ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, December 13, 2024

ኢትዮጵያ ከሞቃዲሾ ሱማልያ ጋር በአንካራ፣ቱርክ ያደረገችው ስምምነት በተመለከተ፡

በአንካራ የተደረገው የኢትዮጵያና የሱማልያ ስምምነት


  • የስምምነቱ ምንነት፣ 
  • ኢትዮጵያ የመዘዘቻቸው ካርዶች ከአስመራ እስከ ካይሮ የፈጠሩት ድንጋጤና ድንዛዜ፣
  • ኢትዮጵያ ያስከበረችው ጥቅሞቿ ምን ምንድን ናቸው? 
  • ስምምነቱ ካለፈው ይልቅ መጪውን የኢትዮጵያ አቅጣጫ ያመላክታል።
===========
ጉዳያችን ምጥን
===========

ኢትዮጵያ ከሞቃዲሾ ሱማልያ ጋር በአንካራ፣ቱርክ ያደረገችው ስምምነት ምንነት?

በያዝነው ሳምንት አጋማሽ ኢትዮጵያ እና ሱማልያ ያደረጉት ስምምነት የሚከተሉትን ነጥቦች ይዟል። እነርሱም፡
  • የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች አንዳቸው የሌላኛቸውን ሉዓላዊነት፣ ነጻነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት እና በአፍሪካ ሕብረት ደንቦች ላይ የሰፈሩ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ለማክበር ተስማምተዋል።
  • በወዳጅነት የመከባበር መንፈስ ያለፉ ልዩነቶችን እና አወዛጋቢ ጉዳዮችን ወደ ኋላ በመተው በትብብር ለጋራ ብልጽግና ወደፊት ለመሥራት ተስማምተዋል።
  • ሶማሊያ በአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ስር ሆነው በአገሯ የተሰማሩትን የኢትዮጵያ ወታደሮች መስዋዕትነት ዕውቅና ትሰጣለች።
  • የሶማሊያን የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር መተላላፊያ ማግኘቷ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ሁለቱ አገራት ዕውቅና ይሰጣሉ።
  • ሁለቱ አገራት በቱርክ አመቻቻነት በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ የቴክኒካዊ ጉዳዮች ድርድር ማድረግ የሚጀምሩ ሲሆን፣ ይህም በአራት ወራት ውስጥ የሚቋጭ ይሆናል።
  • በሉዓላዊ የሶማሊያ መንግሥት ስር ኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ዘላቂ የባሕር መተላላፊ እንድታገኝ የሚያስችል ለሁለቱም አገራት ጠቃሚ የሆኑ የኮንትራት፣ የኪራይ፣ እና ተመሳሳይ የንግድ አሠራር መንገዶችን በጋር በመሆን ለማጠናቀቅ ተስማምተዋል።
  • ሁለቱ አገራት የቱርክን ድጋፍ በመቀበል በስምምነቱ አተረጓጎም እና አተገባበር ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ልዩነቶችን በቱርክ አማካይነት በንግግር እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተስማምተዋል።
 ከካይሮ እስከ አስመራ ከአስመራ እስከ ሞቃዲሾ መሪዎቹን በድንጋጤ ያደነዘዙት ኢትዮጵያ የመዘዘቻቸው ካርዶች 
  • የኢትዮጵያ ፍላጎት ከሱማልያ አንጻር ግልጽ ነው።
    • ሱማልያ የኢትዮጵያ የጸጥታ ችግር እንዳትሆን፣
    • ሱማልያ የኢትዮጵያ ስልታዊም ሆነ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር እንዳታብር፣
    • የጋራ የምጣኔ ሃብት ትብብር እንዲኖር፣
    • ኢትዮጵያ ለሱማሌ ደህንነት በከፈለችው ዋጋ የሚመጥን ልክ ያለው ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር የሚሉት ይጠቀሳሉ።

  • ከእነኝህ ፍላጎቶች አንጻር ሱማልያ ሁሉንም በሚጻረር መልኩ ለማፈንገጥ ሙከራ ማድረግ የጀመረችው የአሁኑ የሱማልያ ፕሬዝዳንት ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ነው። በፕሬዝዳንቱ ሲመት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሞቃዲሾ ድረስ ሔደው መገኘታቸው ይታወሳል። ይህም ሆኖ ግን አዲሱ ፕሬዝዳንት ብዙ ለመዝለል ሙከራ እንደሚያደርጉ ቀድሞውንም ይጠረጠሩ ነበር።

  • ይህ መዝለል እየበዛ መጥቶ ፕሬዝዳንቱ መጀመርያ ኢትዮጵያን መጎብኘት ትተው አስመራ ሲሄዱ ኢትዮጵያ እየተከታተለች ነበር። አስመራ ሄደውም አቶ ኢሳያስ ያሰለጠኑላቸውን ወታደሮች ጎበኙ፣ ምሳ ተበላ፣ ቡና ጠጥተው ወደ ሞቃዲሾ አመሩ።
  • በእዚህ ሂደት መሃል የምስራቅ አፍሪካ የምጣኔ ሃብት ጥምረት ሃሳብ ቀደም ብሎ በቀደሙት የሱማልያ ፕሬዝዳንት በበጎ የተጤነውን ጉዳይ አዲስ ፕሬዝዳንት ቸል አሉት።

  •   በእዚህ መሃል ኢትዮጵያ በእጇ ላይ ያሉትን ካርዶች መዘዘች፣ ጫወታውን ጀመረችው። ይህንንም እኤአ ጥር 1፣2024 ኢትዮጵያ ከሱማልያ ላንድ ጋር የወደብ እና የባሕር ኃይል ጣብያ ለመትከል የመግባብያ ስምምነት ተፈራረመች። የመግባብያ ስምምነት ማለት ዝርዝር ስምምነት ይቀረዋል።ነገር ግን በመሰረተ ሃሳቡ ሁለቱ ሃገሮች ተስማሙ ማለት ነው። 

  • በእዚህ ስምምነት ላይ ከወደቡ ጉዳይ ይልቅ ሱማልያ ላንድ በሃገርነት የመውጣቷ ጉዳይ ሱማልያን አመሰ። ኢትዮጵያ ዝም ብላ ጉዳዩን ትከታተል ነበር።

  • የሱማልያው ፕሬዝዳንት ከአስመራ ካይሮ ተመላለሱ። አቶ ኢሳያስ ድግሷ እንዳማረላት ወይዘሮ ካይሮ መመላለሱን ተያያዙት።

  • ቀጥሎ የግብጹ መሪ አስመራ የአንድ ቀን ውሎ አድርገው ከሱማልያ እና ከኤርትራ ጋር የጋራ ስምመነት ተፈራረሙ።ሱማልያ በቀጣይ የአውሮፓውያን ዓመት የኢትዮጵያ ጦር በሰላም አስከባሪነት በግዛቴ አይቀጥልም ብላ የመግለጫ ጋጋታ አወጣች።ግብጽ የጦር መሳርያ ወደ ሱማልያ መላክ ጀመረች። ሽር ጉድ አበዛጭ

  • በእዚህ ጊዜም ኢትዮጵያ አላወራችም። ይልቁንም ሸምቀቆውን አጠበቀች። በመቀጠል ሁለት እርምጃዎች ወሰደች። እነርሱም የመጀመርያው የግብጽ አየር ኃይል መሳርያ የሚያቀብልባቸው የሱማልያ ዋና ዋና የአይሮፕላይ ማረፍያዎችን ተቆጣጠረች። በመቀጠል በመቶዎች የሚቆተሩ ዘመናዊ ታንኮች የያዘ ሰራዊት ካለፈው ወር ጀምሮ የበለጠ አስገባች።

  • የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሱማሌ በኩል ያላቸው ቁርጠኝነት ኤርትራን እና ግብጽን ብቻ ሳይሆን እራሳቸው የሱማሊያ ፕሬዝዳንትም እጅ በአፍ እንዲያደርጉ አስገደደ። ኢትዮጵያ የግብጽ እንቅስቃሴ በቀጥታ ከኢትዮጵያ የመልስ ምት እንደሚገጥመው ብቻ ሳይሆን የግብጽ ጦር ምን ሊያደርግ መጣ? ስንት ዓመት ሙሉ ያልረዳን ሰራዊት ዛሬ ምን ሊያደርግ መጣ? የሚሉ የሱማሊያ የጎሳ አለቆች ቁጣ አስፈሪ ሆኖ መጣ።

  • የኢትዮጵያ ሰራዊት በሱማሊያ ህዝብ ዘንድ ያለውን ተወዳጅነት እሩቡን ማግኘት ያልቻለው የግብጽ ሰራዊት ግምት እና እወነት ምን ያህል እንደሚለያዩ ግልጽ ሆነለት። በተለይ የኢትዮጵያ ጦር በበለጠ ወደ ሱማልያ መግባቱን ተከትሎ አቶ ኢሳያስ እና አልሲሲ በስልክ ረጅም ሰዓት እየተቀመጡ ጉዳዩን ሲወቅጡት ቢውሉም አንዳችም ጠብ የሚል ውሳኔ መድረስ ብቻ ሳይሆን የበለጠ ፍርሃት ለቀቀባቸው።

  • ይህ በእንዲህ እያለ የሱማልያ ጁባ ግዛት ግጭት ተነሳ፣መላዋ ሱማልያ ወደ ሌላ ሶስት ሃገር ልትከፋፈል እንደምትችል እና የኢትዮጵያ ተጽዕኖ የቱን ያህል የሚነዝር እንደሆነ የሱማልያው ፕሬዝዳንት ቆይቶም ቢሆን ገባቸው። በኢትዮጵያ ወታደሮች የምትጠበቀው ሞቃዲሾ ሳትቀር መልሳ ታመሰች።

  • ይልቁንም በፈረንጆቹ ዓመት መጀመርያ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከወጡ ሱማልያ ምን እንደምትሆን ለመተንበይ በራሱ አስፈሪ ሆነ።

  • ኢትዮጵያ የመዘዘቻቸው ካርዶች አንድ በአንድ ከአስመራ እስከ ካይሮ፣ከካይሮ እስከ ሞቃዲሾ የዘለለውን ሁሉ ጸጥ አደረገው።

  • ሌላው ቀርቶ በሱማልያ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የጀመረችው ቱርክ ካለ ኢትዮጵያ የሱማልያ ጸጥታ የትም እንደማይደርስ የበለጠ ግልጽ ሆነላት።

  • ከእዚህ በተጨማሪ የግብጽ በአፍሪካ ቀንድ ሽር ጉድ ማለት በሊብያ ግብጽን እንዳሳፈረቻት በሱማልያም ማሳፈር እንዳለባቸው የቱርኩ ፕሬዝዳንት ዛቱ።ከሁሉም በላይ የኤርትራ ከግብጽ ጋር ያላት ትስስር ቆይቶም ቢሆን በቀይባርሕር ላይ ቱርክ ያላትን ጥቅም እንደማያስከብር ብቻ ሳይሆን አደጋ መሆኑ ገባቸው። በመቀጠል ኢትዮጵያና ሱማልያን አስማሙ።

  • የኢትዮጵያና የሱማልያ በአንካራ መስምማታን ተከትሎ ካይሮ እና አስመራ ከባድ ድንጋጤ ላይ ወደቁ። ድንጋጤው ይህ ጽሑፍ እየተጻፈም ገና አልለቀቃቸውም።

  • ኢትዮጵያን እንደከዷት የእኛዎቹ ዩቱበሮች በሱማልያ መንግስት ውስጥ ያሉ የኤርትራና የግብጽ አሽቃባጮችም ድንጋጤው አደነዘዛቸው ብቻ ሳይሆን የሱማልያውን ፕሬዝዳንት በሀገር ከሃጂነት ለመፈረጅም ቃ|ጣቸው።
ኢትዮጵያ ያስከበረችው ጥቅሞቿ ምን ምንድን ናቸው?
  1. ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄዋ የቱን ያህል እርቀት እንደሚሄድ ዓለምን አሳምናለች። ሌላው ቀርቶ የሱማልያ ላንድን በሃገር የማወቅ ያህል እርቀት እንደምትሄድ አሳይታበታለች። 
  2. በባሕር በር ጥያቄ ጉዳይ ኢትዮጵያን አያስፈልግሽም የሚል አንድም ሃገር የመናገር ድፍረት አጥቷል።
  3. ኢትዮጵያ ለሱማሌ ላንድ የምትከፍለው መስዋዕትነት የቱን ያህል እንደሆነ አሳይታበታለች። ከአሁን በኋላ ሌላ ሃገር ቀድሞ የሱማልያ ላንድ እውቅና ቢሰጥም የኢትዮጵያና የሱማሌ ላንድ ግንኙነት  በማይበጠስ አንድነት ገምዳዋለች።
  4. የባሕር በር ለኢትዮጵያ ሳይሰጡ በሰላም አድሮ መዋል እንደማይቻል ግልጽ መልዕክት አስተላልፋለች።ይህ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሀገራቱም ህልውና የሚወሰነው በኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት እና አለማግኘት መሆኑ ለሁሉም የጎረቤት ሃገሮች ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል።
  5. ለሱማልያ አሁን የሱማልያ ላንድ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የጁባ ሱማልያ ጉዳይም የኢትዮጵያን ሕክምና እንደሚፈልግ የሱማልያ ፕሬዝዳንት ዘግይቶም ቢሆን እንዲገባቸው አድርጋለች።
  6. ኢትዮጵያ የሱማልያ ላንድ የወደብ ስምምነት ብቻ ሳይሆን ከዋናዋ ሱማልያም የወደብ አገልግሎት እንደምታገኝ በሰሞኑ ስምምነቷ አረጋግጣለች። 
  7. በእዚህ ስምምነት ኢትዮጵያ የግብጽ ተጽዕኖ በሱማልያ እንዳይቀጥል አጥልታበታለች። በመቀጠልም ኢትዮጵያ ጋር የስትራቴጂክ ግጭት የሌለባት ቱርክ በግብጽ እንዲቀየር መንገዱን አመቻችታለች። በእዚህም ኢትዮጵያ የተሻለ የጸጥታ ዋስትና አግኝታበታለች።
  8. በቀጣይ ኢትዮጵያ የወደብ ጉዳይ ከኪራይ እና ውል ሃሳብ ወጥታ ወደ ዘለቄታዊ የባሕር በር ታሪካዊ እና ሕጋዊ ጥያቄዋ እንድትሸጋገር ሁኔታዎችን አመቻችቶላታል።
ስምምነቱ ካለፈው ይልቅ መጪውን የኢትዮጵያ አቅጣጫ ያመላክታል።

የኢትዮጵያና የሱማልያ የሰሞኑ ስምምነት ከሁሉም በላይ በአፍሪካ ቀንድ እና የቀይባሕር አካባቢ ትኩረት ያደረጉ ኃያላን ሀገሮችም ካለኢትዮጵያ ተሳትፎ ዋስትና እንደማይኖረው ስላወቁ እና የአቶ ኢሳያስ ከኢራን ጋር ያላቸው ግንኙነት ብቻ ሳይሆን በምዕራቡ ላይ ያላቸው ጥላቻ እራሷን ግብጽ እንድትወዛገብ ብቻ ሳይሆን ከአቶ ኢሳያስ ጋር መወገን የሚያመጣባትን የወጪ ክምር እያሰበች በከባድ ትካዜ ላይ ጥሏታል። አቶ ኢሳያስም በእዚህ ሳምንት ከጎበኙት የቆዩትን አሰብን ጎብኝተው አካባቢው ደስ አላለኝም ብለው ወደ አስመራ ተመልሰዋል። በትግራይ ለአቶ ኢሳያስ ለማደር የሚታትረው የደብረጽዮን ቡድን በትግራይ ህዝብ ከበባ ውስጥ እንደገባ ገብቶታል። ምናልባት አንድ ቀን ማለዳ ደብረጽዮን አስመራ ሸሽተው ገቡ ሊባል ይችላል። ኢትዮጵያ የባሕር በር ሳታገኝ ውላ ማደሯ ዋጋ እንደሚያስከፍል እንደ የሱማልያው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስም የበለጠ የሚረዱበት ጊዜ ከምንጊዜውም በላይ የቀረበ ይመስላል።መጪው የኢትዮጵያ አቅጣጫም ከእዚህ የተለየ አይመስልም። ዓለምም የሚያስበው ይሄው ነው።

No comments:

የግሪክ አቴንሱ ''ኢትዮጵያዊው'' አውርቶ አዳሪው ''ዲያቆን'' እና ከጥንትም የኢትዮጵያ ጠላት የሆነው የ''አውርቶ አደር'' ማንነት

============= የጉዳያችን ማስታወሻ ============= ከጥንትም የኢትዮጵያ ጠላት የሆነው ''አውርቶ አደር'' ማንነት  የኢትዮጵያ የታሪክ ስብራት ዋነኛዎቹ ምክንያቶች አውርቶ አደሮች ናቸ...