ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, May 14, 2021

ማኅበረ ቅዱሳንንም ኢሳትንም ለሚያውቅ ለእኔ የኢሳትን፣የጋዜጠኛ ሲሳይን አስተያይተም ሆነ የማኅበረ ቅዱሳን መግለጫ የምረዳበት ዓውድ።

>> የአቡነ ማትያስን አባትነንትን ማክበር የቤተ ክህነትን የአስተዳደር ብልሹነት እና ወደፊት የሚወሰደውን የማስተካከልን ሥራ ፈፅሞ ሊጋርደው አይገባም።   

(የጉዳያችን ልዩ ጥንቅር) 

በክፉ ጊዜ ለማኅበረ ቅዱሳን የተሟገተው ኢሳት እና  ጋዜጠኛ ሲሳይም ሆነ ማኅበረ ቅዱሳን ሁሉም  የኢትዮጵያ ሕዝብ የተከበሩ ሐብቶች ናቸው። ሁሉም ለሀገራቸው እና ለወገናቸው መልካም ባደረጉ፣የእድሜ ግማሽ ዘመናቸውን ለኢትዮጵያ በወጡ በወረዱ ማንም እንደፈለገ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሊያደረግባቸው አይገባም።ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚድያ ሶስቱም ላይ የሚፈፀሙት የስም ማጥፋት ዘመቻዎቹ በትክክል ነጥብ በነጥብ ጉዳዩን እያነሱ ከሚሞግቱት ውጪ አጋጣሚውን ተጠቅመው ብስለት የሌላቸው፣ነገር ግን በአጋጣሚው የማኅበረ ቅዱሳንንም፣የኢሳትንም ሆነ የጋዜጠኛ ሲሳይ አጌናን ስም ተገቢ ባልሆነ እና ጨዋነት በጎደለው መልክ በማኅበራዊ ሚድያ የሚያጥላሉ እየተመለከትን እየታዘብን ነው። አንዳንዶቹበሶስቱም ላይ በአመለካከታቸው፣በአሰራራቸው እና በእምነት ጭምር ቀድሞም ሲያጥላሉ የነበሩ ዛሬ በተፈጠሩ ጉዳዮች አስታከው ወደ የለየለት የማጥላላት ዘመቻ ሲገቡ እያየን ነው።ይህ ሊቆም ይገባዋል።በመሃል ነገር የሚያካርሩ እና በአጋጣሚው የግለሰብንም ሆነ የድርጅትን ስም ለማጠልሸት ለሚሯሯጡ ዕድል ሊሰጥ አይገባም።

የሆነው ምንድን ነው? 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደረጃ መምርያ ስር የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን በያዝነው ሳምንት መጀመርያ ላይ መግለጫ አወጣ።መግለጫው ከእዚህ በፊት ማኅበሩ ካወጣቸው መግለጫዎች ጠንከር ያለ መግለጫ ነው።መግለጫው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስደት ላይ ነች በሚል ርዕስ ሆኖ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ  የደረሰው እና ወደፊት የተጋረጠባት አደጋ የከፋ ነው የሚል ሃሳብ ይዟል።በመግለጫው ይዘት ላይ በእዚሁ ሳምንት አጋማሽ ላይ ለአደባባይ ሚድያ ማብራርያ የሰጡት የማኅበሩ አመራሮች በእዚህ ዓመት የተመረጡ እና ወደ አመራር የመጡ ቢሆኑም ከእዚህ በፊት በማኅበሩ አገልግሎት ላይ ግን ረዘም ያለ ጊዜ እንዳላቸው እና የወጣው መግለጫ ግን በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ካለው ፈተና አንፃር እንድያውም ያነሰ መሆኑን ገልጠው መንግስት በተደጋጋሚ ለደረሱት ጥፋቶች ተገቢውን ምላሽ ክብር ባለው መልክ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አለመስጠቱ በራሱ ብዙ ነገር እንደሚያመላክት ገለጡ።

ይህንን መግለጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በዕለታዊ ዝግጅቱ ላይ መግለጫው ላይ ትችት አቀረበ። ትችቱ በተለይ ከእዚህ በፊት ቤተ ክርስቲያን በተለይ በዘመነ ህወሓት የነበረችበት የፈተና ዘመንን በሚገባ አያብራራም፣ይልቁንም ይህንን ጉዳይ መንግስት በትኩረት ሊመለከተው የሚገባ ነው የሚል ሃሳብ ጨምሮ በተለይ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና በቅርብ ወደ ማኅበሩ የመጡ አመራሮች የወቅቱን አመራር የማይደግፉ መሆናቸው ነው የሚል ከሆነ ሰው እንደሰማ የሚገልጠውን ሃሳብ ጨምሮ በውይይቱ ላይ አቀረበ።

 የማኅበረ ቅዱሳንን መግለጫ የምረዳበት ዓውድ።

ማኅበረ ቅዱሳንን ከምስረታው ጊዜ ጀምሮ ብቻ ሳይሆን የዩንቨርስቲ ተማሪዎች በብላቴ በዘመቱበት ጊዜ ከዘማቾቹ አንዱ ስለነበርኩ እና ለማኅበሩ መመስረት እንደ አንድ ጥንስስ የሚቆጠረው በብላቴ አየር ወለድ ማሰልጠኛ ኬስፓን ውስጥ ከዘማቾቹ አንዱ ከሆነው ከሙሐዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት እና ሌሎች ወንድሞች የምሽት ትምሕርት ጀምሮ የማኅበሩን ሂደት አውቀዋለሁ።የማኅበሩም አገልግሎት  ከምንም አድርባይነት የፀዳ መሆኑን ፣እዚህ ላይ መጥቀስ የማያስፈልጉ ብዙ ፈተናዎች አባላቱ የተቀበሉበት ከሁሉም በላይ ከብሄር እና ጎሳዊ አስተሳሰብ ፈፅሞ የፀዳ ለመሆኑ ምስክር ነኝ።ሌብነት እና ሙስና በተንሰራፋባት ሀገር በመልካም ዜግነት የታነፁ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አባላት ያፈራ እና ለኢትዮጵያ ዘመናዊ የሲቪልም ሆነ ወታደራዊ ኃይል መልካም እና ታማኝ  ዜጋ በማፍራት ሂደት የራሱን አስተዋፅኦ ያደረገ ማኅበር ነው።

ማኅበረ ቅዱሳን በሩቅ የሚያዩት አንዳንዶች ከቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውጪ አድርገው የሚያስቡ አሉ።ሆኖም ማኅበሩ በቅዱስ ሲኖዶስ መተዳደርያ ደንቡ ተለክቶ እና ተወስኖ የተሰጠው እንዲሁም በቤተ ክርስያንቱ መዋቅር ስር የሚገኝ ከመሆኑም በላይ እያንዳንዱ የአገልግሎቱን ሪፖርት ለቅዱስ ሲኖዶስ  እና በሚገኝበት መዋቅር ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምርያ የሚያቀርብ የአገልግሎት ማኅበር ነው።

በቅርቡ ማኅበሩ ያወጣው መግለጫ የቤተ ክርስቲያንን ስደት ብሎ የተነሳበት ነጥብ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት የግራው ፖለቲካ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ መሆኑን ነው የገለጠው።ስደት የሚለውን ብዙዎች ከፓትርያሪክ ስደት ጋር ብቻ አያይዘው ቤተክርስቲያን ተሰደደች የሚባለው ከአባቶች ስደት ጋር አያይዘው ግራ የተጋቡ አሉ።ይህ ግን ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ትርጉም ከክርስቲያኖች ስብስብ፣ከሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እና ከአንድ ክርስቲያን በአምሳለ እግዚአብሔር መፈጠሩን በሶስት ከፍሎ የሚሰጠውን የቤተክርስቲያን ትርጉም ካለመረዳት የሚመጣ ነው።ስለሆነም ስደት ሲባል የክርስቲያኖች ከወለጋ እስከ ባሌ፣ከሻሸመኔ እስከ ሐረር በክርስቲያኖች ላይ የደረሰውን ስደት፣ግድያ እና መከራ ሁሉ ቤተክርስቲያን እያንዳንዱ ሰውነትም ናትና የክርስቲያኖች መሰደድ የቤተ ክርስቲያን ስደት ተብሎ ይጠራል። ይህ ብቻ አይደለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በአደባባይ ከሚያከብሯቸው በዓላት ውስጥ እንደ መስቀል እና ጥምቀት ያሉት በዓላት ባሳለፍነው ሶስት ዓመታት ውስጥ በቢሸፍቱ እና ሆሳዕና ጨምሮ በአንዳንድ ቦታዎች ምዕመናን ማክበር አልቻሉም።

ቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ ማኅበረ ቅዱሳንን ምክንያት በሌላው መንገድ ከመውቀስ አልፈው ፈተና ያመጡበት ጊዜም ነበር።ለእዚህም ማኅበሩ የሰጠውን ምላሽ እንደ አንድ ማሳያ መመልከት ይቻላል።ማኅበሩ በፓትርያሪኩ ተወቅሶ የሰጠውን የጽሁፍ  ምላሽ ይህንን   በመጫን ማንበብ ይችላሉ።ይህም ሆኖ ግን ማኅበሩ ፓትርያሪኩን በመንበራቸው ክብር መከበር እንዳለበት ደጋግሞ ሲናገር ቤተክርስቲያኒቱ ከእዚህ በፊት የቤተ መንግስቱ ፖለቲካ ሲቀያየር ቤተክህነቱ ፓትርያሪክ እንዲቀይር የሚደረገው ሴራ ዛሬ ሊደገም እንደማይገባ በአፅንኦት ከማሳሰብ አንፃር የሚታይ ነው።ይህ ማለት ግን የቤተ ክህነት አስተዳደራዊ አሰራርም ሆነ የሙስና ተግባራት ሁሉ አይስተካከል የሚል እንደማይሆን ነው የሚገባኝ።

በአጠቃላይ ማኅበረ ቅዱሳን በእየለቱ ከመላዋ ኢትዮጵያ ካሉት የአገልግሎት መዋቅሮች ከአዲስ አበባ እስከ ታች ወረዳ ያለው የቤተ ክርስቲያን ፈተና ሪፖርቶች በእየሰዓቱ ለዋናው ማዕከል ይደርሱታል።እነኝህ ሁሉ ሪፖርቶች ብዙዎች አያውቁትም።ዛሬ ባሌ፣ከፋ፣አርሲ እና ሐረር በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ ካህናት ጠምጥመው ገበያ ቢወጡ በድንጋይ የመወገር አደጋ ስላለባቸው ጥምጣማቸውን አውልቀው ከቤታቸው እንደሚወጡ የሚያውቅ ጥቂት ናቸው።ይህ አንዱ የቤተ ክርስቲያን ስደት ማሳያ ነው።ሁኔታው በአፋጣኝ ካልተሻሻለ የሀገሪቱ የፀጥታ ችግር እንዳይሆን ከምርጫው በኃላ የሚመጣው መንግስት ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል።

በክፉ ጊዜ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ስር ለሚገኘው ለማኅበረ ቅዱሳን የሞገተው ኢሳትንም ሆነ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌናን በተመለከተ የተረዳሁበት አውድ 

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን ዛሬ አንዳንዶች ከፖለቲካ አስተሳሰብ እና ከገቡበት የዘውግ ፖለቲካ አንፃር በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ሊያጥላሉት ቢሞክሩም፣ኢሳት ላለፉት አስር ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ ተንሰራፍቶ የነበረውን የህወሓት/ኢህአዴግ የጭቆና ስርዓት በግንባር ቀደምትነት በመዋጋት ስሙ ከሚጠሩት ውስጥ ነው።እሳትንም ቀረብ ብዬ እንደመመልከቴ  ሰሞኑን አንዳንዶች ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር እያያዙ እንደሚነቅፉት ፈፅሞ አይደለም።ባለፉት አስር ዓመታት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በስሯ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን ላይ በስርዓቱ እና በቤተ ክህነት ውስጥ በተሰገሰጉ የህወሓት አቀንቃኞች የሚነሱ አቧራዎች ሁሉ ኢሳት ለሕዝብ በማጋለጥ ግንባር ቀደም እንደነበር ምስክር ነኝ።የኢሳት ጋዜጠኞች ሲሳይ አጌናም ሆነ መሣይ መኮንን በማኅበረ ቅዱሳን ላይ እየደረሱ የነበሩትን ቅሰጣዎች ሁሉ እራሱን የቻለ መርሃግብር እያዘጋጁ ለሕዝብ በራድዮ እና በቴሌቭዥን እንዲተላለፍ አድርገዋል።መሳይ መኮንን ማኅበረ ቅዱሳንን አስመልክቶ ባደረጋቸው ወደ ሶስት ጊዜ የሚሆኑ የዜና ዝግጅቶች ላይ እራሴንም ጋብዞኝ በማኅበሩ ላይ እየደረሱ የነበሩ ፈተናዎች በተመለከተ እንድናገር ዕድል ሰጥቶኝ በወቅቱ በራድዮ እና ቴሌቭዥን ፕሮግራሞች ላይ ቀርበዋል (ከእዚህ ፅሁፍ በታች የኢሳትን ማኅበሩ ላይ እየደረሰ ያለውን ፈተና ለሕዝብ ያሰማበት  ልዩ ዝግጅት በቪድዮ ያገኛሉ)።

ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌናም በተለያዩ የዕለታዊ ዝግጅቶች ላይ በማኅበሩ ላይ እየደረሱ የነበሩትን ፈተናዎች ከማቅረቡም በላይ በአንድ ወቅት ራሱን የቻለ ልዩ ዝግጅት አቅርቦ ነበር።አንዳንዶች በወቅቱ ምናልባት ኢሳትን በሚገባ ሳይከታተሉ ዛሬ በአንድ ፕሮግራም በኢሳት ላይም ሆነ በጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ላይ እጅግ ነውረኛ የሆነ የስም ማጥፋት ቃላት ሲጠቀሙ ስመለከት በጣም ያሳዝነኛል። ይህ የሚመለከተው በአግባቡ ሃሳባቸውን የገለጡትን ሳይሆን በማኅበራዊ ሚድያ በወረደ መልኩ ስም ለማጥፋት የሚሞክሩትን ነውረኞች ነው። 

 ሰሞኑን በተደረገው የኢሳት ዕለታዊ ላይ በተለይ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና በማኅበረ ቅዱሳን መግለጫ ላይ የሰጠው አስተያየት በእርግጥ መታረም ያለባቸው ቃላት ቢኖሩበትም መነሻው ብዬ የምረዳው ግን ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት እጅግ ወሳኝ ጊዜ እና   በተለያየ አካላት በተከታታይ ከሚታዩት ሃገራዊ ሴራዎች አንፃር በማኅበሩ መግለጫም ለሀገር ከመጨነቅ አንፃር እረብሾታል።እርሱ የተሰማው ስሜት ደግሞ ማንም ሃገሩን የሚወድ ሰው የሚሰማው ስሜት ነው።ስለሆነም ስሜቱን በነካው መጠን ከሚገባው በላይ ድምፀቱን አክብዶታል።ይህ ማለት በማብራርያው ላይ መታረም ያሉባቸው አንዳንድ  አገላለጦች እንዳሉ ሆነው አንዳንዶች በነውረኛ አቀራረብ በጋዜጠኛው ላይ እና በኢሳት ላይ እንደሚሉት ግን ፈፅሞ አይደለም። 

ባጠቃላይ ግን ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ከእድሜው ከ1/4ኛ በላይ በኢትዮጵያ ጉዳይ የፃፈ፣የታሰረ፣የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያስጨንቀው እና ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሁሉም ዕምነቶች እኩል አክብሮት ያለው ወደፊትም የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያከብረው ጋዜጠኛ ነው። በመሆኑም አንዳንዶች ሰሞኑን በወረደ መልኩ ሊገልጡት እንደሚሞክሩት ያለ ግለሰብ አይደለም። አንድ በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ የተለመደ ክፉ ልማድ፣ አንድ ሰው አንድ ቀን የተሳሳተ ነገር የተናገረ ጊዜ የምናወርድበት ውርጅብኝ እና ለሀገር ስንት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ የተከበሩ የሀገር ሃብቶችን አጥላልተን የምንጥልበት መጠን የከፋ ነው።ይህ ኢትዮጵያን ሰው እንዳይወጣላት ያደረገ አጨንጋፊ ክፉ ልማድ ነው።በተለይ ማኅበራዊ ሚድያ ከመጣ በኃላ ስም እየቀየሩ መፃፍ እና ግለሰቦችንም ሆነ ድርጅቶችን ማብጠልጠል የተለመደ እኩይ ሥራ ነው። 


የመጨረሻው መጨረሻ ግን አንድ ነገር ሳልል ማጠቃለል የለብኝም።ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ማክበር የነቀዘውን የቤተ ክህነት የሙስና አሰራሮችን ማስተካከል እና ሙሰኞችን ከመንቀል ጋር ሊጋጭብን አይገባም።ቤተክህነት አሰራሩን ዘመናዊ ማድረግ አለበት። ሙሰኞች እና በቤተክህነቱ ውስጥ ተጠልለው ለዓመታት ወንጀል የሰሩ ገለል ማለት አለባቸው።
 ይህንን ብንስማማም ባንስማማም እግዚአብሔር የቆረጠበት ቀንን ማንም አይቀይረውም።ክርስቶስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲሸጡ ሲለውጡ የነበሩትን መንጥሮ ለማውጣት ጅራፉን ይዞ የሚመጣበትን ቀን ከፈሪሳውያን እና ፃሕፍት ጋር ተመካክሮ አልወሰነም።ስለሆነም ይህንን ቀን ማንም አያቆመውም።

አዎን! ቤተክርስቲያን ከውጪ እየደረሱባት ያሉት ፈተናዎች ቀላል አይደሉም።ነገር ግን ፈተናዎቹን የውስጥ ችግሯን ቀድማ ከመፍታት ውጪ የውጭ ፈተናዎችን መከላከል ከባድ ነው።ቤተክርስቲያኒቱን የመንግስት ሙሉ አካል ተፃራሪዋ ነው የሚለው የአንዳንዶች አስተያየትም ትክክል አይደለም።ከመንግስት መዋቅሮች ውስጥ በጠላትነት የሚያይዋት አሉ የሚለው የተሻለ አገላለጥ ነው።መንግስት ግን እንደ መንግስት የሀገሪቱ ግማሽ በላይ አካል ከሆነች ቤተክርስቲያን ጋር አለመስራት ብቻ ሳይሆን የተሻለች እና  የቀለጠፈ እንዲሁም የጠለቀ መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት ሕዝቡ መርካቱ ለራሱ ለመንግስት ቢያንስ በፖለቲካዊ የሰመረ  አስተዳደር አንፃርም ብናየው የሚፈልገው መሆኑን አለመረዳት በራሱ የአስተሳሰብ መዛነፍ ችግር ነው።ስለሆነም አንዳንዴ አላስፈላጊ መጠራጠር አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም። ትልቁ ጉዳይ ቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥ የሙስና እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች አስተካክላ እና መንፈሳዊ አገልግሎቷን በትሕትና፣በፍቅር እና በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ማስፋፋት፣ተግዳሮቶቹን ከምዕመኑ ጋር በብልሃት እና በእግዚአብሔር ዕርዳታ እየተጋፈጠች መሄዱ ላይ ነው ቁም ነገሩ።ከእዚህ በተጨማሪ የአገልግሎት ማኅበራት በዋናነት ሊያተኩሩበት የሚገባው ማኅበራዊ  አገልግሎት ማስፋፋት እና መላ ሀገሪቱን በሚሸፍን ደረጃ የማጠናከር ሥራ ላይ ነው።ይህ እጅግ የበዙ ጥቅሞች አሉት።በእዚህም የሀገሪቱን ችግር በመጠኑ ይቀርፉበታል፣ከመንግስት መዋቅሮች ጋር በልማት አጋርነት ይተጋገዙበታል፣ተደማጭነታቸው በሕዝቡም ሆነ በመንግስት ዘንድ ያጎሉበታል።ስለሆነም የትኩረት አቅጣጫዎች በአግባቡ መምረጥ እና የበጎ ተፅኖ  መፍጠርያ ቦታዎችን ለይቶ የቤተ ክርስቲያንን ታሪካዊ ቦታ የማስያዝ አንዱ እና ዓይነተኛ መንገድ እንደሆነ ማወቅ ብልሕነት ነው። ከእዚህ በተረፈ ግን ትሕትናን ገንዘብ እናድርግ! መሰደብ መነቀፍ አያስቆጣን።በክርስትና ሕይወት የምንከተለው የተነቀፈ እና የተሰደበ ብቻ ሳይሆን የተገረፈ እና የተሰቀለ አምላክ እና አንገታቸውን የተቆረጡ ሰማዕታት ናቸው።ለተተቸው እና ለተነቀፈ ጉዳይ ሌላው ቢረዳውም ባይረዳውም በጨዋነት እና በትሕትና ምላሽ እንስጥ።አካሄድን መምረጥ ግብን ለመለየት ይረዳል።አንዳንዶች አካልበው ከሁሉ ጋር እያጋጩ ወደ አልሰከነ አቅጣጫ በመውሰድ እንዳያታክቱን መጠንቀቅ ተገቢ ነው።ያለፉት ችግሮች እንዴት በማስተዋል እና ከሁሉም በላይ በጸሎት እንደተፈቱ ዛሬ ላይ ቆሞ ማስታወስ ተገቢ ነው። 

 በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ከቤተክህነት ጦር ሲወረወርበት የተሟላ ሪፖርት ያቀረበ ኢሳት ብቻ ነበር 
ከእዚህ በታች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2014 ዓም በኢሳት የቀረበ ሪፖርት ነበር። 
(ቪድዮውን እስከመጨረሻው ይከታተሉ በርካታ ከአሁኑ ክስተት ጋር የተገናኙ ነጥቦች ያገኛሉ)


==============///=============

No comments:

ለፕሮፌሰር መራር፣ልደቱ፣ጀዋርና ኢንጅነር ይልቃል ዘፈን ይህችን ዜማ እንምረጥላቸው።

በቅድምያ ስለ አራቱም የመግቢያ ማስታወሻና ወቅታዊ ሁኔታቸው። አራቱም ከመስከረም በኋላ መንግስት የለም ብለው ኢትዮጵያን ለእርስ በርስ ጦርነት ሊነክሯት ሞክረዋል።ዝርዝሩን፣ከእነማን ጋር መክረው እንደነበር፣ለኢትዮጵያ ደግሰው...