Saturday, May 22, 2021

ከትግራይ፣መተከል፣ሰሜን ሸዋ እና ምዕራብ ወለጋ ለተፈናቀለው ሕዝብ ለመድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን በፍጥነት ልትሰራቸው የምትችላቸው አምስት ስራዎች አሉ

ጉዳያችን/Gudayachn

የትግራይ ሕዝብ ህወሓት ለአርባ ዓመታት ካሰቃየው በኃላም ዛሬም የተረፈው ቡድን እየተሹለከለከ ገበሬውን እየገደለ።ንብረቱን እየቀማው ነው።በመሆኑም ጥቂት ቅምጥሎች በስሙ የኖሩትን ሕይወት እየሰማ ዛሬም መልሶ ችግር ላይ መውደቁ ከተሰማ ሰንብቷል።በእርግጥ ከሕግ ማስከበሩ ሥራ ተከትሎ የፌድራል መንግስት ከ40 ቢልዮን ብር በላይ ወጪ አድርጎ የሰብአዊ ድጋፍ እና መልሶ ለማቆም ጥረት ማድረጉን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዛሬ ግንቦት 14/2013 ዓም በቦሌ ክፍለ ከተማ ከሚኖሩ የክልሉ ነዋሪዎች ጋር ባደረገው ውይይት ላይ መገለጡን የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በዜና ሰዓት ላይ አቅርቧል። ከእዚሁ ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ፣ የክልል አመራሮች፣የአማራ እና የትግራይ ክልል አመራሮች እና ባለሀብቶች  በተገኙበት ሕዝቡን መልሶ ወደ ቀዬው ለመመለስ እና በአማራ እና የትግራይ ክልል መሃል የህዝብ ለሕዝብ ማቀራረብ ስራዎችን የሚሰሩ የሀገር ሽማግሌዎች ያሉበት 14 አባላት ያሉት ሀገር አቀፍ ኮሚቴ ተመስርቷል።

በሌላ በኩል በትግራይ የሲቪሎች መገደል በተመለከተ የአቃቢ ሕግ የራሱን ማጣራት አድርጎ 110 ሲቪሎች መገደላቸውን ማጣራቱን ገልጧል።ግድያው በኤርትራ ወታደሮች መፈፀሙን ይገልጣል።ይህ በእንዲህ እያለ በትግራይ የተፈፀሙት የመደፈር ወንጀሎችም መፈፀማቸውን በሰብዓዊ መብት ድርጅቶችም ሆነ በራሱ በመንግስት ማጣራት ተገልጧል።በእዚህ መሰረት ከኢትዮጵያ ወታደሮች በእዚህ ተግባር ተሰማርተው ነበር የተባሉትን መንግስት አጣርቶ ክስ የመሰረተባቸው እንዳሉ ተገልጧል።

ከመተከል፣ሰሜን ሸዋ እና ከምዕራብ ወለጋ የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆችም ችግር ቀላል የሚባል አይደለም።በቅርቡ የአማራ ክልል እንደገለጠው ከግማሽ ሚልዮን በላይ ሕዝብ መፈናቀሉን ማስታወቁ ይታወቃል።ይህ ሁሉ ሕዝብም በቶሎ ወደ ተፈናቀለበት ቦታ መመለስ አለበት።ምክንያቱም አንገብጋቢው ጉዳይ ህዝቡ ዕለታዊ እርዳታ በቶሎ አግኝቶ ከመጪው ሰኔ አጋማሽ በፊት የእርሻ ስራውን እንዲጀምር የማድረጉ ሥራ ነው።ለእዚህ የተቀደሰ ተግባር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከሁሉ ቀድማ ልትሰራው የሚገቡ አምስት ተግባራት አሉ። ከሁሉም ቦታ የተፈናቀለው  ሕዝብ ወደ ቀዬው እንዳይመለስ ደባ እየሰሩ ካሉት ውስጥ የህወሓት ደጋፊዎች በዋሻ እና በውጭ ያሉት ሁሉ ናቸው።ምክንያቱም ህዝቡ ከቤቱ ከተበተነ ለነገ ግጭት ሊጠቀሙበት ይፈልጋሉና ነው።

አሁን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ልትሰራቸው የሚገቡ አምስት ተግባራት አሉ። እነርሱም -

1)  በኢትዮጵያም ሆነ በውጪ ሀገር የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አጥብያዎች እና ገዳማት በሙሉ በሁለት ሰንበት የሚሰበሰበው ገንዘብ በሙሉ ለተፈናቀሉት ወገኖች እንዲሆን መወሰን እና ወደ ተግባር መግባት፣

2) በሁለት ሰንበታት ከሁሉም አጥብያዎች እና ገዳማት የሚሰበሰብ ቁሳቁስ እና አልባሳት ማሰባሰብ 

3) ይህንን የሚያስተባብሩ ከብክነት የሚጠብቁ እና እርዳታው ወደተፈናቃዮች እስከሚደርስ የሚያስተባብሩ በብሔራዊ ደረጃ መምረጥ እና ማስተዋወቅ፣

4) የእርዳታው አሰባሰብ እና አሰጣጥ ሪፖርት በሚገባ ለሕዝብ ግልጥ ማድረግ እና 

5) በውጭ የሚኖሩ ምእመናኖቿ የሚሳተፉበት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የሚተላለፍ  የአንድ ምሽት የቀጥታ ጎፈንድሚ እና የገንዘብ ማሰባሰብያ ዝግጅት ማድረግ እና በዝግጅቱ ላይ ሊቃነ ጳጳሳት፣ሰባክያን እና መዘምራን  እንዲሳተፉ በማድረግ ከሚልንየም አዳራሽ ማስተላለፍ የሚሉት ናቸው።

እነኝህን የዕርዳታ ስራዎች ቤተክርስቲያን በቶሎ እንድትሰራቸው ግፊት ማድረግ የቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ግዴታ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ከብዙ አቅጣጫ እጅግ መፍጠን አለባት።
 ********************************
ማስታወቂያ /Advertisement 
====================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 

Thursday, May 20, 2021

ይህ ትውልድ ከአባቶቹ የተረከበውን የኢትዮጵያን ነፃነት ዳግም የሚያረጋግጥበት ተራው ደርሷል።ለኢትዮጵያ ነፃነት የቆመ ሁሉ ጠ/ሚ/ር ዓቢይን ከጎንህ ነን ማለት አለበት!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

>> ያለንበት ዘመን የዛሬ አንድ መቶ ዓመት የነበርንበት የንግሥት ዘውዲቱ ዘመንን ይመስላል።

ጉዳያችን/Gudayachn

ባለፈው የጉዳያችን ፅሁፍ ላይ የሩስያ ባሕር ኃይል ከሱዳን ጋር ያደረገው ውል በአሜሪካ ከፈረሰ በኃላ ጉዳዩ በኢትዮጵያ አንፃር የአሜሪካንን በትግራይ አሳባ የምታደርገው ተፅኖ ችግር ላይ እንደሚወድቅ አብራርታ ነበር።ኢትዮጵያ በዓለማችን ላይ ካሉት በከርሰ ምድሯ ውስጥ በያዘችው የተፈጥሮ ሀብትም ሆነ በምትገኝበት ስልታዊ አቀማመጥ ለዘመናት ሀገሪቱን ለመቆጣጠር በየዘመኑ የተነሱት ኃያላን ያልሞከሩበት ጊዜ የለም።ባለፉት ሁለት ወራትም በኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፍ የመሸበቢያ ገመድ ለመሸምቀቅ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤትን ለመጠምዘዝ በአሜሪካ፣እንግሊዝ እና ፈረንሳይ የተደረገው ሙከራ በሩስያ እና ቻይና አለመስማማት ሳብያ ከከሸፈ በኃላ አሜሪካ ዛሬ በሴኔቷ አማካይነት ውሳኔ አሳልፋለች።ውሳኔው በትግራይ የተደረገውን የሕግ ማስከበር ሂደት አስታኮ ይወስን እንጂ የአሜሪካ ዋና ምክንያት የአፍሪካ ቀንድ ላይ በህወሓት እጅ በኩል የነበራት ተፅኖ ሽባ እየሆነ በመምጣቱ ነው።በተለይ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሃል የተፈጠረው ድንገተኛ እርቅ የአፍሪካ ቀንድን ፖለቲካዊ፣ምጣኔ ሃብታዊ እና ወታደራዊ ቅርፅ በእጅጉ እንደሚቀይረው ግልጥ ሆኗል።

አሜሪካ እና ግብረ አበሮቿ አፍሪካን ካልከፋፈሉ ወይንም በዓይናቸው ስር በሚገኝ ህብረት ውስጥ ካልሆኑ ለጥቅማቸው አደጋ እንደተጋረጠበት ያምናሉ።በመሆኑም በቀላሉ በአቶ መለስ በኩል ይዘውሩት የነበረው የኢጋድ (የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት ድርጅት) ችላ ብለው የኢትዮጵያ፣ኤርትራ እና ሱማልያ አዲስ የትብብር እና የምጣኔ ሀብት ትብብር ሃሳብ ማንቀሳቀሳቸው እና በተለይ ከኤርትራ ጋር ያለው ትብብር ህወሓትን የማስወገድ የጋራ ወታደራዊ ትብብር ድረስ ተሻግሮ መሄዱ ጉዳዩ የሁለቱ ሀገሮች ግንባር መፍጠር ብቻ የአንድ ሺህ ኪሎሜትር ድንበር ከአፍሪካ ቀንድ ጋር የምዋሰነው እና መካከለኛ እና ሩቅ ምሥራቅን ከአውሮፓ ጋር የሚያገናኘው የቀይባህር በኢትዮጵያ እና ኤርትራ የጋራ ትብብር የማንም የውጭ ኃይል ወፍ ዝር እንዳይል የሚያደርግ ስለሆነ አሜሪካ እና አጋሮቿ ብርክ ይዟቸዋል።ስለሆነም ይህ ከሚሆን ኢትዮጵያ ብትበታተን የሚመርጡ መሆናቸውን በሰሞኑ ድርጊታቸው መረዳት ይቻላል። 

አሁን ምክንያት የምንደረደርበት ወይንም ቅሌን ጨርቄን የሚባልበት ጊዜ አይደለም።ኢትዮጵያ በየዘመኑ የተነሱ ኃያላን ሊያንበረክኩ ሞክረዋል።አሁንም ምንም ዓይነት ቅርፅ ብንሰጠው የባዕዳኑ ፍላጎት አንድ እና አንድ ነው።የተንበረከከች፣እንደፈለጉ ተነሽ እና ተቀመጭ የሚሏት ኢትዮጵያን ማየት ነው።በእዚህም በዋናነት አሁን ኢትዮጵያን ያለውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይን ማገዝ ይጠበቅበታል።አሁን ያለንበት ጊዜ የንግሥት ዘውዲቱ ዘመንን ይመስላል።ከሰገሌ ጦርነት በኃላ የካቲት 4፣1909 ዓም በዕለተ እሁድ አባታቸው ዳግማዊ አፄ ምንሊክ ባሰሩት በአዲስ አበባ በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በአቡነ ማቴዎስ እጅ ተቀብተው ነገሱ።በንግሳቸው ላይ የኢትዮጵያ አዋሳኝ የሆኑት የያኔዎቹ ቅኝ ገዢዎች የእንግሊዝ ሱዳንና የእንግሊዝ ሱማሌ ገዢዎች እንዲሁም የፈረንሳይ የያኔዋ አፋርና ኢሣ ገዢ እንዲሁም በኢትዮያ የሚገኙ ራሶች እና የየአውራጃ ገዢዎች ሁሉ በተገኙበት ነበር።በመቀጠለም በንግስ ስርዓቱ መሰረት በወቅቱ የደጃዝማችነት ማዕረግ የነበራቸው ተፈሪ (በኃላ አፄ ኃይለስላሴ) ራስ ተብለው አልጋወራሽና ባለሙሉ ስልጣን እንደራሴ መሆናቸው በአዋጅ ተነገረ።

ወቅቱ የአንደኛው ዓለም ጦርነት በዓለም የተፋፋመበት፣የባዕዳን ኃይሎች የኢትዮጵያን መሬት በተለይ ከአፄ ምንሊክ እረፍት በኃላ ኢትዮጵያ ትከፋፈላለች ብለው የሚጠብቁበት እና በውስጥ ለመከፋፈል ከፍተኛ ሙከራ የሚያደርጉበት ወቅት ነበር።ይህ በእንዲህ እያለ ዘመናዊ ትምህርት በመጠኑ የቀመሱ ወጣት ኢትዮጵያውያን በንግሥት ዘውዲቱ እና በዙርያቸው ባሉ የአፄ ምንሊክ ያህል በተፈጥሮ ያልሆኑ እና የወቅቱን የዓለም አቀፍ ሁኔታ የማይረዱ ቤተመንግስት መግባታቸው ስጋት ፈጥሮባቸዋል።ይህንን ሁኔታ ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ወቅቱን አስመልክተው ራሳቸው በፃፉት ''ሕይወቴ እና የኢትዮጵያ ርምጃ'' በተሰኘው መፅሐፋቸው ገልጠውታል።የያኔው ራስ ተፈሪ የኃላው አፄ ኃይለስላሴ ግን አርፈው አልተቀመጡም።ይልቁንም አውሮፓ ድረስ ሄደው የውጭው ዓለም ፖለቲካ ተገነዘቡ።ኢትዮጵያ በዓለም ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን) አባል መሆኗ ላይ በወቅቱ ከነበሩት ከነቁት ጋር አብረው ሰሩ። ከንግስት ዘውዲቱ ንግሥ በኃላ የተነሳው ውስጣዊ ሹክቻ በሁለት የተከፈለ እንደነበር ይሄው የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ  መፅሐፍ ያብራራል።አከፋፈሉ የንግሥት ዘውዲቱ እና የፊውዳል ወግ አጥባቂው እና ትምህርት ቀመስ የሆነው ኢትዮጵያን ወደ ዘመናዊ መንገድ ማስገባት ይገባል ለእዚህም ዓይነተኛ ሰው ራስ ተፈሪ ናቸው የሚሉት ነበሩ።
 
ዛሬም ኢትዮጵያ በአማራ፣በትግራይ፣በኦሮሞ በሚል የጎሳ ፖለቲካ ለስልጣን መወጣጫ ያልተሳካ ሙከራ የሚያደርጉ የመኖራቸውን ያህል በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ፣በእዜማ እና በአቶ ኢሳያስም ወገን ጭምር የኢትዮጵያ አንድነት ከጎሳ ፖለቲካ የፀዳ እንዲሆን የሚፍልጉ ናቸው።አንዳንዶች አቶ ኢሳያስን ከእዚህ አስተሳሰብ ሊያወጡ ይሞክራሉ።ለእዚህም ምክንያት የሚያደርጉት የአቶ ኢሳያስን የሴራ ፖለቲካ አድርገው ስለሚያዩት ነው።ሆኖም ግን የአቶ ኢሳያስ ስጋት የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ በቅሎ ኤርትራም እንደማትተርፍ አውቀዋል።ሌላው ዘግይተውም ቢሆን የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ዕድል አንድ መሆኑን በሠላሳ ዓመታት ተሞክሮ ስለገባቸው መሆኑን መረዳቱ ተገቢ ነው።

ኩሩው ጠቅላይ ሚኒስትር 

ኢትዮጵያ በአሁኑ የአሜሪካም ሆነ ግብረአበሮቿ ተግባር አንፃር መቆም ያለባት ከአንድነቱ ጎራ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ጎን ነው።በችግር ጊዜ ያውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይን የመሰለ ኩሩ መሪ ተገኝቶ የባሰ መጥፎ መሪም ቢሆን በኅብረት አብሮ መቆም የግድ ነው።ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያዊነት ኩሩ የነፃነት መንፈስን በሚገባ አንፀባርቀዋል።ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ ወደ አሜሪካ ባደረጉት የመጀመርያ ጉዞ ላይ ዋይት ሃውስ ጎራ ብዬ  ፕሬዝዳንት ትራምፕን ላናግር ብለው ደጅ አልጠኑም።ሕዝባቸውን አናግረው የተሰደዱትን ቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ መርቆርዮስን ይዘው ወደሀገራቸው ገቡ።ይህ ብቻ አይደለም የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ውሃ በቀጠነ እያለች ስትነጫነጭ ልዩ ልዑክ እየላኩ አሜሪካኖች ያስረዱናል ብለው ሲጠብቁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስራቸውን ብቻ ይሰሩ ነበር።በኃላ ቢቸግራቸው ራሳቸው ፕሬዝዳንት ባይደን ልዩ ልዑክ ወደ አዲስ አበባ ሁለት ጊዜ ልከው የኢትዮጵያን አስተሳሰብ ሊያስቀይሩ ሞከሩ።ይህም አልተቻለም።በመሆኑም ግራ የተጋቡት አሜሪካኖች ወደ ምክር ቤታቸው ሄደው በሐሰት የሚድያ ዘመቻ ወደ ሰከረው ምክር ቤት ሄደው ውሳኔ አሳለፉ።ይህ ሁሉ ግርግር ማዕከላዊ መንግስትን አዳክሞ ደካማ ኢትዮጵያን መፍጠር እና ለአሜሪካ መንግስት የሚታዘዝ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ አሻንጉሊት መንግስት ኢትዮጵያ ላይ መመስረት ይህ  ካልሆነ ሀገሪቱን መከፋፈል ነው።ስለሆነም ኢትዮጵያን የሚወድ እና ከማናቸው የባንዳ አስተሳሰብ የጠራ ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይን ከጎናቸው መሆኑን የሚገልጥበት እና ለኢትዮጵያ ነፃነት እና አንድነት በኅብረት የሚቆምበት ወሳኝ ጊዜ ነው።


 ********************************
ማስታወቂያ /Advertisement 
====================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 

Friday, May 14, 2021

ማኅበረ ቅዱሳንንም ኢሳትንም ለሚያውቅ ለእኔ የኢሳትን፣የጋዜጠኛ ሲሳይን አስተያይተም ሆነ የማኅበረ ቅዱሳን መግለጫ የምረዳበት ዓውድ።

>> የአቡነ ማትያስን አባትነንትን ማክበር የቤተ ክህነትን የአስተዳደር ብልሹነት እና ወደፊት የሚወሰደውን የማስተካከልን ሥራ ፈፅሞ ሊጋርደው አይገባም።   

(የጉዳያችን ልዩ ጥንቅር) 

በክፉ ጊዜ ለማኅበረ ቅዱሳን የተሟገተው ኢሳት እና  ጋዜጠኛ ሲሳይም ሆነ ማኅበረ ቅዱሳን ሁሉም  የኢትዮጵያ ሕዝብ የተከበሩ ሐብቶች ናቸው። ሁሉም ለሀገራቸው እና ለወገናቸው መልካም ባደረጉ፣የእድሜ ግማሽ ዘመናቸውን ለኢትዮጵያ በወጡ በወረዱ ማንም እንደፈለገ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሊያደረግባቸው አይገባም።ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚድያ ሶስቱም ላይ የሚፈፀሙት የስም ማጥፋት ዘመቻዎቹ በትክክል ነጥብ በነጥብ ጉዳዩን እያነሱ ከሚሞግቱት ውጪ አጋጣሚውን ተጠቅመው ብስለት የሌላቸው፣ነገር ግን በአጋጣሚው የማኅበረ ቅዱሳንንም፣የኢሳትንም ሆነ የጋዜጠኛ ሲሳይ አጌናን ስም ተገቢ ባልሆነ እና ጨዋነት በጎደለው መልክ በማኅበራዊ ሚድያ የሚያጥላሉ እየተመለከትን እየታዘብን ነው። አንዳንዶቹበሶስቱም ላይ በአመለካከታቸው፣በአሰራራቸው እና በእምነት ጭምር ቀድሞም ሲያጥላሉ የነበሩ ዛሬ በተፈጠሩ ጉዳዮች አስታከው ወደ የለየለት የማጥላላት ዘመቻ ሲገቡ እያየን ነው።ይህ ሊቆም ይገባዋል።በመሃል ነገር የሚያካርሩ እና በአጋጣሚው የግለሰብንም ሆነ የድርጅትን ስም ለማጠልሸት ለሚሯሯጡ ዕድል ሊሰጥ አይገባም።

የሆነው ምንድን ነው? 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደረጃ መምርያ ስር የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን በያዝነው ሳምንት መጀመርያ ላይ መግለጫ አወጣ።መግለጫው ከእዚህ በፊት ማኅበሩ ካወጣቸው መግለጫዎች ጠንከር ያለ መግለጫ ነው።መግለጫው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስደት ላይ ነች በሚል ርዕስ ሆኖ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ  የደረሰው እና ወደፊት የተጋረጠባት አደጋ የከፋ ነው የሚል ሃሳብ ይዟል።በመግለጫው ይዘት ላይ በእዚሁ ሳምንት አጋማሽ ላይ ለአደባባይ ሚድያ ማብራርያ የሰጡት የማኅበሩ አመራሮች በእዚህ ዓመት የተመረጡ እና ወደ አመራር የመጡ ቢሆኑም ከእዚህ በፊት በማኅበሩ አገልግሎት ላይ ግን ረዘም ያለ ጊዜ እንዳላቸው እና የወጣው መግለጫ ግን በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ካለው ፈተና አንፃር እንድያውም ያነሰ መሆኑን ገልጠው መንግስት በተደጋጋሚ ለደረሱት ጥፋቶች ተገቢውን ምላሽ ክብር ባለው መልክ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አለመስጠቱ በራሱ ብዙ ነገር እንደሚያመላክት ገለጡ።

ይህንን መግለጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በዕለታዊ ዝግጅቱ ላይ መግለጫው ላይ ትችት አቀረበ። ትችቱ በተለይ ከእዚህ በፊት ቤተ ክርስቲያን በተለይ በዘመነ ህወሓት የነበረችበት የፈተና ዘመንን በሚገባ አያብራራም፣ይልቁንም ይህንን ጉዳይ መንግስት በትኩረት ሊመለከተው የሚገባ ነው የሚል ሃሳብ ጨምሮ በተለይ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና በቅርብ ወደ ማኅበሩ የመጡ አመራሮች የወቅቱን አመራር የማይደግፉ መሆናቸው ነው የሚል ከሆነ ሰው እንደሰማ የሚገልጠውን ሃሳብ ጨምሮ በውይይቱ ላይ አቀረበ።

 የማኅበረ ቅዱሳንን መግለጫ የምረዳበት ዓውድ።

ማኅበረ ቅዱሳንን ከምስረታው ጊዜ ጀምሮ ብቻ ሳይሆን የዩንቨርስቲ ተማሪዎች በብላቴ በዘመቱበት ጊዜ ከዘማቾቹ አንዱ ስለነበርኩ እና ለማኅበሩ መመስረት እንደ አንድ ጥንስስ የሚቆጠረው በብላቴ አየር ወለድ ማሰልጠኛ ኬስፓን ውስጥ ከዘማቾቹ አንዱ ከሆነው ከሙሐዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት እና ሌሎች ወንድሞች የምሽት ትምሕርት ጀምሮ የማኅበሩን ሂደት አውቀዋለሁ።የማኅበሩም አገልግሎት  ከምንም አድርባይነት የፀዳ መሆኑን ፣እዚህ ላይ መጥቀስ የማያስፈልጉ ብዙ ፈተናዎች አባላቱ የተቀበሉበት ከሁሉም በላይ ከብሄር እና ጎሳዊ አስተሳሰብ ፈፅሞ የፀዳ ለመሆኑ ምስክር ነኝ።ሌብነት እና ሙስና በተንሰራፋባት ሀገር በመልካም ዜግነት የታነፁ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አባላት ያፈራ እና ለኢትዮጵያ ዘመናዊ የሲቪልም ሆነ ወታደራዊ ኃይል መልካም እና ታማኝ  ዜጋ በማፍራት ሂደት የራሱን አስተዋፅኦ ያደረገ ማኅበር ነው።

ማኅበረ ቅዱሳን በሩቅ የሚያዩት አንዳንዶች ከቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውጪ አድርገው የሚያስቡ አሉ።ሆኖም ማኅበሩ በቅዱስ ሲኖዶስ መተዳደርያ ደንቡ ተለክቶ እና ተወስኖ የተሰጠው እንዲሁም በቤተ ክርስያንቱ መዋቅር ስር የሚገኝ ከመሆኑም በላይ እያንዳንዱ የአገልግሎቱን ሪፖርት ለቅዱስ ሲኖዶስ  እና በሚገኝበት መዋቅር ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምርያ የሚያቀርብ የአገልግሎት ማኅበር ነው።

በቅርቡ ማኅበሩ ያወጣው መግለጫ የቤተ ክርስቲያንን ስደት ብሎ የተነሳበት ነጥብ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት የግራው ፖለቲካ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ መሆኑን ነው የገለጠው።ስደት የሚለውን ብዙዎች ከፓትርያሪክ ስደት ጋር ብቻ አያይዘው ቤተክርስቲያን ተሰደደች የሚባለው ከአባቶች ስደት ጋር አያይዘው ግራ የተጋቡ አሉ።ይህ ግን ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ትርጉም ከክርስቲያኖች ስብስብ፣ከሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እና ከአንድ ክርስቲያን በአምሳለ እግዚአብሔር መፈጠሩን በሶስት ከፍሎ የሚሰጠውን የቤተክርስቲያን ትርጉም ካለመረዳት የሚመጣ ነው።ስለሆነም ስደት ሲባል የክርስቲያኖች ከወለጋ እስከ ባሌ፣ከሻሸመኔ እስከ ሐረር በክርስቲያኖች ላይ የደረሰውን ስደት፣ግድያ እና መከራ ሁሉ ቤተክርስቲያን እያንዳንዱ ሰውነትም ናትና የክርስቲያኖች መሰደድ የቤተ ክርስቲያን ስደት ተብሎ ይጠራል። ይህ ብቻ አይደለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በአደባባይ ከሚያከብሯቸው በዓላት ውስጥ እንደ መስቀል እና ጥምቀት ያሉት በዓላት ባሳለፍነው ሶስት ዓመታት ውስጥ በቢሸፍቱ እና ሆሳዕና ጨምሮ በአንዳንድ ቦታዎች ምዕመናን ማክበር አልቻሉም።

ቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ ማኅበረ ቅዱሳንን ምክንያት በሌላው መንገድ ከመውቀስ አልፈው ፈተና ያመጡበት ጊዜም ነበር።ለእዚህም ማኅበሩ የሰጠውን ምላሽ እንደ አንድ ማሳያ መመልከት ይቻላል።ማኅበሩ በፓትርያሪኩ ተወቅሶ የሰጠውን የጽሁፍ  ምላሽ ይህንን   በመጫን ማንበብ ይችላሉ።ይህም ሆኖ ግን ማኅበሩ ፓትርያሪኩን በመንበራቸው ክብር መከበር እንዳለበት ደጋግሞ ሲናገር ቤተክርስቲያኒቱ ከእዚህ በፊት የቤተ መንግስቱ ፖለቲካ ሲቀያየር ቤተክህነቱ ፓትርያሪክ እንዲቀይር የሚደረገው ሴራ ዛሬ ሊደገም እንደማይገባ በአፅንኦት ከማሳሰብ አንፃር የሚታይ ነው።ይህ ማለት ግን የቤተ ክህነት አስተዳደራዊ አሰራርም ሆነ የሙስና ተግባራት ሁሉ አይስተካከል የሚል እንደማይሆን ነው የሚገባኝ።

በአጠቃላይ ማኅበረ ቅዱሳን በእየለቱ ከመላዋ ኢትዮጵያ ካሉት የአገልግሎት መዋቅሮች ከአዲስ አበባ እስከ ታች ወረዳ ያለው የቤተ ክርስቲያን ፈተና ሪፖርቶች በእየሰዓቱ ለዋናው ማዕከል ይደርሱታል።እነኝህ ሁሉ ሪፖርቶች ብዙዎች አያውቁትም።ዛሬ ባሌ፣ከፋ፣አርሲ እና ሐረር በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ ካህናት ጠምጥመው ገበያ ቢወጡ በድንጋይ የመወገር አደጋ ስላለባቸው ጥምጣማቸውን አውልቀው ከቤታቸው እንደሚወጡ የሚያውቅ ጥቂት ናቸው።ይህ አንዱ የቤተ ክርስቲያን ስደት ማሳያ ነው።ሁኔታው በአፋጣኝ ካልተሻሻለ የሀገሪቱ የፀጥታ ችግር እንዳይሆን ከምርጫው በኃላ የሚመጣው መንግስት ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል።

በክፉ ጊዜ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ስር ለሚገኘው ለማኅበረ ቅዱሳን የሞገተው ኢሳትንም ሆነ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌናን በተመለከተ የተረዳሁበት አውድ 

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን ዛሬ አንዳንዶች ከፖለቲካ አስተሳሰብ እና ከገቡበት የዘውግ ፖለቲካ አንፃር በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ሊያጥላሉት ቢሞክሩም፣ኢሳት ላለፉት አስር ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ ተንሰራፍቶ የነበረውን የህወሓት/ኢህአዴግ የጭቆና ስርዓት በግንባር ቀደምትነት በመዋጋት ስሙ ከሚጠሩት ውስጥ ነው።እሳትንም ቀረብ ብዬ እንደመመልከቴ  ሰሞኑን አንዳንዶች ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር እያያዙ እንደሚነቅፉት ፈፅሞ አይደለም።ባለፉት አስር ዓመታት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በስሯ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን ላይ በስርዓቱ እና በቤተ ክህነት ውስጥ በተሰገሰጉ የህወሓት አቀንቃኞች የሚነሱ አቧራዎች ሁሉ ኢሳት ለሕዝብ በማጋለጥ ግንባር ቀደም እንደነበር ምስክር ነኝ።የኢሳት ጋዜጠኞች ሲሳይ አጌናም ሆነ መሣይ መኮንን በማኅበረ ቅዱሳን ላይ እየደረሱ የነበሩትን ቅሰጣዎች ሁሉ እራሱን የቻለ መርሃግብር እያዘጋጁ ለሕዝብ በራድዮ እና በቴሌቭዥን እንዲተላለፍ አድርገዋል።መሳይ መኮንን ማኅበረ ቅዱሳንን አስመልክቶ ባደረጋቸው ወደ ሶስት ጊዜ የሚሆኑ የዜና ዝግጅቶች ላይ እራሴንም ጋብዞኝ በማኅበሩ ላይ እየደረሱ የነበሩ ፈተናዎች በተመለከተ እንድናገር ዕድል ሰጥቶኝ በወቅቱ በራድዮ እና ቴሌቭዥን ፕሮግራሞች ላይ ቀርበዋል (ከእዚህ ፅሁፍ በታች የኢሳትን ማኅበሩ ላይ እየደረሰ ያለውን ፈተና ለሕዝብ ያሰማበት  ልዩ ዝግጅት በቪድዮ ያገኛሉ)።

ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌናም በተለያዩ የዕለታዊ ዝግጅቶች ላይ በማኅበሩ ላይ እየደረሱ የነበሩትን ፈተናዎች ከማቅረቡም በላይ በአንድ ወቅት ራሱን የቻለ ልዩ ዝግጅት አቅርቦ ነበር።አንዳንዶች በወቅቱ ምናልባት ኢሳትን በሚገባ ሳይከታተሉ ዛሬ በአንድ ፕሮግራም በኢሳት ላይም ሆነ በጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ላይ እጅግ ነውረኛ የሆነ የስም ማጥፋት ቃላት ሲጠቀሙ ስመለከት በጣም ያሳዝነኛል። ይህ የሚመለከተው በአግባቡ ሃሳባቸውን የገለጡትን ሳይሆን በማኅበራዊ ሚድያ በወረደ መልኩ ስም ለማጥፋት የሚሞክሩትን ነውረኞች ነው። 

 ሰሞኑን በተደረገው የኢሳት ዕለታዊ ላይ በተለይ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና በማኅበረ ቅዱሳን መግለጫ ላይ የሰጠው አስተያየት በእርግጥ መታረም ያለባቸው ቃላት ቢኖሩበትም መነሻው ብዬ የምረዳው ግን ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት እጅግ ወሳኝ ጊዜ እና   በተለያየ አካላት በተከታታይ ከሚታዩት ሃገራዊ ሴራዎች አንፃር በማኅበሩ መግለጫም ለሀገር ከመጨነቅ አንፃር እረብሾታል።እርሱ የተሰማው ስሜት ደግሞ ማንም ሃገሩን የሚወድ ሰው የሚሰማው ስሜት ነው።ስለሆነም ስሜቱን በነካው መጠን ከሚገባው በላይ ድምፀቱን አክብዶታል።ይህ ማለት በማብራርያው ላይ መታረም ያሉባቸው አንዳንድ  አገላለጦች እንዳሉ ሆነው አንዳንዶች በነውረኛ አቀራረብ በጋዜጠኛው ላይ እና በኢሳት ላይ እንደሚሉት ግን ፈፅሞ አይደለም። 

ባጠቃላይ ግን ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ከእድሜው ከ1/4ኛ በላይ በኢትዮጵያ ጉዳይ የፃፈ፣የታሰረ፣የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያስጨንቀው እና ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሁሉም ዕምነቶች እኩል አክብሮት ያለው ወደፊትም የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያከብረው ጋዜጠኛ ነው። በመሆኑም አንዳንዶች ሰሞኑን በወረደ መልኩ ሊገልጡት እንደሚሞክሩት ያለ ግለሰብ አይደለም። አንድ በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ የተለመደ ክፉ ልማድ፣ አንድ ሰው አንድ ቀን የተሳሳተ ነገር የተናገረ ጊዜ የምናወርድበት ውርጅብኝ እና ለሀገር ስንት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ የተከበሩ የሀገር ሃብቶችን አጥላልተን የምንጥልበት መጠን የከፋ ነው።ይህ ኢትዮጵያን ሰው እንዳይወጣላት ያደረገ አጨንጋፊ ክፉ ልማድ ነው።በተለይ ማኅበራዊ ሚድያ ከመጣ በኃላ ስም እየቀየሩ መፃፍ እና ግለሰቦችንም ሆነ ድርጅቶችን ማብጠልጠል የተለመደ እኩይ ሥራ ነው። 


የመጨረሻው መጨረሻ ግን አንድ ነገር ሳልል ማጠቃለል የለብኝም።ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ማክበር የነቀዘውን የቤተ ክህነት የሙስና አሰራሮችን ማስተካከል እና ሙሰኞችን ከመንቀል ጋር ሊጋጭብን አይገባም።ቤተክህነት አሰራሩን ዘመናዊ ማድረግ አለበት። ሙሰኞች እና በቤተክህነቱ ውስጥ ተጠልለው ለዓመታት ወንጀል የሰሩ ገለል ማለት አለባቸው።
 ይህንን ብንስማማም ባንስማማም እግዚአብሔር የቆረጠበት ቀንን ማንም አይቀይረውም።ክርስቶስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲሸጡ ሲለውጡ የነበሩትን መንጥሮ ለማውጣት ጅራፉን ይዞ የሚመጣበትን ቀን ከፈሪሳውያን እና ፃሕፍት ጋር ተመካክሮ አልወሰነም።ስለሆነም ይህንን ቀን ማንም አያቆመውም።

አዎን! ቤተክርስቲያን ከውጪ እየደረሱባት ያሉት ፈተናዎች ቀላል አይደሉም።ነገር ግን ፈተናዎቹን የውስጥ ችግሯን ቀድማ ከመፍታት ውጪ የውጭ ፈተናዎችን መከላከል ከባድ ነው።ቤተክርስቲያኒቱን የመንግስት ሙሉ አካል ተፃራሪዋ ነው የሚለው የአንዳንዶች አስተያየትም ትክክል አይደለም።ከመንግስት መዋቅሮች ውስጥ በጠላትነት የሚያይዋት አሉ የሚለው የተሻለ አገላለጥ ነው።መንግስት ግን እንደ መንግስት የሀገሪቱ ግማሽ በላይ አካል ከሆነች ቤተክርስቲያን ጋር አለመስራት ብቻ ሳይሆን የተሻለች እና  የቀለጠፈ እንዲሁም የጠለቀ መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት ሕዝቡ መርካቱ ለራሱ ለመንግስት ቢያንስ በፖለቲካዊ የሰመረ  አስተዳደር አንፃርም ብናየው የሚፈልገው መሆኑን አለመረዳት በራሱ የአስተሳሰብ መዛነፍ ችግር ነው።ስለሆነም አንዳንዴ አላስፈላጊ መጠራጠር አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም። ትልቁ ጉዳይ ቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥ የሙስና እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች አስተካክላ እና መንፈሳዊ አገልግሎቷን በትሕትና፣በፍቅር እና በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ማስፋፋት፣ተግዳሮቶቹን ከምዕመኑ ጋር በብልሃት እና በእግዚአብሔር ዕርዳታ እየተጋፈጠች መሄዱ ላይ ነው ቁም ነገሩ።ከእዚህ በተጨማሪ የአገልግሎት ማኅበራት በዋናነት ሊያተኩሩበት የሚገባው ማኅበራዊ  አገልግሎት ማስፋፋት እና መላ ሀገሪቱን በሚሸፍን ደረጃ የማጠናከር ሥራ ላይ ነው።ይህ እጅግ የበዙ ጥቅሞች አሉት።በእዚህም የሀገሪቱን ችግር በመጠኑ ይቀርፉበታል፣ከመንግስት መዋቅሮች ጋር በልማት አጋርነት ይተጋገዙበታል፣ተደማጭነታቸው በሕዝቡም ሆነ በመንግስት ዘንድ ያጎሉበታል።ስለሆነም የትኩረት አቅጣጫዎች በአግባቡ መምረጥ እና የበጎ ተፅኖ  መፍጠርያ ቦታዎችን ለይቶ የቤተ ክርስቲያንን ታሪካዊ ቦታ የማስያዝ አንዱ እና ዓይነተኛ መንገድ እንደሆነ ማወቅ ብልሕነት ነው። ከእዚህ በተረፈ ግን ትሕትናን ገንዘብ እናድርግ! መሰደብ መነቀፍ አያስቆጣን።በክርስትና ሕይወት የምንከተለው የተነቀፈ እና የተሰደበ ብቻ ሳይሆን የተገረፈ እና የተሰቀለ አምላክ እና አንገታቸውን የተቆረጡ ሰማዕታት ናቸው።ለተተቸው እና ለተነቀፈ ጉዳይ ሌላው ቢረዳውም ባይረዳውም በጨዋነት እና በትሕትና ምላሽ እንስጥ።አካሄድን መምረጥ ግብን ለመለየት ይረዳል።አንዳንዶች አካልበው ከሁሉ ጋር እያጋጩ ወደ አልሰከነ አቅጣጫ በመውሰድ እንዳያታክቱን መጠንቀቅ ተገቢ ነው።ያለፉት ችግሮች እንዴት በማስተዋል እና ከሁሉም በላይ በጸሎት እንደተፈቱ ዛሬ ላይ ቆሞ ማስታወስ ተገቢ ነው። 

 በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ከቤተክህነት ጦር ሲወረወርበት የተሟላ ሪፖርት ያቀረበ ኢሳት ብቻ ነበር 
ከእዚህ በታች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2014 ዓም በኢሳት የቀረበ ሪፖርት ነበር። 
(ቪድዮውን እስከመጨረሻው ይከታተሉ በርካታ ከአሁኑ ክስተት ጋር የተገናኙ ነጥቦች ያገኛሉ)






==============///=============

Thursday, May 13, 2021

''ኢትዮጵያን ለረጅም ጊዜ እናውቃታለን እንደ ደራጎን ለረጅም ጊዜ ተኝታ ድንገት የምትነሳ ሃገር ነች ብለው የግብፁ ፕሬዝዳንት ሳዳት ሲናገሩ ሰምቻለሁ'' ኮለኔል መንግስቱ ኃይለማርያም የሰጡት መግለጫ (ኦድዮ) ሁሉም ሰው ሊያዳምጠው የሚገባ

 የኢትዮጵያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም ከኢትዮጵያ ከወጡ ግንቦት 13/2013 ዓም ሠላሳ ዓመት ይሞላቸዋል።ከእዚህ በታች ካለው ሊንክ ላይ የኮ/ል መንግስቱ ቃለ መጠይቅ ያድምጡ።በርካታ አሁንም ያለው የኢትዮጵያ አመራርም ሆነ ሕዝብ ሊማርበት የሚገባ ነጥቦች ይዟል።
  
በቃለ መጠይቁ  
>> ደህንነት ሚንስትሩ ተስፋዬ ወ/ስላሴ መጨረሻ ላይ የሰሩትን ክህደት አንስተዋል፣ 
>> አሜሪካ እንዴት ባለሥልጣናቱን እንዳታለለች፣
>> ወደ ኬንያ የሄዱበት ምክንያት ያወሳሉ፣
>> የስነ ልቦና ጦርነት ምን ያህል አሁንም አደገኛ እንደሆነ ያስረዳሉ።
>> ቅድመ አያቶቻችንን አባቶቻችንንም እኛንም ዛሬ የሚፈትነው አንድ ጉዳይ ምን እንደሆነ ያስረዳሉ።
>> ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቀጥል የሚያስፈልገው አንድ እና አንድ ጉዳይ ያስረዳሉ። 
>> የኢትዮጵያ ሕዝብ የተማረ፣በተፈጥሮ በቀላሉ ሊማር የሚችል ጥሩ መሪ ካገኘ ባጭር ጊዜ ያሰበበት የሚደርስ ነው።
>> የኢትዮፖያ ሀብት ከ400 ሚልዮን ሕዝብ በላይ የሚያስተዳድር ሀብት ያላት ሀገር ነች።
ሌሎች እጅግ ድንቅ የሆኑ መልዕክቶች ይዘዋል።ዛሬ ላለንበት ሁኔታ ምላሽ የሚሰጡ ብዙ ሃሳቦች ይዘዋል።እስከመጨረሻ ይከታተሉ።


Wednesday, May 12, 2021

ሱዳን ለሩስያ የባህር ኃይል ወደብ ለመስጠት የተስማማችውን ውል መሰረዝ ለአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ምን ዓይነት በረከት እና እርግማን ያመጣል?

የሩስያ መርከብ (ፎቶ ታስ ዜና አገልግሎት)

>> የአሜሪካ ኢትዮጵያን በትግራይ ጉዳይ የመጎንተል ሥራ በቅርቡ ወደ መቃብር ይወርዳል።

ጉዳያችን/Gudayachn 


ሱዳን እና ሩስያ የሩስያ ባህር ኃይል ጣብያ በሱዳን ወደብ ላይ የጦር ሰፈር እንዲያገኝ ለመጪዎቹ 25 ዓመታት የሚቆይ ውል መዋዋላቸው የተሰማው ባለፈው ታህሳስ ወር መጀመርያ ሳምንት ላይ ነበር።ስምምነቱ ሩስያ የጦር መርከቦቿን በወደቡ ላይ ከማስፈር ባለፈ የመርከብ ጥገና ስራም የምትሰራበት እንደሚሆን ተጠቅሶ፣የኒኩለር ተሸካሚ መርከቦችን ማሳረፍ የጨመረ ዕድል ለሩስያ ሲሰጣት፣ሱዳን በምላሹ ነፃ የጦር መሳርያዎችን ከሩስያ የማግኘት ዕድል እንደሚከፍት ነው የተነገረው።የሩስያ በሱዳን የባህር ዳር ላይ ቦታ ማግኘት የአፍሪካ መግቢያ በር እንደሚሆናት ታስቦ ነበር።በሌላ በኩል የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ሀገሮች (ናቶ) ወደ ደቡብ የሚያደርገውን መስፋፋት ለመግታት የታሰበ የሩስያ አካሄድ ነው በማለት የተነተኑም ነበሩ።

የሩስያ በሱዳን ወደብ ላይ ቦታ ማግኘቷ በዋናነት የቆጠቆጣት አሜሪካ ነበረች።አሜሪካ ከሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት በቶሎ ከማሻሻል አንስቶ ሱዳንን ከአሸባሪ መዝገብ እንድትሰረዝ እና የዓለም ባንክ ገንዘብም ለወቅታዊ ችግሮቿ እንዲሸፍኑ ተሰጥቷታል። አሜሪካ ሩስያ በሶርያ ያላትን መሰረት ማጠናከሯ እንደትልቅ ስጋት የምታየው ሲሆን ወደ ሱዳን ያደረገችውን ግስጋሴ በሱዳን የውስጥ ጉዳይ በመግባት እና በማባበል ውሉ እንዲሰረዝ ያደረገችው አሜሪካ ነች እየተባለች ትታማለች።

የሩስያ ዜና አገልግሎት ''ታስ'' ከሳምንት በፊት እንደዘገበው ስምምነቱ አንድ ዓመት ሳይሆነው ለማቆም መሞከር ሁለቱም ወገኖች አንዳንዳቸው ለአንዳቸው በማሳወቅ ሳይስማሙበት ሊሆን እንደማይችል ከፍተኛ የሩስያ ባለስልጣን እንደገለጡለት ነው ያስታወቀው።ባለሥልጣኑ ይህንን ይበሉ እንጂ ውሉ መሰረዙን ግን የመካከለኛ ምስራቅ መገናኛ አውታሮች እና የሩስያ ዜና አገልግሎትም ገልጧል።

ጉድዩ ለአፍሪካ ቀንድ ይዞት የሚመጣው በረከት እና እርግማን ምንድነው? የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ነው። ሩስያ ፊቷን ወደ አፍሪካ እንደ ቻይና እና ምዕራባውያን ማዙሯ የአደባባይ ምስጢር ነው።ለእዚህም የሩስያ አፍሪካ ግንኙነት ላይ ያተኮረ ጉባኤ ከአንድ ዓመት በፊት በሩስያ ከተደረገ በኃላ ቀጣይ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ጉባኤ በአፍሪካ እንደሚደረግ መነገሩ ያታወቃል።ጉባኤውን ለማዘጋጀት ኢትዮጵያ ፈቃደኛ መሆኗን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር  እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ደመቀ መኮንን አማካይነት መግለጧ ይታወሳል።አማርኛ አቀላጥፈው የሚናገሩት በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር ኤቭገኒ ተረኪን ሩስያ የኢትዮጵያ አጋር ሀገር መሆኗን ባገኙት አጋጣሚ ሲገልጡ ተሰምተዋል።ሩስያ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ጉዳይ አስታኮ የጠራቸውን ስብሰባዎች በሙሉ በመቃወም ማክሸፍ ከቻሉት ሀገሮች ውስጥ ግንባር ቀደሟ ነች።ከእዚህ በኃላ ነው የተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያከብር እና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ መግባት ተገቢ አለመሆኑን አፅንኦት የሚሰጥ መግለጫ ያወጣው። 

የአፍሪካ ቀንድ በሁሉም የዓለም ኃያላን ዘንድ መጪው ቁልፍ የበለጠ ስልታዊ ብቻ ሳይሆን ግዙፍ ምጣኔ ሀብት ይዞ ይወጣል ተብሎ የሚታሰበው እና ለአንዳንዶች ''የሚፈራው'' ጠቅላይ ዓቢይ ወደ ስልጣን እንደመጡ ያቀነቀኑት የኤርትራ፣ኢትዮጵያ እና ሱማሌ የምጣኔ ሀብት ጥምረት ሃሳብ ነው።ይህ ሃሳብ ግዙፍ የገበያ ማዕከል ብቻ ሳይሆን ይዞ የሚመጣው የቀይ ባህርን በተሻለ ጉልበት የመቆጣጠር ኃይል ለሶስቱ ሀገሮች ይሰጣል።ስለሆነም የሩስያ ቀጣይ መንገድ በኤርትራ የባህር ኃይል መሰረት የማግኘት ዕድል ከገጠማት እና ኢትዮጵያ የባህር ኃይሏን እንደጀመረችው ማደራጀት ከቻለች በአካባቢው ላይ ተፅኖ መፍጠር የሚፈልጉ ኃያላን ጥቅማቸው የሚነካ አድርገው ያዩታል።ስለሆነም ሩስያ እና ቻይና ከሚጠቀሙ የአፍሪካ ቀንድ ቢበታተን የሚመርጡ የሉም ማለት አይቻልም።የሶስቱ ሀገሮች የምጣኔ ሐብት ጥምረት ግን ለሦስቱም ሀገሮች ከፍተኛ ጥቅም ይዞ መምጣቱ አያጠራጥርም።በተለይ  በአንፃሩ የተሻለ የሰው ኃይልም ሆነ የምጣኔ አደረጃጀት ያላት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥላ የምታጠላበት ጥምረት እንደሚሆን ነው የሚታመነው። ስለሆነም ሶስቱ ሀገሮች በሩስያ እና በአሜሪካ አንፃር የሚጫወቱት ጫወታ ከሀገሮቹ ዘላቂ ጥቅም አንፃር በደንብ አጥንተው የሚገቡበት መሆን አለበት ማለት ነው።

የሩስያ ከሱዳን የባህር ኃይል ማረፍያ አለማግኘት ማለት አማራጭ ቦታ የላትም ማለት አይደለም።በኢትዮጵያ አግባቢነት በኤርትራ የማግኘት ዕድል አሁንም አላት።ይህ እንዳይሆን አሜሪካ ኢትዮጵያን የማትለምንበት መንገድ አይኖርም።በእርግጥ ከመለመን በፊት አሜሪካ በትግራይ ጉዳይ አሳባ ብዙ የማወክ ሙከራ በኢትዮጵያ ላይ ላለፉት ስድስት ወራት ስታስኬድ ሰንብታለች።በውጤቱ ግን የተሳካ ሆኖ አላገኘችውም።የግብፅ የደህንነት ባለስልጣናት ለአሜሪካ 'የኢትዮጵያን ነገር ተይው ከውስጥ የጀመርነው ፕሮጀክት አለ' እያለች ስታማልል ብትከርምም በቅርቡ ግን ከቤንሻንጉል እስከ መቀሌ ያለው የተንኮል ድር በሙሉ በመበጣጠሱ አሜሪካ ከሰሞኑ የመለሳለስ መልክ ብታሳይም አይገርምም።

አሁን የአሜሪካ ስጋት ሩስያ ከኢትዮጵያ ጋር ከገጠመች በተለይ በኤርትራ ወደብ የባህር ኃይል ከመሰረተች ከሶርያ ቀጥሎ ሩስያ ቁልፍ ማረፍያ እንዳገኘች ትቆትረዋለች ብቻ ሳይሆን ከመካከለኛው ምስራቅ ወደ አፍሪካ የምታደርገው እመርታ ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነ ተረድታዋለች። ይህም ከቀዝቃዛው ጦርነት በኃላ ሩስያ እንደገና ወደ አፍሪካ አንፃር አንሰራራች ማለት ነው።ስለሆነም የሱዳን ውል ማፍረስ ለኢትዮጵያ ይዞ የሚመጣው አንዱ በረከት አሜሪካ ኢትዮጵያን በትግራይ ጉዳይ መጎንተሏን ታቆማለች ወይንም ታቀዘቅዛለች።በመቀጠልም ሰሞኑን እያሳየች እንዳለው የዓባይ ግድብ አንፃር ኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ሀብት የማልማት መብት አላት የሚለውን አረፍተነገር በመደጋገም ታፈገፍጋለች።ኢትዮጵያ ይህንን የሩስያን ጉዳይ ከኤርትራ ጋር ተመካክራ እንደ ታላቅ ወንድም እያስፈራራች ምርጫውን እና የውሃ ሙሌቷን ከጨረሰች ቀሪውን ውሳኔዋን ከመስከረም አደይ አበባ መፈንዳት ጋር ቀስ ብላ ቡና ፉት እያለች መወሰን ትችላለች።

ለማጠቃለል የአሜሪካ በትግራይ ጉዳይ ኢትዮጵያን የመጎንተል ሂደት በቅርቡ ወደ መቃብር በእዚሁ በሩስያ ጉዳይ እንደሚያበቃ ግን ከወዲሁ መገመት ይቻላል።ይህ ማለት አንዳንድ በሎቢ የቀወሱ ሴናተሮች እና ጋዜጠኞች ዝም ይላሉ ማለት አይደለም። ዋናዎቹ የውጭ ፖሊሲ አውጪዎች ግን አንዳች እርምጃ ሊወስዱ አይችሉም ቢያንስ ለመጪዎቹ አራት ወራት።ሌላው ቀርቶ የአውሮፓ ህብረት አዲስ የሳተላይት መሳርያ ካላስገባሁ፣የምርጫ ውጤቱን እኔ ቀድሜ የመናገር መብት ካላገኘሁ እያለ ትንሽ  ጠገብ ብሎ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ሃሳቡ ተቀይሮ ባላችሁት መሰረት ለምርጫው ታዛቢ እልካለሁ ማለቱ ሁሉ የኢትዮጵያ ቦታ መልሶ መሬት እየቆነጠጠ መሆኑን ብቻ ሳይሆን የሚያሳየው አፍሪካ ቀንድ ላይ ያለው መራኮት ኢትዮጵያን ከሁሉ በላይ አስፈላጊ መሆኗንም ጭምር ነው።ይህ እንግዲህ በመላው አፍሪካ ላይ ያላትን ተፅኖ የመፍጠር አቅም ሳናነሳ ነው።ኢትዮጵያውያን ግን አሁን ማተኮር የሚገባው ግዙፍ እርዳታ በተለይ በቤተ እምነቶች አንፃር ለትግራይ እና በልዩ ልዩ ስፍራ አደጋ እና ጥቃት ለደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን የእርዳታ ሀብት ማሰባሰብ እና መርዳት ነው።የኢትዮጵያ ቁስል ይሽራል።ከትግራት እስከ መተከል፣ከአጣዬ እስከ ወለጋ የተጎዱትን የመርዳቱ ተግባር ግን መቀጠል አለበት።
=======================////=============

Tuesday, May 11, 2021

የክርስትና እና የሙስሊም የእምነት አደረጃጀቶች የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች እንዳይጎትቷቸው መጠንቀቅ አለባቸው።


ጉዳያችን/Gudayachn


ኢትዮጵያ የእምነት ሀገር ነች።ህዝቧ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በፈጠረው አምላክ ያምናል።በችግሩ እና በደስታው ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሰላምታው ጊዜም ሳይቀር አምላኩን የሚጠራ ሕዝብ ነው።ይህ ሕዝብ ካለምንም ማጋነን ከየትኛውም የዓለማችን ክፍል በተለየ እና በፀና ደረጃ በብዙ ፈተና ውስጥም ቢሆን ከፈጣሪው ጋር ግንኙነት አለው።በሌላው ሀገር የማናገኘው የሞራል ልዕልና በኢትዮጵያውያን ላይ የሚታየው ሌላ ሳይሆን የሕዝቡ በፈጣሪው ላይ ያለው ዕምነት ነው።በቅርቡ በአዲስ አበባ አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣን እንደተገለጠው በአዲስ አበባ ብቻ በቀን አንዴ በልተው ለማደር የሚቸገሩ ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ሕዝብ አለ።በእዚህ ደረጃ ችግር ላይ ያለ ሕዝብ ግን የእምነት ሕዝብ ስለሆነ አንዱ አንዱን እየረዳ የሚኖር የተቸገረውም በትሕትና እንጂ በነጠቃ የማይኖርባት ሀገር መሆኗን ይህ በራሱ ምስክር ነው።

ይህ በእንዲህ እያለ ይህ ወቅት የኢትዮጵያ የክርስትናም ሆነ የሙስሊም አደረጃጀቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ነቅተው እና ተግተው የሚቆሙበት ጊዜ ነው።በሁለቱም ዕምነቶች ውስጥ አደረጃጀቶቻቸውን ለመክፈል እና የፀብ መድረክ ለማድረግ በተለያዩ የፖለቲካ አካላት ጉተታ ይታያል።ጉተታዎቹ ሦስት ዓላማዎችን ይዟል። እነርሱም -  የእምነት ድርጅቶቹን እርስ በርስ በውስጣቸው ሰላም እንዳያገኙ ማበጣበጥ፣ከመንግስት ጋር ማጋጨት እና አንዱን እምነት ሌላውን እንዲጠራጠር ወሬ መንዛት ናቸው። 

በእስልምናም ሆነ በክርስትና ውስጥ ያሉ የውስጥ ቁርሾዎችን ማባባስ እና አደረጃጀቶቹ ሰላም እንዳይሆኑ በማድረግ ተከታዩ ምዕመንን ሰላም መንሳት እና በውጤቱ ሀገር እንዳይረጋጋ እና ሰላም እንዲጠፋ በማድረግ ርካሽ የፖለቲካ ግብ መምታት ነው።
በእዚህ መሰረት በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ውስጥ የበላይ አመራር መጅሊሱን ሕዝብ እንዳይቀበል የሚቀሰቅስ ቅስቀሳ በማካሄድ የፅንፍ ኃይሉ የበላይ እንዲሆን የማድረግ ሙከራ ነው።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ውስጥ ተመሳሳይ ድርጊቶች ይታያሉ።በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሰሞኑን ቅዱስ ፓትርያሪኩ ከአንድ ወር በፊት የተቀዳው እና ወቅታዊ የኢትዮጵያን ሁኔታ የተመለከተ ቪድዮ ሰሞኑን መለቀቁን  የቤተክርስቲያኒቱን መዋቅር እና ድምፅ በትክክል የማይወክሉ የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች እዚህም እዝያም በሚድያ እየቀረቡ በቤተክርስቲያኒቱ ስም ሲናገሩ እየታየ ነው።በተለይ የኢትዮጵያ ሚድያዎች የቤተክርስቲያኒቱን ተዋረድ ሳይጠብቁ ያገኙትን ካህን በቤተክርስቲያኒቱ ስም ማናዘዝ እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው።ቤተክርስቲያኒቱም የህዝብ ግንኙነት በተመለከተ በማዕከላዊነት የምትመራበት አንድ ድምፅ እንዲኖራት እና ማንም ከእዚህ ማዕከላዊ የህዝብ ግንኙነት ውጪ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የሚናገር አገልጋይ እንዳይኖር ጥብቅ መመርያ ያስፈልጋታል። 

ሌላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ሆነ የእልምና ተከታዮች በተለያየ ጥግ ሆነው ከመንግስት ጋር እንዲጋጩ የሚሰሩ አሉ። እነኝህ የተለያየ ዓላማ የያዙ ናቸው።በእስልምና ውስጥ እጅግ ፅንፍ የያዘ እና የራሱን መጅሊስ ቆርጥሞ በልቶ እና እውነተኛ አማኙን ከመስጊድ አስወጥቶ በሌሎች ሀገሮች የሚታየው የፅንፍ አስተዳደር በእምነት ስም መለጠፍ የምፈልገው ቡድን በቅድምያ ሙስሊሙ ከመንግስት ጋር እንዲጋጭ ማድረግን እንደዋና ግቡ ወስዶታል።ለእዚህም ያገኘውን  እያሰፋ ነገር ስጎነጉን የሚያድር ነው።ይህንን አብዛኛው ሙስሊም ስላወቀበት አንዳንዴ ተመሳስሎ ሲቆም ይታያል።

በተመሳሳይ መንገድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ውስጥ በተለይ ላለፉት 27 ዓመታት በሌሎቹ የእምነት አደረጃጀቶች ውስጥ የታየው  ፀሐይ የሞቀው የአንድ ብሔር የበላይነት ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ በመጣው ለውጥም ሆነ በቀድሞው ሥርዓት ላይ በቅርቡ የተወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ሳይቀር ስላስከፋው ቤተክርስቲያኒቱን ለመከፋፈል በተለይ በውጭ ሀገር አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ እየታየ ነበር።ይሄውም የትግራይ ካሕናትን ከቅዱስ ሲኖዶስ ስር ለመለየት አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ሲያደርጉ ታይተው በትግራይ ካህናት ሳይቀር ከፍተኛ ተቃውሞ ስለገጠመው አድፍጦ መቀመጡ እየታየ ነው። በተለይ የእዚህ ዓይነቱ ቡድን በትግራይ በሚኖሩ አባቶች ቢሰማ የሚደርስበትን ውግዘት የተረዳው ቡድን ቤተክርስቲያኒቱን ለመረበሽ አንዳንድ ያልተሳኩ እና የማይሳኩ ሙከራዎች እያደረገ ነው።

የመጨረሻው በኢትዮጵያ የክርስትና እና የእስልምና አደረጃጀቶች ውስጥ እየታዩ ያሉ ተግዳሮቶች አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ እንዲመለከት ማድረግ ነው።ይህ ደግሞ የሐሰት ወሬዎች በመንዛት ሲሆን በፅንፍ አካሄድ የሚታወቁ የፖለቲካ ድርጅቶች ዋና አቀጣጣዮች ናቸው።ይህ አለመተማመን የመፍጠር ሂደት በተለይ የእምነቶቹን ሊቃውንት ያገለለ በመሆኑ ''መደዴ'' የሆኑ የእምነቱ ተከታዮች ቀድመው በመናገራቸው ወይንም በመሳደባቸው ''እንደመሪ'' እየሆኑ የሚወጡበት ስለሆነ አደገኛ አካሄድ ይታይበታል።

ባጠቃላይ  የክርስትና እና የሙስሊም የእምነት አደረጃጀቶች የተለያዩ የፖለቲካ እና የፅንፍ ኃይሎች ጉተታ ውስጥ እንዳይገቡ  ከመቼውም ጊዜ በላይ የእስልምናም ሆነ የክርስትና አደረጃጀቶች የውስጣዊ ጥንካሪያቸውን፣በልቃውንቶቻቸው እና በሕጎቻቸው ላይ ብቻ በተመሰረተ መንገድ መመራታቸውን በደንብ መፈተሽ አለባቸው። 99% የሚሆን ሕዝብ በፈጣሪው የሚያምን ሕዝብ  ሀገር የእምነት አደረጃጀቷ ጤነኛ ብቻ ሳይሆን ለሀገር እድገትም አዎንታዊ አስተዋፅኦ ያለው እንዲሆን ያለምንም ወገንተኝነት የማገዝ ግዴታ ደግሞ መንግስት አለበት።መንግስት የኢትዮጵያ የእምነት አደረጃጀቶች መጠናከር እና ምእመናኖቻቸውን በሚገባ ማገልገል ማለት ሃገራዊ ሰላም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን በሰላም የማሸጋገር አንዱ እና ወቅታዊው ወሳኝ ተግባር ነው።ከሁሉም በላይ ወሳኞቹ ግን የክርስትናም ሆነ የእስልምና የውስጥ ጤነኛ፣በፖለቲካ ኃይሎች ያልተዘወረ ግን የእምነት ነፃነቱን የጠበቀ የእምነት አደረጃጀት እንዲኖራቸው ጠንክረው ሲሰሩ ነው። ''እውነት አርነት ያወጣችኋል'' ዮሐንስ 8፣32 እንዲል ታላቅ ሀገር ኢትዮጵያን ነፃ የሚያወጣት፣ እምነቷን ጠብቆ የሚያቆይም እውነት እንጂ የተለያዩ አመለካከቶች ጉተታ እና የእነርሱ ሰለባ መሆን አይደለም።

========================///=============

እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው።"
(ዮሐንስ 8:32)
እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው።"
(ዮሐንስ 8:32)

The Ethiopian Orthodox Tewahedo Church is in turmoil in Athens, Greece.

His Holiness Abune Mathias I, Patriarch of the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church, met with Greece's Ambassador to Ethiopia, Antonios Sg...