ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
>> ያለንበት ዘመን የዛሬ አንድ መቶ ዓመት የነበርንበት የንግሥት ዘውዲቱ ዘመንን ይመስላል።
ጉዳያችን/Gudayachn
ባለፈው የጉዳያችን ፅሁፍ ላይ የሩስያ ባሕር ኃይል ከሱዳን ጋር ያደረገው ውል በአሜሪካ ከፈረሰ በኃላ ጉዳዩ በኢትዮጵያ አንፃር የአሜሪካንን በትግራይ አሳባ የምታደርገው ተፅኖ ችግር ላይ እንደሚወድቅ አብራርታ ነበር።ኢትዮጵያ በዓለማችን ላይ ካሉት በከርሰ ምድሯ ውስጥ በያዘችው የተፈጥሮ ሀብትም ሆነ በምትገኝበት ስልታዊ አቀማመጥ ለዘመናት ሀገሪቱን ለመቆጣጠር በየዘመኑ የተነሱት ኃያላን ያልሞከሩበት ጊዜ የለም።ባለፉት ሁለት ወራትም በኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፍ የመሸበቢያ ገመድ ለመሸምቀቅ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤትን ለመጠምዘዝ በአሜሪካ፣እንግሊዝ እና ፈረንሳይ የተደረገው ሙከራ በሩስያ እና ቻይና አለመስማማት ሳብያ ከከሸፈ በኃላ አሜሪካ ዛሬ በሴኔቷ አማካይነት ውሳኔ አሳልፋለች።ውሳኔው በትግራይ የተደረገውን የሕግ ማስከበር ሂደት አስታኮ ይወስን እንጂ የአሜሪካ ዋና ምክንያት የአፍሪካ ቀንድ ላይ በህወሓት እጅ በኩል የነበራት ተፅኖ ሽባ እየሆነ በመምጣቱ ነው።በተለይ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሃል የተፈጠረው ድንገተኛ እርቅ የአፍሪካ ቀንድን ፖለቲካዊ፣ምጣኔ ሃብታዊ እና ወታደራዊ ቅርፅ በእጅጉ እንደሚቀይረው ግልጥ ሆኗል።
አሜሪካ እና ግብረ አበሮቿ አፍሪካን ካልከፋፈሉ ወይንም በዓይናቸው ስር በሚገኝ ህብረት ውስጥ ካልሆኑ ለጥቅማቸው አደጋ እንደተጋረጠበት ያምናሉ።በመሆኑም በቀላሉ በአቶ መለስ በኩል ይዘውሩት የነበረው የኢጋድ (የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት ድርጅት) ችላ ብለው የኢትዮጵያ፣ኤርትራ እና ሱማልያ አዲስ የትብብር እና የምጣኔ ሀብት ትብብር ሃሳብ ማንቀሳቀሳቸው እና በተለይ ከኤርትራ ጋር ያለው ትብብር ህወሓትን የማስወገድ የጋራ ወታደራዊ ትብብር ድረስ ተሻግሮ መሄዱ ጉዳዩ የሁለቱ ሀገሮች ግንባር መፍጠር ብቻ የአንድ ሺህ ኪሎሜትር ድንበር ከአፍሪካ ቀንድ ጋር የምዋሰነው እና መካከለኛ እና ሩቅ ምሥራቅን ከአውሮፓ ጋር የሚያገናኘው የቀይባህር በኢትዮጵያ እና ኤርትራ የጋራ ትብብር የማንም የውጭ ኃይል ወፍ ዝር እንዳይል የሚያደርግ ስለሆነ አሜሪካ እና አጋሮቿ ብርክ ይዟቸዋል።ስለሆነም ይህ ከሚሆን ኢትዮጵያ ብትበታተን የሚመርጡ መሆናቸውን በሰሞኑ ድርጊታቸው መረዳት ይቻላል።
አሁን ምክንያት የምንደረደርበት ወይንም ቅሌን ጨርቄን የሚባልበት ጊዜ አይደለም።ኢትዮጵያ በየዘመኑ የተነሱ ኃያላን ሊያንበረክኩ ሞክረዋል።አሁንም ምንም ዓይነት ቅርፅ ብንሰጠው የባዕዳኑ ፍላጎት አንድ እና አንድ ነው።የተንበረከከች፣እንደፈለጉ ተነሽ እና ተቀመጭ የሚሏት ኢትዮጵያን ማየት ነው።በእዚህም በዋናነት አሁን ኢትዮጵያን ያለውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይን ማገዝ ይጠበቅበታል።አሁን ያለንበት ጊዜ የንግሥት ዘውዲቱ ዘመንን ይመስላል።ከሰገሌ ጦርነት በኃላ የካቲት 4፣1909 ዓም በዕለተ እሁድ አባታቸው ዳግማዊ አፄ ምንሊክ ባሰሩት በአዲስ አበባ በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በአቡነ ማቴዎስ እጅ ተቀብተው ነገሱ።በንግሳቸው ላይ የኢትዮጵያ አዋሳኝ የሆኑት የያኔዎቹ ቅኝ ገዢዎች የእንግሊዝ ሱዳንና የእንግሊዝ ሱማሌ ገዢዎች እንዲሁም የፈረንሳይ የያኔዋ አፋርና ኢሣ ገዢ እንዲሁም በኢትዮያ የሚገኙ ራሶች እና የየአውራጃ ገዢዎች ሁሉ በተገኙበት ነበር።በመቀጠለም በንግስ ስርዓቱ መሰረት በወቅቱ የደጃዝማችነት ማዕረግ የነበራቸው ተፈሪ (በኃላ አፄ ኃይለስላሴ) ራስ ተብለው አልጋወራሽና ባለሙሉ ስልጣን እንደራሴ መሆናቸው በአዋጅ ተነገረ።
ወቅቱ የአንደኛው ዓለም ጦርነት በዓለም የተፋፋመበት፣የባዕዳን ኃይሎች የኢትዮጵያን መሬት በተለይ ከአፄ ምንሊክ እረፍት በኃላ ኢትዮጵያ ትከፋፈላለች ብለው የሚጠብቁበት እና በውስጥ ለመከፋፈል ከፍተኛ ሙከራ የሚያደርጉበት ወቅት ነበር።ይህ በእንዲህ እያለ ዘመናዊ ትምህርት በመጠኑ የቀመሱ ወጣት ኢትዮጵያውያን በንግሥት ዘውዲቱ እና በዙርያቸው ባሉ የአፄ ምንሊክ ያህል በተፈጥሮ ያልሆኑ እና የወቅቱን የዓለም አቀፍ ሁኔታ የማይረዱ ቤተመንግስት መግባታቸው ስጋት ፈጥሮባቸዋል።ይህንን ሁኔታ ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ወቅቱን አስመልክተው ራሳቸው በፃፉት ''ሕይወቴ እና የኢትዮጵያ ርምጃ'' በተሰኘው መፅሐፋቸው ገልጠውታል።የያኔው ራስ ተፈሪ የኃላው አፄ ኃይለስላሴ ግን አርፈው አልተቀመጡም።ይልቁንም አውሮፓ ድረስ ሄደው የውጭው ዓለም ፖለቲካ ተገነዘቡ።ኢትዮጵያ በዓለም ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን) አባል መሆኗ ላይ በወቅቱ ከነበሩት ከነቁት ጋር አብረው ሰሩ። ከንግስት ዘውዲቱ ንግሥ በኃላ የተነሳው ውስጣዊ ሹክቻ በሁለት የተከፈለ እንደነበር ይሄው የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ መፅሐፍ ያብራራል።አከፋፈሉ የንግሥት ዘውዲቱ እና የፊውዳል ወግ አጥባቂው እና ትምህርት ቀመስ የሆነው ኢትዮጵያን ወደ ዘመናዊ መንገድ ማስገባት ይገባል ለእዚህም ዓይነተኛ ሰው ራስ ተፈሪ ናቸው የሚሉት ነበሩ።
ዛሬም ኢትዮጵያ በአማራ፣በትግራይ፣በኦሮሞ በሚል የጎሳ ፖለቲካ ለስልጣን መወጣጫ ያልተሳካ ሙከራ የሚያደርጉ የመኖራቸውን ያህል በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ፣በእዜማ እና በአቶ ኢሳያስም ወገን ጭምር የኢትዮጵያ አንድነት ከጎሳ ፖለቲካ የፀዳ እንዲሆን የሚፍልጉ ናቸው።አንዳንዶች አቶ ኢሳያስን ከእዚህ አስተሳሰብ ሊያወጡ ይሞክራሉ።ለእዚህም ምክንያት የሚያደርጉት የአቶ ኢሳያስን የሴራ ፖለቲካ አድርገው ስለሚያዩት ነው።ሆኖም ግን የአቶ ኢሳያስ ስጋት የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ በቅሎ ኤርትራም እንደማትተርፍ አውቀዋል።ሌላው ዘግይተውም ቢሆን የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ዕድል አንድ መሆኑን በሠላሳ ዓመታት ተሞክሮ ስለገባቸው መሆኑን መረዳቱ ተገቢ ነው።
ኩሩው ጠቅላይ ሚኒስትር
ኢትዮጵያ በአሁኑ የአሜሪካም ሆነ ግብረአበሮቿ ተግባር አንፃር መቆም ያለባት ከአንድነቱ ጎራ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ጎን ነው።በችግር ጊዜ ያውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይን የመሰለ ኩሩ መሪ ተገኝቶ የባሰ መጥፎ መሪም ቢሆን በኅብረት አብሮ መቆም የግድ ነው።ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያዊነት ኩሩ የነፃነት መንፈስን በሚገባ አንፀባርቀዋል።ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ ወደ አሜሪካ ባደረጉት የመጀመርያ ጉዞ ላይ ዋይት ሃውስ ጎራ ብዬ ፕሬዝዳንት ትራምፕን ላናግር ብለው ደጅ አልጠኑም።ሕዝባቸውን አናግረው የተሰደዱትን ቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ መርቆርዮስን ይዘው ወደሀገራቸው ገቡ።ይህ ብቻ አይደለም የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ውሃ በቀጠነ እያለች ስትነጫነጭ ልዩ ልዑክ እየላኩ አሜሪካኖች ያስረዱናል ብለው ሲጠብቁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስራቸውን ብቻ ይሰሩ ነበር።በኃላ ቢቸግራቸው ራሳቸው ፕሬዝዳንት ባይደን ልዩ ልዑክ ወደ አዲስ አበባ ሁለት ጊዜ ልከው የኢትዮጵያን አስተሳሰብ ሊያስቀይሩ ሞከሩ።ይህም አልተቻለም።በመሆኑም ግራ የተጋቡት አሜሪካኖች ወደ ምክር ቤታቸው ሄደው በሐሰት የሚድያ ዘመቻ ወደ ሰከረው ምክር ቤት ሄደው ውሳኔ አሳለፉ።ይህ ሁሉ ግርግር ማዕከላዊ መንግስትን አዳክሞ ደካማ ኢትዮጵያን መፍጠር እና ለአሜሪካ መንግስት የሚታዘዝ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ አሻንጉሊት መንግስት ኢትዮጵያ ላይ መመስረት ይህ ካልሆነ ሀገሪቱን መከፋፈል ነው።ስለሆነም ኢትዮጵያን የሚወድ እና ከማናቸው የባንዳ አስተሳሰብ የጠራ ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይን ከጎናቸው መሆኑን የሚገልጥበት እና ለኢትዮጵያ ነፃነት እና አንድነት በኅብረት የሚቆምበት ወሳኝ ጊዜ ነው።
********************************
ማስታወቂያ /Advertisement
====================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ?
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ -
No comments:
Post a Comment