው የግብጽ ሰራዊት ግምት እና እወነት ምን ያህል እንደሚለያዩ ግልጽ ሆነለት። በተለይ የኢትዮጵያ ጦር በበለጠ ወደ ሱማልያ መግባቱን ተከትሎ አቶ ኢሳያስ እና አልሲሲ በስልክ ረጅም ሰዓት እየተቀመጡ ጉዳዩን ሲወቅጡት ቢውሉም አንዳችም ጠብ የሚል ውሳኔ መድረስ ብቻ ሳይሆን የበለጠ ፍርሃት ለቀቀባቸው።

  • ይህ በእንዲህ እያለ የሱማልያ ጁባ ግዛት ግጭት ተነሳ፣መላዋ ሱማልያ ወደ ሌላ ሶስት ሃገር ልትከፋፈል እንደምትችል እና የኢትዮጵያ ተጽዕኖ የቱን ያህል የሚነዝር እንደሆነ የሱማልያው ፕሬዝዳንት ቆይቶም ቢሆን ገባቸው። በኢትዮጵያ ወታደሮች የምትጠበቀው ሞቃዲሾ ሳትቀር መልሳ ታመሰች።

  • ይልቁንም በፈረንጆቹ ዓመት መጀመርያ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከወጡ ሱማልያ ምን እንደምትሆን ለመተንበይ በራሱ አስፈሪ ሆነ።

  • ኢትዮጵያ የመዘዘቻቸው ካርዶች አንድ በአንድ ከአስመራ እስከ ካይሮ፣ከካይሮ እስከ ሞቃዲሾ የዘለለውን ሁሉ ጸጥ አደረገው።

  • ሌላው ቀርቶ በሱማልያ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የጀመረችው ቱርክ ካለ ኢትዮጵያ የሱማልያ ጸጥታ የትም እንደማይደርስ የበለጠ ግልጽ ሆነላት።

  • ከእዚህ በተጨማሪ የግብጽ በአፍሪካ ቀንድ ሽር ጉድ ማለት በሊብያ ግብጽን እንዳሳፈረቻት በሱማልያም ማሳፈር እንዳለባቸው የቱርኩ ፕሬዝዳንት ዛቱ።ከሁሉም በላይ የኤርትራ ከግብጽ ጋር ያላት ትስስር ቆይቶም ቢሆን በቀይባርሕር ላይ ቱርክ ያላትን ጥቅም እንደማያስከብር ብቻ ሳይሆን አደጋ መሆኑ ገባቸው። በመቀጠል ኢትዮጵያና ሱማልያን አስማሙ።

  • የኢትዮጵያና የሱማልያ በአንካራ መስምማታን ተከትሎ ካይሮ እና አስመራ ከባድ ድንጋጤ ላይ ወደቁ። ድንጋጤው ይህ ጽሑፍ እየተጻፈም ገና አልለቀቃቸውም።

  • ኢትዮጵያን እንደከዷት የእኛዎቹ ዩቱበሮች በሱማልያ መንግስት ውስጥ ያሉ የኤርትራና የግብጽ አሽቃባጮችም ድንጋጤው አደነዘዛቸው ብቻ ሳይሆን የሱማልያውን ፕሬዝዳንት በሀገር ከሃጂነት ለመፈረጅም ቃ|ጣቸው።
ኢትዮጵያ ያስከበረችው ጥቅሞቿ ምን ምንድን ናቸው?
  1. ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄዋ የቱን ያህል እርቀት እንደሚሄድ ዓለምን አሳምናለች። ሌላው ቀርቶ የሱማልያ ላንድን በሃገር የማወቅ ያህል እርቀት እንደምትሄድ አሳይታበታለች። 
  2. በባሕር በር ጥያቄ ጉዳይ ኢትዮጵያን አያስፈልግሽም የሚል አንድም ሃገር የመናገር ድፍረት አጥቷል።
  3. ኢትዮጵያ ለሱማሌ ላንድ የምትከፍለው መስዋዕትነት የቱን ያህል እንደሆነ አሳይታበታለች። ከአሁን በኋላ ሌላ ሃገር ቀድሞ የሱማልያ ላንድ እውቅና ቢሰጥም የኢትዮጵያና የሱማሌ ላንድ ግንኙነት  በማይበጠስ አንድነት ገምዳዋለች።
  4. የባሕር በር ለኢትዮጵያ ሳይሰጡ በሰላም አድሮ መዋል እንደማይቻል ግልጽ መልዕክት አስተላልፋለች።ይህ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሀገራቱም ህልውና የሚወሰነው በኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት እና አለማግኘት መሆኑ ለሁሉም የጎረቤት ሃገሮች ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል።
  5. ለሱማልያ አሁን የሱማልያ ላንድ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የጁባ ሱማልያ ጉዳይም የኢትዮጵያን ሕክምና እንደሚፈልግ የሱማልያ ፕሬዝዳንት ዘግይቶም ቢሆን እንዲገባቸው አድርጋለች።
  6. ኢትዮጵያ የሱማልያ ላንድ የወደብ ስምምነት ብቻ ሳይሆን ከዋናዋ ሱማልያም የወደብ አገልግሎት እንደምታገኝ በሰሞኑ ስምምነቷ አረጋግጣለች። 
  7. በእዚህ ስምምነት ኢትዮጵያ የግብጽ ተጽዕኖ በሱማልያ እንዳይቀጥል አጥልታበታለች። በመቀጠልም ኢትዮጵያ ጋር የስትራቴጂክ ግጭት የሌለባት ቱርክ በግብጽ እንዲቀየር መንገዱን አመቻችታለች። በእዚህም ኢትዮጵያ የተሻለ የጸጥታ ዋስትና አግኝታበታለች።
  8. በቀጣይ ኢትዮጵያ የወደብ ጉዳይ ከኪራይ እና ውል ሃሳብ ወጥታ ወደ ዘለቄታዊ የባሕር በር ታሪካዊ እና ሕጋዊ ጥያቄዋ እንድትሸጋገር ሁኔታዎችን አመቻችቶላታል።
ስምምነቱ ካለፈው ይልቅ መጪውን የኢትዮጵያ አቅጣጫ ያመላክታል።

የኢትዮጵያና የሱማልያ የሰሞኑ ስምምነት ከሁሉም በላይ በአፍሪካ ቀንድ እና የቀይባሕር አካባቢ ትኩረት ያደረጉ ኃያላን ሀገሮችም ካለኢትዮጵያ ተሳትፎ ዋስትና እንደማይኖረው ስላወቁ እና የአቶ ኢሳያስ ከኢራን ጋር ያላቸው ግንኙነት ብቻ ሳይሆን በምዕራቡ ላይ ያላቸው ጥላቻ እራሷን ግብጽ እንድትወዛገብ ብቻ ሳይሆን ከአቶ ኢሳያስ ጋር መወገን የሚያመጣባትን የወጪ ክምር እያሰበች በከባድ ትካዜ ላይ ጥሏታል። አቶ ኢሳያስም በእዚህ ሳምንት ከጎበኙት የቆዩትን አሰብን ጎብኝተው አካባቢው ደስ አላለኝም ብለው ወደ አስመራ ተመልሰዋል። በትግራይ ለአቶ ኢሳያስ ለማደር የሚታትረው የደብረጽዮን ቡድን በትግራይ ህዝብ ከበባ ውስጥ እንደገባ ገብቶታል። ምናልባት አንድ ቀን ማለዳ ደብረጽዮን አስመራ ሸሽተው ገቡ ሊባል ይችላል። ኢትዮጵያ የባሕር በር ሳታገኝ ውላ ማደሯ ዋጋ እንደሚያስከፍል እንደ የሱማልያው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስም የበለጠ የሚረዱበት ጊዜ ከምንጊዜውም በላይ የቀረበ ይመስላል።መጪው የኢትዮጵያ አቅጣጫም ከእዚህ የተለየ አይመስልም። ዓለምም የሚያስበው ይሄው ነው።

Thursday, November 14, 2024

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሃራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)

ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሐራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)



Tuesday, October 8, 2024

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ

  • ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
  • የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው?
  • የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት ተሰናበቱ ብሎ ታሪክ ይመዝግብ?
  • ለጄነራል ጻድቃንን እና ጌታቸው ረዳ ሐብል ያጠለቀች ሀገር ለሣህለወርቅ ዘውዴ የማታጠልቅበት ምክንያት ሊኖር አይገባም።

======
ጉዳያችን
======

ኢትዮጵያ በወታደራዊው መንግስት ትመራበት ከነበረው የፕሬዝዳንታዊ የመንግስት ስሪት ወደ የጠቅላይ ሚኒስትር አመራር የመጣችው በዘመነ ህወሃት/ኢህአዴግ ዘመን ነው። በእዚሁ የጠቅላይ ሚንስትር አመራር ዘመን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የማንኛውም ፓርቲ አባል ያልሆነ እና በስራ እና የትምህርት ዝግጅት የተ|ሻሉ የተባሉት እና ባለው ስርዓት አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው ፕሬዝዳንቶች ሲሰየሙ ቆይተዋል።
በዘመነ ኢህአዴግ ከተሰየሙት ፕሬዝዳንቶች በተለየ እና ለረጅም ጊዜ በዲፕሎማሲው ዓለም አንቱ የተባለ ልምድ ያላቸው እና የመጀመርያ ሴት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ናቸው።

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በቆዩባቸው ያለፉት ስድስት ዓመታት ዘመናት ሴቶች ወደ አመራርነት የመምጣታቸው አስፈላጊነት እና ይህንንም ውጤታማ እንዲሁን የበኩላቸውን ጥረት አድርገዋል። በእዚህ ጉዳይ ላይ ከሃገር ውስጥ እስከዓለም አቀፍ መድረኮች በርካታ ስብሰባዎች ላይ ይህንኑ ጉዳይ አስተጋብተዋል። 

ያለፉት ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ ባሳለፈቻቸው የውስጥ ፈተናዎች ፕሬዝዳንቷ በመንግስት የስራ አስፈጻሚው የዕለት ተዕለት ስራ ውስጥ መግባት ህጉም ስለማይፈቅድላቸው በአንዳንድ መንግስታዊ የሀገር ውስጥ ውስኔዎች የራሳቸውን ሃሳብ ለማንጸባረቅ እና እንዲህ ቢሆን የሚሉ ሃሳቦች እንደነበሯቸው አልፎ አልፎ በሚናገሯቸው ንግግሮች ተንጸባርቀዋል። ይህም ሆኖ ግን ፕሬዝዳንቷ በኢትዮጵያን መውደድ፣አንዱን ወገን ከአንዱ ላለማስበለጥ እና ለሰላም የጸና እምነት እንዳላቸው ማንም ጥያቄ አያነሳም።

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 25፣2017 ዓም በትዊተር ገጻቸው ላይ የድምጻዊ መሐሙድ አሕመድ ''ዝምታ ነው መልሴ'' እና ''ለአንድ ዓመት ሞከርኩት'' የሚሉ ቃላት ያለው መልዕክት ከለጠፉ ጀምሮ መነጋገርያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል።የሣህለወርቅ ዘውዴ ትዊተር ባሉበት ደረጃ ያሉ ችግሮችን በእዚህ መልክ መግለጽ አለባቸው ብዬ አላምንም። ለምሳሌ የማይስማሙበት ጉዳይ ሲኖር በስልጣን ዘመናቸው ውስጥ ሳሉ ስልጣን እለቃለሁ ማለት ይችላሉ።ወይንም ይህንን ያህል ከተጓዙ በኋላ የፓርላማ ስብሰባ ሊደርገ አንድ ቀን ሲቀረው በትዊተር ላይ ያለፉ ጉዳዮች ከሚያነሱ።አስተማሪ እንዲሆኑ ከፕሬዝዳንትነታቸው በኋላ በመጽሐፍ መልክ አልያም በሚድያ ቃለ መጠይቅ ያላቸውን ሃሳብ መግለጽ ይችሉ ነበር ብዬ አምናለሁ።ከእዚህ በተለየ ግን ክብርት ፕሬዝዳንቷ የመንግስት ስራ አስፈፃሚ የሚወስናቸው ውሳኔዎች እና የችግር አፈታት ላይ የተለየ አስተሳሰብ መያዛቸው ጤነኛ አስተሳሰብ ነው።መርሳት የሌለብን ክብርት ፕሬዝዳንቷ የብልፅግና አባል አይደሉም።ስለሆነም በአንድ ፓርቲ አስተሳሰብና ፕሮግራም አልታሰሩም። በኢትዮጵያ ሕገ መንግስትም ፕሬዝዳንት የሚሆነው ከፓርቲ አባልነት የተለየ ነው።
ክብርት ፕሬዝዳንቷ የግጭቶች አፈታት ላይ በጣም የለሰለሱ አካሄድ መከተል እንደሚገባ በተለያዩ ጊዜ ንግግሮቻቸው ገልፀዋል። ይህ የተለየ ሀሳባቸውን ለመግለፅ ቢፈልጉ የመንግስት ስራ አስፈፃሚ "እኛ ይህን የወሰንነው ብዙ ነገሮች አይተን ነው" ወዘተ በሚል አንዳንድ የመንግስት እና የፓርቲው የቡድን ውሳኔዎች ላይ አይግቡ ብሎ ይሆናል። ክብርት ፕሬዝዳንት ደግሞ የጉዳዮች አካሄዶች ሊያስጨንቋቸው ይችላሉ። እዚህ ላይ ክብርት ፕሬዝዳንቷን ለማንቋሸሽ ብልፅግና ያላዘዛችሁን ክጣርያ በላይ ለመጮኽ የምትሞክሩ ከካድሬ በላይ ካድሬ ለመሆን የምትጋጋጡ አደብ ብትገዙ።በሌላ ጫፍ ደግሞ ክብርት ፕሬዝዳንቷ ይህን አሉ እያላችሁ የዩቱብ ፕሮፓጋንዳችሁ የማረጋገጫ ማኅተም የተመታላችሁ ይመስል "እምቧ ከረዩ" የምትሉ እና የዘር የብልቃጥ መርዛችሁን ለመነስነስ የምትሞክሩ ብትሰክኑ ጥሩ ነው። ክብርት ፕሬዝዳንት የሀገር ሀብት ናቸው።ቢቆጡ፣ለምን ይህ አልሆነም ቢሉ በሀሳቡ ላይ መነጋገር እንጂ መነታረክ አያስፈልግም። ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፣ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅን አክብረው ለማነጋገር፣ለሚሰማቸው ቅሬታና ጥያቄም በትሕትና ለማስረዳት የሞራልና የግብረ-ገብነት ችግር ያለባቸው አይደሉም። ስለሀገር ሲባል ብዙ ከተሳደበ ጌታቸው ረዳ ጋር ለማውራት ዐቢይ አልተቸገሩም። ክብርት ፕሬዝዳንት የተከበሩ ሰው ናቸው።የተለየ ሀሳብ ሊኖራቸው ይችላል። ሀሳቦቻቸውን ከፕሬዝዳንት ዘመናቸው በኋላም ማካፈላቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ።የሀሳብ ልዩነት ለዘላለም ይኑር!

ይህ በእንዲህ እያለ ሰኞ መስከረም 27/2017 በኢትዮጵያ ፓርላማ የተደረገው የአዲስ ፕሬዝዳንት ስየማ ላይ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የስንብት ንግግር ሲያድርጉ አለመታየታቸው ብቻ ሳይሆን መንግስታዊ የሆነ የምስጋና ቃላት ከአፈ ጉባዔውም ሆነ የፕሬዝዳንት ስየማውን አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባስተላለፉት የትዊተር መልዕክት ላይ አልገልትጹም። ይህ በጣም አሳፋሪ አሰራር ነው። ይህ በኢትዮጵያ ልክ የታሰበ አስተሳሰብ አይደለም። ለጄነራል ጻድቃንን እና ጌታቸው ረዳ ሐብል ያጠለቀች ሀገር ለሣህለወርቅ ዘውዴ የማታጠልቅበት ምክንያት ሊኖር አይገባም። በትዊተር ላይ ያውም ያልተብራራ ነገር ተጻፈ ብሎ የሚያኮርፍ ኢትዮጵያን የተረከበ መንግስት ከረሜላውን እንደነጠቁት ህጻን ሲያኮርፍ ማየት ያሳፍራል። መንግስት ስንሆን እንቻል እንጂ፣ዲሞክራሲን ስናሽቀነጥር በእዚህ ልክ መከስከስ ዋጋ ያስከፍላል።አይደለም ፕሬዝዳንት ማንም ሃሳቡን ቢገልጽ ለምን በመንግስት ደረጃ የሃገር ሃላፊነት የወሰዱ በተራ ካድሬ ልክ ለማሰብ እንደሚሞክሩ አይገባኝም።

አሁንም ነገሮችን ማረም ይገባል።ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ በፓርላማ የስንብት ንግግር ቢናገሩ ምን የተለየ የሚያስፈራ ነገር ይናገራሉ? ቢበዛ ስለሰላም አስፈላጊነት፣ስለሙስና፣ስለ ዜጎች መፈናቀል ነው። ይህንን እርሳቸው ባይናገሩስ ጸሃይ የሞቀው ጉዳይ አይደለም ወይ? አሁንም ቢቻል ፓርላማው እንደገና ተሰብስብስቦ የመሰናበቻ ንግግር እንዲያደርጉ መፍቀድ።በመቀጠል ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሌ በብሔራዊ ቤተመንግስት ለቀድሞ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የክብር ሽኝት እንዲደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም እንደልጅ ዝቅ ብለው ሰላምታ ሲለዋወጡ ማየት እንፈልጋለን። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት ተሰናበቱ ብሎ ታሪክ ይመዝግብ? ነገሮች ታርመው ፕሬዝዳንቷ በፓርላማ ንግግር ማድረጋቸው እራሱ የነገሮች የማረም ታሪክ ሆኖ ይጻፋል። ዛሬ ሣህለወርቅ በፓርላማ የስንብት ንግግር ባያደርጉ የሚሉት ነገር ካላቸው ከቤተመንግስት ሲወጡ ሁሉን ይሉታል። ያለነው በ21ኛው ክ/ዘመን ነው። አሁንም የምለው የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።
==================/////===============







Monday, September 2, 2024

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?


=======
ጉዳያችን
=======

በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የፖለቲካ መሸቀጫም ሆኗል።አጋቹም ያግትና መንግስትን ውቀሱ ይላል። አክቲቪስቱም አጋቹን መውቀስ ትቶ መንግስትን መውቀስ ስራዬ ተብሎ ተይዟል።እዚህ ላይ የሀገር ጸጥታ ማስከበር የመንግስት ኃላፊነት መሆኑ ይታወቃል። የእገታ ወንጀል የመሰለ የተለያዩ ባለሃብቶች እና የራሱ የመንግስት አንዳንድ የጸጥታ አካላት በተሳተፉበት ወንጀሎች አንጻር የህዝብ ተሳትፎ ከሌለ ባደጉት ሀገሮችም ጭምር አስቸጋሪ ነው።

የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አካላት

የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አካላት አራት ናቸው።እነርሱም፡ 
  • ሸኔ ብሎ ራሱን የሚጠራው ቡድን፡ 
ሸኔ ከሰሜን ሸዋ እስከ ወለጋ በርካታ ዜጎች አግቷል፣ህይወት አጥፍቷል።
  • ፋኖ ብሎ እራሱን የሚጠራው ቡድን፡
በአማራ ክልል ፋኖ ሰው አላገተም ብለው ለሚናገሩ። የፋኖ ዘመድ ናቸው የተባሉ ሳይታወቁ ሲታገቱ፣የፋኖ አባላት ደውለው ማስለቀቃቸው ያገቱት እነማን እና የት እንደሚገኙ ያውቃሉ ለሚለው አባባል ማረጋገጫ ነው።
  • ተራ ወንጀለኞች እና አንዳንድ ባለሃብቶች
በከተሞችም ሆነ በክልሎች የህገወጥ ታጣቂዎች መብዛት ወንጀለኞች ማገትን የገንዘብ ማግኛ መንገድ አድርገውታል።
  • አንዳንድ የመንግስት የጸጥታ አካላት
የእገታ ወንጀለኞች እኩይ ተግባር የሚሸፋፈነው እና የወንጀል ክትትሉ ደካማ እንዲሆን ያደረገው የአንዳንድ የመንግስት የጸጥታ አካላት የወንጀሉ እና ወንጀሉን ተከትሎ ከሚገኘው ገንዘብ ተካፋይ መሆን ነው።

ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው

ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ህዝብ እና መንግስት ናቸው።

ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

ሁለቱ አካላት ማለት ህዝብ እና መንግስት ምን ይስሩ? ለሚለው ጥያቄ።

ህዝብ
  • ህዝብ ከእድር እስከ እቁብ፣ከአብያተ ክርስቲያናት እስከ መስጂድ በጉዳዩ ላይ መድረክ ከፍቶ መወያየት አለበት፣
  • ህዝብ አካባቢው የሚጠረጥረውን ቤት፣መንደር እና ጉረኖ መፈተሽ ከእገታ ጋር የተያያዘ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተነካኩ ሁሉ ማጋለጥና ወደ ህግ ማቅረብ ይህ ሁሉ ደግሞ በከፍተኛ ህዝባዊ ንቅናቄ መደገፍ አለበት።
  • ንቅናቄው ሁለት ዋና ዋና ተግባራት ሊኖሩት ይችላሉ።እነርሱም ፡
    • በእገታ ፈጻሚዎች እና በዙርያው በተሳተፉ ላይ ማኅበራዊ ቅጣት ማጥበቅ፣
    • ወንጀሉን የፈጸሙ በፎቶም ጭምር በአደባባይ ማጋለጥ፣ለህግ ማቅረብ እና የህግ ሂደቱን መከታተል።
መንግስት
  • በእገታ ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉ ላይ የሞት ቅጣት የሚያሳልፍ ህግ ማውጣት፣
  • በመንግስት የጸጥታ አካላት ውስጥ ሆነው የወንጀሉ ተባባሪዎች ላይ ተመሳሳይ እስከ የሞት ቅጣት የሚያደርስ ቅጣት መወሰን።
  • የጸጥታ ጥበቃ ኃላፊነቱ ከህዝብ ጋር የተሰናሰነ እንዲሆን ማድረግ እና 
  • መገናኛ ብዙኃን በወንጀሉ ዙርያ የተሰሩ ስራዎች እና ወንጀለኞች ምንነታቸው እንዲገለጽ ማድረግ።
=================////==============


Friday, August 9, 2024

''ኢትዮጵያ ልታመልጥ ነው።'' የግብፅ፣የሱማልያ፣የቱርክና የአቶ ኢሳያስ ጭንቀት ጨምሯል። እውን ብልጽግና ''ኒዎ ሊበራሊዝምን'' ሳያላምጥ ውጧል?

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀ ስላሴ በኢትዮጵያ የግብጽ አምባአደር መሐመድ ኦመር ጋድ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተወያዩ በኋላ (ፎቶ ውጉሚ)


==========
ጉዳያችን ወቅታዊ
==========

የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በየቀኑ ብዙ የሚነሱ ጉዳዮች አሉ።በጥቃቅን እና ቅጥልጣይ ጉዳዮች ላይ ብቻ ካተኮርን ትልቁ ሀገራዊ ስዕል ይጠፋል ብዬ አስባለሁ። እንደ ሀገር ብዙ መቀረፍ ያሉብን እራሳችን የፈጠርናቸውም ባዕዳን ያቦኳቸውም ችግሮች አሉብን። ሙስና፣የጸጥታ ችግር፣ጎሰኝነትን ማቀንቀን እና ድህነት ወቅታዊ ችግሮች ሆነው በመሬት ላይ የሚታዩ ችግሮች ናቸው። ሁሉንም ግን በበጎ ህሊና፣በህብረት እና ጠንክሮ በመስራት የሚቀረፉ ለመሆናቸው ቅንጣት ያህል የሚያጠራጥር ጉዳይ የለም።

ከጥቃቅን እና ቅጥልጣይ ጉዳዮች ወጥተን ትልቁ ኢትዮጵያ እየሔደችበት ያለውን ጎዳና ስንመልከት እና ወደመንገድ የገባችበትን አገባብ ተመልክተው የተደናገጡትን የቅርብም የሩቅም ሀገሮች ስንመለከት ከፍተኛ መራወጥ ላይ መሆናቸውን እንመለከታለን። ይህ በእንዲህ እያለም በዶ/ር ዐቢይ የሚመራው መንግስት ከሰሞኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ ብልፅግና ''ኒዎ ሊበራሊዝምን '' ሳያላምጥ ዋጠ የሚል አዲስ ፕሮፓጋንዳ ተከፍቷል።በሁለቱም ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትንሽ እንበል።

''ኢትዮጵያ ልታመልጥ ነው።''  የግብፅ፣የሱማልያና የአቶ ኢሳያስ ጭንቀት ጨምሯል።

ግብጽ በእስራኤል ፍልስጤም ጉዳይ ተወጥራ ከርማ አንድ ዓይኗን ኢትዮጵያ ላይ ጥላ ከርማለች።ቱርክ ወደ 15ኛው ክ/ዘመን የምስራቅ አፍሪካ የባሕር ጠረፍ መቆጣጠር የናፈቃት ትመስላለች። በዘመኑ ቱርክ ከምስራቅ አፍሪካ እስከ ዛንዚባር ያለውን የባሕር ጠረፍ የተቆጥጠረችበት ''ወርቃማ ዘመን'' የምትለው ጊዜን ለማምጣት ሱማልያን ሰፈር ለማድረግ እየሞከረች ነው።በሊያ ጉዳይ ባላንጣ የሆኑት ግብፅና ቱርክ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመምከር ግን አፍ ለአፍ ገጥመው ማውራት ከጀመሩ ሰንብተዋል። አሁን ዘግይቶ የተሰሙ ዘገባዎች ደግሞ ግብጽ በሱማልያ ጦሯን ለማስፈር ማሰቧ ብቻ ሳይሆን የሚሰፍረው ጦር ደግሞ በኢትዮጵያ ድንበር አጠገብ መሆኑ ነው የተሰማው።

በእዚህ ሁሉ መሃል ወጡ እንዳማረላት ወይዘሮ ከካይሮ እስከ ሞቃዲሾ ደብዳቤ በመጻጻፍ እና እራሳቸው ካይሮ ላይ ብቅ ጥልቅ ያበዙት አቶ ኢሳያስ ናቸው።አቶ ኢሳያስ ሠላሳ ሦስት ዓመታት ሙሉ ልማት ያላመጡላት ግን ወጣቶችን በውትድርና በማሰልጠን የተጠመዱት አቶ ኢሳያስ ግራ መጋባታቸው በግልጽ እየታየ ነው። አቶ ኢሳያስ አንዳንዴ ''ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ'' እንዲሉ የግብፅ አማካሪ ብቻ ሳይሆን አልሲሲ ከሚያስቡት በላይ ገፊ ሀሳብ እያመጡ የቆስቋሽነት ሚና የሚጫወቱት ለግብጾች ኢትዮጵያን በሚገባ የሚያውቁ ''ኤክስፐርት'' ነኝ የሚል አቀራረባቸው ነው ሲሉ አንድ የምዕራብ ዲፕሎማት መናገራቸው ተሰምቷል። 

በሌላ በኩል አቶ ኢሳያስ ሎተሪ ያመለጣቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስመራ ድረስ ሔደው ስለ ምጣኔ ሐብታዊ ትስስር በተለይ የአቶ ኢሳያስ መንግስት ወደ ኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት እንዲቀርብ እና በምላሹ የኢትዮጵያን ታሪካዊ እና ጂዮግራፊያዊ ወደብ በር እንዲከፍቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ ያሳዩት ዘገምተኝነት ነው። በወቅቱ የነበረውን ስምምነት ተከትሎ ወደ አሰብ የሚወስደው መንገድ ዕድሳት መጀመሩን እና መፋጠኑን በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሳይቀር ተመልክተን ነበር። ሆኖም ግን አቶ ኢሳያስ ወደነበሩበት የ ''ስኩዌር ዋን '' ጉዳይ ሲመለሱ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጉዳዩን ወደ አደባባይ አመጡት። በመቀጠልም 120 ሚልዮን ሕዝብ በ20 ኪሎሜትር የባሕር እርቀት ላይ ታፍኖ ቢኖር ማንም በሰላም ውሎ እንደማያድር ይህ ተፈጥሯዊ ጉዳይ እንጂ ብዙ ትንተና እንደማያስፈልገው በግልጽ ተናገሩ። ይህ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ ከሱማሌ ላንድ ጋር የባሕር ወደብ ብቻ ሳይሆን የባሕር ኃይል ሰፈርም እንደሚኖራት እኤአ ጥር 1፣2024 ዓም አዲስ አበባ ላይ ይፋ ሆነ። 

''ኢትዮጵያ ልታመልጠን ነው '' የሚለው የግብፅ፣ቱርክ፣ሱማልያ እና የአቶ ኢሳያስ ጭንቀት የኢትዮጵያ በቀይባሕር በኩል የመከሰቷ ጉዳይ ቀዳሚ ቦታ ይዟል። ይህንን ጉዳይ ደግሞ ከእነኝህ ሀገሮች ውጭ ዓለም አቀፋዊው ነባራዊ ሁኔታ በግልጽ መግለጫ አያውጣ እንጂ የኢትዮጵያን በቀይባሕር የመከሰት ጉዳይ የተቃወመ የለም። ይልቁንም አቶ ኢሳያስ ከየመን ሁቲ አማጽያን ያላዳኑት የቀይባሕር ባለ 120 ሚልዮን ህዝብ ሀገር እና በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ ምጣኔ ሐብት ያላት ኢትዮጵያ የተሻለ የንግድ መስመሩን ልትጠብቅ እንደምትችል ዓለም ገብቶታል።

ይህ በእንዲህ እያለ ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካን ብቻ ሳይሆን የግብጽና የኤርትራን ጂኦፖለቲካ የመሳብ ሚና (Pulling role) ኢትዮጵያ በሁለት መንገዶች እየተጫወቸች መሆኑ በግብፅም ሆነ በኤርትራ ላይ ጥላውን አጥልቷል። ይህ ጥላ ደግሞ ኢትዮጵያ አመለጠችን በሚል ያዙኝ ልቀቁኝ አስከትሏል። የኢትዮጵያ የመሳብ ሚና በግብጽ አንጻር የተከሰተው በዓባይ ግድብ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቅ ተረጋግጧል።በአጭሩ የግብፅ የቧንቧ ውሃ መክፈቻና መዝግያ በኢትዮጵያ እጅ መገኘቱን ዓለም አቀፍ ኃይሎች ግልጽ ሆኖላቸዋል። ኢትዮጵያ ደጋግማ የአባይ ውሃን በጋራ ተጠቃሚነት ላይ እንደምታምን መግለጿ ይታወቃል።ይህም ሆኖ ግን የጂኦ ፖለቲካውን የመሳብ አቅሟ ከግብፅ አንጻር መቶ ከመቶ የተረጋገጠ መሆኑ ላይ የሚጠራጠር የለም።

በሌላ አንጻር የኢትዮጵያ በህንድውቅያኖስና የቀይባሕር አካፋይ አካባቢ በባሕር ኃይል ይዛ መከሰቷ በጂቡቲም ሆነ በኤርትራ በኩል ከመሬት ሌላ በባሕር ኃይል መገኘቷ የኤርትራን ጂኦ ፖለቲካ ላይ በቀጥታ ያጠላበታል። ይህ ጥላ ደግሞ ያድጋል። አድጎ የት እንደሚደርስ አሁን ለመናገር አይቻል ይሆናል። ነገ ግን ይቻላል።

ቱርክ በሌላ በኩል ሱማልያ ከረጅሙ የእርስበርስ ጦርነት እንዳገገመች በመጀመርያ ከኢትዮጵያ ቀጥላ የተገኘች ሀገር ነች። ቱርክ በሱማልያ ግዙፍ የአይሮፕላን መንደርደርያ፣መዝናኛ ሆቴል እና ሌሎች ስራዎች ላይ መሰማራት የጀመረችው ቀድማ ነው። በያዝነው ዓመት ኢትዮጵያ ከሱማልያ ላንድ ጋር የወደብ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ ደግሞ የወታደራዊ ስምምነት ከሱማልያ ጋር ለመፈጸም አልዘገየችም። ቱርክ ሱማልያ ላይ ያላት ፍላጎት የተፈጥሮ ሃብት ዝርፍያ እና አካባቢያዊ ተጽኖ ፈጣሪ ሆኖ መከሰት ፍላጎቷ ነው።ይህም ሆኖ ቱርክ ግብጽ ወደ ሱማልያ እንድትመጣባት አትፈልግም። ግብጽና ቱርክ በሊብያ በነበረው ጦርነት በነከሩት እጅ መጠን መቆሳሰላቸው ቢታወቅም ኢትዮጵያን ለመክበብ እና የሱማልያን የተፈጥሮ ሃብት ለመዝረፍ ግን ለመስማማት ሲሞክሩ ይታያሉ።
ይህም ሆኖ ግን ቱርክ በኢትዮጵያ ያላት መዋዕለ ንዋይ እና ከኢትዮጵያ ጋር መጣላት በምስራቅ አፍሪካም ሆነ በአፍሪካ አንጻር ያለውን ወጪ ስላሰሉት በኢትዮጵያ እና በሱማልያ መካከል የሰላም ንግግር አንካራ ላይ ማስጀመራቸው እና ሰሞኑንም ሁለተኛውን ክፍል ንግግር ለማድረግ እየተዘጋጁ ነው። እዚህ ላይ ግን ግብፅ፣ቱርክ፣ሱማልያ እና አቶ ኢሳያስ የገባቸው ጉዳይ አንድ ነገር ነው። ኢትዮጵያ ልታመልጣቸው መሆኑ ገብቷቸዋል። ሊያስቆሟት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። ነገር ግን አልቻሉም። አሁን እየሞከሩት ያለው ከበባ ለመፈፀም ነው። ቱርክ እና ግብጽ በሱማልያ በኩል፣ አቶ ኢሳያስ በሰሜን በኩል ኢትዮጵያን ለመክበብ ይሞክራሉ። ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል መከሰቷ የሚያማቸው እንግዲህ ከበባው የተሟላ የማያደርገው ይሄው የኢትዮጵያ በባህር በር በኩል መከሰት ነው።

እውን ብልጽግና ''ኒዎ ሊበራሊዝምን'' ሳያላምጥ ውጧል?

ሰሞኑን አንድ ወዳጄ ደወለልኝና የእርሱ አባባል ነው፣ስለ ቃሉ ይቅርታ እየጠየኩ ''አንድ እንቁራሪት የዋጠ የሚመስል ዩቱበር ያቀረበውን ዘገባ ሰማህ?'' አለኝ። ዘገባው አቶ መለስን የኒዎ ሊበራል ተከላካይ እና የሀገር ሉዓላዊነት ጠባቂ አድርጎ ያቀርብና ብልፅግና ''ኒዎ ሊበራሊዝም ሳያላምጥ የዋጠ'' በማለት ያቀርበዋል።

ዘገባውም ሆነ ዘጋቢው አፍቃሪ ህወሓትም ቢሆንም የሚነገረን ታሪክ ግን የጥንት ታሪክ ሳይሆን በሕይወታችን ያየነውን እና የምናውቀውን ጉዳይ ነው። አቶ መለስ ''ልማታዊ መንግስት '' በሚል በዓለም ንግድ ማዕከል የነገሩን እና ሀገር ውስጥ መሬት ላይ የሰሩትን ማስታወስ ነገሩን ግልጽ ያደርገዋል። እዚህ ላይ ኢትዮጵያ በወታደራዊው መንግስት ዘመን በነበራት ምጣኔ ሀብት ደረጃ አቶ መለስ አቆይተዋታል የሚል ክርክር እያነሳሁ አይደልም። በመኖር ብቻ የሚመጣም ዕድገት አለ። ነገር ግን ልማታዊ መንግስት ብለው ኢትዮጵያን በምጣኔ ሀብት መንገድ የገፏት ወዴት ነበር? ብሎ መጠየቅ ግን ተገቢ ነው።

አዎን! አቶ መለስ በዓለም ንግድ ኮንፍረንስ ላይ የግል ባንክ አናስገባም፣ ቴሌን አንሸጥም ብለዋል። ቀጥለው ግን ወደፊት ግን እናደርጋለን የሚል ጨምረውበታል። ወደ ፊት ያሉት በ2016 ዓም ነው ወይንስ በፊት አይታወቅም። እርሳቸውን ሞት ስለቀደማቸው። አቶ መለስ ግን ይህንን ካሉ በኋላ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት በአፍሪካ ግዙፍ ብለው አቦይ ስብሐት በጠሩት በትግራይ ልማት ማኅበር የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት ጠፍረውት በዓለም መድረክ ግን ልማታዊ መንግስት ነን የሚል ንግግር ማሰማታቸውን የዘነጋን ካለን የማስታወስ ችግራችን እንጂ በዘመናችን ያየነው እውነት ነው። ይህ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ በጎሳ በተደራጀ የምጣኔ ሀብት አደረጃጀት ተፈርዶባት፣ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ብድር ወስዳ ጨርሳ ኮሜርሻል ብድር የገባች ሀገር ብቻ ሳትሆን፣ 'ግሎባል ፋይናንሻል እንተክግርቲ'' የተሰኘ አለምአቀፍ ድርጅት ባወጣው ሪፖርት ከ 2000  እስከ 2009 ዓም እኤአ   ብቻ ከኢትዮጵያ ከ 11.7(አስራአንድ ነጥብ ሰባት ቢልዮን ዶላር) ቢልዮን ዶላር በላይ በህገወጥ መንገድ መውጣቱን የገለጠው በአቶ መለስ የልማታዊ መንግስት ስም በተጀቦነ ፖሊሲ በክሉ መሆኑን ከረሳነው እናስታውሰው።

በዶ/ር ዐቢይ የሚመራው የብልፅግና መንግስት ''ኒዎ ሊበራሊዝምን '' ሳያላምጥ ውጧል? የሚለውን ጥያቄ የጠየኩት መጀመርያ ለራሴ ነው። ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአማካሪ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ጋር የሄዱበት መንገድ ''ኒዎ ሊበራሊዝምን '' ሳያላምጡ የዋጡ መሪ አያደርጋቸውም። ይህንን ለመረዳት በመጀመርያ ኒዎ ሊበራሊዝም ምንድን ነው? የሚለውን በመጠኑ ማሳየት ያስፈልጋል።

ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም ጀምሮ የኒዎ ሊበራሊዝም ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ፍልስፍና በአለማችን ላይ በምዕራቡ ዓለም ሰፍኖ የቆየ ብቻ ሳይሆን የምስራቁን የኮሚኒስት ዓለም መገዳደርያ ርዕዮተ ዓለም ሆኖ በአዲስ መልክ ተነቃቃ። አዲሱ ሊበራሊዝም (Neo-liberalism) እንደ ሰደድ እሳት በተለያዩ አህጉሮችና ሀገራት ውስጥ እንዲቀጣጠል ያደረገው በእንግሊዝ የጠቅላይ ሚኒስትር ታቸር ወደ ስልጣን መምጣት እና በአሜሪካ ደግሞ የሮናልድ ሬገን ዋይት ሃውስ መግባት ለኒዮ ሊበራሊዝም መስፋፋት ወርቃማ ዘመኑን አመጣ። ኒዎ ሊበራሊዝም መሰረታዊ ፍልስፍናው ምጣኔ ሀብቱን ለግል ባለሃብቱ በመልቀቅ መንግስት ያለውን ሚና በሂደት እየለቀቀ ይምጣ የሚል ሃሳብ ገዢው ሀሳብ ነው። 

ይህንን መሰረታዊ ሃሳብ በምጣኔ ሀብት ጠበብት የራሱ የሆነ መከራከርያ ነጥቦች ቢይቀርቡበትም በኢትዮጵያ ግን ከኒዎ ሊበራሊዝም አንጻር የአቶ መለስ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ አፈጻጸም በትንሽ ብልጭታ አንስተን መሄዱ ብዙ ነገር ግልጽ ያደርጋል ብዬ አምናለሁ። የአቶ መለስ የምጣኔ ሀብት አፈጻጸም ግዙፉን የምጣኔ ሀብት ባለቤትነት ኤፈርት ተቆጣጥሮ የቀረውን የመንግስት ተቋማት ደግሞ አሁንም በጎሳዊነት ላይ የተመሰረተ አሿሿም ላይ የተመሰረተ አካሄድ ተከትለዋል። ለምሳሌ የሜቴክን እንቅስቃሴ ማስታወስ በቂ ነው። ሜቴክ የህወሃት የጦር ሹማምንት የግል ንብረት በመሰለ መልኩ በኢትዮጵያ ሃብት ሲመዘብር ምዝበራውም በጎሳ በተደራጁ ግለሰቦች ኪስ እንዲገባ ተደርጎ ኖሯል።

የአቶ መለስ ልማታዊ እየተባለ የተጠራው ፖሊሲ የመንግስትን ተቋማት አጠናክራለሁ ቢልም ቁልፍ የሆኑ የኢትዮጵያ የገንዘብ ተቋማት ከማዳከም አልፎ ለመዘጋት እሩብ ጉዳይ አድርሶት ለውጡ መጥቷል። ለእዚህ ማሳያ የሚሆነው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ላይ የደረሰው ጥፋት ነው። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተለይ ከ5 ቢልዮን ብር በላይ ዕዳ የገባው በብሔር የተደራጁ ብድር በጋምቤላ ለታደሉት ጠፍ መሬት በመስጠት ነበር። ከኒዎ ሊበራል የራኩ ነኝ። ኒዎ ሊበራልን ሳላላምጥ አልውጥም አሉ የተባሉት አቶ መለስ በተቃራኒው የመንግስታዊ ቁልፍ ተቋማትን ግን በእዚህ ደረጃ ሲያጎሳቁሉ ተዉ ያለ የለም።

ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ የደከሙባትን ቁልፍ መንግስታዊ ተቋማት ያጠናከረችባቸው ዓመቶች ናቸው። በኪሳራ መንገድ ላይ ሲቆዝም የነበረው የልማት ባንክ ዛሬ ከኪሳራ ወጥቶ በርካታ የሀገሪቱን ማክሮ ፕሮጀክት ላይ መሳተፍ ጀምሯል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መስርያቤቱን ከመጨረስ አልፎ የነበሩበትን የተበላሹ ብድሮች ከመቀነስ አልፎ አሁን መልሶ የመሪነቱን ሚና በሚገባ እየተጫወተ ነው። የኢትዮጵያ ቴሌ ኮምዩኒኬሽን ዛሬ ከግዙፍ የመንግስት ተቋማት አንዱ ከመሆን አልፎ የገንዘብ ማስተላለፍ ስራ አልፎ በሚሰጠው የኦንላይን ክሬድት ጨምሮ ከ70 ሚልዮን በላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ተደራሽ ያደረገው ባለፉት አምስት ዓመታት ነው። 

ለማጠቃለል የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግስት ባለፉት አምስት ዓመታት ያሳየን የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ጭልጥ ብሎ የኒዎ ሊበራል መንገድን የተከተለ ላለመሆኑ ማሳያው የመንግስት ሚና ከምጣኔ ሀብቱ ውስጥ መገለል አይደለም ዋና ተዋናይ መሆኑን የሚያምን መሆኑን ለማወቅ ባለፉት አምስት ዓመታት ትኩረት ሰጥቶ ያጠናከራቸው ቁልፍ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን መመልከት ነው። ሌላው ቀርቶ በቅርቡ ከዓለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍ ጋር በነበረው የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ድርድር ላይ የመንግስትን ቁልፍ የምጣኔ ሀብት ተዋናይነት ለድርድር አለማቅረብ ብቻ ሳይሆን ዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍልን መደጎም የሚለውን ሀሳብ የዓለም ባንክ የማይደግፈው ሃሳብ ቢሆንም መንግስት ለድርድር ያላቀረበው ብቻ ሳይሆን መንግስት በመሪነት የሚፈጽመው መሆኑን ገልጾ የገባበት ስራ ነው። በኒዎ ሊበራል ሀሳብ መንግስት በፍጥነት ከሁሉም የምጣኔ ሀብት ሚና ይውጣ የሚለው አባባል ሳትቀበል መሄድ የሚከፈልበት ዋጋ አለ። መንግስት ''ኒዎ ሊበራልን '' ሳያላምጥ ዋጠው ከማለት፣ የመንግስት በምጣኔ ሃብት ዘርፍ የሚጫወተውን ሚና እያጎላ የግል ዘርፉን ለኢንቨስትመንት በሚያግዝ መልኩ ለምሳሌ የውጭ ምንዛሪ ተመን እጁን አነሳ የሚለው አገላለጥ የተሻለ ነው። በውጭ ምንዛሪ ተመን አንጻርም አሁንም የአንበሳው ድርሻ የሚይዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመሆኑ ተመኑ ላይ አሁንም መንግስት በሚፈልገው መንገድ የማጥላት ዕድሉ ከተወሰኑ ወራት በኋላ አይመጣም ማለት አይቻልም። ምክንያት አሁንም አብዛኛውን የውጭ ምንዛሪ በንግድም ሆነ በብድር እጁ የማስገባት የአንበሳው ድርሻ የመንግስት መሆኑ ከኢትዮጵያ አንጻር ቢያንስ በአሁኑ ሰዓት ግልጽ ነው። ባጭሩ መንግስት ''ኒዎሊበራሊዝምን '' ሳያላምጥ ሲውጥ ቢያንስ በገሃዱ ዓለም አላየንም።ዩቱብ ላይ ግን እንደመጣ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ማውራት ይቻል ይሆናል።
========================//////=============


 


Tuesday, July 9, 2024

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።



==========
ጉዳያችን ወቅታዊ
==========

የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለም በፖለቲካ፣ምጣኔሃብት ግንኙነት እና የወታደራዊ አሰላለፎች በየጊዜው የተለያዩ ቅርጽ እየያዙ ብቻ ሳይሆን ፍጥጫዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ እያየሉ መጥተዋል።

እነኝህ ለውጦችበበለጠ በቅርብ ቀጣይ ጊዜም ቀጣይ ለመሆናቸው ብዙ ማሳያዎች ቢኖሩም፣የተወሰኑትን ለመጥቀስ፡
  • የመካከለኛው ምስራቅ ከአርባ ዓመታት በላይ በመለስተኛ ግጭት ውስጥ ቆይቶ አሁን በእስራኤል እና በኢራን እንዲሁም ከሊባኖስ ጋር ያለው ግጭት ከቱርክ እስከ ኳታር ያዘለው ሌላ ደመና አለ።
  • አውሮፓ ሩስያ ከዩክሬን በመቀጠል ትወረኛለች በሚል ስጋት ላይ ነው።የኔቶ ጉባዔ ዋና አጀንዳው ዩክሬን ይሁን እንጂ የሩስያ ቀጣይ መንገድ ወዴት ነው? የሚለው ውዥንብር ላይ የጠራ አቋም መያዝ የጀርባ አጀንዳ ነው።
  • አሜሪካ በቀጣዩ ምርጫ የሚመጣው ገና አልታወቀም። ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ለኔቶም ሆነ ለአውሮፓ ጸጥታ አሜሪካ የምትገፈግፈው ገንዘብ ትክክል አይደለም ባይ ናቸው። አውሮፓ ከእዚህ አንጻርም የጸጥታ ዋስትናው ላይ መደናገር አለ።
  • ሩስያና ሰሜን ኮርያ ከሰሞኑ ያደረጉት የቆየውን የወታደራዊ ትብብር ማደስ ሩቅ ምስራቅ ላይ ያለውን አሰላለፍ ቀይሮታል።
  • ብሪክስ የአሜሪካንን ዶላር አስቀርቶ በራሱ በሃገራቱ ገንዘብ ንግድ ለማካሄድ ስራ ጀምሯል።
  • ምስራቅ አፍሪካ የሚሆነው ሁሉ የኢትዮጵያን አካሄድ ተከትሎ ወዴት እንደሚሄድ አላወቀም።ጂቡቴ ኢትዮጵያ ከሱማልያ ላንድ ጋር በወደብ እና የባሕር ኃይል ጣብያ የመመስረት ውል ተከትሎ ገቢዋ እንደሚቀር አውቃ ሱማሌ ላንድን ለመበጥበጥ ስታሰላስልና ስትሞክር ተይዛለች።
  • ሱማልያና የአቶ ኢሳያስ ኤርትራ ጧት ማታ እየተገናኙ በኢትዮጵያ ላይ ይዶልታሉ።ግብጽ በእያንዳንዱ የኤርትራና የሱማሊያ ዱለታ ላይ ሁሉ አለች።
  • ሱዳን በጦርነት እየታመሰች ነች፣ሱማልያም በፈረሰ መንግስት ላይ የተቀመጠ መንግስት አላት።ኬንያ በውስጥ የታመቀ የብሶት ጠኔ ላይ ለመሆኗ የሰሞኑ አመጽ ማሳያ ነው።
  • ቀይ ባሕርን የአቶ ኢሳያስ አስተዳደርም ሆነ የሳውዲ ባሕር ኃይል የሚያልፉትን መርከቦች ከሁቲ አማጽያን ለማስጣል የማይችሉ መሆናቸውን የዓለም ንግድ ሲታወክ ምንም ማድረግ አለመቻላቸውን ዓለም ተመልክቷል።
  • ዓለምን ሰላሟን ለማስጠበቅ አቅም ያለውም ሆነ ተጽዕኖ ፈጣሪ ተቋም አልባ ሆናለች።የዓለምን ሰላም ማስጠበቅ አንዱ ስራው ሆኖ የተመሰረተው የተባበሩት መንግስታት የምስራቅና የምዕራብ መራኮቻ ብቻ ሳይሆን ''ሳንድዊች '' ሆኖ የሚናገረው የማይሰማ፣የሚለው የማይደመጥ ሆኗል።ለእዚህ ማሳያው በዩክሬንም ሆነ በመካከለኛው ምስራቅ ባለፉት ወራት ውስጥ ለተፈጠረው ግልጽ ጦርነት አንዳች ሚዛን የሚደፋ የመፍትሄ ሃሳብ አቅርቦ ያልተደመጠበት መሆኑን ብቻ መመልከት በቂ ነው።
ከላይ ያለው ወቅታዊው የዓለማችን ሁኔታ የሚከተሉትን አዝሎ እንደሚመጣ ግልጽ ያልሆነልን ካለን ቢያንስ መገመት ብንጀምር መልካም ነው። አዝሎ ከሚመጣቸው ጉዳዮች ውስጥ ፡
  • የአለማችን የምግብ ቀውስ ሊባባስ ይችላል።
  • በማናቸውም ጊዜ ምንም ሊሆን ይችላል።
  • በቅርብም ሆነ በሩቅ ሀገሮች መሃከል ጦርነቶች፣ወረራዎች እና ግጭቶች በማንኛውም ሰዓት ሊፈጠሩ ይችላሉ።ምሽት በሰላም ተኝቶ ማለዳ ላይ የአንድ ሃገር ይዞታ በአየር እየተደበደበ መመልከት ሊደጋገም ይችላል።
  • የአካባቢ ''ግልገል ኃያላን '' ይህንን የዓለም አቀፍ ህግ መላላት ተከትለው በተፈጥሮ ሃብት ሲመኟቸው የኖሩ ሀገሮችን ለመውረር እና የውስጥ ቀውሳቸውን ለማስታገስ ሊሞክሩ ይችላሉ።
  • የዓለማችን የኃያላን ሀገሮች ፍጥጫ እና ግጭት በቀጥታ ሳይሆን በ''ግልገል ኃያላን'' በኩል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ይሮጣሉ።
  • የቀኝ አክራሪዎች እና የስደተኛ ጠል ፓርቲዎች በወቅቱ የዓለም ችግር እያስታከኩ በሀገራቸው የበለጠ የመደመጥ ዕድል የሚያገኙበትና የዘረኝነት አካሄዶች የበለጠ ሊባባሱ ይችላሉ።
ወቅታዊ የኢትዮጵያ፣የአፍሪካ እና የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።

ከላይ በመጠኑ ለመዘርዘር የተሞከሩት እየመጣ ያለው እና ወቅታዊው የዓለማችን ሁኔታ ለኢትዮጵያ ከአደጋ ይልቅ ባብዛኛው ዕድል ይዘው መጥተዋል። ይህ ግን እኛው በኛው ካልገፋነው እና ካላጨናገፍነው ነው።ይህ ወቅት የዓለም  የእጥፋት(turning point) ወቅት ነው።ብዙ ሀገሮች የዓለም እጥፋት ወቅት በተነሱላቸው መሪዎች ተጠቅመው ሃገራቸውን አስፈንጥረዋል። ኮርያ፣ሲንጋፖር፣ታይዋን፣ህንድ በምስራቁና የምዕራቡ ፍትግያ ውስጥ በአንዱ ጎራ ከመግባት እስከ ገለልተኝነት ፖሊሲ ተከትለው ሃገራቸውን ያስፈነጠሩ ናቸው።

ኢትዮጵያ በጂኦ ፖለቲካዊ አቀማመጥ፣በህዝብ ብዛት፣በመላው ዓለም በሰለጠነ የሰው ኃይል፣በታሪክ ሃብት ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ በነበራት እና በቀላሉ መልሳ ልታነሳው የተዘጋጀ ማንንነት ባለቤት መሆኗ እና የተፈጥሮ ሃብቷ ጭምር የሩቅም ሆነ የቅርብ ሀገር የምታማልል ሃገር ነች።ኢትዮጵያ ይህንን የእጥፋት ጊዜ እጅግ ስልታዊ በሆነ መንገድ መጥቀም ከቻለች ትልቅ ዕድል ከፊቷ ይጠብቃታል።

ኢትዮጵያ ዛሬ በጎጥና በመንደር የሚነተርካት፣ ልጆቿን በጦርነት የሚማግድ አጀንዳ የሚፈለፍልባት፣ የእኔ መንደር ሰው ብቻ ስልጣን ሲይዝ ሀገር ይረጋጋል እያለ የሚሰብክባት፣በልጆቿ ግጭት ባሕር ማዶ ሆኖ በጦርነት ስም ገንዘብ እየሰበሰበ የማይሞላ ሆዱን የሚሞላ ሰው አያስፈልጋትም። ጊዜው ለኢትዮጵያ ወሳኝ ጊዜ ነው። ወቅቱ ኢትዮጵያ የዓለም እጥፋት እንዲያስፈነጥራት መስራት የሚገባበት ጊዜ ነው።ይህንን ለማድረግ ብዙ ዕድሎች መንገዶች ከፊታችን አሉ።የውስጥ ንትርኮችን ለማጥገግ የምክክር ኮሚሽን ጥረት እያደረገ ነው።የዓለምን የእጥፋት አካሄድ ብቻ ሳይሆን ምን ላይ ማትኮር እንዳለባት የሚረዳ መሪ ኢትዮጵያ አላት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተለያዩ ንግግሮቻቸው የዓለም የእጥፋት ጊዜን መጠቀም እና ሀገር ማስፈንጠር እንደሚገባ እና እንደሚቻል ተናግረዋል።
በሀገር ውስጥ ቁልፍ ጉዳዮች በሚል ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚሰሩት ስራዎችን ስንመለከት ብዙ ጉዳዮች ለኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች አሉ።ይህ ማለት የሚያስከፉ፣የሰዎች ሞት፣መፈናቀል እና ስደት ቆሟል ማለት አይደለም። እነኝህ ፈተናዎች ግን እኛው በሚድያ፣በውሸት ትርክት፣ለገንዘብ እና ለስልጣን ተብሎ የሚደረግ የስግብግብ ''ኤሊት '' ፖለቲካና የባዕዳን ሴራ ውጤት መሆኑን ለማመን ብዙ እርቀት መሄድ አያስፈልግም።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የዓለምን እጥፋት ተከትሎ እየሰራች ላለቸው ማሳያዎች በርካታ ማሳያዎች አሉ።ከእነዚህ ውስጥ ፡ የዲፕሎማሲው በሱዳን ጉዳይ ሳይቀር የመካከለኛውን ምስራቅ የሚገዳደር ደረጃ እንዲደርስ ብቻ ሳይሆነ የግብፅ ቦታ እሲኪደበዝዝ ድረስ እየተሄደ ያለው ሂደት፣ኢትዮጵያ ከሦስት አስር ዓመታት በላይ ሳታነሳው የቆየው የባሕር በር ጉዳይ በግልጽ ይዛ የወጣችበት ሁኔታ፣በምግብ ራስን ለመቻል የምትሰራው ስራ፣ኢትዮጵያን አረንጓዴ ለማልበስ የተደረጉት ዘመቻዎች፣ ቱሪዝምን ያማከሉ የሪዞርት ግንባታዎች፣ የአርቴፊሻል ኢንተለጄንስ ስራ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ያለው ለውጥ፣ የመከላከያ ማዘመን ሁሉ የዓለም የእጥፋት ሂደት ውስጥ በብዙ እንዴት ለማትረፍ እንደምትችል እና የሚገባትን ቦታ ለመያዝ የምታደርገው ጥረት አካል ሆኖ ይታየኛል። ከውጭ ሆነን ጦርነት የምንጎስም፣መንግስት እንደሸሚዝ ለመቀየር የምንመኝ፣ የእኔ ሰፈር ሰው ቤተመንግስት ካልገባ ኢትዮጵያ አትኖርም እያልን የምንሰብክ ሁሉ በኢትዮጵያ ወሳኝ ጊዜዋ ላይ ቆመን ለማሰናከል የምንታትር የልጅ እርግማን ሆነንባታል። ያልገባን ካለን፣ እስኪገባን ዝም ብንል። የዓለም እጥፋት ኢትዮጵያን እንዲያስፈነጥር የገባን ካለን ዝምታችንን ሰብረን፣ ኢትዮጵያን እና ለኢትዮጵያ የሚለፉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ብናበረታታ እና ሀገር ብናግዝ። ከእዚህ ውጪ ለኢትዮጵያ እናቷን ሙቀጫ እንደምትወቅጥ ዘነዘና ባንሆንባት? ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።
_________________________________





Monday, June 3, 2024

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታላቅ ተልዕኮ የሚኖረው ሀገራዊ የምምክር ኮሚሽን በተመለከተ ምን ያህል እናውቃለን?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባካተተ መልኩ አዋቅሯል።


በእዚህ ጽሑፍ ስር የሚከተሉት ነጥቦች ምላሽ ያገኛሉ፡ 
  • ኮሚሽኑ እንዴት ተመሰረተ? 
  • የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመረጡ?
  • የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እነማን ናቸው? የትምሕርት ዝግጅታቸውና ልምዳቸውስ?
  • የኮሚሽኑ ርዕይ፣ተልዕኮ፣ዓላማው እና መርሆዎቹ ምንድን ናቸው?
  • የኮሚሽኑ ተግባርና ኃላፊነቶቹ ምንድን ናቸው?
  • የኮሚሽኑ ምክርቤት ተግባርና ሥልጣን ምን ምን ናቸው?
  • የምክክር ኮሚሽኑን የኢትዮጵያ ደህንነት እና ሰላም አንዱ እና ዋናው መፍትሄ አድርጎ መውሰድ ይቻላል?
  • የውይይት ሰነዶች ከውይይት በኋላ ምን ይሆናሉ?

=========
ጉዳያችን ልዩ 
=========

መነሻ 


ኢትዮጵያውያን ላለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ከመሰረታዊ ችግሮቻችን ውስጥ ደጋግመው የሚነሱት እና ለሀገር መቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ደጋግሞ ሲወሳ ከነበረው ውስጥ አንዱ የተቋማት መመስረት እና መጠናከር ጉዳይ ነው። የመንግስት መምጣት እና መሄድ ጉዳይ አንድን ሀገር ለመተራመስ እንዳይዳረግ ከሚያደርጉት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የጠንካራ ሀገራዊ ተቋም የመኖር ፋይዳ ነው።

ባለፉት ስድስት ዓመታት እያየን ያየነው አንዱ እና በጎ ተግባርም ይሄው የሃገራዊ ተቋማት መፈጠር ነው። ተቋማቱ ደግሞ ካለፉት መንግስታት እጅግ በተሻለ እና አንዳንዶቹ በጥሩ ነፃነት የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው ነው። ምንም እንኳን የተቋማቱ አመሰራረት ሕጋዊ ዕውቅና የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ይስጥ እንጂ የተቋማቱ የትኩረት አቅጣጫ፣የመሪዎቻቸው ነፃነት እና የአፈፃፀማቸው ውጤት እጅግ ተስፋ ሰጪ ነው። ከእነኝህ ተቋማት ውስጥ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣የምርጫ ቦርድ እና የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን መጥቀስ ይቻላል። የዛሬው ትኩረቴ የኢትዮጵያ ምክክር ኮሚሽን በተመለከተ በተለይ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ የመረጃ ክፍተት እንዳይኖረው በሚል በእዚህ ጽሑፍ ውስጥ አስፈላጊ መረጃ ይሰጣሉ ያልኩትን ለመግለጽ እሞክራለሁ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዴት ተመሰረተ?

ታኅሳስ 1፣2014 ዓም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ መሠረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች በተለያዩ ጎራዎች የተሠለፉ የፖለቲካ ልሂቃንም ሆኑ ምልዓተ ሕዝቡ ተቀራራቢና በአገራዊ አንድነት ገንቢ አቋም እንዲይዙና አካታች አገራዊ ምክክር ተግባራዊ ለማድረግ፣ ይህንኑ ምክክር በገለልተኝነት ለመምራትና ለማስተባበር የሚችል ቅቡልነት ያለው ተቋም ለማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውሳኔ ላከው።

በእዚህ መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታኅሳስ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፣ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር ዕይታ ለምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶት የነበረ ሲሆን በእዚሁ ውይይት ላይ  የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የፍትሕ ሚኒስትርና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎችም አካላት ተሳትፈዋል፡፡በውይይቶቹ ውስጥ ከተነሱት እና አጽንኦት እንዲሰጥባቸው ከተወሱት ውስጥ የኮሚሽነሮች አሰያየም፣ አወቃቀርና የኮሚሽኑ አደረጃጀት ላይ ያላቸውን ሥጋትና የገለልተኝነት ሁኔታዎች ላይ ጥልቅ  ውይይት በኃላ ታኅሳስ 20፣2014 ዓም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በረቂቁ ላይ ተወያይቶ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን 11 ያለመከሰስ መብት ያላቸው ኮሚሽነሮች አሉት።በኮሚሽነሮቹ መብዛት ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሃሳብ ሰጥተዋል። የኮሚሽኑ ዋና ተግባር ልዩነትና አለመግባባት ለማርገብና ለመፍታት ሰፋፊ አገራዊ የሕዝብ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ አገራዊ መግባባት ለማምጣት የሚሠራ ነው።

የኮሚሽነሩ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመረጡ?

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማኅበረሰቡ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዕጩ ኮሚሽነሮችን እንዲጠቁም በማድረግ ከ600 በላይ ዕጩ ኮሚሽነሮች መጠቆማቸውን ይፋ ሆነ።
ከእነዚህ ውስጥም ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዕጩ ኮሚሽነር ይሆናሉ ያላቸውን 42 ግለሰቦች ህብረተሰቡ አስተያየት እንዲሰጥባቸው ዝርዝራቸውን ይፋ አደረገ።

በመቀጠል ምክርቤቱ ከማህበረሰቡ የተገኘውን ግብዓት መሰረት በማድርግ መስፈርቱን በከፍተኛ ደረጃ አሟልተዋል ያላቸውን 11 ኮሚሽነሮች ሾሟል።

የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እነማን ናቸው? የትምሕርት ዝግጅታቸውና ልምዳቸውስ?

1.ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ፡

የትምህርት ደረጃ፡ ፒ ኤች ዲ በአእምሮ ህክምና

የስራ ልምድ ፡ በአእምሮ ህክምና ዘርፍ ከ30 አመታት በላይ ያገለገሉ፣ ከ30 በላይ ጥናታዊ ጽሁፎችን ያሳተሙ፣ ብሄራዊ የኤች አይ ቪ ሴክሬታሪያት እንዲቋቋም ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ፣ በተለያዩ የሀገራችን ከፍሎች በመዘዋወር ሆስፒታሎችን የመሩ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና በአማኑኤል ሆስፒታሎች በኃላፊነት ያገለገሉ፣ በተለያዩ ሀገራዊ የሰላም መድረኮች በሚያቀርቧቸው አስተማሪና መካሪ ሀሳቦች በመነሳት ለሀገራዊ መግባባት እየሰሩ ያሉ፡፡

2. ወይዘሮ ሒሩት ገብረስላሴ ፡

የትምህርት ደረጃ: በህግ ማስተርስ ዲግሪ ያላቸው
የስራ ልምድ፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ልዩ መልእክተኛ ሆነው ያገለገሉ፤ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሰሩ

3. ዶክተር ተገኘወርቅ ጌቱ

የትምህርት ደረጃ: ፒ ኤች ዲ እና ሁለት ማስተርስ በኢኮኖሚክስና ፖለቲካ
የስራ ልምድ፡ በተመድ ልማት ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉ፤ በሀገራት የልማት ፕሮግራሞች የመሩ፤ በርካታ ፅሁፎችን ያበረከቱ፤ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ያስተማሩ፤ የልማት ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ያገለገሉ፤ ግጭቶችን ለመፍታት አለም አቀፍ ተሞክሮ ያላቸው፤የተመሰከረ የአመራርና የአስተዳደር ክህሎት ያላቸው

4. አምባሳደር ዶክተር አይሮሪት መሐመድ

የትምህርት ደረጃ: ፒ ኤች ዲ በህግ የስራ ልምድ፡አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ፤ በተለያየ የሀላፊነት ቦታ የሰሩ

5. ወይዘሮ ብሌን ገብረመድህን

የትምህርት ደረጃ: ማስተርስ ዲግሪ

የስራ ልምድ፡የህግ መምህር የነበሩ፤ ያለም አቀፍ ልማት ማዕከል ቢሮ ሀላፊ የነበሩ፤ በቀይ መስቀል ማህበር ውስጥ በአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ በህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ሆነው የሰሩ፤ በሰብአዊ መብት ኮሚሽን እያገለገሉ ያሉ፤

6. ዶክተር ዮናስ አዳዬ

የትምህርት ደረጃ: ፒኤችዲየስራ ልምድ፡ ተመራማሪ እና አሰልጣኝ

7. አቶ ዘገየ አስፋው

የትምህርት ደረጃ: በህግ የማስተርስ ዲግሪ
የስራ ልምድ: ላለፉት 40 አመታት ለሀገራቸውና ለህዝባቸው የሚችሉትን ሁሉ አገልግሎት የሰጡ

8. አቶ መላኩ ወልደማሪያም

የትምህርት ደረጃ: በህግ የመጀመርያ ድግሪ
የስራ ልምድ፡ ጠበቃና የህግ አማካሪ፣ በህዝባዊ ተቋማት በርካታ ሁኔታ አገልግሎት የሰጡ፣ በሽግግር መንግሰት ምክር ቤት በህግ አማካሪነት፤ በመንግስት ምክር ቤት በህግ ባለሙያነት፤ በኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ጉባኤ (ኢሠመጉ) ዋና ፀሀፊነት፤ በልማት ማህበራት በአመራርነት የሰሩ፡፡

9. አምባሳደር መሃሙድ ድሪር

የትምህርት ደረጃ : በህግ የማስተርስ ድግሪ
የስራ ልምድ፡በምክር ቤት አባልነት፤ በአምባሳደርነት፤ በሚንስትርነት፤ በከፍተኛ አማካሪነት፤ በኢጋድ አስተባባሪነት፤ በሱዳን ልዩ መልእክተኝነትና በአፍሪካ ቀንድ ሰፊ ልምድና እውቀት ያላቸው።

10. አቶ ሙሉጌታ አጎ

የትምህርት ደረጃ፡ በህግ የማስተርስ ዲግሪ
የሥራ ልምድ፡ ለ 4 ዓመታት በከፋ ዞን የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ እና ፕሬዚዳንት፣ በደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መ ጠ/ፍ/ቤት ዋና ሬጅስትራርነት ለአንድ ዓመት የሰሩ፣ በዳኝነት ለሰባት ዓመት የሰሩ፣ በም/ ፕሬዚዳትነት ለሁለት ዓመትና በፕሬዚዳንትነት ለ8 ዓመታት ያገለገሉ

11. ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ

የትምርት ደረጃ: በሶሻል አንትሮፖሎጂ ፒኤችዲ

የስራ ልምድ፡ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በመምህርነት እና በአሁኑ ሰዓት በሰላምና ዲያሎግ ከፍተኛ አማካሪነት እያገለገሉ ያሉ ፤ በማክስ ፕላንክ የስነ ህዝብ ጥናት ተቋም ያገለገሉ እና በዚሁ ተቋም የማህበራዊ አንትሮፖሎጂ ተቋም በግጭትና ውህደት ክፍል ውስጥ የድህረ ዶክትሬት ጥናት አድርገዋል::

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ርዕይ፣ተልዕኮ፣ዓላማው እና መርሆዎቹ ምንድን ናቸው?

ርዕይ

የኮሚሽኑ ርዕይ እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ተፈጥሮ ማየት ነው፡፡

ተልዕኮ

በኢትዮጵያ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ ፣ በተለዩ አጀንዳዎች ላይ ሀገራዊ ምክሮችን በማካሄድ፣ ምክረ ሀሳቦችን በማቅረብ እና ለተግባራዊነቱም የመከታተያ ስርዓ በመዘርጋት ለሀገራዊ መግባባት ምቹ ሁኔታ መፍጠር፡፡

ዓላማዎች

  • በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተጠሩ ልዩነቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በመለት እና ውይይቶቹ የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመለየት ምክክር እንዲደረግባቸው ማመቻቸት፤
  • የሚካሄዱት ሀገራዊ ምክክሮች አካታች፣ ብቃት ባለውና ገለልተኛ በሆነ አካል የሚመሩ፣ የአለመግባባት መንስዔዎችን በትክክል በሚዳስስ አጀንዳ የሚያተኩሩ፣ ግልፅ በሆነ የአሠራር ሥርዓት የሚመሩ እና የምክክሮቹን ውጤቶች ለማስፈፀም የሚያስችል ዕቅድ ያላቸው እንዲሆኑ በማድረግ ውጤታማ የሆኑ ሀገራዊ የምክክር ሂደት ተግባራዊ ማድረግ፤
  • የሚካሄዱት ሀገራዊ ምክክሮች በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እንዲሁም በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል፣ መተማመን የሰፈነበትና አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር በሚያስችል አግባብ ውይይቶቹ እንዲካሄዱ ሥርዓት መዘርጋት፤
  • ከምክክሮቹ የተገኙ የመፍትሔ ምክረ ሃሳቦች በሥራ ላይ እንዲውሉ ድጋፍ በማድረግ በዜጎች መካከል እንዲሁም በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመን የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲገነባ ማስቻል፤
  • ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ባህል ለማዳበር እና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምቹ መደላድል መፍጠር፤
  • ወቅታዊ ችግሮች ዘላቂ በሆነ መንገድ ተፈተው አስተማማኝ ሰላም የሚረጋገጥበትን የፖለቲካ እና የማኅበራዊ መደላድል ማመቻቸት፤
  • ለአገራዊ መግባባት እና ጠንካራ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ጽኑ መሠረት መጣል ናቸው።

የምምክር ኮሚሽኑ ተግባርና ኃላፊነቶች

  • ምክክሮችን የሚያመቻቹና ሚያስፈጽሙ፣ የተለያዩ ጥናቶችን የሚያካሂዱ እና ምክረ ሃሳቦችን የሚያመነጩ ኮሚቴዎችን እና የባለሙያ ቡድኖችን ያቋቁማል፤
  • ከዚህ በፊት በመንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት የተደረጉ ሀገራዊ የምክክር ሂደቶችን እና የተገኙ ውጤቶችን ያጠናል፣ በቀጣይ ለሚያካሂዳቸው ሀገራዊ ውይይቶች በግብዓትነት ይጠቀማል፤
  • በተለያዩ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉትን ልዩነቶች በጥናት፣ በሕዝባዊ ውይይቶች ወይም ሌሎች አግባብነት ያላቸውን መንገዶች በመጠቀም ይለያል፤
  • በዚህ አንቀጽ ንዑስ አቀጽ (፫) መሰረት በተገለፁት ዘዴዎች የለያቸውን ጉዳዮች መሰረት በማድረግ የምክክር አጀንዳዎችን ይቀርፃል፣ ምክክር እንዲደረግባቸው ያመቻቻል፣ ምክክሮችን እና ውይይቶችን ያሳልጣል፤
  • ከመላ ሀገሪቱ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እና አካላትን የሚወክል ተሳታፉዎች የሚሳተፍባቸው፣ ሀገራዊ መግባባት ለማምጣት የሚያስችሉ የተለያዩ የምክክር ስብሰባዎችን በፌደራል እና በክልሎች ደረጃ እንዲካሄዱ ያመቻቻል፤
  • በሀገራዊ የምክክር ጉባዔ ላይ የሚሳተፉ ተሳታፉዎችን ግልፅ በሆኑ መሥፈርቶች እና የአሠራር ሥርዓት መሠረት ይለያል፣ በምክክሮች ላይ እንዲሳተፉ ያደርጋል፤ ይህን የተመለከተ ዝርዝር መመሪያ ያወጣል፤
  • ምክክሮቹ በኮሚሽነሮች ወይም የኮሚሸነሮች ምክር ቤት በሚሰይማቸው አወያዮች አማካኝነት እንዲመሩ ያደርጋል፤ በአወያይነት የሚመድባቸዉ ሰዎችም በተቻለ መጠን በዚህ ሕግ አንቀጽ ፲፫ ላይ የተመለከቱትን ለኮሚሽነርነት የሚያበቁ መስፈርቶችን የሚያሟሉ መሆናቸዉን ያረጋግጣል፤
  • በምክክር ሂደቶች የሚደረጉ ምክክሮችን ቃለ ጉባዔ የሚዙ፣ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችን የሚያጠናቅሩ እና አደራጅተው ለኮሚሽነሮች ምክር ቤት የሚያቀርቡ ባለሙያዎችን ይመድባል፤
  • የጽህፈት ቤቱን የውስጥ የአሠራር ሥርዓት፣ የምክክር አጀንዳዎች ወይም አርዕስት የሚመረጡበትን የሚመለከት፣ በሀገራዊ ውይይቶች ላይ የሚሳተፉ አካላት የሚለዩበትን ሥርዓት ለመዘጋትና መሰል ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችሉ ውስጠ ደንቦችን እና መመሪያዎችን ያወጣል፣ በሥራ ላይ ያውላል፤
  • የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ አጀንዳዎችን፣ የምክክሮቹን ሂደት፣ በምክክሮቹ የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን እንዲሁም ምክረ ሃሳቦቹ በተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉበትን ሥልት የሚገልጽ ሰነድ በማዘጋጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለአስፈጻሚ አካሉ እና ሌሎች የሚመለከታቸዉ የመንግስት አካላት ያቀርባል፤ ለሕዝብም ይፋ ያደርጋል፤
  • መንግሥት ከሀገራዊ ውይይቶች የሚገኙ ምክረ ሃሳቦችን በተግባር ላይ ለማዋል እንዲችል ግልፅ እና ተጨባጭ የሆነ ዕቅድ እንዲዘጋጅ አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋል፤
  • የምክረ ሃሳቦቹን አፈፃፀም መከታተል የሚያስችል ሥርዓት ይዘረጋል፤ ዓላማውን ለማስፈፀም የሚያስፈልጉ ሌሎች ተግባራትን ያከናውናል።

የኮሚሽኑ ምክርቤት ተግባርና ሥልጣን

  • የሕዝብ ምክክር የሚደረግባቸውን አጀንዳዎች በዝርዝር በመፈተሽ ምክክር እንዲደረግባቸው መወሰን፤
  • በኮሚቴዎች ተዘጋጅተው የሚቀርቡ እና በሕዝባዊ ውይይቶች የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን በዝርዝር በመፈተሸ እና በማጠናቀር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአስፈፃሚ አካላትና ሌሎች የሚመለከታቸዉ የመንግሥት አካላት እንዲቀርብ ማፅደቅ፤
  • የጽህፈት ቤቱን ዓመታዊ በጀትና ዕቅድ መርምሮ የማፅደቅ፤
  • የጽህፈት ቤቱን አጠቃላይ ሪፖርት መርምሮ የማፅደቅ፤
  • አስፈላጊ ኮሚቴዎችን የማቋቋም፤
  • በክልሎች የጽህፈት ቤቱን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች እንዲቋቋሙ የመወሰን፤
  • የጽህፈት ቤቱን የኦዲት ግኝት መርምሮ የማፅደቅ፤
  • የምክር ቤቱ ዋና ኮሚሽነርና ምክትል ዋና ኮሚሽነር በተመሳሳይ ጊዜ በሥራ ገበታቸው ላይ ለተከታታይ አስር ቀናት ካልተገኙ ከአባላቶቹ መካከል ጊዜያዊ ሰብሳቢ የመምረጥ፤
  • የጽህፈት ቤቱን መዋቅራዊ አደረጃጀት የማፅደቅ፤
  • የጽህፈት ቤቱን ኃላፊ ሹመት የማፅደቅ፤
  • አዋጁን ለማስፈፀም የሚያስፈልጉ መመሪያዎችን የማውጣት፤
  • የኮሚሽነሮች የሥነ ምግባር መመሪያ የማውጣት፤
  • የጽህፈት ቤቱን የመተዳደሪያ ደንብ የማውጣት፤

የምክክር ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ ደህንነት እና ሰላም አንዱ እና ዋናው መፍትሄ አድርጎ መውሰድ ይቻላል?


የዛሬ ሦስት ዓመታት በታኅሳስ አጋማሽ ላይ የእዚህ ዓይነት ተቋም አስፈላጊነት ላይ ውይይት በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ‹‹ሰላም፣ ደኅንነት፣ ዲፕሎማሲና ልማት በኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ ምን ይደረግ?›› በሚል ርዕስ  ምሁራንን ያካተተ የፓናል ውይይት ተደርጎ ነበር።በእዚሁ ውይይት ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም መምህርና ‹‹ብሔራዊ ደኅንነት በኢትዮጵያ›› በሚል የጥናት ርዕስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እየሠሩ ያሉት አቶ ዮናስ ታሪኩ ‹‹ደኅንነት›› በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ በተለይ ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ ‹‹የማንን ደኅንነት እናስጠብቅ›› የሚለው ላይ አለመግባባት መኖሩንና በዚህም ምንክያት የአገሪቱ ደኅንነት ፍትጊያ ውስጥ መግባቱን መናገራቸው ተዘግቧል።

በእርሳቸው ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ እንደተገለጠው የሃገረ መንግስቱ መጠበቅ የቡድን መብት መጠበቅ ለምሳሌ በቋንቋ እና ማንንነት ላይ ያለው ከለላ ትኩረት እንዲሰጠው የሚፈልጉ የመኖራቸውን ያህል በተቃራኒው ሃገረ መንግስቱ መጠበቅ ላይ ኢትዮጵያዊነትን በሚገባ ይዞ መጓዝ እንዳለበት አጥብቀው የሚያሳስቡ እንዳሉ ገልጠዋል። አቶ ዮናስ ማብራርያቸውን በመቀጠል የሁለቱ ቡድኖች ሃሳብ እርስ በርስ የሚጋጩ አስመስሎ በማቅረብ ችግር የመፍጠር ሁኔታ መሆኑን ገልጠው ይህ ግን ወደ ግጭት ሊያመራ እንደማይገባ አብራርተዋል።ይህ እና ሌሎች ጥናቶች የሚያሳዩት የምክክር ኮሚሽን ተግባር ለኢትዮጵያ የደኅንነት እና ሰላም አንዱ እና ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ነው።|

የውይይት ሰነዶች ከውይይት በኋላ ምን ይሆናሉ?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገራዊ ደረጃ የማያግባቡ አጀንዳዎችን መርጦ በሰነድነት አዘጋጅቶ ለውይይት የሚያቀርብ አና የሚቋጩትን በመቋጨት ያልተቋጩትን ደግሞ በውይይት እንዲፈቱ የማድረግ ትልቅ ሀገራዊ አደራ ተቀብሏል። ሌላው እና የኮሚሽኑ ትውልድ ተሻጋሪ መሆኑን የሚያሳየው የኮሚሽኑ ተግባር ደግሞ የውይይት ሰነዶቹ ሂደት ጭምር ለቀጣይ ትውልድ መማርያ እንዲሆኑ በሚገባ በሰነድነት ሰንዶ ለብሄራዊ ቤተ መዛግብት የሚያስረክብ ሲሆን፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሰነዶቹን በፈለገ ጊዜ ለመመልከት እንዲችል ሁኔታዎች የሚመቻቹ መሆናቸው ነው።

ለማጠቃለል

የኢትዮጵያ ምክክር ኮሚሽን ዓይነት ኮሚሽኖች በበርካታ ሀገሮች ሀገራዊ ችግሮችን ፈትተዋል፣ችግሮች ለመጪው ትውልድ እንዳይሻገሩ እና ከወዲሁ ተፈትተው ትውልድ እንዲሻገር አድርገዋል። በኢትዮጵያም የዛሬ ሀምሳ ዓመታትም ስለችግሮቻችን ብንወያይ መፍትሔው መነጋገር እና የምክክር ኮሚሽኑን ዓይነት አደረጃጀት ይዞ ከመጓዝ ሌላ አዲስ ዘለቄታዊ መፍትሔ ማምጣት አይቻልም። ስለሆነም በሀገር ውስጥም ሆነ በተለይ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የእዚህ ዓይነት በጎ አካሄዶችን ሳይደግፍ፣ሳይሳተፍ እና የመፍትሔ አካል ሳይሆን እንዲሄድ በኋላ ቀር አስተሳሰብ ሊሰብኩት የሚሞክሩትን ያለሁን 21ኛው ክ/ዘመን ላይ ነኝ።ለመጪው ትውልድ የጸብ ዕዳ አላስተላልፍም! ለልጆቼ ሕይወት ዛሬ የችግር እና የግጭት አጀንዳዎችን ከወዲሁ ዘግቼ የተሻለች ኢትዮጵያን አወርሳለሁ! ብሎ በአንድነት የኮሚሽኑን ተግባር ቢችል በመሳተፍ፣ካልሆነ በማገዝ፣ ይህም ካልሆነ ባለመንቀፍ እና ዝም በማለት መተባበር መልካም ነው።
======================///////==============

የመረጃ ምንጮች ፡ 



The Ethiopian Orthodox Tewahedo Church is in turmoil in Athens, Greece.

His Holiness Abune Mathias I, Patriarch of the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church, met with Greece's Ambassador to Ethiopia, Antonios Sg...